Wednesday, November 7, 2012

ተጐጂው ማን ነው?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
                      (ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፣ በገ/እግዚአብሔር ኪደ)
  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድልዋችሁና ስለሚያሳድድዋችሁም ጸልዩ” የሚል ይገኝበታል /ማቴ.5፡43-44/፡፡
 ብዙዎቻችን ይህን ቃል ብናውቀውም ጠላቶቻችንን የምንወድበት፣ የምንመርቅበትና ስለ እነርሱ የምንጸልይበት ምክንያት ምን እንደሆነ ካለማስተዋላችን የተነሣ ይህን ለማድረግ እንቸገራለን፡፡ “ጌታ እንደዚያ እንድናደርግ ስላስተማረን ነው” በማለት እንደ ትእዛዝና ግዴታ ብቻ አድርገን የምንመለከተውም አንጠፋም፡፡
 ሆኖም ግን ከላይ የጠቀስነው የጌታችን ቃል እንዲህ የተባለበት የጠለቀ ምክንያት አለው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጥያቄአዊ በሆነ አመክንዮ እንዲህ በማለት ያብራራልናል፡-
“ልጆቼ! ሌላ ሰው አደረሰብኝ የምትሉት ጉዳት ምንድነው? ተቆጥቶ ሰደበኝ፤ ያለ ስሜም የሆነ ስም ሰጠኝ የሚል ነውን? ታድያ ይኼ ምን ጉዳት አለው? በፍጹም ጉዳት የለውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጉዳቶች ሳይሆኑ ትዕግሥተኞች ከሆናችሁ ጥቅማቸው የበዛ ነውና፡፡ ሲጀምር በእናንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈልገው ሰው የሚያደርገውን አያውቅም፡፡ የሚያደርገው ሁሉ ወዶና ፈቅዶ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እናንተን የጐዳ ቢመስለውም ራሱን እየጐዳ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ችግር ጐጂውና ተጐጂው ማን መሆኑን ለይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ምክንያቱም ይኼንን ለይተን ብናውቅ ኖሮ ራሳችንን ለመጉዳት ባልተነሣሣን ነበር፤ ሌሎች ክፉ ይደርስባቸው ዘንድ ባልጸለይን ነበር፤ ማንንንም መጕዳት እንደማንችል በገባን ነበር፡፡ ትልቁ በደል ደግሞ ክፉን መቀበል ሳይሆን በሌሎች ላይ ክፉትን መፈጸም ነው፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምራችሁ ሌላ ሰውን በድላችሁ ከሆነ ራሳችሁን ውቀሱ፤ ሌላው ክፉ አድርጐባችሁ እንደሆነ ግን ለእናንተ ያደረገው ነገር መልካም ነውና ጸልዩለት፡፡ ምንም እንኳን ሰውዬው እናንተን ለመጥቀም ብሎ ያደረገው ባይሆንም በመታገሣችሁ ግን ትልቅ ጥቅምን ታገኛላችሁ፡፡ ክፉ አደረገብኝ የምትሉት ሰውዬ ድርጊቱ ክፉ እንደሆነ ሰዎችም የእግዚአብሔር ቃልም ይፈርዱበታል፤ እናንተ ግን እንዲህ ስትታገሡ ለጊዜው ምንም የተጐዳችሁ ቢመስላችሁም ጌታ እንደተናገረ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነው” ይላል /Homily on the Gospel of St. Matthew, Hom.18/፡፡
 ከዚህ መረዳት እንደምንችለው አንድ ሰው እኛ ላይ ክፉ ቢያደርግ ቅዱሱ እንደተናገረው ትዕግሥተኞች ከሆንን ወደ ሹመት፣ ወደ ሽልማት ነው እየገፋን ያለው ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን እርሱ የሚታየው የቅርቡ ማለትም እኛን መጕዳቱ ስለሆነ የምናገኘው ሹመት ሽልማት አይታየውም፡፡ ቢታየው ኖሮ ግን (ይህን አክሊል ሽልማት እንደምናገኝ ስለሚረዳ) የሚያደርገውን ነገር ባላደረገ ነበር፡፡ ስለዚህ በእኛ ላይ እንዲህ ለሚያደርግ ሰው የምንጸልይለት አንደኛ ምረረ ገሃነምን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ካለማወቁ የተነሣ እርሱ ራሱ እየተጐዳ ስለሆነ፤ ሁለተኛ እኛን ወደ ሹመት ሽልማት እየገፋን ስለሆነ ነው ማለት ነው፡፡
 በቤተ ክርስቲያናችን አንድ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ ይኸውም አንድ ዓላዊ ሰው አንድ ክርስቲያንን መከራ ያጸናበታል፡፡ ክርስቲያኑም፡- “ጌታዬ ምረረ ገሃነምን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ባያውቅ ነውና እባክህ ይህን እንዲያውቅ አድርገው” እያለ ይጸልይለታል፡፡ በኋላም ዘመነ ዓላውያን አልፎ ዘመነ ክርስቲያን ይሆናል፡፡ ዓላዊዉም፡- “(ያ መከራ ሳጸናበት የነበረው ክርስቲያን) ዛሬ ቢያገኘኝ (በተራው) እንደምን ባደረገኝ ነበር?” ይላል፡፡ ይህን የሰሙ ሌሎች ሰዎችም፡- “እርሱስ ቀድሞም ቢሆን እንዲህ እያለ ይጸልይልህ ነበር” አሉት፡፡ ዓላዊውም “እኒህ ክርስቲያኖች ምግባራቸው የቀና መሆኑ ሃይማኖታቸው የቀና ቢሆን አይደለምን?” ብሎ ተመልሶ አምኗል፤ ተጠምቋል /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
  ስለዚህ እኛም እንዲህ የሚያደርጉብንን ሰዎች ልንወቅሳቸው ልንከሳቸው አይገባም ማለት ነው፡፡ ይልቁንም ስንታገሣቸውና ስንጸልይላቸው ከላይ እንደጠቀስነው ክርስቲያን ለድኅነታቸው ምክንያት እንሆናለን፡፡
 እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ስናደርግ ከማየት በላይ የሚያስደስተው ምንም ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የባሕርዩ የሆነው እንዲሁ የማፍቀር ልምምድ በአርአያውና በአምሳሉ በተፈጠርን ልጆቹ ስለሚመለከት፡፡ እግዚአብሔር ከባሕርዩ የተነሣ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሓይን ያወጣል፤ በጻድቃንና በኃጥአን ላይ ዝናቡን ያዘንባል፡፡ ዳግመኛ ከእርሱ የተወለድን እኛም እርሱን መስለን ሁሉንም እናፈቅር ዘንድ ይሻል፡፡ ይኸውም እንደ ሕግና ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን አስቀድመን እንደተናገርን ብዙ ረብሕ የምናገኝበት ስለሆነ ነው፡፡
 ሳውል አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያንን አብዝቶ የሚያሳድድ ፈሪሳዊ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ተስማምቶም የአይሁድን ልብስ ይጠብቅ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ግን ስለ እርሱ አብዝተው ይጸልዩ ነበር፡፡ የጻድቅ ሰው ጸሎትም በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለችና ሳውል ማሳደዱን ተወ፡፡ መተው ብቻም አይደለም፡፡ እርሱም በተራው ጳውሎስ ተብሎ ሲያሳድዳት የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ያገለግላት ጀመር እንጂ፡፡ እንዲያውም ራሱ እንደተናገረው ከሌሎች ሓዋርያት ይልቅ እጅግ ደከመ፡፡ ለሚያሳድዱትም ሁሉ አብዝቶ ይጸልይ ነበር /ሮሜ.9፡3/፡፡
  እንግዲያውስ ተወዳጆች ሆይ! መውቀስ መክሰስ ስንፈልግ የሚሰድቡንን፣ የሚረግሙንን፣ የሚያሳድዱንን ሳይሆን ራሳችንን መውቀስ እንችላለን፡፡ ስለ ሠራነው ኃጢአት ራሳችንን መክሰስ ጥቅም እንጂ ጕዳት የለውምና፡፡ ስንጸልይም እንዲሁ ስለ ሠራነው ኃጢአት እንጂ ስለ ሌሎች ክፋት በማሳሰብ ሊሆን አይገባም፡፡ በቅጥነተ ሕሊና (በማስተዋል) ስናየው እኛው ራሳችን ራሳችንን ካልጐዳን በስተቀር እኛን መጕዳት የሚችል ማንም የለም፡፡
 ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount