በደቀ መዝሙር ተስፋሁን ነጋሽ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 4 ቀን
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንዲት ባለጠጋ እናት አሉ፡፡ ታዲያ ቀደም ሲል ካከበርናቸው ዐበይት በዓላተ እግዚእ መካከል
አንዱ የሆነውን በዓለ ጰራቅሊጦስ አብሬአቸው እንዳሳልፍ በክብር ጋብዘውኝ ከቤታቸው ተገኘሁ፡፡ እኒያ እናት
ሦስት ልጆች ያላቸው ሲሆን የልጆቹ ውበት ልዩ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ወዳጄ የልጆቹን መልክ ዓይቶ ‹‹በሥላሴ አምሳል የተፈጠሩትስ
እኒህ ልጆች ናቸው›› ሲለኝ በፈገግታ ማለፌን አልዘነጋውም፡፡ አንዱን አይታችሁ ወደ ሌላኛው ስትዞሩ የባሰ እንጂ ያነሰ ቁንጅና
አታዩም፡፡ በመሆኑም ወደዚያ ቤት የገቡ እንግዶች ሁሉ ስለ ልጆቻቸው ቁንጅና ሳይናገሩ አይወጡም፡፡ ስለ ትልቁ ልጃቸው ግርማ ሞገስ፣
ስለ ተከታይዋ ሸንቃጣነት፣ ስለ ትንሹ ልጃቸው ቅላት አንዱ ከሌላው አፍ እየነጠቀ የልቡን አድናቆት ይገልጣል፡፡ እናት ስለ ልጆቻቸው
የሚባለውን ሁሉ ከሰሙ በኋላ ግን ‹‹ልክ ናችሁ ልጆቼ መልክኞች ናቸው፤ ግን ኃይለኞች አይደሉም›› ይላሉ፡፡ ይህ ንግግራቸው እኔን
ግራ ስላጋባኝ ‹‹ምን ማለትዎ ነው? አሁን እነዚህ ልጆች ምን ይወጣላቸዋል?›› በሚል የአድናቂነት ወግ ጠየቅኋቸው፡፡ እርሳቸውም
‹‹መልሱ ያለው ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ላይ ነው›› አሉኝና ‹‹የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ››
የሚለውን ቅዱስ ቃል አነበቡልኝ፡፡ /2ኛ ጢሞ. 3፤5/
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ካፈራቸው፣ ከሚወዳቸውና ከሚጠነቀቅላቸው ደቀመዛሙርት መካከል አንዱ
የኤፌሶኑ ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ነው፡፡ በመልእክቱም ላይ ሐዋርያው ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ያለውን የልብ አሳብና መሻት ይገልጻል፡፡
ስለዚህም ከ‹‹መልከኞቹ›› ይርቅ ዘንድ አዘዘው፡፡ ምክንያቱም ከእነርሱ ጋር በተቀራረበ ቁጥር ጠባያቸው ይጋባበትና እነርሱን ወደ
መምሰል ያዘነብላልና ነው፡፡ ‹‹ተመረቅሁ ብለህ ከተረገመ ጋር አትዋል›› እንዲሉ፡፡ ኃጢአት በአንድ ጊዜ አይወርሰንም፡፡ በመለማመድ
ግን ግዛቱ ያደርገናል፡፡ ለዚህም የባልንጀርነት ተጽእኖ አንዱ ነው፡፡ በባልንጀሮቻቸው ስማቸውና ሕይወታቸው የተለወጠ እንዳሉ ሁሉ
መልካምነታቸውንም የከሰሩ አሉና፡፡ ስለዚህ ባልንጀራዬ ማን ነው? የሚል መጠይቅ ሊኖረን ይገባል፡፡ ‹‹አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት
መልካሙን አመል ያጠፋል›› እንዲል፡፡ /1ኛቆሮ. 15፤33/
ሁላችንም እንደምናውቀው የሜዳ አህያ በቤት ካለው አህያ ይልቅ በብዙ ነገር የተሻለ ነው፡፡
ይኸውም መልኩ ያምራል፣ ጉልበት አለው፤ ፈጣን ነው፡፡ ነገር ግን ለገበሬ ጥቅም አይሰጥም፡፡ ከእርሱ ይልቅ በቤት ያለ ሰባራ ፈረስ
ይጠቅማል፡፡ ቢቀመጡበት ወይ ዕቃ ቢጭኑበት ያገለግላልና፡፡ ብዙዎች ለእግዚአብሔር እንደ ሜዳ አህያ ናቸው፡፡ እውቀት፣ ሥልጣንና
እምነት ቢኖራቸውም እግዚአብሔርን እንደሚገባ አያገለግሉትም፡፡ በማየት የሚመላለስ ሰው አቋራጭም አማራጭም ይፈልጋል፡፡ በማመን የሚኖር
ግን ለመንገዱ አቋራጭ፣ ለሕይወቱም አማራጭ አይፈልግም፡፡ እግዚአብሔር አያሳፍረውምና፡፡ የዘመናችን ሰው ግን መልካም ተግባሩን በጥሩ
ንግግር ተክቶ የሚኖርና ከእውነት ጋርም ላለመጓዝ የሚጠነቀቅ መልከኛ ነው፡፡ የክርስትና መልኩ ግን እምነትና ሥነ ምግባር ነው፡፡
የዛሬ አበባ፣ የነገ አፈር ነንና፡፡ ‹‹ውበትም ሐሰት ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች፡፡››
እንዲል፡፡ /ምሳ. 31፤30/
የሰዎች ልብ ከሚሸነፍበት ነገር አንዱ መልክ /ውበት/ ነው፡፡ የሌላቸው ለማምጣት፣ ያላቸው
ደግሞ ለመጠበቅ ዋጋ የሚከፍሉበትም የኑሮ ክፍል፡፡ በእርግጥ ቆንጆዎችን የሚጠላቸው ባይኖርም ቅሉ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከውስጥ ይልቅ
ለውጫዊው ውበትና መልክ ሲንበረከኩ ማየት ይታያል፡፡ ታዋቂው ሠዓሊና ቀራጺ ሚካኤል አንጀሎ ሥራውን በሚሠራበት ክፍል ውስጥ አንድ
ድንጋይ ነበር፡፡ ሚካኤል ይህን ድንጋይ ትኩር ብሎ ሲያየው ድንጋዩ ውስጥ ዳዊትን አየው፡፡ መሮውንም አንሥቶ ሲጠርብ ከውስጡ ዳዊት
ወጣ፡፡ በዚህን ጊዜ ሚካኤል አንጀሎ ሲናገር ‹‹ጥረት ያደረግሁት ዳዊትን ለመቅረጽ ሳይሆን ዳዊት ያልሆነውን ለማስወገድ ነው፡፡
ያን ጊዜ ዳዊት ወጣ›› ብሏል፡፡ እኛም ስንፈጠር የሆነውና ያልሆነው አለ፡፡ እግዚአብሔር ያየልን መልክ አለ፡፡ ሠዓሊውና ቀራጺው
ጌታ ሁል ጊዜ ያየናል፡፡ በቃሉ መሮም ያልሆነውን ሲያስወግድልን የሆነው ውበት ይገለጣል፡፡
እኛ ግን የፊት ለፊት መልክን እናደንቃለን፡፡ ሆኖም የማያስነቅፍ ደም ግባት፣ ቁመትና ቅርጽ
በብዙዎች ላይ ይታያል፡፡ የዚህም ስስት የያዛቸው ይኖራሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ግን የማያስነቅፍ ማንነት ያለው አለ ወይ? ነው፡፡
ቁመናው ዘለግ ያለውንና ናዝራዊ የሚመስለውን ሳይሆን ልቡ ንጹሕ የሆነውን፣ ሃሳቡ የተቃናውን፣ ማግኘት የማይለውጠውን፣ ይቅርታ አድራጊውን፣
ለእውነት ተቆርቋሪውን፣ ተለሳልሶ የማይናደፈውን፣ እያገሳ የማያስደነብረውን፣ ጥበብና ማስተዋልን የሚሻውን፣ ለቆዳው ሳይሆን ለቅንነቱ
የሚጨነቀውን ሰው ሁሉ ይፈልገዋልና፡፡ ምድራችን የመልከኞች ሆናለች፡፡ ማስመሰል ቀላሉ የኑሮ ዘይቤ ተደርጎ እየተቆጠረ ነው፡፡
‹‹አርሜ ኮትኩቼ የሎሚ ዘንጌን፣ መልከኛ ወሰዳት ወይ ገባር መሆን›› እንደሚባለው ድካሙ ኃይሉ ያለው አራሚው /ኮትኳቹ/ ጋር ሲሆን
ሴቲቱ የተሸነፈችው ግን ለመልከኛው ነው፡፡
በእኛም ዘንድ መልከኛ መንፈሳዊነት /የሚመስል ግን ያልሆነ ክርስትና/ በጉልህ ይታይብናል፡፡
በተወለደሁበት ሀገር አንድ የሚደንቀኝ የኦሮሞ ተረት ‹‹ሲያዩህ ድመት ትመስላለህ፣ ውስጥህ ግን ነብር ነህ›› ይላል፡፡ ሲያዩን
ለስላሳ ድመት ሲጠጉን ግን ደም የጠማው ነብር፣ ሲያዩን የምንለሰልስ ውስጣችን ግን የሚዘነጥል፣ ሲያዩን የቤት እንስሳ ውስጣችን
ግን የጫካ አውሬ፣ ሲያዩን ምግብ የምንልምን በውስጣችን ግን ሰጪውን ጭምር የምንበላ ሆነናል፡፡ ይሁን እንጂ የግምገማ ጊዜ አለ፡፡
ትልቁ ኃጢአት ሰውን እንደራስ አለማየት ነው፡፡ ትልቁ በጎነትም ሰውን እንደራስ መውደድ /ማየት/ ነው፡፡ አዎ! ካልተነካን በጎች
ስንንካ ደግሞ ነብሮች መሆን የለብንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ ስለሚፈርደው ራሱን ግን በብዙ ይቅር ስለሚለው ወግ አጥባቂ
አይሁድን ሲመክር ‹‹እንግዲህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን?›› ብሏል፡፡ /ሮሜ. 2፤21/፡፡ እንግዲህ
እንደ ዘመኑ አጭበርባሪ ሰባኪ ‹‹የምላችሁን አድርጉ እንደ እኔ አታድርጉ›› ከሚል አጉል መመጻደቅ እንራቅ፡፡ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል››
የሚሉ ብዙዎች ናቸውና፡፡ /መዝ. 4፤6/
የእግዚአብሔር ቃል እረኛውን በሚመለከት ‹‹የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ›› ይላል፡፡
/ምሳ. 27፤23/፡፡ መልክ መለያና ማንነት በመሆኑ እረኛ በጎቹን በየክፍላቸው እንዲመድባቸውና እንዲመግባቸው እንዲሁም ያለበትን
ሁኔታ በአግባቡ እንዲያውቅ ያስፈልጋል፡፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ፤
የራሴም በጎች ያውቁኛል›› እንዲል፡፡ /ዮሐ. 10፤14/ በቁጥር ሳይሆን በቅድስና ለመብዛት መተዋወቅ ይገባል፡፡ አንድ ምእመን
ወደ ካህኑ ቀርቦ ‹‹በዛሬ ዘመን እውነተኛ እረኛ የለም›› ቢላቸው ካህኑም መልሰው ‹‹ምን እረኛ ብቻ እውነተኛ በግም የለም››
በማለት ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም በእግዚአብሔር ቃል ከሚገሥጿቸው ይልቅ በከንቱ ተስፋና በሽንገላ ቃል የሚሰብኳቸውን የሚመርጡ፣
ሕይወታቸውን እና ዘመኑን እንዲመረምሩ የሚነግሯቸውን መስማትም ማየትም የማይፈልጉ፣ ሐሰተኞች መምህራንን ግን ለመከተል የሚሏቸውንም
ለማድረግ የሚጣደፉ ምእመናንን በምድራችን ላይ እየበዙ ማየት ሌላው የቤተ ክርስቲያን አስከፊ ገጽታ ነው፡፡
በመሠረቱ ክፉዎች በክፋታቸው እየቀጠሉ የሚሄዱት ቁሙ የሚላቸው ስለሌለ ነው፡፡ ሆኖም ‹‹ውሻን
በምን ይፈሩታል? ቢሉ በአጥንት›› እንደሚባለው የመልከኞችን ጠባይ በአግባቡ መረዳት ይገባል፡፡ በእውነትና በመንፈስ ስለማምለክ
ተረድተን እንደ ፈቃዳችን ካመለክን፣ በመንፈስ ጀምረን በሥጋ ከጨረስን፣ ከእግዚአብሔር አሳብ አፈንግጠን ለዓለሙ ፈቃድ የምንገዛ
አስመሳዮች ከሆን በእርግጥም መልከኞቹ እኛ ነን፡፡ ማስመሰል ጊዜያዊ ጠባያችን ብቻ ሳይሆን ባሕላችንም ሆኗል፡፡ የሚመስል ነገር
በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ስለሚገዛን እውነተኛውን አካል እናሳድደዋለን፡፡ ፍቅር ለሚመስል አመንዝራነት፣ አንድነት ለሚመስል አድመኝነት፣
ብልሃት ለሚመስል ብልጠት፣ ራእይ ለሚመስል ቅዠት፣ ግልጽነት ለሚመስል እብደት፣ ደግነት ለሚመስል ስርቆት፣ እምነት ለሚመስል ክህደት
እና አምልኮ ለሚመስል ጣዖት እጅ ሰጥተናል፡፡
ላይዋሽ በእውነት የጸናው ዳንኤል በዐራቱ ነገሥታት ሥር ሲያልፍ በታማኝነት በመገኘቱ ሰው ብቻ
ሳይሆን እግዚአብሔርም ‹‹አንተ እጅግ የተወደድህ›› ብሎታል፡፡ /ዳን.9፤23/ ጠላቶቹ እንኳን አድመው ሊከሱት ቢነሡም ከአምላኩ
ሕግ በስተቀር ምንም አላገኙበትም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ‹‹እምዬ ኢትዮጵያ
ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› እንደሚባለው በመልከኞቹ ተወረናል፡፡ ነገር ግን ሕሊና እንጂ መልክዕ አያስብም፡፡
አንደበት እንጂ መልክዕ አይናገርም፡፡ መልካምነት እንጂ መልክዕ ከሰው አያኖርም፡፡ ደግሞም መልክ የላይ ማንነትን እንጂ የውስጥ
ሰብእናን አይገልጥም፡፡ ፊት ቀልቶ ልብ ሊጠቁር፣ ውጪ አጊጦ ውስጥ ሊቆሽሽ ይችላል፡፡ ስለዚህ ኃይል አልባን ሞቅታ ማስወገድ ግድ
ይለናል፡፡ ‹‹እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትንም ሁሉ የተሞሉ በኖራ
የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ›› እንዲል፡፡ /ማቴ. 23፤27/፡፡ ምክንያቱም ጨረቃ ከፀሐይ የተቀበለችውን ብርሃን
መልሳ ለጨለማው ዓለም እንደምታበራው ሁሉ ክርስትናም በማኅበራዊ ኑሮ የክርስቶስ እውነተኛ መልክ ይገልጣልና፡፡ ‹‹አስቀድሞ ያወቃቸውን
የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና›› እንዲል፡፡ /ሮሜ. 8፤29/
እስኪ ጠበል አጥማቂዎችን /ባሕታውያን መሳዮች/ ተመልከቷቸው፡፡ እያከታተሉ በሰው ላይ ይረጫሉ፡፡
በሰው ላይ ያን ሁሉ ሲረጩ ቢያንስ ይታፈናሉ አይሉም፡፡ በራሳቸው ላይ ግን አንድ ጣሳ ጠበል ሲረጭ ይፈራሉ፡፡ ግን በሽተኛ በሽተኛውን
እንዴት ይፈውሳል? ለማዳን መዳን ይቀደማልና፡፡ ዝንጀሮዎቹ አንዱ የአንዱን መቀመጫ እያዩ ይሳሳቃሉ፡፡ መቀመጫቸው የተላጠ፣ ፍም
የመሰለ ነውና፡፡ ጦጣ ግን በዛፍ ላይ ሆና ትታዘብ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ጦጣ ‹‹ባታይው ነው እንጂ ሁልሽም ሙሽልቅ ነሽ›› አለች
ይባላል፡፡ ሰው የሚመስል ሁሉ ሰው አይደለም፤ አሻንጉሊትም አለና፡፡ መልከኞች በጥሩ ቀለም የተዋቡ፣ በጥሩ መካኒክ የተገጣጠሙና
ሲያዩዋቸው ምራቅ የሚያስውጡ ቤንዚን አልባ አውቶሞቢሎችን ይመስላሉ፡፡ አብሯችን የሚዘልቀው መልካችን ሳይሆን ሰውነታችን መሆኑን
ማን በነገረን!
ከማኅበራዊ ኑሮአችን ጋር አጣምረን የምንይዘው ክርስትና መልከኛ ሊሆን አይገባም፡፡ ‹‹በመንፈስ
ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ›› ተብሏልና፡፡ /ኤፌ. 5፤25/ የምድር ሰልፍ ሁሉ ኑሮ ነው፡፡ ይህን ሰው ሁሉ ከብዶትም ቀሎትም
ይኖረዋል፤ መንፈሳዊነትን ግን መልከኞች ሳይሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ ይኖሩታል፡፡ የኑሮ ክብሩም ወደ መንፈሳዊነት ሲያድግ ነው፡፡ ስለ
ኑሮ ከምድር በላይ ማሰብ አይቻልም፡፡ ‹‹ውሎ ውሎ ከቤት፣ ኑሮ ኑሮ ከመሬት›› ነውና፡፡ ስለ መንፈሳዊነት ግን ከፀሐይ በላይ ማሰብ
ይቻላል፡፡ ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር
ያለውን አይደለም፤ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና›› እንዲል፡፡ /ቆላ. 1፤13/ ሰው ከሞተበት
ሥፍራ መጥፋቱ አይቀርም፡፡ እናም ለመልከኝነት ኑሮ ከሞትን ለእውነት እንኖራለን፡፡ አልጠግብ ባይነትና ስግብግብነት መልከኝነት ሲሆን፤
ራስን በመግዛት የእግዚአብሔርን በረከት መቀበል ግን መንፈሳዊነት ነው፡፡
እግዚአብሔር በሚታየውና በሚሰማው የሚወሰን አምላክ አይደለም፡፡ ክርስትና በራሱ ከሚታየውና
ከሚሰማው በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር አለወይ? ካለስ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ጥያቄ ፍልስፍና ብቻ ሊመስል
ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ሰዎች ቅን ፍርድን ሲጠሙ እንዲያ ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር አለ ካልን ምን እየሠራ ነው? የሚለው ጥያቄ ዘመናዊ
/የዛሬ/ ብቻ አይደለም፡፡ ሕይወት ሞጋች፣ የሰው ባሕርይ የማይጨበጥ የሆነባቸው ሰዎች ሁሉ ሲያነሡት የኖሩት ጥያቄ ነው፡፡ መከዳት
የደረሰባቸው፣ ከዘሩት ተቃራኒ ያጨዱ፣ በግፍ ንጹሐን ሲወድቁ ያዩ ሁሉ ይህን ጥያቄ አሰምተዋል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ
በሰባተኛው ቀን ማረፉን ሊቁ ሲያስተምሩ የሰሙት ዐፄ ቴዎድሮስ ‹‹ዛሬስ ምን እየሠራ ነው?›› አሉ፡፡ ሊቁም ለመመለስ ሲቸገሩ ንጉሡ
ራሳቸው ‹‹የዛሬው ሥራውማ የእኛን አመል መሸከም ነው›› አሉ ይባላል፡፡
ጸጉራቸው የተፍተለተለ፣ ጢማቸው የተንዥጎረጎረ ሰዎች መኖራቸው የጸጉር አስተካካይ አለመኖርን
አያመለክትም፡፡ እነርሱ ግን ወደ ጸጉር አስተካካይ ለመሄድ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም አያሌ የተዝረከረኩ ነገሮች መታየታቸው
እግዚአብሔርን የለም አያሰኝም፡፡ ሰዎች በንስሐ ወደ እርሱ ለመቅረብ ስላልፈለጉ የምናየው ጉድ ሁሉ ሆነ፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር
በእኛ ሊሰሠራ የሚልገውን ነገር ወርዶ እንዲሠራ ብንሻ ትክክል አይደለም፡፡ ለድሆች ስንቆጭ ሰጥተናል ወይ? ማለት ያስፈልጋል፡፡
መልከኞች /አስመሳዮች/ የሆኑትንም ስናይ መከላከል አለብን፡፡ በዚህ መሐል ታዲያ የተለያዩ ተግዳሮቶች ይኖራሉ፡፡ ቢሆንም ግን ብርቱካን
ሲጨመቅ እንደሚጠጣው እና ዕጣን ሲጠበስ እንደሚሸተው ሁሉ ለተግባራዊው ክርስትና ስንጋደል እውነተኛ መልካችን ይወጣል፡፡
እንግዲህ በመረጃ /በእውቀት/ መሞላት ብቻ ክርስትናን አይወክልም፡፡ ትልቁ ቁም ነገርም ያነበብንውንና
የሰማውን ለጠባይ ብሎም ለሕይወት ለውጥ መጠቀም ነው፡፡ ይኸውም ስመ እግዚአብሔርን ከሚዘልፉ፣ ሃይማኖትን ከሚነቅፉ፣ ሥርዓትን ከሚያዛንፉ
ወገኖች ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ በክርስትና ሕይወት ውስጥ እውቀት ወደ ተግባር፣ መረጃ ወደ ሥራ ይለወጣል፡፡ በተግባር ልምምድ ውስጥ
ሥነ ምግባራትን ሁሉ ገንዘብ በማድረግ በመንፈሳዊነት ልምምድ የሕይወት ለውጡን ያጸናል፡፡ በዚህም በማኅበራዊ ኑሮው ውስጥ ክርስትናን
ያጣጥመዋል፡፡ አረም ተክሎችን ተጥግቶ መብል እንደሚካፈል የሚመስል ነገርም እውነተኛውን ነገር ተጠግቶ የማይገባውን ክብር ለመካፈል
ይሞክራልና ልናውቅበት ይገባል፡፡ መልከኛ እምነት፣ ኑሮ እና ራእየ
ጎጂ ነውና፡፡ ከአበባ ይልቅ የሚታይ ውበት አለ፤ ከሠርግ ዘፈን ይልቅ የሚጣፍጥ ማኅሌት አለ፡፡ እናም ከመልከኞቹ እንራቅ፡፡
ወስብሐት
ለእግዚአብሔር!
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ReplyDeleteKalehiwot Yasemalin
ReplyDelete