Saturday, July 23, 2016

ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ በ‹‹ያ! ትውልድ›› መካከል … ‹‹ሞትህ ደጅ አደረ››! ክፍል ሁለት…!

በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.):- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ ጊዜ-ሞት፣ ድኅረ-ሞት...ሞትህ ደጅ አደረ!
ከሞመቱ በፊት ስብዕናውን ለመግደል ተሞከረ፡፡ ሲሞት የፓትርርክነት ወግና ሥርዓቱ ቀርቶ ሞቱን ለሙት በሚገባ ክብር ሳያደርጉለት ቀሩ፡፡ ድኅረ-ሞት ታሪኩን ለማስተሀቀር ተሽቀዳደሙ፡፡ ሞቱን፣ እረፍቱን ከለከሉት፤ ሞቱን ደጅ አሳደሩበት፡፡ ሰቆቃውን አበዙበት፡፡ ስለሰቆቃው መዛግብት ካኖሩልን ልናወጋ ጀምረናል፡፡
3.1. ቅድመ-ሞት…የተሐድሶ ጉባኤ (የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ)!
3.1.1. የ1966 ዓ.ም አብዮት እየጋመ፣ እየፋመ፣ እየተቀጣጠለ የንጉሡን ዙፋን በይፋ ለመገልበጥ 25 ቀናት ሲቀሩት ነሐሴ 11 ቀን 1966 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለኮ/ል አጥናፉ የሆነ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክሕነት እስከ አሁን በምትሠራበት ደንብና ሥርዓት ሥራዋን ስትቀጥል…ከጎን ሆኖ የሚሠራ›› በሚል ሽፋን ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥኝ ጊዜያዊ ጉባኤ›› ተቋቋመ(ድምጸ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ ሐምሌና ነሐሴ 1983 ዓ.ም፡ገ.7)፡፡ ይሕ ጉባኤ በቤተ ክህነት አካባቢ ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ›› በሚል ሲታወቅ የጉባኤው አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ደግሞ ‹‹የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ›› ይሉታል፡፡ በወቅቱ ሸዋ ክፍለ ሀገርን ወክለው የደርግ ሸንጎ(መማክርት ጉባኤ) አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው እንዴት የኮ/ል አጥናፉ ኮሚቴ አባል እንደሆኑና የኮሚቴውን አባላት ዝርዝር ሲገልጹ ‹‹…ኮ/ል አጥናፉ አባተ ጠርቶኝ ‹ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ወጥታ ራሷን የምትችለበትን መንገድ የሚፈልግ ኮሚቴ ልናቋቋም ነውና በአባልነት እንዲያገለግሉ እፈልጋለሁ› አለኝ፡፡ ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ገብረማርያም፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ቄስ ዳኛቸው ካሳሁን፣ ዶክተር ክንፈርግብ ዘለቀ፣ አቶ ፍቅረድንግል በየነ፣ አቶ መርስዔኀዘን አበበ፣ አቶ አእምሮ ወንድማገኘሁ፣ አቶ(በኋላ ሊቀ ማዕምራን) አበባው ይግዛው የኮሚቴው አባላት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ኮሚቴው ሊቀ መንበር ሲመርጥ…ዶ/ር ክነፈርግብ ዘለቀ ተመረጠ›› ይላሉ(ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፡ገ.202)፡፡ የኮሚቴው አባላት 9 ሰዎች ነበሩ ማለት ነው፡፡

Thursday, July 21, 2016

ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ በ‹‹ያ! ትውልድ›› መካከል … ‹‹ሞትህ ደጅ አደረ››! ክፍል አንድ…!

በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የአቡነ ቴዎፍሎስ ዝክረ-ሥምዕ በቤተ ክህነቱም በአዲሱ ትውልድም ዘንድ እየተዘነጋ ሄደ፡፡እኛ ስንዘነጋው ታሪካቸው በቆናጽላን (ተሐድሶዎች) እንዳልሆነ-እንዳልሆነ ተተረከ፡፡የአቡነ ቴዎፍሎስን በመሥዋዕትነት የከበረ ታሪክ የቤ/ ታሪክ አድርጎ ለማየት ፍላጎት ጠፋ፤ሰቆቃቸው የሚዲያ ሽፋን ተነፈገ፡፡እንዲያ ተሰማኝ!ይሕን ሁሉ ችለን ሕመማችንን እንዳናስታምም ወዲህ ከቤተ ክህነት፣ወዲያ ከአብዮታውያን ወገን ያሉ ትሩፋን አበው ጭራሽ አጽመ-ቴዎፍሎስን በግፍ በወደቀበት እንበለ-ርኅራኄ አነወሩ፡፡ሲሻቸው ለቀ.. ተቆርቋሪ መስለው፣ሲሻቸው የሲሶ ግዛትን ተረክ ከለላ በማድረግ 2 ወገን በሚወረወር የብዕር ፍላጻ መቃብሩን እየፈለሱ በወደቀበት አለሳርፍ አሉት፡፡መንበሩን በግፍ ከለቀቀ 40 ዓመት የደፈነው ግፉዕ እረፍት አጣ፡፡ አላስተኛ አሉት፡፡ዘለግ ያለችውና መቼቷ 1953-1971 . የሆነው የዚህች ክታብምክንያተ-ጽሕፈትይኸው ነው--ሕማሙ፡፡የሚከተሉት አርእስት ለነዚህ ዐፅመ-ቴዎፍሎስን እንቅልፍ ለሚነሱ ልብ ሰባሪ ከሳሾች ‹‹እናንት የዛሬ ሕያዋን!ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፤ሟች ሞቱን ይሙትበት፤ዐፅሙን ሰላም አትንሱ!›› ለማለት ያህል ከማስረጃ ጋር ተከረተሱ፡-
1.  የሲሶ ግዛት ተረክ …‹‹ሲሶ ግዛት›› ወይስ ‹‹የቶፋ ሥርዓት››?! 
2.  አብዮታዊ -አማኒነትና የአቡነ ቴዎፍሎስ ምዕዳን!
3.  ሰቆቃወ ቴዎፍሎስቅድመ-ሞት፣ጊዜ-ሞት፣ድኅረ-ሞት...ሞትህ ደጅ አደረ! 
4.  ዝክረ-ቴዎፍሎስ በአፈ-ጳጳሳት ወሊቃውንት!
የሚሉ አርእስትን መራኅያን አድርጌ በተቻለኝ መጠን ስሜቴን ገትቼ (እንዲያው መግታቱ ከሆነልኝ) የመዛግብቱን ሀቅ ለማሳየት እሞክራለሁ፤ለዚህም የአምላከ ግፉዐን ረድኤትና ጥበቃ እንደማይለየኝ አምናለሁ፡፡

Wednesday, July 20, 2016

አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ!


በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንድን የሥጋ ቁስል ለመፈወስ ለእያንዳንዱ ሰው ከባድ ነው፤ የነፍስን ቁስል መፈወስ ግን ለኹሉም ቀላል ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ለመፈወስ መድኃኒት ብሎም ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነፍስን ለመፈወስ ግን ቀላል ብሎም ወጪን የማይጠይቅ ነው፡፡ ሥጋን ከዚያ ከሚያሰቃይ ቁስሉ ለመፈወስ አድካሚ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀዶ ጥገና ምላጭ መቀደድ አለበት፤ መራራ መድኃኒቶችም ሊጨመሩበት ይገባል፡፡ ነፍስን ለመፈወስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አያስፈልግም፡፡ ፈቃደኛ መኾን ብቻ በቂ ነው፤ ፍላጎቱ ካለ ኹሉንም ነገር ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የእግዚአብሔር መግቦቱም እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው፡፡

Saturday, June 18, 2016

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : በዓለ ጰራቅሊጦስ

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : በዓለ ጰራቅሊጦስ: (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ግንቦት ፴ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም)፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!     “ጰራቅሊጦስ” ማለት በጽርዕ ልሳን “አጽናኝ” ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን በ፩ኛ ዮሐ.፪...

Wednesday, June 8, 2016

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : ዕርገተ ክርስቶስ

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : ዕርገተ ክርስቶስ: (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፳ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!! ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ዕለቱን ወደ ሰማይ አላ...

Monday, May 23, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፮ (የመጨረሻው)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 15 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በዛ ቢልም በትዕሥት ኾነው ያንብቡት፡፡
ጉባኤ ኦአክ
በክፍል አምስት ለመግለጽ እንደተሞከረው ቴዎፍሎስ በቅዱስ ኤጲፋንዮስ አማካኝነት ሊያደርገው ያሰበው ነገር አልሰመረለትም፡፡ ነገር ግን በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ላይ እርሱ ራሱ ከሳሽና ዳኛ ለመኾን እጅግ ሲጨነቅና ሲጠበብ ቆይቷል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነገሮች እንደ ድሮ እንዳሉ በማሰብ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንደ ወጣ ማለትም በዚህ በወርሐ ግንቦት አጋማሽ ላይ ስለ ሴቶች አለባበስ አስደናቂ የኾነ ስብከትን ሰበከ፡፡ አውዶክስያም ይህን ስብከት ሰማች፡፡ አንዳንድ ሰዎችም - በተለይ ሴቪሪያን የተባለ - ስብከቱ እርሷን ያነጣጠረ እንደ ኾነ ነገሯት፡፡ እጅግ ተናደደች፡፡ ይህንንም ይዞ ወደ አርቃድዮስ (ወደ ባለቤቷ) ሔደች፡፡እኔን ሰደበ ማለት አንተንም ሰደበ ማለት ነውአለችው፡፡ ብዙዎቹ የታሪክ ጸሐፊዎች የቅዱስ ዮሐንስና የአውዶክስያ ግንኙነት የሚሻክረው በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ 

Sunday, May 22, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፭


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 14 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተዋዳጆች ሆይ! ክፍል አምስትን ሳላቀርብላችሁ ዘገየሁ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ ከዓቅሜ በላይ የኾነ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡
ቁስጥንጥንያ ከተማ
እስኪ ስለ ቁስጥንጥንያ ጥቂት እንበል! ከአንጾኪያ ይልቅ ቁስጥንጥንያ ከቤተ ክርስቲያናዊም ኾነ ከፖለቲካዊ ፋይዳዋ ከፍ ያለ ነው፡፡ መሥራቿ ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነው፤ 330 ..፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺሕ ኗሪ ነበራት፡፡ መንበረ ፓትሪያሪኩ ለቤተ መንግሥቱ በጣም ቅርብ ነው፤ ሃጊያ ሶፍያ (ቅድስት ጥበብ - መድኃኔ ዓለም በሉት፡፡ ጥበብ ክርስቶስ ነውና)፡፡ በከተማይቱ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡- 381 .. ጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተካሔደበትና ከሃጊያ ሶፍያ 150 ሜትር ገደማ የሚርቀው ሃጊያ ኢረነ (ቅድስት ሰላም) ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ የቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በዮሐንስ መጥምቅ ምትረተ ርእስ የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ በቅዱሳን ስም ቤተ ክርስቲያንን መሰየም የቅርብ ዘመን ታሪክ እንዳልኾነ እያስተዋላችሁ ነውን?

FeedBurner FeedCount