Wednesday, August 15, 2012

ምሥጢረ ደብረ ታቦር!

ገብረ እግዚአብሔር ኪደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም.)፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ለደቀመዛሙርቱ “ሰዎች  የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠይቋቸው ነበር፡፡ እነርሱም “አንዳንዶች ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ቅዱስ ነውና ኤርሚያስ ነው ይሉሀል፤ አንዳንዶቹ ድንቅ የሆነ ልደትህንና የምታጠምቀውን አዲስ ጥምቀት አይተው መጥምቁ ዮሐንስ ነው ይሉሀል፤ ሌሎች ደግሞ ለአባቶችህ ቤት ያለህን ቅናት አይተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” እያሉ መልሰውለት ነበር፡፡ ጌታችንም መልሶ፡-እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የሐዋርያት አፈጉባዔ የሚሆን ሊቀ ሐዋርያት ዱስ ጴጥሮስምአንተ ክርስቶስ  የሕያው እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ነህብሎ መልሷል፡፡ ጌታምየዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም (ምድራዊ መምህር) ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህብሎታል፡፡ 
 ከዚህ በኋላ ጌታችን በኢየሩሳሌም ካህናት ሊቀካህናት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለሚያደርሱበት መከራ ስለሚሞተው ሞት ይነግራቸው ጀመር፡፡ ሰይጣንም አስቀድሞ በቀዳማይቱ ሔዋን እንዳደረገው አሁንም በስምዖን ጴጥሮስ አንደበት ወዳጅ መስሎ “አይሆንም አይደረግም” በማለት መከራከር ጀመር፡፡ ጌታችን ግን ጴጥሮስን አድርጎ ሰይጣንን ይገስጸው ጀመር፡- “ጴጥሮስ ሆይ! የእኔ አመመጣጥ ለምን እንደሆነ አታስተውልምን? የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በቤተልሔም ተወልጄ ከሴቶች ለሚወለዱ ሕፃናት ሁሉ ደስታ እንደሆንኩላቸው አሁንም የእኔን እዚያ መውረድ እየተጠባበቁ የሚገኙትን ቅዱሳን ወደ ገነት እመልስ ዘንድ ሲዖል መሄድ አለብኝ፡፡ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን ይህን ሊያዩ ይመኛሉና፤ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ይናፍቃልና፡፡ ስለዚህ አያቸው ዘንድ መውረድ አለብኝ፤ እጎበኛቸው ዘንድ ልሞት ልሰቀል ይገባኛል፡፡ በእውነት ሰይጣን ካልሆነ በቀር የእኔን መሰቀል የሚቃወም የነፍሳትም ነፃ መውጣት የማይናፍቅ ማን ነው? አንተ ጴጥሮስ! ይህን ሁሉ የምትለኝ ሰይጣን በአንተ ተመስሎ አንድም አንተው ራስህ ለእኔ ካለህ ፍቅር የተነሣ መሆኑን ብረዳም ጀሮህ ትንቢተ ነቢያትን ባይሰማ ይልቁንም ዓሣ ማጥመድን ብቻ ስለሚያውቅ ነውና ወግድ” አለው፡፡   
  ይህም በሆነ በሰባተኛው ቀን ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ማለትም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ ክርስቶስ ባይሞት እንዴት ያለ ክብር እንደሚቀርባቸው ያሳያቸው ዘንድ ምስክርም እንዲሆኑ እነዚህን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ይዞ ወጣ፡፡ በዚያም እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ መድኃኔዓለም ክብረ መንግሥቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን ገልጠላቸው፡፡ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ደብረታቦር የዚህ ታሪክ መታሰቢያ ነው ፡፡ በዚህ ዕለት ሕፃናት ጅራፋቸውን ገምደው እያስጮኹ ይጨፍራሉ፡፡ ይኸውም ጅራፍ ሲጮህ እንደሚያስደነግጥ ሁሉ ከጌታ ጋር የነበሩት ሦስቱ ደቀ መዛሙርትም አብ በደመና ሆኖ ሲናገር መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡

  ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራራባዊ ደቡብ በኵል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣  ከናዝሬት ከተማ በስተምሥራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ተራራው ከባሕር ወለል በላይ 572 ከፍታ አለው፡፡ ብዙ ሰዎች ከላይ ወደታች ሲታይ ታቦር ተራራ ቅርጹ የተገለበጠ የሻይ ስኒ ይመስላል ይላሉ ፡፡

        ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡
1.           ትንቢቱን ለመፈጸም
    ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ” እንዲል /መዝ. 8812/፡፡

2.           ምሳሌውን ለመፈጸም

 ይህ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል /መሳ.46/፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበር፡፡… ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር” /መሳ 4.1-3/፡፡ ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልናከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋልየተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው  /1ቆሮ. 10-13/፡፡ እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡ እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱምእግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ” /መሳ. 4.15/፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ፡፡በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር /ዕብ. 11.32-34/፡፡ ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርግበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን( የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ ከዚህም በመነሣት ነውበዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው” የሚባለው ፡፡
            ለምን ሦስቱን ሐዋርያት  ብቻ ይዞ ወጣ?
1. ጌታ “እሞታለሁ፤ እሰቀላለሁ” ባለው ጊዜ ጴጥሮስ “ልትሞት አይገባም፤ ይህ ላንተ አይገባም” ብሎ ተቃውሞት ነበርና በአብ ቃል “እርሱ ያላችሁን ስሙት፤ ይህ ለአንተ አይገባም አትበሉት፤ አትቃወሙት” ለማለት፡፡
2. ጌታ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ደቀመዛሙርቱን በጠየቃቸው ጊዜ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎት ነበርና አሁንም አብ “አዎ ልክ ነህ! እመለክበት ዘንድ ለተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ለማረጋገጥ፡፡
3. ለፍቅሩ ስለሚሳሱ ነው፡፡ ይህም በዕብራይስጡ ኬፋ በግሪኩ ጴጥሮስ ፤ በግዕዙ ኰኲሕ (ዐለት) የተባለው የዮና ልጅ ስምዖን ጌታችን  “እሞታለሁ” እያለ ሲናገርአይሁንብህ” ማለቱ አስቀድመን እንደተናገርን ለጌታ ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ ነው” ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡ ዮሐንስም በወንጌል “የጌታ ወዳጅ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ያዕቆብ ደግሞ ጌታን በእጅጉ እንደሚወደው በኋላ ታውቋል፡፡ ይኸውምእኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ?”  /ማቴ.20፡20/ሲባሉአዎ” ብሎ መመለሱና በዚህም በሄሮድስ ዘአግሪጳ ሰማዕት ሆኖ መሞቱ ምስክር ነው፡፡
4. በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ኃጥእ ሰው የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ያርቁታልእንዲል /ኢሳ 26:13/ እርሱን ጥሎ አሥራ አንዱን ወደ ተራራ ይዞ ቢወጣ ከምሥጢር ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት እንዳይል፡፡ ያም ባይሆን  ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ለምን ይከለከላሉ ቢሉ አልተከለከሉም በርዕሰ ደብር (በተራራው አናት) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጸው ምስጢር በእግረ ደብር (በተራራው ግርጌ) ለነበሩት ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህም በደብረሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠ ምሥጢር በከተማ ለነበሩት ለኤልዳድና ሙዳድ እንደተገለጠ ማለት ነው /ዘኁ.1126/፡፡
              ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
1.  በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን ፡-በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀውሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርምጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይምብሎት ነበር /ዘጸ. 33.1323/፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡ እንዲህ ማለቱአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ” ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን በአካለ ነፍስ አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡ 
2. ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡-አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶየእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡  ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡ 
3.  በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትንሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱሙሴ ነው ይሉሃል እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ አምላከ ሙሴ እግዚአ ኤልያስ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡
4. አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ /ዮሐ.9፡16፣ 10፡33/ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡
5. ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡
6. የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡
7. ጽድቃቸው ከእነዚህ ከሙሴና ከኤልያስ የበለጠ ሊሆን እንደሚገባ ለማሳየት /ማቴ.5፡20/፡፡ ምክንያቱም ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ቢመራ ምድረ ፍልሥጥኤምን ለማውረስ ነው፡፡ እነዚህ ግን ሕዝቡን መርተው የሚያስገቡት መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ኤልያስ ሰማያትን ቢለጉምም ከጊዜአዊ ዝናም ነው፡፡ እነዚህ ግን ለዘለዓለም መንግሥተ ሰማያትንም የመለጎም ሥልጣን አላቸውና፡፡

  ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ሲል ተደምጧል፡፡ ይህም የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ ቃል በቃል (Literaly)ስናየው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ “አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ እነዚህ መከራ ያደርሱቡኛል ይገድሉኛል ያልካቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዳይመጡ በደመና እየጋረደ፣ ቢመጡም አልያስ እሳት እያዘነመ እያባረራቸው በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ሲሆን ምሥጢራዊው መልእክቱ ግን “የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በሚታመንበት፣ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ሰይጣን ድል በተደረገባት በታቦር ተራራ ምሳሌም በምትሆን በወንጌል ሕይወት፣ አንድም በቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ነው፡፡
             ታቦር ተራራ የወንጌል ምሳሌ ነው!
     ተራራ ሲወጡት ያደክማል፣ ከወጡት በኋላ ግን ጭንጫውን፣ ግጫውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ትከብዳለች በኋላ ግን ጽድቅን እና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡

            ታቦር ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው!

.     በታቦር ተራራ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ኤልያስና ሙሴን፣ ከሐዲስ ኪዳን ሦስቱን ሐዋርያት እንደተገኙ በቤተክርስቲያን ብሉይ ከሐዲስ እንዲነገር ያጠይቃል ሐዋርያት የሰበኩት ወንጌል አስቀድመው ነቢያት በምሳሌና በትንቢት የተናገሩት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ነቢያት በቀየሱ ሐዋርያት ገሰገሱ” እንዲል ጳውሎስም በሐዋርያት በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” ይላልና /ኤፌ 220/፡፡
.    በታቦር ተራራ ከመዓስባን (ባለትዳር) ሙሴን ከደናግል ደግሞ ኤልያስ እንደተገኙ በቤተክርስቲያን በድንግልና የሚኖሩ መናንያን መነኮሳት፣ በሕግ በሥርዓት የሚኖሩ ባለትዳሮችም ይገኛሉና፡፡

ታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው!

1.     ተራራ በብዙ ችግር እንዲወጡት ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናልና /ሐዋ 1422/፡፡
2.    በታቦር ተራራ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያት እንደተገኙ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም፣ ሐዋርያትም አንድ ሆነው ይወርሷታልና፡፡
3.    በታቦር ተራራ ከመዓስባን ሙሴ ከደናግል ደግሞ ኤልያስ እንደተገኙ መንግሥተ ሰማያትንም ደናግልም መዓስባንም በአንድ ላይ ይወርሷታልና፡፡
4.    በታቦር ተራራ ሞተው ከተቀበሩት መካከል ሙሴን በብሔረ ሕያዋን ካሉት ደግሞ ኤልያስን እንደመጡ መንግሥተ ሰማያትንም ሞተው የተቀበሩትም በብሔረ ሕያዋን ያሉትም በአንድነት ይወርሷታልና፡፡

 በአጠቃላይ ታቦር ተራራ የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የተመሠከረበት፣ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት የተሰጠበት ፈጣሪ ከቅዱሳን ሰዎቹ ጋር የተገኘበት  በልበ ሐዋርያት የነበረ ሰይጣን ድል የተደረገበት፤  የሐዋርያት በተለይም የሦስቱ ባለሟልነት የተገለጠበት፤ አሉባልታና ተራ ወሬ የከሸፈበት፤ የቅዱሳንን ክብር ለሚያናንቁ ተራራም እንኳንቅዱስእንደሚባል የተማርንበት፤  የብሔረ ሕያዋን መኖር የተመሰከበረበት የትንሣኤ ሙታን ዋስትና የተገለጠበት የክብር ሰገነት፣ የምሥጢር መቅደስ፣ ታላቅ ትምህርት ቤትም ጭምር ነው፡፡
 ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እስከ መጨረሻዋ ሕቅታ ድረስ በታቦር ተራራ በተመሰለች ቤተክርስቲያን በሃይማኖታችን ጸንተን የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን!!

4 comments:

  1. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete
  2. betam des yemil neger new betkerstanaiachen habtam nat

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ተባረክ !

    ReplyDelete
  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount