Wednesday, November 12, 2014

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (ደረጃ አንድ)

በዲ/ ሳምሶን ወርቁ

  (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ኅዳር ቀን፣ ፳፻፯ ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 
ለዓለም ጀርባችንን እንስጥ

 እግዚአብሔር ለሰው እውቀትና ነጻ ፈቃድ ሰጥቶ አክብሮ ፈጠረው፡፡ አንዳንዶች ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው እውነተኛ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆኑ፤ አንዳንዶች በስንፍናቸው ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ልግመኛ ክፉ አገልጋይ ሆኑ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስእኔ ከየትኛው ነው የምመደበው? ከእውነተኞቹ አገልጋዮች ወይስ ከሀሰተኞቹ?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይለናል፡፡ የተጠመቀ ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ አይደለም፣በጠባቡ ደጅ የሚገባ ሁሉ በጽናት ላይጓዝ ይችላል (ማቴ 713)፡፡ መጠመቃችን በራሱ ብቻውን ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ዋስትና አይደለም፡፡ ጥምቀት (ከኃጢያትና በኃጢአት ከመጣብን ፍዳ መዳን) ወደ ድኅነት የመግቢያ በር እንጂ ብቻውን የድኅነት መደምደሚያ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትን መጀመራችን በራሱ ፍጻሜአችንን መልካም ያደርጋል ለማለት አያስችለንም፡፡  ይህ ማለት ያመነ ሊክድ ያወቀ ሊጠራጠር እና በጎ አገልጋይ ወደ ክፉ ባሪያነት ሊለወጥ የሚችልበት እድል ዘወትር አለ፡፡ አንዳንዶች በመጠመቃቸው ብቻ እንደሚድኑ የሚያስቡ አሉ፡፡ ነገር ግን ጥምቀት ብቻውን ከእግዚአብሔር የተገባልንን ቃልኪዳን አያስጠብቅልንም፡፡ ስለዚህ የመንፈሳዊ ሕይወታችንን ትክክለኛ አቅጣጫ ልንመለከት ልንመረምር ይገባል፡፡ማንም ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ አይገባም የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂእንዲል (ማቴ 721)፡፡

ታዲያ እንዴት አድርገን ወደ እግዚአብሔር መድረስ ይቻላል? ወደ እርሱ የምናደርገውንስ ጉዞ እንዴት እንጀምር? ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ይለናልወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምናደርገውን ጉዞ ለዓለምና በውስጡ ላለው ሐላፊ ጠፊ ነገር ሁሉ ጀርባችንን መስጠትን የመጀመሪያ ፍላጎታችንና ትኩረታችን ይሁን፡፡ ይህን የማድረግ ፍላጎት ሲኖረን እና ስንችል ብቻ ነው እግራችን የመንፈሳዊ ሕይወት መሠላል ደረጃ ላይ መውጣት የሚጀምረው፡፡
ለዓለም ጀርባ መስጠት፤ ዓለምን መናቅ ማለትበሚታየው ዓለም የማይታየውን ዓለም መለወጥ ማለት ነው፡፡ በፍቅሩ መነካትና መንግስትና ጽድቁን ማስቀደም ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ብዙዎቻችንክርስቲያኖች ነን፤ ሀገራችን በሰማይ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ነውብለን የምናምንና የምንናገር ብንሆንም በሐላፊው ዓለማዊ ሐሳብና ቁሳቁስ በቀላሉ እንማረካለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህየእኛ የሰው ልጆችን በሀላፊው ዓለም መማረክ የኛን ጊዜያዊ ደስታ ወዳድነትን የሚያሳይ ጠባይ ነውይለናል፡፡
ለሥጋዊ ፍላጎትን አስቀድመን ስለነፍሳችን ሳንጨነቅ ሰውነታችንን ለምድራዊ ፍላጎት እርካታ ስንል ስንት ጊዜ አሳደፍን? ስለዚህ ነው ነፍሳችን ወደ ጥንተ ተፈጥሮ መመለስ የሚያስፈልጋት፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው እኛ በፈቃደ ሥጋ ላይ የፈቃደ ነፍስ ገዢነትዋን አምነን ስንመርጥ ነው፡፡ ይህን በእርግጥ ስንሰማው ስንናገረው የምናምነው የምንቀበለው ሀሳብ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ወደ ተግባራዊነቱ ስንገባ እንቸገራለን፡፡ እዚህ ጋር አንድ ነገር እናስተውላለን፡፡ ፈቃደ ሥጋ ቅድምናው እንዲወሰድበት አይሻምና ፈቃደ ነፍስን ይቃወማል፡፡ የሥጋም ሆነ የነፍስ ፈቃድ አይሆንም የሚለውን መልስ አይቀበሉም፡፡ ይህ ልዩነት የመጣው ደግሞ ከአዳም ውድቀት በኋላ ነው፤ አባታችን አዳም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላለፈና ወደቀ፡፡ በዚህ ፈቃደ ሥጋ ከፍቃደ ነፍስ በላይ ሆኖ ለጊዜውም ቢሆን ታየ፡፡ ከውድቀት በፊት ሥጋ የነፍስ መገልገያና አገልጋይ ነበር፡፡ ከውድቀት በኋላ  ግን ፍቃደ ነፍስ የፍቃደ ሥጋ እስረኛ ተገዢ ሆነች፡፡
ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ለመድረስ የነፍስ ፈቃድ ወደ ቀደመ ሥፍራው ይህም በፍቃደ ሥጋ ላይ የነበረው የበላይነቱን ማስመለስ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለሥጋችን የሚገባው ሥፍራ የት መሆን እንዳለበት ይህም ፍቃደ ነፍሳችን ለፍቃደ ሥጋ ተገዢ አለመሆኑን እራሳችንን በአግባቡ ማስተማር ማሰልጠን ይገባል፡፡ 
ቅዱስ ዮሐንስበገዛ ሥጋዊና ደማዊ ፈቃዳቸው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ለመሄድ የሚፈልጉ ሰዎች እጣ ፋንታቸው አመጽና የማያቋርጥ ስቃይ ነው፡፡ በተለይ የክርስትና ሕይወትን ስንጀምረው አስቀድሞ ልባችን ከዓለም አምሮት እና ከልብ ደንዳናነት ወጥቶ በታላቅ የእግዚአብሔር ፍቅር መነካት ይኖርበታልይለናል፡፡ በእርግጥ ይህ ከባድ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ምናልባትም ለጊዜው ዝንጉዎች ከመሆናችን የተነሳ ፈጥነን በፍቅሩ ባለመነካታችን ልንጨነቅ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን  በፍቅሩ ለመነካት በቅድሚያ አምርረን ኃጢአትን መጥላትና ቅድስናን መሻት መውደድ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚያም በቀላሉ ከክፋት ነጻ ወጥተን በጽኑ ቅድስናን ወደ መሻት ወደ መውደድና በፍቅሩ ወደመነካት እንመጣለን፡፡
እግዚአብሔር ይመስገንና ይህን የቅድስና ሕይወት ለመኖር እግዚአብሔር ብቻችንን አልተወንም፡፡ ይልቅስ ጌታ ራሱ በድካማችን ሊደግፈን፣ ከውድቀታችን ሊያነሳን፣ በሐዘናችን ሊያጽናናን ዘወትር ይጠባበቀናል፡፡ ይህ ለእኛ በፈተና ውስጥ ያለ ጣፋጭና ደስ የሚያሰኝ መልካም ነገር ነው፡፡ ዘወትር በክርስትና ሕይወታቻን ያለው ውጣ ውረድ ግቡ መንግሥተ እግዚአብሔርን መውረስና  በፍጹም ደስታ በመንግሥተ ሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፡፡ የዚህን የክርስትና ሕይወት ግብ ሳይረዱ በክርስትና ሕይወታችን በሚያጋጥሙን ፈተናዎች ተግዳሮቶች መጽናት ያዳግታል፡፡ ብዙዎች የክርስትና ግቡን ሳይረዱ ረጅም ርቀት የተጓዙ መስሏቸው በመንገዳቸው  ተሰነካክለው እውነተኛ ክርስትና ሂደቱን ግቡን ባለመረዳታቸው ወድቀው ቀርተዋል፡፡ የክርስትና ግቡን ሳይረዳ ሰው ዓለምን ንቄአለሁ ብሎ ቢኖርም ትርጉም የለውም፡፡ እግዚአብሔር ግን በእውነት እንደ አግባቡ ዓላማቸውን ተረድተው የክርስትናን ሕይወት ለተጓዙት ሊፈርድላቸው ይጠባበቃል፡፡
አንዳንዴ ባለማወቅ የምንኖርበትን የአሁኑን የዚህን ዓለም ኑሮ ፍጹምእውነተኛነው ብለን እናምናለን፡፡ እንዲህም ብለን ስለምናምን በጥቂቱ ወደ እግዚአብሔር እየቀረብን ስንመጣ በዓለም ያለውን ኃላፊ ጠፊ ነገር ስንንቅ እኛእውነተኛነው ብለን ከምናስበው ሕይወት የራቅን ይመስለናል፡፡ እውነታው የቱን ያህል ተገላቢጦሽ ነው? ኃጥያተኛን ሰው እግዚአብሔር ባለአእምሮ አድርጎ ፈጥሮት ሳለ ነገር ግን ከእንስሳ እንኳን ያንሳል (መዝ 49÷20)፡፡ ዘላለማዊ ሆኖ ሳለ ይሞታል፡፡ ከእውነተኛ ሕይወት ይሸሻል፡፡ በምንኖርበት ዓለም በውስጧም ባለው ነገር ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወት፡፡ የለም ቅዱስ መጽሐፉም የሚነግረን ይህን ነው፡፡ዓለምንና በዓለም ያለውን ነገር ሁሉ አትውደዱ …………. ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ” (1 ዮሐ፡21517)፡፡ ስለዚህ ከእውነት እየራቅን ሳይሆን ወደ እውነት እየቀረብን መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡
በአዳም ኃጢአት ሞት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ነገር ግን እኛ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የምንመላለስ  ከሆነ እውነተኛ ሕይወትን እናገኛለን፡፡ እርሱ የሕያዋን አምላክ ብቻ ነውና፡፡ ለሰው ይህን በእውነት ተረድቶ ወደ ሕይወት መተርጎም ምንያህል አስጨናቂ ነው፡፡ በተለይ በምንኖርበት ዓለም ሰዎች የዚህን ዓለም ኃላፊነት ከንቱነት ባልተረዱበት ሁኔታ ራሳችንን ከዓለም ለይተን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ያስጨንቃል፤ ስለማታልፈውም እውነተኛ የእግዚአብሔር መንግሥት ማሰብ ከባድ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በተጋድሎአችን እንድንበረታ ብርታቱን ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሲያጸናከዓለማዊ የሕይወት ምልልስ ተለዩና በቤተ ክርስቲያን የክርቲያኖች ህብረት በሚገለጽባቸው ከጸሎታቱ ከምስጋናው ከጉባኤው አትለዩይለናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ህብረት ውስጥ ስንኖር ዓለምን ያሸነፉትን ሰዎች የማየት እድሉ ስለሚኖረን እነርሱ ዓለምን እንዴት እንዳሸነፉ ስለምንረዳና እንድናሸንፍም ስለሚያበረቱን    በዚህ እንጠቀማለን፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው ቤተ ክርስቲያን (የክርስቲያኖች ህብረት) ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ በምናደርገው ጉዞ አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው የምንለው፡፡ በዚህ ህብረት ውስጥ ስንኖር አንዳችን ለአንዳችን ስለምንኖር በጸሎታችን አንድነት ስለሚኖረንና ህብረት ስለምናደርግ ወደ እግዚአብሔር ለምናደርገው ጉዞ በእጅጉ ይጠቅመናል፡፡
ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የምናደርገው ጉዞ የተናጠል ከሆነ በቀላሉ ልንወድቅ ልንሰናከል እንችላለን፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን በሕብረት ከቅዱሳኑ ጋር ሆነን ወደ እግዚአብሔር በምናደርገው ጉዞ ብንወድቅ እንኳን እንደገፋለን፤ እንደጋገፋለን ዘወትር በጸሎት የመተሳሰቡን ጥቅም በዚህ እንረዳለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስለብቻዬ ሮጬ ወደ እግዚአብሔር እደርሳለሁ ለሚል ሰው ወዮታ ይገባል፤ በላዩ ፈተና በጸና ሐዘን ድካም ተስፋ መቁረጥ በወደቀበት ጊዜ ማንም ከጎኑ ሆኖ ሊደግፈው ሊያጽናናው የሚችል ሰው የለውምናይለናል፡፡
ታዲያ ማነው ብልህና የታመነ ክርስቲያን ጀርባውን ለዓለም ሰጥቶ ፊቱን ወደ እግዚአብሄር የመለሰ? እርሱ የክርስትና ሕይወቱን ያለማቋረጥ ዕለት ዕለት በምግባሩ በትሩፋት እያሞቀ እያቀጣጠለ፣ መንክር እግዚአብሔር እያለ በውስጡ ቅንዐተ እግዚአብሔር እየነደደበት፣ በፍቅር ላይ ፍቅር እየጨመረ እስከ ዘመነ እረፍቱ የሚኖር እርሱ ብልህና የታመነ ክርስቲያን ይባላል፡፡ እንግዲህ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ነው ማንም በዚህ ደረጃ ላይ እግሮቹ የቆሙ ሰው ፈጽሞ ወደ ኋላ አይመለከትም፤ እርፍ ይዞ ወደ ኋላ የለምና፡፡

                                                ወስብሐት ለእግዚአብሔር! 
 

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን በጣም ደስ የሚል አቀራረብ ነው እንግዲህ በአንድም በሌላም እግዚአብሔር ይናገራል ሰው ግን… ነውና የተማርነውን በልቦናችን የሳልብን

    ReplyDelete
  2. ዲ/ንሳምሶን አገልግሎትዎን ያስፈፅምልን ከታላቅ አክብሮትና ይቅርታ ጋር ትንሽ አስተያየት አለኝ እንደኔ እንደኔ ለመያዝ እንዲመቸን በቁጥር መዘርዘር ቢቻል ብየ ነው የህውም ለምሳሌ በዛሬው አርእስት ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ።በሚለው ላይ ።እንዳንደርስ የሚያደርጉን ምንድን ናቸው 1 ኛ,2ኛ, እያልን ለመድረስ ምን እናድርግ 1ኛ,2ኛ, በማለት ብቀርብ በጣም ለመያዝም እኛም ከዚህ ተምረን ሰንበት ት/ት ቤት እንጠቀምበታለን።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount