Wednesday, August 26, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍለ ዐሥራ አራት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የሰኞ (ሠኞ) ፍጥረት
ሰኞ የሚለው ቃል “ሰነየ - ሰኑይ” ከሚል የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፥ ትርጓሜውም መሰነይ፣ ኹለት ማድረግ፣ ኹለተኛ ዕለት ማለት ነው፤ ሥነ ፍጥረትን ለመፍጠር ኹለተኛ ቀን ነውና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፥ ሠኑይ ማለት ሠነየ፣ ሠናይ፣ አማረ፣ ተዋበ፣ በጌጥ በመልክ ደስ አሰኘ ማለት ነው፤ ይኸውም በዚህ ዕለት ብርሃን ስለ ተፈጠረ ነው፡፡
      ለሰኞ አጥቢያ በጊዜ ሠርክ (የመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት) እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ “ብዢ ተባዢ፤ ስፊ ተስፋፊ” ብሏት የነበረችው ውኃ ከምድር ጀምራ እስከ ኤረር ድረስ መልታ ነበር፡፡ በዚሁ ዕለት ማለትም በዕለተ ሰኑይም፥ ጠፈርን ፈጠረ /ዘፍ.1፡6-9/፡፡ እግዚአብሔር ጠፈርን በፈጠረ ጊዜም በዓለም መልቶ የነበረው ውኃ በአራት ተከፍሏል፡-
ü  የምናየው ሰማይ (ጠፈር) (ሥዕለ ማይ)፣
ü  ከጠፈር በላይ የተሰቀለው ሐኖስ፣
ü  ለምድር ምንጣፍ የኾነ ውኃና፣
ü  በምድር ዙርያ እንደ መቀነት የተጠመጠመው ውኃ (ውቅያኖስ) ተብሎ፡፡ በምድር ላይ የምናያቸው ውኆች በምድር ዙርያ ከተጠመጠመው ከዚህ ውቅያኖስ የቀሩ እንጥፍጣፊ ናቸው፡፡

ጠፈር የሚባለው ይህ ቀና ብለን የምናየው የምድር ባጥ ወይም ጣራ፣ ከዋክብት የሚመላለሱበት ሰሌዳ ሲኾን፥ ቃሉም ጽናት፣ ኃይል፣ ጥንካሬ ማለት ነው፡፡ ይህን ስያሜ ያገኘውም ትንሽ ቆይተን እንደምንመለከተው፥ ለሐኖስ ውኃ ጽናት፣ ኃይል ስለኾነው ነው /የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ፣ ገጽ 9/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም፥ ጠፈር የሚለውን ቃል በተለያየ ቦታ ኃይል፣ ጽናት ሲለው እናገኘዋለን፡- ለምሳሌ በመዝ.17፡3 ላይ “እግዚአብሔር ኃይሌና አምባዬ ነው” ተብሎ ተገልጧል፡፡ እዚህ ጋር “ኃይሌ” የሚለው ቃል በቀጥታ ወደ አማርኛ ቢመለስ “ጠፈሬ” የሚል ነው፤ የ1980ው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂም “ዓለቴ” ብሎታል፡፡ መዝሙር 150፡1 ላይም፥ የ2000 ዓ.ም. መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ “እግዚአብሔርን… በኃይሉ ጽናት አመስግኑት” ሲል፤ የ1980ው ቅጂ ደግሞ “በኃይሉ ጠፈር” ይሏል፡፡ ሰማይ ተብሎ መጠራቱ ግን ልዕልናውን፣ ከምድር ከፍ ማለቱን ለመናገር ነው /ዘፍ.1፡8/፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ጠፈር ተፈጥሮ ሲናገር፡- “እኔ እንደሚመስለኝ፡- ጠፈር ጽኑዕ አካልና ፈሳሽን መምጠጥ የሚችል እንዲሁም የሚነዋወጽን ውኃ ማረጋጋት የሚችል ሲኾን ጥንተ ተፈጥሮው ከውኃ ነው፡፡ ነገር ግን ውኃው ረግቶ ወይም ደግሞ አንዳንድ ዐለት ቀልጦ እንደሚፈጠረውና በውስጡ ምንም ዓይነት ክፍተት የሌለው ዓይነት አይደለም” ይልና ከዚህ በላይ ግን መሔድ እንደማይችልና ይህን እንዳያደርግም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስጠነቅቀው ተናግሮ ወደ ሌላ ትምህርት ይቀጥላል /አክሲማሮስ፣ ክፍለ ትምህርት 3 ቍ.4/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ልክ እንደዚሁ እንዲህ ይለናል፡- “ይህን ጠፈር ምን ትሉታላችሁ? የረጋ ውኃ ወይስ የተጠቀጠቀ ነፋስ ወይስ ሌላ ነገር? ስለዚሁ ጠፈር ሊናገር የሚችል ማንም ባለ አእምሮ ሰው የለም፡፡ በማናውቀውና ከእኛ የመረዳት ዓቅም በላይ የኾነውን ነገር ገብተን እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው እያልን ከመዘባረቅ ይልቅ የተነገረውን ቃል (“እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ” የሚለውን) ዝም ብሎ መቀበል ይሻላል” /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ክፍለ ትምህርት 4 ቍ.7/፡፡
      ጠፈር ኹለት ሺሕ በሮች አሏት፡፡ በእያንዳንዱ በሮቿም ትእምርተ መስቀል ያልያዘ (ማንም ያልተፈቀደለት ፍጥረት) ከታች ወደ ላይ ከላይ ወደ ታች እንዳይወጣ እንዳይወርድ ኹለት ኹለት መላእክት ሰይፍ እያስመዘዘ በእያንዳንዱ ደጅ አጋፋሪ አቁሞበታል፡፡
እግዚአብሔር ከጠፈር በላይ ያለው ባሕረ ሐኖስ፥ ጠፈርን እንዳይጫነው ባቢል የሚባል ነፋስ ወደ ላይ አውጥቶ ሐኖስን አሸከመው፡፡ ባቢልም የረጋ ነፋስ ነው፡፡ ጠፈርን ከታች፥ ባቢልን ከመካከል፥ ሐኖስን ደግሞ ከላይ አድርጎ አጸናቸው፡፡ እግዚአብሔር ጠፈርን ወደ ታች፥ ሐኖስን ወደ ላይ አድርጎ መፍጠሩም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወጪትና ምንቸት ያለ ውኃ ቢጣዱ የእሳት ሙቀት ሲበዛባቸው እንደሚሰበሩና እንደሚፈነዱ ኹሉ፥ ጠፈርም ሐኖስ በላይ ባይጫነው ኖሮ የፀሐይ ሙቀት ሲጸናበት በፈረሰ፤ በተናደ ነበርና፡፡ የሚያፀናው የሐኖስ ጠል ነው፡፡
ጠፈር ሲፈጠር፥ ጎበብ ተደርጐ ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩና ጥበቡ ያደረገው ነው፡፡ ይኸውም፡-
·         አንደኛ በዕለተ ረቡዕ የሚፈጥራቸው ፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት ብርሃናቸውን ወደ ላይ ሳይኾን ወደ ታች ወደ እኛ መንዛት እንዲችሉ አስቦ፤
·         ኹለተኛ ዓይናችን ማረፍያ አጥቶ ተፈንጥሮ እንዳይወድቅ ወድዶ፤
·         ሦስተኛ ለዓይናችን ተስፋ፣ ለሰውነታችን ቤዛ እንዲኾን፥ ማለትም ጠፈርን እያየን ሰማያዊ ሕይወታችንን እንድናስብ፤
·         አራተኛ የፀሐይን ሙቀት ማቀዝቀዝ እንዲችል፡፡
እዚህ ጋር ምናልባት፡- “ጠፈር ጎበብ ብሎ የተፈጠረ ከኾነ እንዴት የላይኛውን ማለትም የሐኖስን ውኃ መያዝ ይችላል?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፉ ላይ፥ ይህን ሲመልስልን እንዲህ ይላል፡- “የውስጠኛው ክፍል ጎበብ ብሎ መታየቱ የላይኛው ክፍልም የግድ እንዲጎብጥ የሚያስገድድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከዐለት የተፈለፈሉ ዋሻዎችንና የመቅደስ ጣራዎችን እንመልከት፡፡ ከውስጥ ኾነን ስናየው ጎበብ ያለ ነው፤ ከውስጥ እንዲህ መኾኑ ግን ጣሪያው ከውጪ ጠፍጣፋ መኾንን አይከለክለውም” /ክፍለ ትምህርት 3 ቍ.4/፡፡
      የጠፈር ሕብሩ እጅግም ነጭ፥ እጅግም ቀይ ወይም ጥቁር አለመኾኑ ከዓይናችን ጋር እንዲስማማ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል ጠቢበ ጠቢባን እንደኾነ፥ የሰው ልጅንም እንደምን እንደሚወደውና እንደሚያስብለት ታስተውላላችሁን?
እስከዚህ ድረስ ምድር ከውኃው እንደ ተለየች ነፋስ አልነፈሰባትም፤ ፀሐይ አልመታትም፤ ጭቃ እንደኾነች ነበር፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ግን፥ ዐሥራ ኹለቱን የእሳት አለቆች በዐሥራ ኹለቱ መስኮቶች፥ ዐሥራ ኹለቱን የነፋስ አለቆች በዐሥራ ኹለቱ መስኮቶች /ኄኖ.21፥5-9/፥ “መጥታችሁ ምድርን አድርቋት አጽንዋት” ብሎ አዘዘ፡፡ እነዚህ 24ቱ አለቆች በ24ቱ መስኮቶች ወጥተውም የምሥራቁ ወደ ምዕራብ፣ የምዕራቡ ወደ ምሥራቅ፣ የደቡቡ ወደ ሰሜን፣ የሰሜኑ ወደ ደቡብ ወዲያና ወዲህ ቢያመላልሱት ታላላቅና ታናናሽ ተራራዎች ተቆለሉ፤ ደጋው ተደለደለ፤ ቆላው ጎደለ፤ ወንዙ ተከፈለ /ኢሳ.40፥12-13/፡፡ ድንጋዩ በብረት የማይወጋ ኾነ፡፡ ምድር ግን፥ ገና ከሥላሴ ቃል ዘር የሚወድቅባት ናትና እጅግም አልደረቀችም፤ እጅግም አልረጠበችም፡፡ ከዚህ ይልቅ፥ ውኃን ምጥጥ አድርጋ ጠጥታ አማረች፤ ለሰለሰች፡፡ በዚህም ጊዜ፥ መሬት እሳትና ነፋስ ሲመላለሱባት ምድር ደመናን አስገኘች፡፡ ደመናይቱንም ለውቅያኖስ አለበሳት፤ ባሕርን ከእናቷ ሆድ በወጣች ጊዜ በበሮች አጠራት፤ ልብሷንም ደመና አደረገላት፡፡ በጉምም ጠቀለላት፡፡ ይህን ካከናወነ በኋላ፥ እሳትንና ነፋስን በየመስኮታቸው እንዲገቡ አደረገ፤ በዚያም ጸኑ፡፡ ዛሬ በዚህ ዓለም ላይ የምናያቸው ነፋስና እሳት እግዚአብሔር በጥቂት በጥቂቱ ከፍሎ የተዋቸው ናቸው፡፡ ይኸውም፥ አዝርእቱን ለመቀስቀስ፣ ውኃዉን ለመቀደስ፣ በደመ ነፍስ የተፈጠረውን ፍጥረት ኹሉ ለማናፈስ የሚጠቅሙ ናቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ በወሰነላቸው ቦታ አጸናቸው፡፡ ምድርንና ውኃን ግን አልለያያቸውም፡፡ ምድርን እንደ መርከብ አድርጐ በውኃው ላይ አንጥፎታል /መዝ.135፥6/፡፡ ይህ በእውነት ዕፁብ ድንቅ ከማለት በቀር ምንም ማለት አንችልም፡፡ ምክንያቱም ምድርን የምታህል ከባድ ዓለም በውኃ ላይ እንደ መርከብ ማንሳፈፍ፥ ከሕሊናት የሚያልፍና ምንም ያህል ብንመራመር መመለስ የማንችለው ግብር አምላካዊ ነው፡፡
እግዚአብሔር ከዚያች ብዢ ተባዢ ካላት መሬት፥ ብሩህ ብሩሁን ወደ ላይ ትቶ ጥቁር ጥቁሩን ብርቱ ብርቱውን መሬት ወደ ታች አውርዶ ዕመቀ ዕመቃት አሰፈራት፡፡ (ከላይ ወደ ታች፡- መሬት - ውኃ  - እሳት - ነፋስ - ጥቁሩንና ብርቱዉን የመሬት ዓለም)፡፡ ይህ ጥቁሩና ብርቱው የመሬት ዓለም፥ የፍጥረት ኹሉ መስፈሪያ እንድትኾን መሠረት አደረጋት፡፡ ይህችም እልፍ አእላፍ ፀሐይ ቢገባባት ጨለማዋ የማይገፋ ነው፡፡ በብረት እንደማይወቀር ድንጋይ አድርጎ አጸናት፤ ስሟንም በርባሮስ አላት፡፡
እመቤታችንና ዕለተ ሰኞ
በሰኞ ዕለት የብርሃን ማኅደር የኾነው ጠፈር ተገኝቷል /ዘፍ.1፡6-7/፡፡ ከእመቤታችንም ብርሃን ክርስቶስ ተገኝቷልና እመቤታችን በዕለተ ሰኞም ትመሰላለች /ዮሐ.1፡5-9ውዳሴ ማርያም ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው፣ ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ 15-17/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

1 comment:

FeedBurner FeedCount