Friday, August 7, 2015

“ኹል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” ፊልጵ.4፡4



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 1 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
      ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክታቱ ላይ ደጋግሞ ከሚናገራቸው ኃይለ ቃላት አንዱ ስለ ደስታ ነው፡፡ አራት ምዕራፍ ብቻ ባላት በፊልጵስዮስ መልእክት ብቻ እንኳን “ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል፤ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ ደስ ይበላችሁ፤” እያለ ዐሥራ አምስት ጊዜ ተናግሯል፡፡
ለመኾኑ ምንድነው ይኼ ደስታ? አንድን ነገር (ለምሳሌ ልጅ፣ ሥራ፣…) ባገኘን ጊዜ ደስ እንደሚለን ያለ ደስታ ነውን? ወደ መዝናኛ ስፍራዎች በሔድን ጊዜ አፀዱን፣ አዕዋፉን፣ ፏፏቴዉን ባየን ጊዜ፣ ምግቡን በበላን፣ ወይም መጠጡን በጠጣን ጊዜ ደስ እንደሚለን ያለ ደስታ ነውን? አይደለም! እንዴት ነው ታዲያ?
በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ፣ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም” ብሎ እንደተናገረው /ዮሐ.14፡27/፥ ይህ ደስታም በዚህ ዓለም በምናገኛቸው ነገሮች ወይም በምንደርስባቸው ስኬቶች የሚገኝ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ብቻ የምናገኘው ደስታ ነው እንጂ፡፡ ይህም ደስታ በግሪኩ “ቻራ” ይሉታል፡፡ ይህም ማለት ቋሚ ከኾነው ከእግዚአብሔር የሚገኝና፡- ብናገኝም ብናጣም፣ ብንጠግብም ብንራብም፣ በተሳካልንም ባልተሳካልንም ጊዜ፣ ጤና ስንኾንም ስንታመምም፥ በአጠቃላይ በዚህ ዓለም በዙርያችን በሚለዋወጡ ኹኔታዎች አብሮ የማይለዋወጥ ነው፡፡
    
      ኹሉም ሰው ይህን ደስታ ይፈልጋል፡፡ ስንፈጠርም በዚህ ደስታ ኾነን እንድንኖር ነው፡፡ በመኾኑም “ኹሉም ሰው ይህን ደስታ ይፈልጋል” ሲባል በተዘዋዋሪ ዓለም እንደሚሰጠን ጊዜአዊ ያይደለ ዘለዓለማዊ ደስታን ከሚሰጠን ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን እንፈልጋለን ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ሐዘን፣ መቈርቈር፣ መተከዝ፣ ፍርሐት፣ ድንጋጤ እና የመሳሰለው ኹሉ በራሱ ክፉ ባይኾንም የሰው ልጅ ጥንተ ተፈጥሮ ግን አይደለም፡፡  
ነገር ግን ይህን ደስታ የምንፈልግበት መንገድ የተዛነቀ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ወደ መዝናኛ ሥፍራዎች በመሔድ በዘፈን ዳንኪራና የተለያዩ ዓይነት ምግቦችንና መጠጦችን በመብላት እንፈልጓለን፡፡ አንዳንዶቻችን ለብዙ ሰዓታት እግር ኳስን ወይም ሌላ ትእይትን በማየት እንፈልጓለን፡፡ ግማሾቻችን ብዙ ገንዘብን በመክፈል ከሀገር ሀገር በመዞር እንፈልጓለን፡፡ ከፊሎቻችንም በተለያዩ የኃጢአት ሥራዎች ውስጥ እንፈልጓለን፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው ኹሉ ለጊዜው ደስታውን ያገኘነው እንደሚስለን ያደርጋሉ፡፡ ጥቂት ቆይተው ግን ይጠፋሉ፤ አንዳንዴም ጸጸት ብቻ ኾነው የሚቀሩ ይኾናሉ፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን መጥፎ መኾናቸውን እንኳን እያወቅን፥ እነዚህ ደስታን የሚሰጡ የሚመስሉ ነገሮችን ደጋግመን የምንሠራቸው፡፡
የዛሬው ጽሑፋችን በተነሣንበት ርእስ ላይ ሐዋርያው “ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ” እንዳለው ጊዜአዊ ባይደለ በዘለዓለማዊ፣ በዓለም ያይደለ በእግዚአብሔር፣ በአፍኣ ያይደለ በውሳጤአችን ደስታን እንደምን ገንዘብ ማድረግ እንደምንችል መጠቆም ነው፡፡ ለዚህም ጥቂት ነጥቦችን እንመለከታለን፡-
1.  ማንነታችንን ማወቅ
ከሰማይ በታች እንደ ሰው ያለ ድንቅ ፍጥረት የለም፡፡ እንደ ሰው ያለ ክቡር ፍጥረት የለም፡፡ ቪላ ቤትም ይኑረው፤ መንገድ ላይም ይተኛ እንደ ሰው ያለ ፍጥረት ግን የለም፡፡ እግዚአብሔር ወደ ሰው በገቢር የወረደው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ ገና ከምድር አፈር አንሥቶ ሲፈጥረው ነው የወረደው /ዘፍ.2፡7/፡፡ ይህ ለማንም ፍጥረት ያልተደረገ ለሰው ብቻ የተደረገ ነው፡፡
በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረው ብቸኛው ፍጥረት ሰው ነው፡፡ ከሰማይ በታች ካሉት ፍጥረታት ትንሣኤ ሕይወት ያለው፣ ገና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ሕሊና ርስተ መንግሥተ ሰማያት የተዘጋጀለት የሰው ልጅ ብቻ ነው /ማቴ.25፡34/፡፡ እያንዳንዳችን ወደዚህ ምድር ስንመጣ በእናታችንና በአባታችን ፈቃድ አይደለም፤ ርስቱን መንግሥቱን እንድንወርስ በፈጠረን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፈቃድ እንጂ፡፡
ባለጸጋዉም ድኻዉም በእግዚአብሔር ፊት እኩል ክቡር ነው፡፡ የሥራ ክፍፍል ካልኾነ በስተቀር፥ አንዳችን የበላይ አንዳችን የበታች አይደለንም፡፡ አንዳችን ባርያ አንዳችን ገዢዎች አይደለንም፡፡ የእግዚአብሔር መልክ አንድ ነውና፤ አንድ ደግሞ አይነጻጸርም፡፡
እያንዳንዳችን ነገሥታት ነን፤ በምድር ፍጥረታት አንድም በፈቃዳችን ላይ የተሾምን ነገሥታት፡፡ በመኾኑም ምድራዊ ቤተ መንግሥት ውስጥም እንኑር በደሳሳ ጎጆም እንኑር፣ የግል አውሮፕላንም ይኑረን በባዶ እግራችንም እንሒድ ኹላችንም እኩል ነገሥታት ነን፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ወዳጄ ሆይ! ንጉሥ ስትኾን ራስህን (የኃጢአት) ባርያ አታድርግ” ያለው፡፡
ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም የሰውን ክብር ሲዘረዝር እንዲህ ይላል፡- “አንደኛ በእጁ ነው የፈጠረው፤ ኹለተኛ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎበታል፤ ሦስተኛ በገነትና በምድር ኹሉ ላይ ገዢ እንዲኾን ተሾሟል፤ አራተኛ የጸጋ ክብርን አልብሶታል፤ አምስተኛ የሚያስብ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡”  
የሚበላውም የማይበላውም፣ የሚታየውም የማይታየውም፣ በቤት ያለውም ከቤት የራቀውም ፍጥረት ኹሉ ለእኛ ጥቅም ለእኛ ረብሕ የተፈጠረ ነው፡፡
ከፍጥረታት መጨረሻ መፈጠሩ እንኳን ሰው ምን ያህል ክቡር እንደኾነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ይበልጥ ሲያብራራልን እንዲህ ይላል፡- “ይህን አስረዳችሁ ዘንድ ወደ አንዲት ከተማ ከሚገባው ንጉሥ ጋር አነጻጽሬ ልንገራችሁ፡፡ ንጉሡ ወደ ከተማይቱ ከመግባቱ በፊት ማረፊያውን ያዘጋጅለት ዘንድ አስቀድሞ አጃቢውን ይልካል፡፡ ንጉሡ የሚገባው፥ አጃቢው ለንጉሡ የሚኾን ማረፊያ ካዘጋጀለት በኋላ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በሌሎች ፍጥረታት ላይ የጸጋ መንግሥት ነግሦ የሚኖረው የሰው ልጅም፥ ከመፈጠሩ በፊት ልዑል እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጠረለት፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ሰውን እንደምን እንዳከበረው ዐወቅን፤ ተረዳን” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ድርሳን 8/፡፡
ሰው ማይክሮ ኮስም ይባላል፤ ትንሹ ዓለም ማለት ነው፡፡ ምድራዊም ሰማያዊም ነውና፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ በኋላ ደግሞ ኹለቱንም አንድ የሚያደርግ ፍጥረትን ፈጠረ፤ እርሱም ሰው ነው፡፡ ሰው ይህን ክብሩን ሲያጣ እንኳን ጌታችን መጥቶ እንደገና እነዚህን አዋሕዶ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው መልሶታል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው፣ የተሰደደው፣ በጥቂት በጥቂቱ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በሞገስ ያደገው፣ የጾመው፣ የጸለየው፣ ያስተማረው፣ የደከመው፣ የተንገላታው፣ የተገረፈው፣ የተሰቀለው፣ የሞተው፣ ወደ መቃብር የወረደው፣ የተነሣው ለእኛ ነው፡፡ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፡፡ እንዲህስ ባይኾን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሔዳለሁና፡፡ ሔጄም ስፍራ ባዘጋጀሁላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትኖሩ ኹለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሎን ያረገው ለእኛ ነው /ዮሐ.14፡2-3/፡፡ መንፈስ ቅዱስን የላከው ለእኛ ነው፡፡ ይህ ለማንም ያልተደረገ ለእኛ ለሰው ልጆች ብቻ የተደረገ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ! እንግዲህ ምን ያህል ክቡራን፣ ምን ያህል ልዑላን፣ ምን ያህል ውድ ፍጥረታት እንደኾንን ታስተውላላችሁን? በሰው ዘንድ እንዲህ ልንኾንም ላንኾንም እንችላለን፡፡ እውነተኛው ማንነታችን ግን እንዲህ ከላይ እንደተገለጸው በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ማንነታችን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ የምንቈርጠው፣ አስታዋሽ እንደሌለን ኾነን በጭንቀት የምንኖረው ይህን ስለምንረሳው ነው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው እንዳለ ይህን ልናስብ “ኹል ጊዜም በጌታ” ደስ ሊለን ይገባል፡፡   
2.  ዓይነ ልቡናችንን በሥላሴ ላይ ማኖር
እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ስናስብ በመናገርስ ይቅርና በማሰብም መግለጥ አንችልም፡፡ እንኳንስ እኛ ብቻ አስበን፥ የሰማይ ሠራዊት፥ ከመጀመሪያው አዳም ጀምሮ መጨረሻ እስከሚፈጠረው ሰው ድረስ በአንድነት ተሰብስበን ብናስብ የሥላሴን ቸርነት በጥቂቱስ እንኳን መግለጽ አይቻለንም፡፡
እስኪ ይህን ያስረዳልን እንደኾነ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተናገረው አንድ ኃይለ ቃል ተነሥተን በጥቂቱ እንመልከተው፡፡ እንዲህ ብሎ ከተናገረው፡- “የአብ ፍቅር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከኹላችሁ ጋር ይኹን” /2ኛ ቆሮ.13፡13/፡፡
የአብ ፍቅር! አብ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ እኛን የወደደበት የመውደዱ መጠን ከራሱ በቀር ማን ሊናገረው ይችላል? አብ እኛን ያየን እንደ ሰውነታችን፣ እንደ ደካማነታችን አይደለም፤ በልጁ ውስጥ እንጂ፡፡ አብ እኛን የተመለከተን እንደ እኛ በደል አይደለም፤ እንደ ራሱ ፍቅርና እንደ ልጁ ንጹሀ ባሕርይነት እንጂ፡፡ የወደደን የሚወደድ ነገር ከእኛ ዘንድ አግኝቶ አይደለም፤ ገና ጠላቶቹ ሳለን እንዲሁ ወደደን እንጂ፡፡ ልጆቹ ያደረገን ልጆች ለመባል በቅተን ስለተገኘን አይደለም፤ እንዲሁ ያለ ምክንያት እንጂ /ዮሐ.3፡16/፡፡
በየትኛውም ዓይነት ኃጢአት ውስጥ ብንወድቅም እንኳን፥ እስካልሞትን ድረስ እኛ አባትነቱን ብንተወዉም ልጅነታችንን አይፍቀውም፡፡ ለዚህም ነው በብዙ ዓይነት ኃጢአት ውስጥ ቆይተን ወደርሱ ስንመለስ በድጋሜ የማንጠመቀው፤ በድጋሜ ልጅነትን ለማግኘት የማንወለደው፡፡
አንድ በጣም ባለጸጋ የኾነ ወደ እኛ መጥቶ፡- “ሀብቴን፣ ንብረቴን እንድትወርሰኝ እፈልጋለሁ፡፡ ልጅ እንድትኾነኝ እሻለሁ፡፡ አንተ የእኔ ልጅ ለመኾንም ምንም መስፈርት የለውም” ቢለን ምን ይሰማናል? እጅግ የምንደሰት አይደለምን? ይህ ግን ምድራዊ ነው፡፡ ጊዜአዊ ነው፡፡ ሐላፊ ጠፊ ነው፡፡ የአብ ፍቅሩ ግን እንኳንስ በኪደተ እግር በኪደተ ሕሊናም የማይደረስበት ነው፡፡ ዓይናችን ከዚህ አባት ባይነቀል ሐዋርያው እንዳለ ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል፡፡  
የወልድ ቸርነት! ቸርነት ስጦታ ነው፤ በብድር ሳይኾን በነጻ የሚሰጥ ስጦታ፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ነጻ የመደወያ ሰዓት ለአንድ ሳምንት ቢሰጠን ምን ይሰማናል? የጌታችን ነጻ ስጦታ ግን የአንድ ቀን አይደለም፤ የአንድ ሳምንት አይደለም፤ የአንድ ሺሕ ዓመትም አይደለም፤ የዘለዓለም ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ይህን ስጦታ ያገኘነው ስለተገባን አይደለም፤ ስለ ቸርነቱ እንጂ፡፡ የጠፋውን ልጅ ታሪክ ስንመለከተው ያጠፋው ኹሉንም ነው፡፡ እኛም ያጠፋነው ኹሉንም ነው፡፡ ቅድስናችንን፣ ልጅነታችንን፣…፡፡ ነገር ግን ርሱ ተወልዶ ልጆች አሰኘን፡፡ ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን አሰኘን፡፡ ይህን ስናስብ ሐዋርያው እንዳለ በጌታ ኹልጊዜ ደስ ይለናል፡፡  
የመንፈስ ቅዱስ አንድነት! ከዓለም መጽናናትን ልናገኝ አንችልም፡፡ በዓለም ልንረጋጋ አንችልም፡፡ የምንጽናናው፣ የምንጸናው፣ የምንረጋጋው፣ የምንደሰተው የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከእኛ ጋር ስላለ ብቻ ነው፡፡ በምንም ዓይነት ኃጢአት ብንወድቅም መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ ከእኛ አይርቅም፡፡ ከእኛ አይለይም፡፡ ለዚህም ነው ንስሐ ገብተን ስንመለስ በአርባና በሰማንያ ቀናችን እንደኾነው ድጋሜ ምሥጢረ ሜሮን የማይፈጸምልን፡፡
ተወዳጆች ሆይ! የሥላሴን ቸርነት እንደምን ጥልቅ፥ እንደምንስ ምጡቅ እንደኾነ ታስተውላላችሁን? ዓይነ ልቡናችን እነርሱ ላይ ሲኾን ኹልጊዜ ደስ ይለናል፡፡  
3.  ልቡናችን በሚደርስብን ጊዜአዊ መከራ ሳይኾን በምናገኘው ዘለዓለማዊ አክሊል ሽልማት ላይ ማድረግ
መከራ ሲባል የግድ እንደ ሰማዕታት በሰይፍ አንገት መቀላት፣ በመንኮራኩር (በወፍጮ) መፈጨት፣ በእሳት መቃጠል፣ በፈላ ውኃ መቀቀል፣ በመጋዝ መተርተር፣ ወደ ባሕር መጣል ብቻ አይደለም፡፡ ለጸሎት ስንቆም የሚሰማን ድካም፣ ጾመን ስንውል የሚሰማን ረሀብና ጥም፣ በየምንውልበት ቦታችን በየምንሰማራበት የሥራ መስካችን ትዕግሥታችንን የሚፈተታተኑ ነገሮች በራሳቸው፥ እንደ ዓቅማችን ወደ እኛ የሚመጡ መከራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ልቡናችንን ለጊዜው በሚሰማንን ድካም፣ ረሀብ፣ ጥም እና በመሳሰለው ኹሉ ሳይኾን እነዚህን በመታገሣችን በምናገኘው አክሊል ሽልማት ብንመለከት ሐዋርያው እንዳለ ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል፡፡ ከጊዜ አንጻር እንኳን ስንመለከታቸው እነዚህ እጅግ በጣም ለአጭር ጊዜ የሚደርሱብን ነገሮች ናቸው፡፡ በእነርሱ ምክንያት የምናገኘው ሹመት ሽልማት ግን እስከ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ይህን የምናውቀው ግን አሁን አይደለም፤ ከትንሣኤ በኋላ እንጂ፡፡ አንድ ገበሬ በጥቂቱ እንኳን እርሻውን አለስልሶ፣ ማዳበሪያ ጨምሮ፣ እኽሉን ዘርቶ፣ አረሙን አርሞ፣ አጥሩን አጥሮ፣ መከር ሲደርስ አጭዶ ምርቱን ሲሰበስብ እጅግ ደስ ይሰኛል፡፡ ያ ኹሉ ድካም እንደ ኢምንት ይቈጥሯል፡፡ እንደዉም፡- “አሁን ከደከምኩት ድካም በላይ ደክሜ ብኾን ከዚህ በላይ ምርት አገኝ ነበረ” ይላል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትም እንደዚህ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “በመጨረሻይቱ ቀን ያ የክርስቶስ የርኅራኄ ፊት ከሚለወጥብኝ፥ በዚህ ምድር በሚኖረኝ ዘመን ኹሉ ዕለት ዕለት የሰማይ መብረቅ ቢዘንብብኝ ይሻለኛል” ያለው፡፡   
ከማይበሉ የዓሣ ዝርያ ውስጥ የሚመደብ “ኦይስተር” የተባለ ዓሣ አለ፡፡ በሰውነቱ ውስጥም ለጌጣ ጌጥ የሚያገለግል ቅርፊት አለው፡፡ ነገር ግን ይህ ዓሣ እስካልተገለጠ ድረስ ይህ ክብሩ አይታይም፡፡ የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ ክርስቶስ እስካልተገለጠ ድረስ ክብራችን አይገለጥም፤ የተሰወረ ነው /ቈላስ.3፡3/፡፡ በመኾኑም በአፍአ ስናየው በዚህ ዓለም የሚደርስብን መከራ ልንደናገጥ እንችላለን፡፡ ተስፋ ልንቈርጥ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እውነተኛው ሕይወታችን በክብር የሚገለጠው ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ ነው /ቈላስ.3፡4/፡፡
በመኾኑም ዓይነ ልቡናችንን በሚደርስብን ጊዜአዊ መከራ ሳይኾን በምናገኘው ዘለዓለማዊ አክሊል ላይ የምናኖር ከኾነ፡- “እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ኾነው ስለተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” እንዲል /ሐዋ.5፡41/ እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል፡፡
4.  በጎ ምግባርን ማዘውተርና ኃጢአትን መጸየፍ
እንደ ኃጢአት አዋራጅ የለም፡፡ ኃጢአትን የሚያደርግ ሰው በሐፍረት ካባ ብቻ የሚከናነብ አይደለም፤ አስቀድሞ ከነበረው ማስተዋልና ማገናዘብም ይዋረዳል እንጂ፡፡ ይህንንም ለመረዳት የአዳም የቀድሞ ክብሩን ማሰብ እንችላለን፡፡ ዳግመኛም ኃጢአትን ከሠራ በኋላ ያገኘውን ውርደት እንመልከተው፡፡ “በሠርክ ጊዜ ጌታ በገነት ውስጥ ድምፀ ሰኰና ብእሲ እያሰማ ወደነርሱ ሲመጣ በሰሙ ጊዜ አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ፊት በገነት ዕንጨት መካከል ተሰወሩ” /ዘፍ.3፡8/፡፡ በዚህስ አዳም እንደምን ባለ ውርደት እንደተያዘ ታስተውላላችሁን? ምክንያቱም ሙሉእ በኵለሄ ከኾነው፣ ፍጥረታትን ካለ መኖር ወደ መኖር ካመጣው፣ የተሰወረውን ኹሉ ከሚያውቀው፣ የሰውን ልቡና የፈጠረና በኀልዮ የሠሩትን ዐውቆ ከሚፈርደው /መዝ.33፡15/፣ ልብ ያሰበውን ኵላሊት ያጤሰውን መርምሮ ከሚያውቀው /መዝ.7፡9/፣ ልቡናችን ያሰበውን ከሚያውቀው /መዝ.44፡21/ ከእግዚአብሔር ሊሸሸግ መውደዱ ከማወቅ ወደ ድንቁርና ከክብር ወደ ኃሣር እንደሔደ ያመለክታል፡፡ እኛም ኃጢአት ስንሠራ እንደዚህ ነው፡፡ መሸሸግ ባንችል እንኳን መሰወርን እንሻለን፡፡ ይህን ማድረጋችንም በኃጢአታችን ምክንያት ክብራችን እንደምን እንዳጣን፣ ሐፍረታችንን መሸፈንም እንደምን እንዳቃተን ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ኃጢአትን የሠራ ሰው እንኳንስ በረኻ በኾነች በዚህች ምድር በገነት መካከልም መደበቅ አይችልም፡፡
በቅጥነተ ሕሊና ስናስተውለው ግን ዓሣ ከውኃ ሲወጣ ወደ ውኃው ይገባ ዘንድ እንደሚቻኮለው፥ እኛም እንዲህ በኃጢአት ምክንያት ውስጣዊ ሰላም ማጣታችን ወደ ሰላሙ ወደባችን፣ የእውነተኛ ደስታ መፍሰሻ ወደ ኾነው ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንዳለብን ነው የሚያሳየው፡፡ በጎ ምግባር ትሩፋት ምን ያኽል ደስታን እንደሚሰጥ ነው የሚያመለክተው፡፡   
በአጠቃላይ ማንነታችንን ያወቅን፣ ዓይነ ልቡናችንን ከሥላሴ ያልነቀልን፣ የሚያገኘንን ጊዜአዊ መከራ ሳይኾን የምናገኘውን ዘለዓለማዊ አክሊል ሽልማት የተመለከትን፣ በጎ ምግባርን ያዘወትርን ኃጢአትንም የተጸየፍን እንደኾነ እንደ ፀሐይ እንደ ጨረቃ እንኾናለን፡፡ ኹልጊዜ በጌታ ደስ ይለናል፡፡  
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
† ይህ ጽሑፍ በሐምሌ እትም የሐመር መጽሔት የወጣ ነው፡፡

1 comment:

  1. አሜን!!!!አሁን ውን እላለሁ በጌታ ደስ ይበለን ...ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount