Sunday, August 26, 2012

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

   ኢትዮጵያዊው ሊቅና ጻድቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ታላቅ ቦታ የያዘ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡  አባ ጊዮርጊስ የተወለደው 1357 . በወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ ወላጆቹ ልጅ ስለሌላቸው ዘወትር እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት መሆኑን ድርሳነ ዑራኤል ይተርክልናል፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ አምኃ ጽዮን ይባላሉ፡፡  አባቱ ጠቢብና የመጻሕፍት ዐዋቂ፤ የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳንሥዕል ቤትከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ሲሆን የሰግላ ሀገረ ገዥም ነበር፡፡  የአባ ጊዮርጊስን እናት እምነ ጽዮን ከወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና/  ከሹማምንት ወገን የሆነች ደግ ሰው ነበረች፡፡

 አባ ጊዮርጊስ በመጀመርያ እናቱ ፈሪሐ እግዚአብሔርን እያስተማረች በጥበብና በዕውቀት አሳደገችው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ነበር፡፡ ምክንያቱም አባቱ የመጻሕፍት ሊቅ መሆኑን ስንመለከትና ገድሉም አባ ጊዮርጊስን በተመለከተወሶበ ልሕቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆንየሚለውን ስናጤነው አባቱ የመጀመርያውን ደረጃ ትምህርት ካስተማረው በኋላ በ1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጳጳስ የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መተርጕም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል ማለት ነው፡፡
                                             
  ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ተላከ፡፡ ወደ ሐይቅ የገባው በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መሆኑን ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያዩ ሊቃውንት የሚገኙባት፣ በብዙ መጻሕፍት የተሞላችና ዙሪያዋን በሐይቅ በመከበቧ የተማሪን ሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነች ቦታ ናት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎችይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ ?” ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረውብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግንአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግልብሎ እንደ ገና ላከው፡፡

 አባ ጊየርጊስ በቀለም ትምህርት እንዲሰንፍ ምክንያት የሆነው ከመማር ይልቅ በሥራ እየደከመ የገዳሙን አባቶች መርዳትና ብሕትውናን ይማርከው ስለ ነበር ነው፡፡ በገዳሙ  እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር ፡፡ አባ ጊዮርጊስ እህል ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮ እስከ አሁን በገዳሙ አለ፡፡

  አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረውና ጓደኞቹ በትምህርት ሲቀድሙት ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም

Friday, August 24, 2012

ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ- የዮሐንስ ወንጌል የ35ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.7፡37-ፍጻሜ)!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

  በ33ኛ ሳምንት ጥናታችን እንደተናገርን አይሁድ የዳስ በዓልን የሚያከብሩት ሰባት ቀን ሙሉ እንደ አንድ ቀን ነው /ዘሌ.23፡34/፡፡ በበዓሉ እኩሌታ ማለትም በአራተኛው ቀንም ጌታ በሕቡዕ ያይደለ በይፋ በስዉር ያይደለ በግልጥ ማስተማሩን መገሰጹን ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በበዓሉ በኋለኛው ቀን፣ የደስታ ቀን ብለው በሚያከብሩበት በመካተቻው፣ በመጨረሻው፣ በመሰባበቻው ቀን እንዲህ ብሎ አሰምቶ ተናገረ፡- ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” /ቁ.37-38/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- ማንም ጽድቅን የተጠማ ቢኖር፣ ማንም ሕይወትን የናፈቀው ቢኖር፣ ማንም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የሚፈልግ ቢኖር፣ ማንም እኔ የምሰጠውን የጽድቅ ውኃ መጠጣት የሚሻ ቢኖር፣ ማንም እኔ የምሰጠውን ሀብታተ ምሥጢራትን ጸጋውን መቀበል የሚፈልግ ቢኖር… ወደ እኔ ይምጣ፤ በእግረ ሥጋ ሳይሆን በእግረ እምነት ወደ እኔ ይቅረብ፤ በእግረ በቀል ሳይሆን በእግረ ፍቅር ወደ እኔ ይጠጋ፤ ቀርቦም የምሰጠውን ውኃ ይጠጣ፤ መጥቶም ከዙፋኔ የሚወጣውን እንደ ብርሌም ሚያንጸባርቀው የሕይወትም ውኃ ከሚሆን ወንዝ ይጠጣ ይቀበል /Augustine, On the Gospel of St. John, tractate 32:2./፡ ሙሴ ከሰጠው ጊዜአዊ ጥምንም ከሚያረካው ውኃ ተላቆ ይምጣና አማናዊውን የሕይወት ውኃ ምንጭ ዐለት በውስጡ ያኑር፡፡ ይህን እንዴት ማግኘት እችላለሁ ብሎ የሚቸገርም ከቶ አይኑር፡፡ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው የተናገሩለት፣ ሱባዔ የቆጠሩለት መሲሕ ክርስቶስ እርሱ ነው ብሎ በእኔ ይመንና መጽሐፍ እንደተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል (በእርሱ ምክንያት ቃሌ ሲነገር ልጅነት ሲሰጥ ብዙዎች ሲያምኑበት ይኖራል)፤ በፈሳሾች አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች ይሆናል /ኢሳ.44፡3/፤ ከተድላ ፈሳሽ ይጠጣል /መዝ.36፡8/፤ የሕያዋን ምንጭ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል /ኤር.2፡13/፤ የእግዚአብሔርን ቸርነት ይቀምሳል ያያልም /መዝ.34፡8/፤ በኢዩኤል ነብይ የተነገረው ትንቢት በእርሱ ላይ ይፈጸማል” /ኢዩ.2፡28-32፣ Saint Cyril the Great, Commentary on the Gospel of John, Book 5/፡፡

 ይህም አስቀድመን እንደተናገርን ያመኑበት ሰዎች ሊቀበሉት ስላላቸው ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ የተናገረው ነው፡፡ ይህን ያለው ምእመናን በመንፈስ ቅዱስ ስለሚያገኙት ምሥጢር፣ በመንፈስ ቅዱስ ስለሚገኙት ልጅነት ሲገልጽ ነው፡፡ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ (ያስተውሉ! ከዚያ በፊት ክብሩ በሰው ዘንድ አልታወቀም አልተገለጠም ነበር ለማለት እንጂ ሎቱ ስብሐትና ክብር አልነበረውም ማለት አይደለም፡፡ በብዙዎች ዘንድ ጌታ መሆኑ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ የታወቀው ከስቅለቱ በኋላ ከትንሣኤም በኋላ ስለ ሆነ ነው) ስላልተሰቀለ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና /ቁ.39/። ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት በሰው ልጆች ላይ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በነቢያት ነበረ፤ መጽሐፍ እንደተናገረ አስቀድሞ በእመቤታችን ላይ ወርዷል፤ ወንጌል እንደመሰከረ መንፈስ በስምዖን አረጋዊ ላይ ነበረ፤ በነቢይቱ ሀና ላይ ነበረ፡፡ ስለዚህ አሁን እየነገረን ያለው አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከበዓለ ኃምሳ በኋላ ሊሆን ስላለው ሁኔታ ነው /Augustine, tactate 32:7. /፡፡

  ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ፣ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ” የሚል የጌታችን የፍቅር ግብዣ ሲያደምጡ በአራት ምድብ ተከፋፈሉ፡፡ በአንደኛው ምድብ የነበሩት ይህ በእውነት ሙሴ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል ብሎ የተናገረለት ነቢዩ ነው” አሉ /ዘዳ.15፡18/፤ ሁለተኛው ምድብ የነበሩት፡-ነቢዩ አይደለም ይህ ክርስቶስ ነው” አሉ፤ በሦስተኛው ምድብ የነበሩትና አወቅን ጠነቀቅን ያሉት ደግሞ፡-ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን?”  በማለት ጌታ በናዝሬት ገሊላ ማደጉ ናዝሬት ገሊላ የተወለደ ስለመሰላቸው ተደናገሩ /መዝ.132፡11፣ ሚክ.5፡2/። አራተኛው ምድብ ደግሞ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ከአለቆቹ ጋር ያበሩና ጌታን ለመግደል የሚያስቡ ሎሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሎሌዎች ክርስቶስን ለመያዝ ወደው ነበር ይዘውም ለአለቆቻቸው አሳልፈው ይሰጡት ዘንድ ሽተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቃሉ ተማርከው አምነውበታልና አንድም ጊዜው አልደረሰምና ይህን ማድረግ አልተቻላቸውም /ቁ.40-44፣ Saint Cyril the Great, Ibid/፡፡

 አስቀድመን እንደተናገርን የመጨረሻው ቀን ማለት አይሁድ በደስታ የሚያከብሩት ቀን ነው፡፡ ዛሬ ግን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የደስታ ቀን ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ የደስታ ምንጭ የሆነውን ክርስቶስን ሊገድሉበት ፈለጉ እንጂ እርሱን ተቀብለው ደስታቸውን ፍጹም ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡ ውስጣቸው በቅንአት ተጠፍሯልና ይህን የክርስቶስ ፍቅር ማየት አልተቻላቸውም፡፡ የደስታ ቀን በሆነው ዕለት መንፈሳዊ ተግባራቸውን ትተው ሊገድሉት የሚፈልጉትን ክርስቶስ ይጠባበቁ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፡፡

  ሎሌዎቻቸው (አራተኛው ምድብ ያልናቸው ናቸው!) ክርስቶስን ሳይዙ በመጡ ጊዜ፣ አስረን እናመጣዋለን ብለው ሄደው አምነው እየተደነቁ በመጡ ጊዜ፡-ለምድነው ያላመጣችሁት?” ብለው ተቈጡዋቸው። ሎሌዎቹ ግን አሳማኝ ምክንያት ነበራቸው፡፡ አለቆቻቸው ባይቀበልዋቸውም እንዲህ ሲሉ ሳይፈሩ አስረድዋቸው፡-አለቆቻችን ሆይ! ይህን ሰው ለምን ይዛችሁት አልመጣችሁም ብላችሁ የምቆጡን አትሁኑ፤ ይህ ሰው እንደተናገረው በዓለም ታይቶም ተሰምቶም ከቶ ከቶ አይታወቅም፡፡ እኛ መጻሕፍትን እናውቃለን ብለን እናስብ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ገና አላዋቂዎች መሆናችንን ዛሬ አይተን ተረድተን መጣን፡፡ እርሱ የሚናገረው ነገር ፍጹም መለኰታዊ ቃል ነውና፡፡ ይህ ሰው የሚናገረው ማንም ምድራዊ መምህር ሊያስተምረው ሊናገረው የሚቻለውም አይደለምና፡፡ ስለዚህ ይህን ሰው ፈጽመን ልንገድለው አይገባንም፡፡ በአፉ ተንኰል አላገኘንበትምና እንደ ሕጋችን ንጹሕ ሰው ልንገድል አይገባንም፡፡ እንደውም በሰቂለ ሕሊና ስናስተውለው ስናደምጠው እንደ እግዚአብሔር በኃይልና በሥልጣን ይናገራል እንጂ እንደ ዕሩቅ ብእሲ አይናገርም፡፡ ምክንያቱም ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ያለ ነቢይ ሰምተንም አይተንም አናውቅምና፡፡ ታላቁ አባታችን ሙሴ እንኳን አንድ ቀንም ቢሆን በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ሲል አልሰማነውምና፡፡ ይህ ሰው ግን ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ፤ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል እያለ በሥልጣን ይናገራል፡፡ የሚናገረው ሁሉ ዕሩቅ ብእሲ የሚናገረው አይደለም” ብለው መለሱላቸው /ቁ.45-46፣St. Cyril the Great, Ibid/። ተወዳጆች ሆይ! የክርስቶስን ፍቅር የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን አለቆች እጅግ ከማፍቀሩ የተነሣ እንዲጠፉበትም ካለመፈለጉ የተነሣ ይመለሱለት ዘንድ ልባቸው ደንዳና ሆነ እንጂ ሊያደምጥዋቸው በሚችሉ ሰዎች ሲያስረዳቸው ነበርና፡፡

  ስለዚህ አለቆቹ ጭራሽ እንዲገባቸው አልፈቀዱምና ባሰባቸው፡፡ ሎሌዎቻቸውንም፡-እናንተ ደግሞ እንደነዚያ ሐዋርያት ሳታችሁን?” አልዋቸው /ቁ.47/፡፡ በክርስቶስ ማመን መሳት ነው አሉዋቸው! የሕይወትን ውኃ ማግኘት መታለል ነው አሉዋቸው፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ሞት ነው አልዋቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን እንዲህ አሳምኖ እንዳይወስድባቸው በመጨነቅ ለመሆኑ ከተሳሳቱት ሕዝብ በቀር ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?” ብለው ጠየቁዋቸው /ቁ.48/፡፡ አሁንም ብስጭታቸውን ቀጠሉና አስተምረውት የማያውቁትን ሕዝብ ሕግን ኦሪትን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ብለው ሕዝቡን መሳደብ ጀመሩ፤ ሎቱ ስብሐትና ክርስቶስን “ዕሩቅ ብእሲ” አድርገውት ፍጡርን የሚያመልኩ እነዚህ የተረገሙ ናቸው አሉ /ቁ.49/። የአምላካቸውን ድንቅ ሥራ አይተው ያመኑትን ሕዝብ ሕግን የማያውቁ እያሉ ወቀስዋቸው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሕዝቡ አምላኩን አውቆ ስላመነበት ሊበሳጩ አይገባም ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሕግን የማያውቁና የተረገሙ ክርስቶስንም ከማመን የዘገዩ እነርሱ ራሳቸው ነበሩ /St. John Chrysostom, Homily 52/፡፡

 የሚደንቀው ግን ይህን አላዋቂነታቸው ይነግራቸው ዘንድ እግዚአብሔር በመካከላቸው ምስክር ማስቀመጡ ነው፡፡ እርሱም በሌሊት ቀድሞ ወደ ጌታ መጥቶ የነበረው የማታው ተማሪ ኒቆዲሞስ ነው /ዮሐ.3፡2/፡፡ ብስጭታቸውን በሰማ ጊዜ፣ ሕዝቡን አላዋቂ ሲሉት ባደመጠ ጊዜ፡-ኦሪታችን ሥራውን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ ሳይመረምር በሰው ላይ ይሙት በቃ ይፈርዳልን?” አላቸው /ቁ.50-51/ እውነት ነው! ኦሪት “ንጹሑን ሰው አትግደል” ትላለች /ዘዳ.19፡16-21/፡፡ ተራውን ሕዝብ በሕግ አፍራሽነትና በአላዋቂነት እየፈረጁና እየረገሙ እንጠብቀዋለን የሚሉትን ሕግ የሚያፈርሱት እነርሱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ አላዋቂዎች እነርሱ መሆናቸውን ኒቆዲሞስ ይነግራቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን አሁንም በኒቆዲሞስ ንግግር ተበሳጩ፡፡ “ለምን ታድያ ከገሊላ መጣ?” ብለው ከመጠየቅ ይልቅ ኒቆዲሞስን መስደብ ጀመሩ፡፡አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምር አንብብና እይ” ማለትን አስቀደሙ /ቁ.52/። ለምን ከገሊላ መጣ ብለው ቢጠይቁ ግን ክርስቶስ እርሱ ኢየሱስ ናዝራዊ ይባል ዘንድ በናዝሬት ገሊላ ያደገ ነገር ግን በቤተልሔም የተወለደ መሆኑን ባወቁ በተረዱ ነበር /ማቴ.2፡1 እና 23/፡፡ እነርሱ ግን ለስድብ ተቻኮሉ፡፡ በዚህ ንግግራቸው ኒቆዲሞስን እንደ አላዋቂ አድርገው በማየት መናቃቸው ነበር /St. John Chrysostom, Ibid/፡፡

 በመጨረሻም ምንም ሳይስማሙ  ተለያይተው እያንዳንዳቸው ወደየቤታቸው ሄዱ /ቁ.53/።

  ተወዳጆች ሆይ! ቅናት ክፉ ነው፡፡ ቅናት ዓይነ ልቡናን ያሳውራል፡፡ ቅናት ክርስቶስን ከማየት ይከለክላል፡፡ ቅናት ከዐለቱ (ከክርስቶስ) የሕይወት ውኃ እንዳንጠጣ ያደርጋል፡፡ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን እንዳንቀበል ያደርጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል” እንዳለ ቅናት የሚጐዳው ቅናተኛውን ነው /ምሳ.26፡27/፡፡ ቅናት ስለ እኛ የተቸነከረው በደምም የጨቀየውን ያ የፍቅር እጅ እንዳንመለከት ያደርጋል፡፡ ቅናት ተድላ መንግሥተ ሰማያትን እንድናጣ ያደርጋል፡፡ ወዮ አባት ሆይ! ራሳችንን እንዳንጐዳ በቅዱስ መንፈስህ ምራን! ከቅናት ከበቀል ጠብቀን! ፈሪሳዊ ቁጣና ብስጭት ከእኛ የራቀ ይሁን! አሜን! 

Wednesday, August 22, 2012

በአዲሲቷ ቆሮንቶስ መኖር(ለሕፃናት)!


  እንደምን አላችሁ ልጆች? ጾመ ፍልሰታ እንዴት አለፈ? ጾማችኋል አይደል? ጐበዞች!
ለዛሬ አንድ በጣም ጣፋጭ ታሪክ ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችሁ አይደል? ጐበዞች!
   ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ማርቆስ ሁል ጊዜ ከሚያጠናባት ክፍል ተቀመጠና መጽሐፍ ቅዱስን አንሥቶ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ 13 ላይ ስለ ፍቅር ማንበብ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ደጋግሞ ቢያነበውም ፍቅር ምን ማለት እንደሆነና እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ አልገባ አለው፡፡ እያሰላሰለ ሳለም በተቀመጠበት ወንበር እንቅልፍ ወሰደውና ደስ የሚል ሕልም አየ፡፡ ከነቃ በኋላም ያየውን ሕልም በወረቀት እንዲህ ብሎ ጻፈው፡-
“የሆነ አንድ ፌርማታ ላይ የአውቶብሳችንን መምጣት እየጠበቅኩ የነበርኩ ይመስለኛል፡፡ ከጎኔም አንድ ሰውዬ እንደኔ አውቶብስ ሲጠብቅ ቆሞ አየሁኝ፡፡ ሰውዬውም፡- እኔ ጋር ና አለኝ፡፡ እኔም ሄድኩና አንድ ላይ ተሳፈርን፡፡ ፊት ለፊትም እየተያየን ተቀመጥን፡፡ አውቶብሳችን መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም አውቶብሳችን የመጀመርያው ፌርማታ በምትሆን “አዲሲቷ ቆሮንቶስ” በምትባል ስፍራ ደረስን፡፡ ሁለታችንም ወረድን፡፡ አንድ ላይ በእግር እየተንሸራሸርን ሳለ (Walk እያረግን ሳለ) ሰውዬውን ቀና አልኩና ትኩር ብዬ ተመለከትኩት፡፡ እርሱም ፈገግ ብሎ አየኝ፡፡ በፊቱ የሆነ የሐሴትና የደስታ ነገር ይነበባል፡፡ እኔም በውስጤ ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡ በዚያ አከባቢ እንደኛ ሲንሸራሸሩ የማያቸው ሰዎች ሁሉም በእርጋታ ቀስ ብለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሳስተውላቸው አንድ ሰው ስንኳ ፊቱ የተቋጠረ የለም፡፡ እኛም ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ የፍቅር አደባባይ ወደተባለ አደባባይ ደረስን፡፡ በአደባባዩ መኻከል ላይ አንድ ትልቅ የውኃ ፏፏቴ (ፋውንቴን) ይታያል፡፡ አደባባዩ ዙርያው በትልልቅ ሥዕሎች (ቢል ቦርዶች) ተሞልቷል፡፡ ሰውዬም በጣቱ ወደ አንድ ሥዕል እየጠቆመ፡- “እዛ ጋር ያለው ትልቁን መስቀል አየኸው? ይህ ሥዕል የክርስቶስን ነገረ ስቅለት የሚያሳይ ሥዕል ነው” አለኝ፡፡ እኔም ክርስቶስ የተሰቀለበትን ሥዕል ለማየት ቀና ስል ወዲያው እንዲህ የሚል ጽሑፍ ከስሩ አነበብኩኝ፡- “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” /ዮሐ.15፡13/፡፡ ከአጠገቡ ወደ ነበረው ሌላ ሥዕል ስመለከት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በጉልበቱ ተንበርክኮ ሲጸልይ አየሁት፡፡ ሲጸልይ የተናገራቸው ቃላትም ከሥዕሉ ግርጌ እንዲህ ተጽፈዋል፡- “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” /ሐዋ.7፡60/፡፡ ዐይኔን ወደ ሌላኛው ማዕዘን ሳሻግረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ወዳጇን ታቅፋ አየኋት፡፡ እመቤታችን ያቀረበችው የምስጋና መዝሙርም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፡፡ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደረጋለች፡፡ የባርያይቱን ውርደት ተመልክቷልና፡፡… ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው” /ሉቃ.1፡46-49/፡፡ ወደ ሌላኘው ማዕዘን ዐይኔን ሳማትር የጠፋው ልጁን ለመቀበል ሐሴት የሚያደርገውን አባት ተመለከትኩት፡፡ በዚያም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ፡- “እንብላ ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልም” /ሉቃ.15፡23-24/፡፡
  ከዚያ በኋላ የሆነ መቀመጫ አገኘንና አንድ ላይ ተቀመጥን፡፡ ሰውዬውን “አደባባዩን በጣም ወደድኩት” አልኩት፡፡ ሰውየውም ሐሳቤን በአወንታ ተቀብሎ ራሱን ነቀነቀና እንዲህ አለኝ፡- “አየህ ልጄ! በዚህ አደባባይ ቂም በቀል የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ አንዱ በአንዱ አይቀናም፡፡ ሰላም ሲባባሉ ራሳቸውን ጐንበስ አድርገው በትሕትና ነው፡፡ ፍቅራቸው በጣም ልዩ ነው፡፡ ጌታ እንዳስተማረው እዚህ የምታየው ሰው ሁሉ ባደረገው ነገር “እኔ እኮ እንዲህ አደረግኩ” ብሎ አይመካም፡፡ ሁሉም ተራ በተራ ይደማመጣሉ እንጂ አንድ ሰው ስንኳ ድምጹን ከፍ አድርጎ አይናገርም፡፡ አንድ ስንኳ ተቈጥቶ የሚናገር የለም፡፡ እንደ አንተ ዓይነት ሕፃን በዚህ ቦታ ወይም በመማርያ ክፍል ከጓደኞቹ ጋር ከተቀመጠና እየተናገረ ከሆነ ሁሉም በጽሞና ያደምጡታል፡፡ እርሱም ሌሎች ሕፃናት ሲናገሩ በጽሞና ያደምጣቸዋል፡፡ ከጓደኛቸው አንዱ ምናልባት የተለየ ሐሳብ እንኳን ቢኖረው ያሳምናቸዋል እንጂ የእኔ ብቻ ነው ትክክል አይላቸውም፡፡ አሁንም ሌላ ሕፃን ምናልባት… ምናልባት ተሳስቶ ልክ ያልሆነ ነገር ቢናገር ቀስ አድርገው ልክ የሆነውን ይነግሩታል እንጂ ማንም ስለተሳሳተ አይስቅበትም፡፡ በቃ! እንዲህ እያደረጉ እከሌስ ጥሩ ልጅ አይደለም ተብሎ ሰው ሲያወራለት የነበረው ልጅ በአንዴ ይለውጡታል፡፡ እርሱም ጐበዝ ልጅ ይሆናል፡፡ ተራ በተራ ሁሉም ከተናገሩ በኋላ በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ይጨርሳሉ፡፡ ሲጨርሱም ሁሉም ተቃቅፈው እየተጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ ሲጫወቱ ደግሞ ሐቅ ሐቁን ብቻ ይነጋገራሉ እንጂ አይወሻሹም፡፡ የሚደባበቁት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ አንዱ በሚናገረው ነገርም ሌላው ያምኗል፡፡ እናም በቃ ሁሉም ነገር የሚያደርጉት በፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ወደየቤታቸው ሲገቡም ተጨባብጠው ደኅና እደሩ ተባብለው ይለያያሉ፡፡”
 ከዚህ በኋላ ሰውዬውን፡-“ወይኔ! ሁል ጊዜ እዚህ በሆንኩኝ? ከእነዚህ ልጆች ጋር መጫወት እፈልጋለሁ?” አልኩት፡፡ ሰውዬውም ልብ ውስጥ በሚዘልቅ ፈገግታ ራሴን እየዳበሰ እንዲህ አለኝ፡- “ይህን በሕይወትህ ማድረግ እኮ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሁሉም ነገር የምትወስነው አንተ ነህ፡፡ ልብህ በእነዚህ ልጆች እንዳየኸው አድርገህ ሁሉም ሰው እኵል የምታፈቅር ከሆነ በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ እዚህ ያየሃቸው ሁሉም በአንተ ሕይወት ይከናወናሉ፡፡ እንዲህ ስታደርግ ሁሉም ነገር በፍቅር ማየት ትጀምራለህ፡፡ ሊደርሱብህ የሚችሉ ችግሮች እንኳን በጣም ጠቃቅንና በቀላሉ የምትፈታቸው ይሆናሉ” አለኝ፡፡ እኔም ንግግሩን አቋረጥኩትና፡- “የሆነ የሰፈራችን ልጅ ዝም ብሎ የሚሰድበኝ ከሆነ ምንም ነገር ሳልመልስለት እንዴት እችላለሁ? እንዲህ ዓይነቱን ልጅስ እንዴት ልወደው እችላለሁ?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ሰውዬውም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፡- “አየህ! ፍቅር ከሁሉም ይበልጣል የተባለው ለዚህ ነው፡፡ አንተ በአዲሲቷ ቆሮንቶስ ከእነዚህ ልጆች ጋር መኖር ከፈለግክ ሁል ጊዜ ፍቅርን በተግባር በመግለጥ መለማመድ አለብህ፡፡ አንተ በምትኖርባት መንደር ሆነህ በልብህና በሐሳብህ እዚች ከተማ መኖር ትችላለህ፡፡ ፍቅር ከስጦታዎች ሁሉ እንደምትበልጥና የመልካም ምግባር ሁሉ እናት እንደሆነች ታውቃለህ?” ሲለኝ ከእንቅልፌ ብንን ብዬ ነቃሁ፡፡ ዓይኔን አሻሽቼ ዙርያዬን ስመለከት ሰው የለም፡፡ ባየሁት ሕልም ግን በጣም ተደሰትኩኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሴንም ሳዬው 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ እንደተገለጠ ነበር፡፡ 

 ልጆች! ታሪኩን ወደዳችሁት አይደል? ጐበዞች! “እኛም እንደ አዲሰቱ ቆሮንቶስ ልጆች እንሆናለን” እንደምትሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በሉ ሌላ ጊዜ ሌላ ታሪክ ይዤላችሁ እስክመጣ ድረስ ደኅና ሰንብቱ! እወዳችኋለሁ እሺ?!
(ምንጭ፡-The Coptic Orthodox Diocese of the Southern USA, Sunday school Curriculum, Grade 8)
   

FeedBurner FeedCount