Saturday, November 3, 2012

የምንጽፍበት ሰሌዳ!


 በዲ/ን ዳንኤል ክብረት



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 ሁለት ጓደኞች ሞቃታማ በሆነው በረሃ እየሄዱ ነው። ብዙ ነገር እያነሡ ይወያያሉ። ታድያ የሆነ ጊዜ ወደ ክርክር ይገባሉ። አንዱ "እንዲህ ነው!" ሲል ሌላኛው "አይደለም" ይላል። "ነው" "አይደለም" "ነው" "አይደለም" እየተባባሉ ሲከራከሩ ፈርጠም ያለው ሌላኛውን በጥፊ አጮለው። በጥፊ የተመታው ደነገጠ። ቆይቶ ራሱን አረጋጋና ምንም ሳይናገር ቁጭ አለ። አጎንብሶም አሸዋው ላይ በጣቱ "ዛሬ በጣም የምወደው ጓደኛዬ በጥፊ መታኝ።" ብሎ ጻፈ። መቺው ቆሞ ያያል። ጓደኛውን በመምታቱና የተመታው ጓደኛውም ምንም ቃል አለመተንፈሱ ልቡን ነካው። ነገር ግን ይቅርታ እንኳ አላለውም።


 ጉዞው ለተወሰነ ርቀት በዝምታ ቀጠለ። አንዳቸው ባነሡት ሐሳብ ዝምታው ተሰበረና እንደቀድሞ ሌላ ነገር መጨዋወት ጀመሩ። ሲጓዙም አንድ ሐይቅ አገኙ። በበረሃው ሐሩር የደረቀ ጎሮሯቸው ሊያርሱ ጥማቸው ሊያረኩ እረፍት ወሰዱ። ወደ ውሃው ቀረብ ብለው ከጌዴዎን ምርጥ ወታደሮች ተምረዋል መሰል አጎንብሰው በእጃቸው መጠጣት ጀመሩ። ታድያ አንዱ (በጥፊ የተመታው) ሳሩ አዳልጦት ወደ ሀይቁ ገባ። መቺውም ጓደኛውን ለማዳን ብሎ ራሱን ውኃው ውስጥ ይወረውርና ጓደኛውን ያወጣዋል።

 ሁሉም ነገር ከተረጋጋ በኋላ የዳነው ጓደኛ አንድ ትልቅ አለት ጋር ጠጋ ብሎ ጽሑፍ መቅረፅ ጀመረ። መጨረሻም "ዛሬ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ከሞት አዳነኝ፡፡" የሚል አንድ አረፍተ ነገር ተነበበ።
 አሁንም ጓደኛው እስከ መጨረሻ ቆሞ ያየዋል። በመገረምም "ጓደኛዬ! ቅድም በጥፊ ስመታህ በአሸዋ ላይ ፃፍክ። አሁን ደግሞ አሸዋ ከአጠገብህ ሳለ እዚህ መጥተህ በዓለት ላይ ትቀርፃለህ ለንምድነው?" ብሎ ይጠይቃል። ጓደኛውም ቀና ብሎ አየውና እንባን ባቀረቀሩ ዐይኖቹ ምስጋና እያቀረበ "አየህ ጓደኛዬ! ሰዎች ክፉ ሲያደርጉብን በአሸዋማው የልባችን ሰሌዳ መጻፍ አለብን። ሌላ ጊዜ የፍቅር ነፋሳት መጥተው እንዲደመስሱልን። ጥሩ ነገር ሲያደርጉልን ደግሞ በአለታማው የልባችን ሰሌዳ መጻፍ ይጠበቅብናል። እስኪ አሁን ተመልሰን ወደ መጣንበት ብንሄድ በመንገድ በጥፊ እንደመታኸኝ የጻፍኩት ነገር የምናገኘው ይመስልሃል? አይገኝም። ለምን? የጻፍኩት በአሸዋ ላይ ነውና ነፋስ መጥቶ በቀላሉ ይደመስሰዋል። እሺ አሁንስ የምንፈልገውን ቦታ ደርሰን ስንመለስ ይህ በድንጋይ የጻፍኩት የሚደመሰስ ይመስልሃል? ምን ጊዜም አይደመሰስም።
ሰዎች ክፉ አድርገውብን በዓለት ላይ ከጻፍነው በሐሳብ መንገድ ተውጠን አጋጣሚ እነርሱን ካገኘናቸው ማለት ካስታወስናቸው ያንን በዓለት የጻፍነው እናገኘውና እየረገምናቸው፣ እነርሱንም ክፉ እንዲያጋጥማቸው እየተመኘን፣ ከቻልንም ለመበቀል እያሰብን ልባችንን በንዴት እናቃጥለዋለን እናቆስለዋለን። አሸዋ ላይ ብንጽፈው ግን በቃለ እግዚአብሔር ግፊት በይቅርታና በፍቅር ነፋሳት ይደመሰስና ብናስባቸውም ከቅ/እስጢፋኖስ ጋር ሆነን "ጌታ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህችን በደል አትቁጠርባቸው።" እያልን በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር እንድንነጋገር ይጋብዙናል።

ሰዎች ያደረጉልንን ዓለት ላይ ከጻፍነው ደግሞ እነርሱን ባሰብን ጊዜ የጠራው የገነት ውሃ ልባችን ውስጥ ይፈስና ነፍሳችንን ያረካታል በሐሴትም ከሰማዩ አባታችንና ከቅዱሳን ማኅበር እንገናኛለን። ስለዚህ የምንጽፍበትን ሰሌዳ መለየት አለብን። በምን ላይ ምን መጻፍ እንዳለብን ካልለየን ግን ሕይወታችን ሰላማዊ ማድረግ ከባድ ይሆንብናል" አለው።
ይህን ሰምቶ ይቅርታ ሳይሉ ማለፍ ከባድ ነበርና ይቅርታ ጠይቆ በፍቅር መንገዳቸውን ቀጠሉ።
የምንጽፍበት ሰሌዳ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
        
     

1 comment:

  1. it is very intersting.Thank u.Please post such kind of stories it is so amazing for us.

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount