በደቀ መዝሙር ተስፋሁን ነጋሽ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 4 ቀን
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንዲት ባለጠጋ እናት አሉ፡፡ ታዲያ ቀደም ሲል ካከበርናቸው ዐበይት በዓላተ እግዚእ መካከል
አንዱ የሆነውን በዓለ ጰራቅሊጦስ አብሬአቸው እንዳሳልፍ በክብር ጋብዘውኝ ከቤታቸው ተገኘሁ፡፡ እኒያ እናት
ሦስት ልጆች ያላቸው ሲሆን የልጆቹ ውበት ልዩ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ወዳጄ የልጆቹን መልክ ዓይቶ ‹‹በሥላሴ አምሳል የተፈጠሩትስ
እኒህ ልጆች ናቸው›› ሲለኝ በፈገግታ ማለፌን አልዘነጋውም፡፡ አንዱን አይታችሁ ወደ ሌላኛው ስትዞሩ የባሰ እንጂ ያነሰ ቁንጅና
አታዩም፡፡ በመሆኑም ወደዚያ ቤት የገቡ እንግዶች ሁሉ ስለ ልጆቻቸው ቁንጅና ሳይናገሩ አይወጡም፡፡ ስለ ትልቁ ልጃቸው ግርማ ሞገስ፣
ስለ ተከታይዋ ሸንቃጣነት፣ ስለ ትንሹ ልጃቸው ቅላት አንዱ ከሌላው አፍ እየነጠቀ የልቡን አድናቆት ይገልጣል፡፡ እናት ስለ ልጆቻቸው
የሚባለውን ሁሉ ከሰሙ በኋላ ግን ‹‹ልክ ናችሁ ልጆቼ መልክኞች ናቸው፤ ግን ኃይለኞች አይደሉም›› ይላሉ፡፡ ይህ ንግግራቸው እኔን
ግራ ስላጋባኝ ‹‹ምን ማለትዎ ነው? አሁን እነዚህ ልጆች ምን ይወጣላቸዋል?›› በሚል የአድናቂነት ወግ ጠየቅኋቸው፡፡ እርሳቸውም
‹‹መልሱ ያለው ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ላይ ነው›› አሉኝና ‹‹የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ››
የሚለውን ቅዱስ ቃል አነበቡልኝ፡፡ /2ኛ ጢሞ. 3፤5/