በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ኅዳር ፬ ቀን፣ ፳፻፯ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ለዓለም ጀርባችንን እንስጥ
እግዚአብሔር ለሰው እውቀትና ነጻ ፈቃድ ሰጥቶ አክብሮ ፈጠረው፡፡ አንዳንዶች ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው እውነተኛ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆኑ፤ አንዳንዶች በስንፍናቸው ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ልግመኛ ክፉ አገልጋይ ሆኑ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ “እኔ ከየትኛው ነው የምመደበው? ከእውነተኞቹ አገልጋዮች ወይስ ከሀሰተኞቹ?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይለናል፡፡ የተጠመቀ ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ አይደለም፣በጠባቡ ደጅ የሚገባ ሁሉ በጽናት ላይጓዝ ይችላል (ማቴ 7፡13)፡፡ መጠመቃችን በራሱ ብቻውን ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ዋስትና አይደለም፡፡ ጥምቀት (ከኃጢያትና በኃጢአት ከመጣብን ፍዳ መዳን) ወደ ድኅነት የመግቢያ በር እንጂ ብቻውን የድኅነት መደምደሚያ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትን መጀመራችን በራሱ ፍጻሜአችንን መልካም ያደርጋል ለማለት አያስችለንም፡፡
ይህ ማለት ያመነ ሊክድ ፣ ያወቀ ሊጠራጠር እና በጎ አገልጋይ ወደ ክፉ ባሪያነት ሊለወጥ የሚችልበት እድል ዘወትር አለ፡፡ አንዳንዶች በመጠመቃቸው ብቻ እንደሚድኑ የሚያስቡ አሉ፡፡ ነገር ግን ጥምቀት ብቻውን ከእግዚአብሔር የተገባልንን ቃልኪዳን አያስጠብቅልንም፡፡ ስለዚህ የመንፈሳዊ ሕይወታችንን ትክክለኛ አቅጣጫ ልንመለከት ልንመረምር ይገባል፡፡ “ማንም ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ አይገባም የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂ” እንዲል (ማቴ 7፡21)፡፡