Sunday, August 26, 2012

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

   ኢትዮጵያዊው ሊቅና ጻድቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ታላቅ ቦታ የያዘ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡  አባ ጊዮርጊስ የተወለደው 1357 . በወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ ወላጆቹ ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት መሆኑን ድርሳነ ዑራኤል ይተርክልናል፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ አምኃ ጽዮን ይባላሉ፡፡  አባቱ ጠቢብና የመጻሕፍት ዐዋቂ፤ የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳንሥዕል ቤትከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ሲሆን የሰግላ ሀገረ ገዥም ነበር፡፡  የአባ ጊዮርጊስን እናት እምነ ጽዮን ከወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና/  ከሹማምንት ወገን የሆነች ደግ ሰው ነበረች፡፡

 አባ ጊዮርጊስ በመጀመርያ እናቱ ፈሪሐ እግዚአብሔርን እያስተማረች በጥበብና በዕውቀት አሳደገችው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ነበር፡፡ ምክንያቱም አባቱ የመጻሕፍት ሊቅ መሆኑን ስንመለከትና ገድሉም አባ ጊዮርጊስን በተመለከተወሶበ ልሕቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆንየሚለውን ስናጤነው አባቱ የመጀመርያውን ደረጃ ትምህርት ካስተማረው በኋላ በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጳጳስ የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መተርጕም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል ማለት ነው፡፡
                                             
  ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ተላከ፡፡ ወደ ሐይቅ የገባው በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መሆኑን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያዩ ሊቃውንት የሚገኙባት፣ በብዙ መጻሕፍት የተሞላችና ዙሪያዋን በሐይቅ በመከበቧ የተማሪን ሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነች ቦታ ናት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎችይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ?” ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረውብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግንአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግልብሎ እንደ ገና ላከው፡፡

 አባ ጊየርጊስ በቀለም ትምህርት እንዲሰንፍ ምክንያት የሆነው ከመማር ይልቅ በሥራ እየደከመ የገዳሙን አባቶች መርዳትና ብሕትውናን ይማርከው ስለ ነበር ነው፡፡ በገዳሙ  እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር ፡፡ አባ ጊዮርጊስ እህል ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮ እስከ አሁን በገዳሙ አለ፡፡

  አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረውና ጓደኞቹ በትምህርት ሲቀድሙት ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም
በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ጀመረ፡፡ ሁልጊዜም በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከየአባቶቻችን አምላክ፣ የምህረት ጌታ፣ ሁሉን በቃልህ የፈጠርክ፣ ሰውንም በረቂቅ ጥበብ የፈጠርክ አቤቱ አንተ ከልዑል ጌትነትህ ጥበብን ስጠኝ በእውነትም አትናቀኝ አኔ ባርያህ ነኝና የባርህም ልጅ ነኝና” እያለ በጠለቀ ተመስጦ ልቦና እንባን በማፍሰስ ይጸልይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በነሐሴ 21ኛው ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና «አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ» አለችው፡፡ ጽዋዕ ልቦናም አጠጣችው፡፡

 ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ የዜማ የቅኔና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የያሬድን ዜማ ከአቡነ ሳሙኤል ዘጋርማ እንደተማረው ገድሉ ይነግረናል፡፡ በዚያ ዘመን በዐፄ ዳዊት አማካይነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያሬድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድ ተሾሞ ያስተምር ነበር፡፡

  የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋልወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእም አሜሃ አሐዙ ይስአሉ እም ኀቤሁ ኩሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኩሉ ቃለ ማኅሌት፡፡

 ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡

  አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስሥላሴን አንድ ገጽ” ብለው ያምናሉ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ውሸት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡

 በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በድንግልና ጸንቶ ለመኖር እንደሚፈልግ ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው መነኮሰ፡፡

   ከመነኮሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ታላላቆች፣ ለንቡራነ እድና ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡

 አባ ጊዮርጊስ በሸግላ በነበረ ጊዜ በወባ በሽታ ታምሞ ሊሞት ደርሶ እንደ ነበር ገድሉ ይናገራል፡፡ ታምሞ በነበረ ጊዜ አንድ ሌሊት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተገልጠውለትከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ልንወስድህ” መጣን አሉት፡፡ እርሱምየድርሰት ሥራዬን ሳልሠራና እግዚአብሔርንም አብዝቼ ሳላመሰግነው አሁን አትውሰዱኝ” ሲል ለመነ፡፡ እነርሱም ልመናውን ተቀብለውት ከሕመሙ ፈውሰውት ሄዱ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከበሽታው እንደ ተፈወሰ ወድያው የድርሰት ሥራውን የጀመረው፡፡

 የመጀመርያ መጽሐፉን ጽፎ እንደ ጨረሰ ጠፍቶበት እንደ ነበር ገድሉ ይተርካል፡፡ በቤቱ ውስጥ የነበሩትን መጻሕፍት ሁሉ እያገላበጠ ቢፈልገውም ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ሌሊት በአገልግሎት ላይ እያለ እመቤታችን ተገልጣለምን አስቀድመህ ሳትነግረኝ ጻፍክ?” ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም «አንቺን ደስ ያሰኘሁ መሰሎኝ ነውና ይቅር በይኝ» ሲል መለሰላት፡፡ ከዚህ በኋላ የድርሰት ሥራውን ፈቅዳለት ተሠወረችው፡፡ወሶቤሃ በርሃ ልቡ ከመ ፀሐይ ወሐተወ ውስተ ኅሊናሁ ባሕረየ መለኮት፤ ወነጸረ ኩሎ ኅቡአት - ከዚህ በኋላ ልቡ በራለት፣ ኅሊናውም ነገረ መለኮትን ዐወቀ፡፡ የተሠወረውንም ሁሉ ተመለከተይላል ገደሉ፡፡

  የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን  የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ ስለ አርጋኖን ድርሰቱ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጠዋልወሰመዮ በሠለስቱ አስማት ዘውእቶሙ አርጋኖነ ውዳሴ፣ ወመሰንቆ መዝሙር ወእንዚራ ስብሐት - በሦስት ስሞችም ሰየማቸው እነርሱም አርጋኖነ ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙርና እንዚራ ስብሐት  ይባላሉ፡፡

  እመቤታችን አርጋኖንን ስለ ወደደችለት ዚማት በሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም”  ብላዋለች፡፡ ዐፄ ዳዊትም ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም እንዳጻፈው ገድሉ ይገልጣል፡፡

  ከዚህ በኋላ የደረሰው ደርሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን /ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን/መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ ይህን መጽሐፍ «መጽሐፈ ብርሃን» ብሎ የሰየመበትን ምክንያት ገድሉ ሲያበራራአስመ ውእቱ ያበርህ ወያስተርኢ ፍናወ ስብሐቲሁ ለእግዚአብሔር ወፍናወ ስብሐቲሆሙ ለትጉኃን ወለኩሎሙ ማኅበረ ቅዱሳን ልዑላነ ብርሃን ወዓዲ ይነግር እንዘ ያስተሐውዝ ውዳሴሃ ለድንግል ንጽሕትየእግዚአብሔርን የምስጋናውን መንገድ ያበራል /አብርቶ ያመለክታልና፣ ልዑላነ ብርሃን የሆኑትን የማኅበረ ቅዱሳንንና የትጉኃንን የምስጋናቸውን መንገድ ያመለክታልና፣ የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና/ ይላል፡፡

  በዚያ ጊዜ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቁርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግንይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም” ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡

  አባ ጊዮርጊስና አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተገናኙት አባ ጊዮርጊስ ወደ ዳሞት በሚጓዝ ጊዜ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ አለባበሱ እንደ ተርታ ሰው በመሆኑ አቡነ ሳሙኤል በመጀመርያ አላወቁትም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አባ ጊዮርጊስ ቅር ብሎት ወደ ዳሞት ተመለሰ፡፡ እንደ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ግምት ሁለቱን ያላግባባው ሥርዓተ ጸሎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚያ ጊዜ በዋልድባ ሥርዓተ ጸሎቱ ሰባት ጊዜ በቀን መጸለይን የሚያዝ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በቀን ሰባት ጊዜ ብቻ መጸለዩ ለእግዚአብሔር ያንሰዋል ብሎ ያምን ነበር፡፡ ምናልባትም በዚያን ጊዜ 22 ሰዓት የሚፈጀውን ሰዓታት ሳያዘጋጅ አልቀረም፡፡

  ከዚህ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ ሆነ፡፡ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ከጠየቀ በኋላ የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀቱን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቅዳሴያት ደራሲያቸው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍንጭ የሚሰጠን ይሆናል፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው አንዳንድ ካህናት የአባ ጊዮርጊስን ቅዳሴ ተቃውመው ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አርዮስን በቀጣበት መንገድ ቀጥቷቸዋል፡፡

   አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

   ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀ መርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- “እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?” ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

 በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱምእንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ” ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?” በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡

 አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱበምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም”  የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡

 ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ” የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

  አባ ጊዮርጊስ በወኅኒ ቤት እያለ ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ ውዳሴ ሐዋርያት የተሰኘውንና ከሐምሌ 5 ጀምሮ በ12ቱም ወራት የሚመሰገኑበት የሐዋርያትን ምስጋና የያዘውን መጽሐፍ ያዘጋጀው በወኅኒ በነበረ ጊዜ ነው፡፡

  ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስ ከማ /ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ/ እንደ ነበሩ ገድሉ ይናገራል፡፡

  ነገር ግን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡

  የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ 1399 . መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡

   አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ ዳግመኛም የጦሩ አዛዥ የሚሆን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ፍካሬ ሃይማኖት  የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱና ባነበቡ ጊዜ በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቁስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች ብለው አደነቁይላል ገድሉ አባ ጊዮርጊስ ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘውንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውንና የምታወግዘውን በግልጥና በዝርዝር የጻፈበትን መጽሐፍ እንዴት እንደ ደረሰው ሲገልጥ፡፡ ፍካሬ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እምነት በግልጥና በዝርዝር በማስቀመጥ ረገድ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመርያው ሥራ ይመስላል፡፡ የዘረዘራቸው የመናፍቃን ስሞችን እና ክህደታቸውን ስናይ በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንት ስለ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያላቸውን ዕውቀት ያሳየናል፡፡

  አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት ነበር፡፡ ገድሉ እንደሚተርከው በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሰዎች የርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ የተነሣ መከበሩ አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡

 ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዐለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ፀፀተው፡፡ አገልጋዮቹንም ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠውአባ ጊዮርጊስ ሞቷል” ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡

  አባ ጊዮርጊስ ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት አውሎ ንፋስን ላከው፡፡ አውሎ ንፋሱ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሄድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለ መሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም እሳት አስነድዶ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውኃም ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ጨመራቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስንም ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡

 አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀበለው፡፡ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከውም ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳ፡፡

 ከግዞት ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን ተገልጣለት መከራው ሁሉ እንደ ሐዋርያት መሆኑን ገለጠችለት፡፡ አእምሮውን ብሩህ፣ ልቡናውን ትጉኅ የሚያደርግ እጅግ ብዙ ምሥጢር ነገረችው፡፡ ተሰናብታው ከሄደች በኋላእጅግ ብዙ መብራት አቅርቡ አምስት ፈጣን ጸሐፊዎችንም አምጡብሎ አዘዘ፡፡ እርሱ እየነገራቸው እነርሱ እየጻፉ እረፍት ሳያደርጉ ሦስት ቀን ሙሉ አስጽፎ መጽሐፈ ምሥጢር የተሰኘውን መጽሐፍ ፈጸመ፡፡ አምስቱ ጸሐፍትም የየድርሻቸውን አጠናቅቀው በአንድ አደረጉት፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህን ተመልክቶ በእጅጉ አደነቀ፡፡እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አፍ ተናገረ እንጂሲል በወቅቱ መመስከሩን ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህንም መጽሐፍ መጽሐፈ ምሥጢር ሲል ሰየመው፡፡ የጻፈው 1409 . እድሜው 52 በደረሰ ጊዜ ሲሆን የዚህ መጽሐፍ ቅጅ በነጋድያን እጅ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ በወቅቱ ሄዶ እንደ ነበር ገድሉ ያስረዳል፡፡

  ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ ምድረ ሰዎን የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጥቶት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰዎን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለ ነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አደረገ፡፡

 ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1417 . 60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡

  እስካሁን ድረስ ያሉን ምንጮች የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ቁጥራቸው ከዐርባ በላይ እንደሆኑ ይገልጣሉ፡፡ በስም የምናውቃቸው ግን የሚከተሉትን ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡

1. ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት

2. ኖኅተ ብርሃን /ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል/

3. ውዳሴ መስቀል

4. ቅዳሴ

5. ውዳሴ ሐዋርያት

6. አርጋኖነ ውዳሴ

7. ፍካሬ ሃይማኖት

8. መጽሐፈ ምሥጢር

9. ውዳሴ ስብሐት

10. እንዚራ ስብሐት

11. ሕይወተ ማርያም

12. ተአምኖ ቅዱሳን

13. መጽሐፈ ብርሃን

14. ጸሎት ዘቤት ቤት

 ጸሎቱና በረከቱ ከመላ ሕዝበ ክርስቲያን ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን አሜን!!

ምንጭ፡- 1.የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች በዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ገጽ 591-605
       2.መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 5-9

5 comments:

  1. kale hiwot yasemaln..........gin "yimeslegnal" "meselegn" yemilutn ababaloch btarmuachew melkam new..... God bless u

    ReplyDelete
  2. bewnetu yabatochachin tegadilona tirufat lasawekachihun ejig adirgen be EGIZIABIHER sim enameseginalen

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን:: የአባታችን የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጸሎቱና በረከቱ ከመላ ሕዝበ ክርስቲያን ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን አሜን!

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን:: የአባታችን የአባ ጊዮርጊስ ጸሎቱ በረከቱና አማላጅነቱ ከመላ ሕዝበ ክርስቲያን ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን:: አሜን!

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን thanks for sharing

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount