Saturday, November 15, 2014

አብሬሽ ልመለስ



በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ቅዳሜ ኅዳር 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ከክብር ማረፊያው ከገሊላው ቤትሽ
ሰማሁ መፍለስሽን ወደ ግብጽ ወደ ኩሽ
ፀሐይ ሲያከትራት ያቺን የበረሃ ዖፍ
ጼዋዌን ስትናፍቅ ላንዲት ቅጽበት ሳታርፍ
ሰማሁኝ ስደቷን መጠጊያ ሳታገኝ በልቤ ላይ ስታልፍ



....ፈላሲተ ቁስቋም ወዴት ነው ሀገርዋ
ኀበ ሖረት ላቲ በብካይ እትልዋ
ናዛዚት እም ኃዘን ሁሉ ያላት ለማኝ
የምድረ በዳ ዖፍ ጎጆዋን እስካገኝ
መኃልየ ብካይ ኃዘንዋ እየሆነኝ
..... እፈልጋታለሁ
እፈልጋታለሁ....እፈልጋታለሁ
እንዲያም ያጣኋት ለት..... ፈልጊኝ እላለሁ
አልያማ
ያለ ምዕራፈ ክብር....ያለ ነፍሴ አስኬማ
ያለ ብሔረ ሰላም ....ያለ ጽድቅ ከተማ
ያለ ጽናት አክሊል ..... ያለ ፍቅር ማማ
ምሕረትን ሲርበኝ ..... ይቅርታን ስጠማ
ከበረሃ እንዳልቀር .... ድምጼ ሳይሰማ
..... እፈልጋታለሁ
እፈልጋታለሁ....እፈልጋታለሁ
እንዲያ ያጣኋት ለት..... ፈልጊኝ እላለሁ
ዋዕየ ፀሐይ ዘመዓልት.... ክምር ኃጢዓቴን ንጄ
የሌሊቱን ቁረ ገዳም ... ፈቃደ ሥጋውን ክጄ
ካንቺው ጋራ ልመለስ ..... ከግብጽ ተሰድጄ
" ውስተ ርስትኪ ሰድኒ... እም ብኄረ ዓለም ባዕድ
በቤተልሔም ቤትኪ …..አልቦ አመጻ ወሃይድ "
................ አይደለም አብሬሽ ልመለስ
ክብርሽን አክብሬ ውድሽን ሳወድስ.... እያልኩ ሥሉስ ቅዱስ
ሥጋ ዓለሜን ጥዬ ከነፍስ ሀገር ልድረስ
................ አይደለም አብሬሽ ልመለስ
የነፍሴ ወደቧ ወደ ልጅሽ ልድረስ
ያለ እርሱ እምነት የለም ያላንቺም ክርስቶስ
................ አይደለም ካንቺው ጋር ከኋላ
መርተሽ አሳርፊኝ በብሔረ ተድላ
ለፈጣሬ ዓለማት አንቺ ነሽ መጾሩ
ለተስፋ ስዱዳን ህጽንሽ ነው አገሩ
የጢሮስ አምኃ ... ከቤተልሔም ግብጽ ... ተከትሎሽ ሲፈልስ
ከግብጽ ቤተልሔም .... ካንቺ ጋር ሲመለስ
የልጅሽ ፍጥረቱ እኔም ከዚያ እንዳላንስ
ምን ባልገባ እንኳን ስምሽን ባልቀድስ ..... ልጅሽን ባላወድስ
ጠልተሽ አትጣይኝ ፍኖትሽን ሳስስ
እነሆ ልጅ ልባል ጎልጎታ ልድረስ
................ አይደለም አብሬሽ ልመለስ
ትተሺኝ አትውጪ ውስተ ምድረ ነኪር
ስደትን ታውቂያለሽ ተሰድጄ እንዳልቀር
መከራን ታውቂያለሽ ተመክሬ እንድኖር
አብሬሽ ልመለስ ወደ ነፍሴ ደብር
እንዳትረሺኝ ከመንገዱ .... አንቺ ቀሊል ደመና
ጥለሽኝ አትሂጂ ከበረሃው .... አማናዊት የሲና መና
በእቅፍሽ ያለው ህብስተ ሕይወት .... የምሕረት ዝናብ ነውና
ዘመንሽ ነውና ዘመኑ .... መጠንሽም ነውና መጠኑ
ለሥጋ ማረግ መሰላሉ .....ለቃል መውረድም ዙፋኑ
ያላንቺማ "እስከማዕዜኑ..."
እንዲህ እየተከዙ እንድያም እያዘኑ...
ጽድቅን እየገፉ ፍዳ እየመዘኑ
ያላንቺማ "እስከማዕዜኑ..."
በንሰሃ እንባ ኃጢዓትን ሳይከድኑ
ከነአንን ናፍቀው ግብጽን ቢኮንኑ
ከስጥመተ-ባህር ከጥፋት ላይድኑ
ከሀገር ተለይተው በስደት ቢጸኑ
ያላንቺማ "እስከማዕዜኑ..."
የበጎቹ መሰማርያ..... እምነ ጽዮን እያሉ
ካንቺ ነውና ሚጠለሉ ..... ከእቅፍሽ ነውና ሚውሉ
መፈውስ ነሽና ለቁስለ ነፍስ .....እባክሽን አዛኝቱ
አስከትለሽው ተመልሽ ልጅችን ጥሪው ለቤቱ
ሊቁ እንደነገረን ....
"ብጹዕ ዘርእየኪ በህልሙ ሌሊተ
አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ሐምሰ ዕለታተ"
እኔም ደሞ ናፍቃለሁ ....አንዲት ነገር ልለምንሽ
በነፍሴ ላይ ስትበርቂ.... ጽልመት ግብሬ ፈርቶ እንዲሸሽ
አንድ ጊዜ ባይነ-ልቤ.... ላንዲት ቅጽበት በህልሜ ልይሽ
.....ልመለስ አብሬሽ!

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

    ReplyDelete
  2. የአገልግሎት ዘመንህን ያብዛልን።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount