Monday, November 10, 2014

ለይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ የተሰጠ ምላሽ (ክፍል ሦስት)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ኅዳር 2 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የሥላሴ ትምህርት በቅድመ ኒቅያ አበው
ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችኁ? በጥያቄና መልስ ዓምዳችን ለይሖዋ ምስክሮች የስሕተት ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ ምላሽ መስጠት ከዠመርን የዛሬው ሦስተኛው ክፍል ነው፡፡ በክፍል አንድ ምላሻችን የይሖዋ ምስክሮች የስሕተት ትምህርቶች ምን ምን እንደኾኑ፥ እንዲኹም መሠረታዊ የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በመጠኑ ዐይተናል፡፡ በክፍል ኹለት ትምህርታችንም ከብሉይ እና ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በማመሳከር ምሥጢረ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንደኾነ ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር በረዳን መጠን ከሐዋርያነ አበው ዠምረን እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምን ብለው እንዳስተማሩ እንመለከታለን፡፡ ይኽን የምናደርግበት ምክንያትም የይሖዋ ምስክሮች የሥላሴ ትምህርት የተወሰነው በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ አስገዳጅነት ነው ስለሚሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን አሜን!!!

 የሦስቱም አካላተ ሥላሴ ዋሕድነት (በመለኮት አንድ መኾን) በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይኾን ከኒቅያ ጕባኤ በፊት በነበሩት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጽሑፎችም በስፋት የምናገኘው ትምህርት ነው፡፡ እስኪ ይኽን በጥቂት በጥቂቱ እንመልከት፡-
አግናጥዮስ ዘአንጾክያ
 ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾክያ “ለባሴ እግዚአብሔር” የሚል መጠሪያ ያገኘ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ጌታችንን “በመንግሥተ ሰማያት ከኹሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ሕፃንን ጠርቶና በመካከላቸው አቁሞ፡- “እውነት እላችኋለኁ ካልተመለሳችኁ እንደዚኽም ሕፃን ካልኾናችኁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ብሎ በምሳሌነት ያቀረበው ሕፃን ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾክያ ነው /ማቴ.18፡1-5፣ አንድምታው/፡፡
 ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾክያ ከዚኽ ጊዜ ዠምሮ ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጋር ያደገ ሲኾን በተለየ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር፡፡ በኋላም በአባቶች እግር ተተክቶ ሦስተኛው የአንጾክያ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ ተሹሟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ወንጌልን ያለ ድካም ሲሰብክ ቆይቶም በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
 ይኽ በሐዋርያት እግር ሥር ያደገው ቅዱስ አባት ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ካስተማረው ትምህርት የሚከተለው ይገኝበታል፡- “ፍጥረታትን ኹሉ የፈጠረ እግዚአብሔር የፍጥረቱን ኹሉ ሹመትና መዐርግ መሥጠት የሚቻለው በመልክ፣ በገጽ ፍጹም በሚኾን በሦስት አካል በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ ኹሉን የሚገዛ ነው፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በእመቤታችን በንጽሕት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡ … አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው እንደኾነ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው እንደኾነ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው እንደኾነ እናምናለን፡፡ ይኽቺ ሦስትነት ያለ መለየት ያለ መለወጥ በሦስት አካላት በአንድ መለኮት የተተከለች ናት፡፡ …” /ሃይ.አበ.11፡2-9/፡፡
 ከላይ እንደተናገርነው ቅዱስ አግናጥዮስ የሐዋርያት ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ያስተማረውም ትምህርት ከአባቶቹ የተማረውን ነው፡፡
የሲምርናው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፖሊካርፐስ
 ቅዱስ ፖሊካርፐስ በ64 ዓ.ም. ላይ በሰርምኔስ ከተማ የተወለደ ሲኾን የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዛሙር ነው፡፡ ይኽን በማስመልከት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዲኽ ብሏል፡- “ነፍስ እስከማውቅና በሕይወቴ እስኪዋሐደኝ ድረስ በሕፃንነቴ የተማርኩትን አኹን ከምማረው በላይ ወለል ብሎ ይታየኛል፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሲቀመጥበት የነበረውን ቦታ፣ የትምህርት አሰጣጡ ዘዴ፣ እንዴት ይገባና ይወጣ እንደነበር፣ ክርስቲያናዊ ሕይወቱና የሰውነቱ መልክዕ፣ ለምእመናን ያስተማረውን ትምህርት፣ ከወንጌላዊ ዮሐንስና ከሌሎች ጌታችንን በዓይን ካዩት ደቀ መዛሙርት ጋር ስለነበረው ትውውቅ፣ ትምህርታቸውን እንዴት ያስታውሰው እንደነበር፣ ስለ ጌታ ከእነርሱ ምን እንደሰማ፣ ጌታችን ያደረጋቸውን ተአምራትና ያስተማረውን ትምህርት ይኽንና ይኽን የመሰለ ኹሉ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከቃሉ አገልጋዮችና ምስክሮች እንደምን እንደተቀበለና ለእኛ እንዴት እንዳስተላለፈልን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አዋሕዶም እንዴት እንዳስተማረን አስታውሳለኁ፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት ረድቶኝ፥ በሕፃንነት አዕምሮዬ እነዚኽን ነገሮች ለመስማትና በወረቀት ሳይኾን በልቤ ጽላት እጽፋቸው ዘንድ ደግሞም ዘወትር አስባቸው ዘንድ እጅግ እጓጓ ነበር” /Fr. Tadros Y. Malaty, Tradition and Orthodoxy, pp 23 /፡፡
 ቅዱስ ፖሊካርፐስ የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ከመኾኑ በፊት ቡኩሎስ ከተባለ ሊቀ ጳጳስ የሃይማኖትን ትምህርት ተምሮ ዲቁና ተሹሟል፡፡ ሊቀ ጳጳስ ቡኩሎስ ሲያርፍም ዮሐንስ ወንጌላዊ የሰርምኔስ ሊቀ ጳጳስ አድርጐ ሹሞታል፡፡
 ይኽ ቅዱስ አባት በዚያን ጊዜ ከነበሩት መናፍቃን (መርቅያናውያንና ቫለንቲናውያን) ጋር ብዙ ተጋድሏል፡፡ ብዙዎችንም ወደ ርትዕት ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡
 ቅዱስ ፖሊካርፐስ በሰማዕትነት ከማረፉ በፊት ሦስት ጥያቄዎችን ተጠይቆ ነበር፡፡ የመዠመሪያው ጥያቄ ክርስቲያኖችን “ከሐዲዎች ይጥፉ” ብሎ እንዲረግም ነበር፡፡ ርሱ ግን ወደ ራሳቸው ወደ ከሓዲያኑ እያመለከተ “ከሓዲዎች ይጥፉ” አለ፡፡ ኹለተኛ ዕድል ተሰጠው፡፡ “ክርስቶስን ካድ፤ ስደበውም” ተብሎም ታዘዘ፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ግን “ለ86 ዓመታት ጌታዬን አገልግዬዋለኹ፡፡ እስከ አኹንም ምንም ያስቀየመኝ ነገር የለም፡፡ ስለዚኽ እንዴት ጌታዬንና መድኃኒቴን ክፉ ቃል እናገረዋለኹ? እንዴትስ እክደዋለኁ?” አለ፡፡ አኹንም ሌላ ሦስተኛ ዕድል ተሰጠው፡፡ “በቄሣር ስም ማል” ተባለ፡፡ ርሱም “እኔ ክርስቲያን ነኝ፡፡ እናንተም ክርስትናን ማወቅ ከፈለጋችኁ ላስተምራችኁ” አላቸው፡፡ በዚኽ የተቈጣው ንጉሡ ወደ እሳት ጨምረው እንዲገድሉት አዟል፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስም በ86 ዓመቱ የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጀ፡፡
ይኽ ቅዱስ አባት ስለ ሥላሴ ካስተማረው ትምህርት አንዱን ብቻ ብንጠቅስ የሚከተለው ይገኝበታል፡-“እግዚአብሔር ሆይ! ከዘለዓለም አንሥቶ የባሕርይ ልጅህ ከሚኾን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለ ኹሉም ነገር አመሰግንሃለኁ፡፡ አከብርሃለኁ፡፡ ከፍ ከፍም አደርግሃለኁ፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን” /የፖሊካርፐስ ሰማዕትነት፣ 14/፡፡
እንግዲኽ እውነትን ማን ያስተምረን? ሐዋርያትና የሐዋርያት ደቀ መዛሙርት ወይስ በ19ኛው ምእተ ዓመት የነበረው ቻርለስ ራስል?
ሰማዕቱ ዮስጢኖስ (Justin the Martyr)
ሰማዕቱ ዮስጢኖስ በፍልስጥኤም ከተማ የተወለደ ሲኾን በወጣትነቱ ፍልስፍናን ጠንቅቆ ተምሯል፡፡ በኋላ ላይ ስለ ክርስትና ለማወቅ ባደረበት ፍላጐት ክርስቲያን ኾኗል፡፡ “ብቸኛ እውነት ክርስትና ነው” በማለትም ተናግሯል፡፡ ለትውልድ የተረፉ ሥራዎቹ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚኽ ሥራዎቹ ውስጥ ስለ ቅድስት ሥላሴ ያስተማረውን ትምህርት ስንመለከትም እንዲኽ የሚል እናገኛለን፡-  
v “የዓለማት ኹሉ ፈጣሪ የኾነው አብ አንድ የባሕርይ ልጅ አለው፤ ርሱም በባሕርዩ እግዚአብሔር የኾነ አካላዊ ቃል ነው” /የመዠመሪያው ዕቅበተ እምነት፣ ምዕ.63/፡፡
v “ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እና የሠራዊተ መላዕክት ጌታ ነው” /ከአይሁዳዊው ትሪፎ ጋር የተደረገ ውይይት፣ ምዕ. 36/፡፡
ሶርያዊው ታቲያን
ታቲያን ሶርያዊ ሲኾን ወደ ሮም መጥቶ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በመመልከት ክርስትናን የተቀበለ ነው፡፡ የሰማዕቱ ዮስጢኖስ ደቀ መዝሙርም ነበረ፡፡
 በሶርያውያን ዘንድ “ዲያተሳሮን” የተባለ መጽሐፍ በስፋት ይታወቅለታል፡፡ ዲያተሳሮን የአራቱም ወንጌል ወጥ በኾነ ታሪክ የተሰባጠረ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በዚኹ መጽሐፍ ተንተርሶ ትርጓሜ አዘጋጅቶለታል፡፡
 ሌላው ታቲያን የሚታወቅበት ሥራው ለአሕዛብ (በዚያ ሰዓት ጽርዓውያን) የጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡ ይኽ ሥራ አምልኮ ጣዖትን በእጅጉ የሚጸየፍና የክርስትናን ርቱዕነት አበክሮ የሚናገር ነው፡፡ በዚያም ውስጥ ስለ ሥላሴ ትምህርት አስተምሯል፡፡ አንዱን ለመጥቀስ ያኽልም፡- “እናንተ ፈላስፎች ሆይ! አምላክ ሰው ኾኖ ተወለደ ስንል የስንፍና ጨዋታ እየተጫወትን እንደኾነ አታስቡ፡፡ ስሜት የማይሰጥ ንግግር እየተናገርን እንደኾነም በፍጹም አታስቡ” የሚል ይገኝበታል /ለግሪኮች የተላከ መልዕክት 21/፡፡ በዚኽ ትምህርቱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ወልደ አምላክ፣ ብርሃን ዘእም ብርሃን ብላ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን በዚያም የሥላሴን ትምህርት ተናግሯል፡፡
ቅዱስ ሄሬኔዎስ
 ቅዱስ ሄሬኔዎስ ሃይማኖተ አበው የተባለው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ “የሐዋርያት ደቀ መዝሙራቸው፣ ተከታያቸው፣ ኤዶም በምትባል ሀገርም ኤጲስ ቆስነት የተሾመ” ይሏል /ሃይማኖተ አበው 7፡1/፡፡  
v “ከአብ የተወለደ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ የዘለዓለም ንጉሥ ርሱ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ነው” /ሃይማኖተ አበው 7፡8/፡፡
v “ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኹሉን የፈጠረ በሥራ ኹሉ ያለ” /ሃይ.አበ.7፡5/፡፡
v “ቤተ ክርስቲያንን (ምእመንን) የሚዋሐዳት፣ ያመኑትን የሚጠብቃቸው፣ ኪሩቤልን የፈጠረ፣ እግዚአብሔርነቱን የሚያገለግሉ ሠራዊተ መላዕክትን የሚመራቸው፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በውነት የዘለዓለም ገዥ ነው” /ሃይ.አበ.7፡18/፡፡
v “የከበሩ መጻሕፍት ክርስቶስ ሰው እንደኾነ እንደሚነግሩን አምላክም እንደኾነ እነርሱ እንዲኹ ይነግሩናል፡፡ ግዙፍ እንደኾነ እንደሚነግሩን ረቂቅም እንደኾነ፥ የእግዚአብሔር ቃልም እንደኾነ ርሱም ራሱ እግዚአብሔር እንደኾነ እንዲኹ ይነግሩናል” /ሃይ.አበ.7፡19/፡፡
v “ርሱ የዳዊት ልጅ እንደኾነ እንዲኹ የዳዊት ፈጣሪ ነው፡፡ ከአብርሃም ዘር እንደተገኘ እንዲኹ ከአብርሃም በፊት አለ (ነበር)” /ሃይ.አበ.7፡24/፡፡
v “ርሱ በኹሉ ሙሉዕ ሲኾን ወደ መቃብር ለመውረድ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ተሸክመዉት ታየ፡፡ በሥጋ ሞተ፤ ይኸውም ለዘለዓለም ሕያው ነው” /ሃይ.አበ.7፡31/፡፡
ተወዳጆች ሆይ! ታድያ ምን ያዘገያችኋል? ከሐዋርያት ደቀ መዛሙርት ተማሩ፤ ንስሐ ገብታችኁም እውነትና ሕይወት ወደ ኾነው ክርስቶስ ተመለሱ፡፡ ይኽቺ የዘለዓለም ሕይወት ናትና፡፡   
ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ
 የእስክንድሪያው ቀሌምንጦስ በ150 ዓ.ም. አከባቢ ከአሕዛብ ወላጆች የተወለደ ሲኾን ፍልስፍና እየተማረ ቆይቶ በኋላ ክርስቲያን ኾኗል፡፡ ቀሌምንጦስ ስለ ጥምቀትና ስለ ሥጋ ወደሙ ዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጪነትን በስፋት አስተምሯል፡፡ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ካስተማረው ትምህርትም ለማሳያ ያኽል የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ü “ከሥላሴ ውጪ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ሦስተኛው አካል መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ኹለተኛው አካል ወልድ ነው፡፡ በርሱ ቃልነትም አብ ፍጥረታትን ኹሉ ፈጠረ” /Stromata, Book V, Chap. 14/፡፡
ü “ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመዠመሪያ ቃል ነበረ ሲል ዘለዓለማዊ ልደቱን ሲናገር ነው፡፡ ይኸውም የባሕርይ ልጅነቱን ሲናገር ነው፡፡ ስለዚኽ ነበረ የሚለው አገላለጥ መዠመሪያ የሌለውን ዘለዓለማዊነትን የሚያስረዳ ቃል ነው” /fragment in Eusebius History, Bk 6 Ch 14; Jurgens, p.188)፡፡
ጠርጡለስ
 በ160 ዓ.ም. በቅርጣግና የተወለደው ጠርጡለስ (ተርቱሊያን) የሕግ ባለሙያ ሲኾን የክርስቲያኖች ሕይወት ማርኮት ክርስቲያን የኾነ ሊቅ ነው፡፡ ፕራክሲያ ለተባለ አይሁዳዊ የላከው መልዕክት በሙሉ በሚባል መልኩ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚያብራራ ነው፡፡
Ø “ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ ስለ ቅድስት ሥላሴ ግልጽ ትምህርት ያስተምሩናል” /Against Praxeas, ch 11/፡፡
Ø “እግዚአብሔር ሰውን በአርአያችን በምሳሌአችን እንፍጠር ባለ ጊዜ የተናገረው ለኹለተኛውና (ለአካላዊ ቃሉና) ለሦስተኛው አካላተ ሥላሴ (ለመንፈስ ቅዱስ) ነው” /Against Praxeas, ch 12/፡፡
ጐርጐርዮስ ገባሬ መንክራት
 የቀጶዶቅያ አውራጃ በምትኾን በቂሣርያ ኤጲስ ቆጶስነት የተሾመ፣ ተአምራትን ያደረገ ይኸው ቅዱስ ጐርጐርዮስም በ262 ዓ.ም. ገደማ የሥላሴን ምሥጢር በተናገረበት ድርሳኑ እንዲኽ ይለናል፡- “ከሦስት ግብራት የተነሣ ሥራውን ኹሉ ዕወቅ፡፡ ግብራትም የተባሉ ስሞች ናቸው፡፡ ይኸውም ፍጥረት ስም ዘመድ ነው፡፡ ሰው ተገዥ ሹም ይባላል፡፡ ሰው መባሉ ስለ ባሕርዩ መገኘት፥ ተገዥ መባሉም ስለ ተገዥነቱ ነው፡፡ ሹም (መጋቢ) መባሉም ስለ ተሾመ ነው፡፡ አኹን ደግሞ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ እንላለን፡፡ ግን አካላት ተቀድመው ተገኝተው እሊኽ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው አይደለም፡፡ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም አይደለም፡፡ ባሕርዩ ነው እንጂ፡፡ ለሰዎች ኹሉ ከእነርሱ ለእያንዳንዱ የተለየ ስም አላቸውና፡፡ እነዚኽም አዳም፣ አብርሃም፣ ይሥሐቅ፣ ያዕቆብ ናቸው፡፡ የሰዎቹ ስማቸው ይኽ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አቃኒም ስሞች ናቸው፡፡ ስሞችም አቃኒም ናቸው፡፡ አቃኒም ማለት በገጽ፣ በመልክ ፍጹማን የሚኾኑ ባለመለወጥም ጸንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነው፡፡ ባሕርዩ አንድ ሲኾን ሦስቱ አካላት ጸንተው በሚኖሩ በእነዚኽ ስሞች ይጠራሉ፡፡ ሦስት አካላት አንድ መለኮት ናቸው” /ሃይማኖተ አበው 13፡1-6/፡፡
 የይሖዋ ምስክሮች ሆይ! ታድያ በየትኛው ታሪክ ነው፥ የሥላሴን ትምህርት ያስተማረው ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ነው የምትሉን? እውን እነዚኽ ከላይ የጠቀስናቸውን ሊቃውንት በ325 ዓ.ም. በተደረገው በጉባኤ ኒቅያ የነበሩ ናቸውን? ኧረ በፍጹም!!! እንኪያስ ንስሐ ግቡ፤ ወደ አንዱ መንጋም ተቀላቀሉ፡፡ የዘለዓለምንም ሕይወት ያዙ፡፡ ለዚኽም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳችኁ /ኢሳ.9፡6/፡፡ አሜን!!!
 እግዚአብሔር ቢረዳንና ብንኖር በቀጣይ ምክንያተ ጕባኤ ኒቅያ ስለኾነው ስለ አርዮስ አስተምህሮ፣ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ጕባኤውን ለምን እንደጠራና በጕባኤው ላይ ስለ ነበረው ሚና እንዲኹም ስለ ጕባኤው አጠቃላይ ሒደት ተመልክተን ስለ ሥላሴ የምንሰጠው ምላሽ እናጠቃልላለን፡፡ ይቆየን!!!  


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount