Monday, November 3, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል አምስት)


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 25 ቀን፣ 2007 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


ሐ) ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድ


 እንደምን ሰንበታችኁ ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች? ትምህርተ ሃይማኖት በሚለው ተከታታይ ትምህርታችን ውስጥ ለዛሬ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ኦርቶዶክሳዊ አረዳድን እንማማራለን፡፡ በዚኽ ጽሑፍ ውስጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንነት፤ በቤተ ክርስቲያን ያለው ቦታ ምን እንደሚመስልና እንዴት መረዳት እንዳለብን እና ሌሎች ተያያዥ ሐሳቦችን እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 መጽሐፍ ቅዱስ ጥሬ ቃሉ ከኹለት የግእዝ ግሶች የተገኘ ሲኾን በአንድነት የተሰበሰበ የተለየ፣ የከበረ፣ ቅዱስ ጽሑፍን ያመለክታል፡፡ ይኽም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ የማይወሰነው የእግዚአብሔር ቃል በሚወሰነው የሰው ልጅ ቃል የተገለጠበት የመጀመሪያ ሥጋዌ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ቃል ማለት ነው፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቤተ ክርስቲያናችን ቅድስና ከምትሰጣቸው (ቅዱስ ብላ ከምትጠራቸው) ነገሮች ቅዱሳት መጻሕፍት ይካተታሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽን ቅድስና የሰጠችበት ምክንያትም፡-
·        አስገኚው እግዚአብሔር ስለኾነ /1ኛ ሳሙ.23፡2፣ ዘጸ.17፡14/፤
·        ሰውን ወደ ቅድስና ስለሚያደርስ /ራዕ.2፡6፣ 2ኛ ጢሞ. 3፡15/፤
·        በእግዚአብሔር መንፈስ የታገዙ ቅዱሳን ስለጻፉት /2ኛ ጴጥ.1፡22 ፣ መዝ. 102:18 ፤ ኢሳ.30፡8/፤
·        የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት ስላለው ኹኔታ እና ስለሚመጣው ኹሉ በእርግጠኝነት ስለሚናገር /ዘፍ. 1፡1 ፣ ኢሳ. 7፡14 ፣ ራዕ. 21፡1 ፣ ማቴ.25/፤
·        የሚያነቡትን እና የሚሰሙትን ስለሚባርክ /ራዕ.1፡3/፡፡
 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሐፍት የሚለው በቅድስናው ብቻ አይደለም፤ በታሪኩም ጭምር እንጂ፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ላይ ተጠርዞ ከአምላክ የተሰጠ (የወረደ) አይደለም፡፡ ይልቁንም ከ4000 ዓመታት በላይ ፈጅቶ በተለያዩ ቅዱሳን፣ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ባሕል የተጻፈ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ከ1500 ቅ.ል.ክ. በሲና በረኻ አምስቱን የሕግ መጻሕፍት የምንላቸውን በዕብራይስጥ ቋንቋ ጻፈ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በ600 ቅ.ል.ክ. ላይ በባቢሎን ትንቢተ ዳንኤልን፤ መጽሐፈ ሶስናን እና መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅን በአረማይክ ቋንቋ ጻፈ፡፡ በሓዲስ ኪዳን ያሉትን ስንመለከትም ከ10 በላይ ጸሐፊያን በተለያየ ቦታ አብዛኛውን በግሪክ ቋንቋ ጽፈዋል፡፡
 ይኽን ታሪክም እንዲኹ የምንዘረዝረው አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ስላለው እንጂ፡፡ ቤተ ክርስቲያን እኛ አኹን የምናውቀውን መጽሐፍ ለእኛ ለማቆየት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች፡፡ የመጻሕፍት መቃጠል፣ የሐሰተኛ መጻሕፍት መቀላቀል፣ የመጻሕፍት መጥፋት እና የመሳሰሉት ኹሉ አልፋ መጻሕፍትን ከያሉበት ሰብስባ፣ ለእያንዳንዱ ስያሜ ሰጥታ፣ በዓይነት በዓይነት ጠርዛ፣ ምዕራፍና ቁጥር አውጥታ፣ በጥንቃቄ ከቋንቋ ወደ ቋንቋ በመተርጎም ለትውልድ አስረክባለች፡፡ ፊደላትና ሆህያት ለሌላቸው እንኳን ፊደላትንና ሆህያትን በመቅረጽ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲተዋወቁ አድርጋለች፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ ብንወስድ እኛ የምንጠቀምበት የግእዝ ፊደል አኹን ያለውን ቅርጽ ያስያዙት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. የመዠመሪያው ጳጳስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ናቸው፡፡
  በዚኹ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቤተ ክርስቲያን እንግባና መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን አንድ አካል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ከርሱ ጋር የማይጋጩ ሌሎች መጻሕፍትን ከሕይወቷ ጋር አስማምታ ይዛለች፡፡
  በባለፈው ትምህርታችን እንደተማማርነው ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን አስገኘች እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን አላስገኛትም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የቤተ ክርስቲያን  አባል ነበሩ፡፡ የጻፉትም ታሪክን ጠብቆ ለማቆየት ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን (በተለያየ ሀገር ላሉ የክርስያኞች አንድነት) ነው፡፡
 መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ታሪክ መጽሐፍ፥ በታሪክ ቅደም ተከተል (chronology) የተጻፈ አይደለም፡፡ ይልቁንም በዓይነት በዓይነት የተጻፈ (የተሰበሰበ) ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ብንመለከት የሕግ ክፍል፣ የታሪክ ክፍል፣ የመዝሙር ክፍል እና የትንቢት ክፍል ኾነው ተቀምጠዋል፡፡ ይኽንም ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍቱን ስያሜ በመስጠት፣ ምዕራፍ እና ቁጥር በማውጣት፣ በመተርጎምም ጭምር መጽሐፍ ቅዱስን ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፋለች፤ እያስተላለፈችም ነው፡፡ በአጠቃላይ በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ላይ ግልፅ የኾኑ የቤተ ክርስቲያን አሻራዎች አሉ፡፡
 ግኖስቲኮች ከጻፉአቸው ሐሰተኛ መጻሕፍት ጋርም ቤተ ክርስቲያን ትግል አካሒዳ ክፉዎቹን መጻሕፍት ከእውነተኞቹ ለይታ ለእኛ እንዳስረከበች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ የሚያጠና ሰው የሚረዳው ነው፡፡ ክርስቶስ እንዳዘዘው ሐዋርያት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ወንጌልን በመስበክ ለዓለም አዳርሰውታል፡፡ ይኽም በክርስቲያኖች ዘንድ የተዳረሰው የወንጌል መሠረታዊ ሐሳብ የሐሰተኛ መጻሕፍትን ሥራ በይፋ አጋልጧል፡፡ እውነቱንም ከሐሰቱ እንዲለዩ አስችሏቸዋል፡፡ በዚኽም የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ብቻ ሳትኾን ጠባቂም እንደኾነች እንረዳለን፡፡
 ባለፈው ትምህርታችን እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስ የትውፊት አንድ አካል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ያስገኘው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ነው፡፡ ስለዚኽ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳትም ለመተርጎምም የሚቻለው በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ወይም በትውፊት ያለን እንደኾነ ብቻ ነው፡፡
 ይኽን ለመግቢያ ያኽል ካየን ወደ ተነሣንበት ርእሰ ጕዳይ እንመለስ፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንረዳ?” የሚለው ጥያቄ የአብዛኞቹ ክርስትያኖች ጥያቄ ነው፡፡ በዓለም ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ ኹለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ የመዠመሪያዎቹ የእግዚአብሔር ቃል እንደኾነ የሚያምኑ ግን የማያነቡት፤ ከሼልፍ እና ከትራስ ሥር በዘለለ ምንም የማይጠቀሙበት ናቸው፡፡ ኹለተኞቹ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ያነባሉ ግን በትክክል ስለማያነቡት አይረዱትም (ይሰናከሉበታል)፡፡ ኹለቱም ኦርቶዶክሳዊ አካሔዶች አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን  ማክበር አለብን፤ ማንበብም እንደዛው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ርሱን በመሳም ወይም በመተሻሸት አንረዳውም፡፡ ገልጠን ማንበብ አለብን፡፡ ስናነብ ግን ከሌሎች መጻሕፍት በተለየ ጥንቃቄ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ታግዘን መኾን አለበት፡፡
 ዛሬ በዓለማችን አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ኖሮ ብዙ የክርስትና ክፍፍሎች መኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል አለመረዳት ምን ያኽል ስሕተት ውስጥ እንደሚጥል የሚያስረዳ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
 ስለዚኽ አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ (ማጥናት) ከመዠመሩ በፊት ማወቅ የሚገባቸው ነጥቦች አሉ፡፡ የተወሰኑትንም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
1.    በትሕትና ማንበብ
  ጌታችንን ይከተሉት የነበሩት አምስት ገበያ (5000) ሰዎች ኹሉም ተመሳሳይ የመዳን ዓላማ እንዳልነበራቸው ኹሉ፥ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎችም ልክ እንደዚኽ ናቸው፡፡ መረጃ ለማግኘት ብቻ የሚያነብ አለ፤ ስሕተት ለመፈለግ የሚያነብ አለ፤ ሥነ ጽሑፋዊ ዘይቤው ደስ ብሎት ብቻ የሚያነብ አለ፡፡ ይኽ ኹሉ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማ አንፃር ሲታይ ምንም አይጠቅምም፡፡ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለመዳን (በድኅነት ጉዞ ውስጥ ባለው ድርሻ) ማንበብ አለባቸው፡፡ ይኽም በትሕትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግ (አላዋቂ በማድረግ) መኾን አለበት፡፡ መጽሐፍ እንዲኽ እንዳለ፡- “ወደዚኽ ወደ ትሑት መንፈሱም ወደ ተሰበረ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለኁ” /ኢሳ.66፡2/፡፡
2.   ጽሙና
 ቅዱስ መጽሐፍ በመዠመሪያ ማስተማር ያለበት አንባቢውን ነው፡፡ ስለኾነም ሰው “የማስተምረው” ብሎ ሳይኾን “የምማረው” እያለ በተረጋጋ መንፈስ ማንበብ ይገባዋል፡፡ ይኽ መረጋጋት ሕግጋቱን (መጻሕፍቱን) በዓይነ ሥጋ ከማንበብ ባሻገር በዓይነ ልቡናው ዘወትር እንዲመለከታቸው ይረዳዋል፡፡ ነቢዩ “ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ - ሕጉን በቀንም በሌሊትም የሚመለከት ሰው ንዑድ ክቡር ነው፡፡ በፈሳሽ ውኃ እንደተተከለችና ፍሬዋን በየጊዜው ለባለቤትዋ እንደምታቀርጽ ዕፅ ይኾናልና” እንዲል /መዝ.1፡6/፡፡ ይኽም ማለት በቀን ያነበበውን በሌሊት፥ በሌሊት ያነበበውን ሕግ በቀን የሚፈጽመው በጽሙና በማንበቡ ነው፡፡ በየሰዓቱ ባነበበው ሕግ ጸንቶ መገኘቱ ከዕለቱ ሙሉ ጊዜ እንዳነበበ እንዳስቆጠረለት እናስተውል፡፡
3.   ያልተረዳነውን ለጊዜው ማለፍ
ሰው ቅዱስ መጽሐፍን ሲያነብ ኹሉንም አነጋገሮችና ምሳለዎች ይረዳል ማለት አይቻልም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም ኾነ አንባቢው ሰው፥ የአንዱ መነበብ የሌላው ማንበብ በፈቃደ እግዚአብሔር በጸጋ እግዚአብሔር ነውና ሰው ያልተረዳውን ለእግዚአብሔር መግለጥ መተው አለበት፡፡ እንዲኽ ሳያደርግ በራሱ ታግሎ ለመተርጐም የሚሞክር ከኾነ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያት ሃይማኖትን ሳይኾን ክሕደትን ያመጣል፡፡
4.   መጽሐፍ ቅዱስን በቤተ ክርስቲያን መረዳት
  ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው፥ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ነው፡፡ የምንረዳውም በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን  መጽሐፍ ቅዱስ የሚገድል ፊደል ነው /2ኛ ቆሮ.3፡6/፡፡ ይኽ በቤተ ክርስቲያን መረዳት የምንለው ሐሳብ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ልዩ ያደርጋታል፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መተርጎም ያለባቸው ካህናት (የሃይማኖት አባቶች) ብቻ ናቸው” ብላ ታስተምራለች፡፡ የፕሮስቴስታንቱ ዓለም ደግሞ “ማንም እንደገዛ ፈቃዱ ማንበብ እና መተርጎም አለበት” ብሎ ሌላ ጽንፍ ያስተምራል፡፡ እኛ ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ እንዳመኑትና እንደጸኑት የቤሪያ ክርስቲያኖች “ክርስቲያኖች ኹሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አለባቸው፤ መረዳታቸውም በቤተ ክርስቲያን መሠረተ ሃይማኖት እና በአባቶች ሕይወት ላይ የተመሠረተ (የማይጻረር) መኾን አለበት” እንላለን /ሐዋ.17/፡፡ ይኽንንም በሚፈስ ወንዝ እንመስለዋለን፡፡ ውኃው በመኻል የሚፈስባቸው ኹለቱ ግድግዳዎች (ዳርቻዎች) የቤተ ክርስቲያን ሕይወትን (አስተምህሮን) ሲወክልልን፥ የእኛ መረዳት ደግሞ በመኻል የሚፈሰውን ውኃን ይመስላል፡፡ የምንተረጕመው እዛው ወንዝ ውስጥ ብቻ ኾነን ነው፡፡ ነጻነታችን የተጠበቀ ቢኾንም ከወንዙ ዳርቻዎች ማለፍ አንችልም፡፡ እንዲኽ ካልኾነ የቤተ ክርስቲያን መረዳት (Mind of the Church) እንስተዋለን፤ የቤተ ክርስቲያን ያልኾነና የእኛን ሐሳብም እንጨምራለን፡፡
 ከብሉይ ኪዳን ዠምሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመገናኛቸው ቀን መጻሕፍትን ያነቡ ነበር፡፡ ይኽም በሐዲስ ኪዳን ቀጥሎ በሐዋርያት ሥራ እና በሌሎች የአበው ጽሑፍ ውስጥ እንደሰፈረው፥ ክርስቲያኖች ጉባኤን ባደረጉ ጊዜ ኹሉ ከብሉይ ኪዳንም ከሐዲስ ኪዳንም የተውጣጡ ክፍለ ምንባባትን ያነብቡ ነበር፡፡ ይኽ ትውፊት አኹንም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያን የዘመን አቈጣጠር እና ከሚከበሩ በዓላት ጋር ተስማምቶ የተሠራውን የዕለቱ ንባብ (ግጻዌው) የዚኹ መገለጫ ነው፡፡ ቅዳሴውን ስናስቀድስ የማንሰማው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ ብሉይ ኪዳኑ አለ (ምስባኩ)፡፡ ሐዲስ ኪዳኑ አለ (ወንጌል፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት፣ ሌሎቹ መልዕክታት እንዲኹም የዮሐንስ ራዕይ)፡፡ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴ አለ፡፡ በቅዳሴው የሚደረገውን እያንዳንዱ ሥርዓተ አምልኮውን ስንመለከት በእጅጉ እንደነቃለን፡፡ በመኾኑም አንድ ክርስቲያን በአግባቡ የሚያስቀድስ፣ ከምሥጢራቱ የሚካፈል፣ ምንባባቱን በአግባቡ የሚከታተልና የሚያነብ፣ ሥርዓተ አምልኮውንም የሚያገናዝብ ከኾነ መጻሕፍትን በቀላሉ መረዳት ይችላል፤ የቤተ ክርስቲያን መረዳት (Mind of the Church) አለውና፡፡
5.    የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከሉ ክርስቶስ ነው፡፡
 መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ቋንቋ  እንደ መጻፉ የተበታተነ መጽሐፍ አይደለም፡፡ አንድ ዓላማ ያለው ርስ በርሱ የማይጻረር መጽሐፍ ነው፡፡ ማዕከሉም ዓላማውም ክርስቶስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በምሳሌ፣ በትንቢት እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ክርስቶስን የሚወክሉ ነገሮች አሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዘንድም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ ሰው ኾኖ የሠራው የማዳን ሥራ፣ በርሱ ያመኑ የመዠመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ታሪካቸው እና ትምህርታቸው ክርስቶስን ማዕከል አድርጎ ተጽፎልናል፡፡ መጽሐፍም ስለዚኽ ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየኁ። ብርቱም መልዐክ፥ መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማጸሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየኁ፡፡ በሰማይም ቢኾን በምድርም ቢኾን ከምድርም በታች ቢኾን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም፡፡ መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ ዘለቀስኁ፡፡ ከሽማግሌዎቹም አንዱ፡- አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የኾነው አንበሳ ርሱም የዳዊት ሥር መጽሀፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቷል አለኝ” /ራዕ.51-6/፡፡ የተዘጋ መጽሐፍ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ይልቁንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ ድል የነሣው አንበሳ የተባለውም ክርስቶስ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ክርስቶስ ፈሪሳውያኑን እንዲኽ ብሎ ገስጿቸዋል፡- “እናንተ በመጻሕፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችኁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችኁ፡፡ እነርሱም ስለ እኔ የሚሰክሩ ናቸው፤” /ዮሐ.539/፡፡

6.   ለእኛ እንደተጻፈ ማሰብ
  “ኩሎ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ” እንደተባለ /ሮሜ.15፡4/ የተጻፈው ኹሉ እኛን ለመገሠጽ ነው፡፡ ክቡር ዳዊትም “እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል” ይላል /መዝ.86፡6/፡፡ ስለዚኽ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ሐሳብ የሚናገርበት አንዱ መሣሪያ ነው፡፡
 አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ሦስት ደረጃዎችን ማለፍ አለበት፡፡ የመዠመሪያው ታሪኩን ማጥናት ነው፡፡ ኹለተኛው ራሳችን በባለታሪኩ ቦታ ማስገባት ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ያንን ታሪክ ለግል መንፈሳዊ እድገታችን መጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ከሉቃ.10፡30 ዠምሮ ያለውን የደጉ ሳምራዊን ታሪክ ስናነብ፥ ታሪኩን ካጠናን በኋላ ራሳችንን በተደበደበው ሰው ቦታ፣ በአይሁዳዊው እና በካህኑ ብሎም ባዘነለት ሳምራዊው ቦታ አስገብተን ሥነ ምግባራዊና ነገረ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመውሰድ ለግል መንፈሳዊ እድገታችን የሚጠቅሙ ነገሮችን መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡
 ዛሬ በዓለማችን ብዙ ሰዎች ለመዠመሪያ ጊዜ ከተጻፈላቸው ሰዎች የዘለለ ትርጉም (ድርሻ) እንደሌለው አድርገው ያስባሉ፡፡ ይኽ ግን ስሕተት ነው፡፡ እያንዳንዱ ቃል እኛን ለማስተማር ለእኛው ጥቅም በመለኮታዊ ጥበብ እገዛ የተከተበ ነው፡፡
7.   ጸሎት
  እነዚኽ ከላይ የተመለከትናቸውን ነጥቦች ራሳችን ማድረግ ከቻልን ከዚኽ ጸሎትን በመጨመር ማንበብን መዠመር አለብን፡፡ መጸሐፍ እንዲኽ እንዳለ፡- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለኹሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለርሱም ይሰጠዋል” /ያዕ.1፡5/፡፡
 እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ሲያናግር፣ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በጸሎት እግዚአብሔርን ትጠይቃለች፡፡ በሃይማኖት የጸና ምላሿን ትሠጣለች፡፡ ምን ጊዜም በቤተ ክርስቲያን ወንጌላትና መልዕክታት ከመጽሐፍ ቅዱስ ከመነበባቸው በፊት ለሚነበበው መጽሐፍ ይነበባል፡፡ “ጸልዩ በእንተ ወንጌል ቅዱስ” እንዲል፡፡ እኛም “ይረስየነ ድልዋነ ለሰሚዐ ወንጌል ቅዱስ - ቅዱስ ወንጌልን ለመስማት የበቃን የተዘጋጀን አድርገን” እንላለን፡፡ በጸሎት መንፈስ ቅዱስ በእኛ ዘንድ ኾኖ ለቅዱሳን የገለጠውን ቅዱሳት መጻሕፍቱን ይገልጥልን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምናለን፡፡ ይኽ ጸሎት ልቡናችንን በምድራዊ ግብር ከመባከን ለይቶ ወደ ሰማያዊው ምሥጢር በጸጋ እግዚአብሔር ይሰቅለዋል፡፡
       ከዚኽ ጋር አያይዘን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ጥቂት እንመልከት፡፡
·          መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የሚናገር መጽሐፍ ነው /ኢሳ. 61-5 ዮሐ. 11 ኢዮ. 425 መዝ. 733/
·        መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድር ታሪክ (የሚታይ ታሪክ) ብሎም የማይታየውን ረቂቅ ታሪክ ከተመረጡ ሕዝቦች (አባቶች) ጋር ጨምሮ የያዘ መጽሐፍ ነው፤
·         መጽሐፍ ቅዱስ ነገረ ቅዱሳንን (መውደቃቸውንና መነሣታቸውን) የሚያዘክር መጽሐፍ ነው /ሐዋ.9 2 ሳሙ.11/፡፡ ለምሳሌ በውስጡ የክቡር ዳዊትን እንዲኹም የቅዱስ ጴጥሮስን መውደቅና መነሣት ይዘክራል፤
·        መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጽሐፍ ብቻ አይደለም፤ ታሪክም መዝሙርም ሕግጋትንም ከወንጌል ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፤
·        መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ በጠለቀ ሥነ ጽሐፍ ጥበብ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ለዚኽ ምሳሌ የጠቢቡ ሰሎሞንን እና የቅዱስ ጳውሎስን መጽሐፍት መጥቀስ ይቻላል፡፡
·        ወዘተ……
የመጽሐፍ ቅዱስ ዝግጅት
በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የማያውቁትን እና የማያምኑበትን እየጻፉ እንደ ድምጽ ማጉያ ያገለገሉበት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እና የሰዎች ድርሻ የተካተተበት ጽሑፍ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድርሻ ምንድን ነው? ቢሉ
·        መጥራትና ማነሣሣት /ኤር.15 ኢሳ.68/
·         እንዲያስተውሉ ማድረግ /ዮሐ.145-26/
·         ማናገር እና ማጻፍ /1 ሳሙ.232 ኤር362/
·         ምሥጢር መግለጥ፤
·         ከስሕተት መጠበቅ፡፡
የቅዱሳን ጸሐፊዎቹ ድርሻ ደግሞ ነጻነታቸውንና ዕውቀታቸውን ተጠቅመው በፍላጎታቸው የሚያምኑበትን እና የኖሩበትን እውነት መጻፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ
ü የትምህርተ ሃይማኖት ምስክር ነው፡፡
ü የመልካም ምግባራት ምስክር ነው፡፡
ü የሥርዓተ አምልኮ ምስክር ነው፡፡
ü የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምስክር ነው፡፡
 ምንጫቸው ግን ከዚኽ በፊት እንደተነጋገርነው ቅዱስ ትውፊት ነው፡፡ መገኛቸውም ክርስቶስ ነው፡፡
አባታችን ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እንዲኽ ይላል፡- “የእግዚአብሔር ቃል የመላዕክት ምግብ ነው፡፡ ይኽም ነፍስን የሚመግብ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ነፍሱን የሚጠግን (የሚመግብ) ከኾነ በጎነትን በመረዳት ይሞላል፡፡ ክፋትንም ይጸየፋል፡፡ይኽ የሊቁ ቃል ከላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የጠቀስነውን ቃል አጠናክሮ ከእኛ ሕይወት ጋር የሚያዋሕድ ነው፡፡
 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ኃይለ ቃላት ኹሉ በነጠላ ትርጓሜያቸው የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ዳግመኛም ኹሉም ሥነ ምግባራዊ ትምህርትን የሚያስተምሩ አይደሉም፡፡ በትርጓሜ ረገድ ሦስት ዓይነት ትርጓሜዎች አሉ፡፡ ነጠላ ትርጓሜ፣ ምሳሌያዊ ትርጓሜ እና ምሥጢራዊ ትርጓሜ ይባላሉ፡፡ በአረዳድ ደረጃም ሥጋዊ ደረጃ፣ ነፍሳዊ ደረጃ እና መንፈሳዊ ደረጃ የምንላቸው ታሪኩን መረዳት፣ ሥነ ምግባራዊ ትምህርቶችን መውሰድ እና ስለ ክርስቶስ፣ ቤተክርስቲያን እና ቅዱሳን ያሉ ትምህርቶችን በቅደም ተከተል የሚያስረዱን የትርጓሜ ደረጃዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር እነዚኽን በሌላ ጊዜ በዝርዝር እንመለስባቸዋለን፡፡  
ማጠቃለያ
 የነገረ ሃይማኖት ምንጩ የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድና በተለያየ ኅብረ አምሳል የገለጠውን እውነት የምናገኘው ደግሞ ደጋግመን እንደተናገርነው በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ነው፡፡ ስለዚኽ እግዚአብሔር በመጽሐፍ የገለጠውን እውነት መተርጐም የምትችለው ይኽቺ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ ይኽ ትርጓሜ እንዳይዛባ የሚጠብቀውም በበዓለ ኃምሳ በምልዓት በቤተ ክርስቲያን ያደረው የእውነት መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእውነት ዓምድና መሠረት መባሏ ከዚኹ የተነሣ ነው /1 ጢሞ.315/፡፡
 መጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም ይፈልጋል፡፡ አፍአዊ ፊደላቱን አይደለም፤ ጽንሰ ሐሳቡን፡፡ ይኽን ጽንሰ ሐሳብ መተርጐም የምትችለውም አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነች፡፡ ለምን?
አንደኛ) የምሥጢሩ ተቀባይ ርሷ ናት፤
ኹለተኛ) የሐሳቡ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ያለው በርሷ ውስጥ ነው፤
ሦስተኛ) የክርስቶስ ሕዋስ እንደ መኾኗ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ምሥጢሩን ኹሉ ይገልጥላታል፡፡
  “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻየሚሉት ሰዎች ርስ በርሱ የሚላተምን አረዳድ የያዙት፥ ከላይ የተገለጠውን ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስን አረዳድ ባለመገንዘባቸው ነው፡፡ ሌላው ነገር መጽሐፋችን የተገለጠ የሚኾነው በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ላሉና ከምሥጢራት ለሚሳተፉ ክርስቲያኖች ነው፡፡ ለሌሎቹ ግን የታተመ እና የተዘጋ ፊደል ብቻ ነው፡፡
“እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” /ሮሜ.10፡17/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount