Tuesday, October 30, 2012

ጌታ ሆይ አምናለሁ -የዮሐንስ ወንጌል የ40ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.9)


       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  በምዕራፍ 8 እንደተመለከትን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግራቸውን ነገር ከማመን ይልቅ አይሁድ “ጋኔን አለብህ” /8፡48/ ብለው በድንጋይ ሊወግሩት ሽተው ነበርና አንድም “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” /8፡58/ ብሏቸው ነበርና ቁጣቸውን አብርዶ ቀዳማዊነቱን በገቢር (በሥራ) ያስረዳቸው ዘንድ ወደደ /መዝ.51፡4/፡፡ ስለዚህም ሲያልፍ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው (ሲለምን) አየ /ቁ.1/። ይህ ዐይነ ሰውር ሰው የዓይን ምልክት እንኳን አልነበረውም፡፡ እንዲሁ ልሙጥ ግንባር ነበረው እንጂ፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ሳይሆን ክርስቶስ አየው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ክርስቶስ ዕዉሩን በልዩ እይታ (በፍቅርና በሐዘኔታ) እንዳየው አስተዋሉ፤ ደነቃቸውም፡፡ አስቀድሞ መጻጉዑን ሲፈውሰው፡- “ዳግመኛ እንዳትበድል” ብሎት ስለነበረ /5፡14/ “ይህ ዕዉር ሆኖ የተወለደውም ዕዉርነቱ ከበደል የተነሣ ነው ማለት ነው” ብለው አሰቡ፡፡ አሳባቸው ግን ግራ አጋባቸው፡፡ ስለዚህም፡-  መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ነው ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጌታን ጠየቁት /ቁ.2/። ጌታችንም፡-እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ኃጢአት ይቀጣል እንጂ አባት ስለ ልጅ ልጅም ስለ አባት አይቀጣምና /ዘዳ.24፡16/፡፡ ታድያ እርሱ ነውን? ብትሉም አይደለም እላችኋለሁ፡፡ እንግዲያ ስለምን ዓይነ ስውር ሆነ? ብትሉም የእግዚአብሔር ሥራ (አስቀድሞ አዳምን ከምድር አፈር የፈጠርኩት ቀዳማዊ የምሆን እኔ መሆኔን) በእርሱ እንዲገለጥ ነው እላችኋለሁ /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatation’s Diatessaron, 28 /፡፡
ቀን ሳለ (በመዋእለ ሥጋዌ ሳለሁ) የላከኝን ሥራ (ሁሉን ማድረግ እንድችል ታዩ ዘንድ፣ አይሁድ እንደሚከሱኝ ዕሩቅ ብእሲ ሳልሆን ከአባቴ ጋር የተካከልኩ አምላክ ወልደ አምላክ እንደሆንኩ እንድታውቁ በዚህም እንድታምኑ ሁሉን) ላደርግ ይገባኛል፤ (እኔ ሳልሆን ሌላ) ማንም (ሰው) ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች (በሌላ አገላለጽ ይህን የመሰለ ተአምራት አሁን ካላሳየሁት ማንም ሰው ልመን ቢል ማመን የማይችልት ወቅት ይመጣል፤ ይኸውም ከትንሣኤዬ በኋላ ነው)። (ስለዚህ በዚህ) በዓለም (በሕይወተ ሥጋ) ሳለሁ የዓለም ብርሃን (የሰው እውቀቱ) ነኝ” ብሎ መለሰላቸው /ቁ.3-5፣ St. John Chrysostom, Homily 56 on the Gospel of John/። ይህንንም የሚለው ከተነሣ በኋላ ብርሃንነቱ ይቀራል ማለት ሳይሆን ሰዎች (ክርስቶስ) ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንደሆነ በቀላሉ የሚያምኑት በሕይወተ ሥጋ ሳለ ያሳያቸውን ስለሆነ ነው /ዮሐ.20፡31/፡፡
 ይህን ብሎም ወደ መሬት እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና፡- ሂድ! በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፡፡ ሰሊሆም ማለት የተላከ (ሃጅ፣ ፈሳሽ፣ ወራጅ) ማለት ነው። ዐይነ ስዉሩም “ከቻልክ አንተ ራስህ አድነኝ እንጂ ግንባሬን በጭቃ ቀብተህ ወደ ሰሊሆም መጠመቅያ ሂድ ትለኛለህን? በዚህ ውኃማ በጣም ብዙ ጊዜ ታጥቢያለሁ፤ ሆኖም ግን እስከ ዛሬ አልተሻለኝም፤ ደግሞስ ጭቃ ዓይንን ያጠፋል እንጂ ዓይን ያበራልን?” ብሎ እንደ ንዕማን /2ነገ.5፡11/ የስንፍና ቃል ሳይናገር በፍጹም እምነት ሄደ፡፡ ስለዚህ ጌታችን የቀባለት ጭቃ የዓይን ምልክት (ምክንያት) ሆኖለት ሄደ፤ ሲመለስ ግን እያየ መጣ፡፡ እየተመራ ሄደ፤ ሲመለስ ግን እያየ መጣ፡፡ ይህም በጣም የሚያስደንቅ ነው፡፡ ከነተረቱ “ዓይንና አፈር” እንዲል ጭቃ ዓይንን ያሳውራል እንጂ ዓይንን ሲያበራ አይተንም ሰምተንም አናውቅም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁለንተናው ፈውስ ነው፡፡ እንኳንስ እርሱ “ፈውስ ሁን” ያለውም ሁሉ ፈውስ ነውና ከተአምራት በላይ የሆነው ይህን ተአምራት አደረገ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ይዞ “እምኩሉ ዘየዐቢ እነግር ዘገብረ (በዜማ የምትችሉት በዜማ አዚሙት!)-ከሁሉ የበለጠው ክርስቶስ ያደረገውን ተአምራት እናገራለሁ፤ ፅዉር የዐውር ሕያወ ዐይነ- ጭቃ ደኅነኛውን ዓይን ያጠፋል እንጂ ዓይን ያበራልን? እርሱ ግን በምራቁ ጭቃውን ለውሶ ዓይኑን ቀባውና አዳነለት፤ ስለዚህ ከፍ ያለ ተአምር ይህን እናገራለሁ” እያለ በአንክሮ ይዘምራል፡፡ በረከቱ ይደርብን /የቃል መረጃ ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ፣ መቐለ/!
  ከእናንተ መካከል፡-“ጌታ ዐይነ ስዉሩን ወደ ሰሊሆም እንዲሄድ ሳያደርግ ለምን አላዳነውም?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ጌታ ይህን ያደረገው የዐይነ ስዉሩ የእምነት ታላቅነት የአይሁዳውያኑም ደንዳናነት ይገለጥ ዘንድ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በዚያ ጸበል የሚፈውሰውም እርሱ ራሱ እንደሆነ ያሳያቸው ዘንድ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፈሪሳውያን ጌታችንን የሚያዩት እንደ አንድ ዕሩቅ ብእሲ ነውና፡፡ እርሱ ግን የባሕርያችን መመኪያ በትሆን በሥጋ ማርያም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ቢታይም የትም ቦታ የሚገኝ ሥግው ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ያስረዳቸው ዘንድ ዐይነ ስዉሩ ወደ ሰሊሆም ሄዶ እንዲታጠብ አደረገ /St. John Chrysostom, Homily 57/፡፡
  ከዚህ በኋላ ጐረቤቶቹ ቀድሞ ሲለምን ስለሚያውቁት ተደነቁ፤ መደነቅ ብቻ ሳይሆን ግራም ገባቸው፡፡ እርስ በእርሳቸውም “(እንዴ) ይህ (ሰው) ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። ሌሎችም “(አዎ! ሲለምን የነበረው) እርሱ ነው” አሉ፡፡ ሌሎች ግንኧረ አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ ሌላ ነው” አሉ፡፡ እርሱም ይህን ሲነጋገሩ በሰማ ጊዜ ምንም ሳያፍር “(አዎ! ቀድሞ ተቀምጬ ስለምን ያያችሁኝ የቀድሞ ዐይነ ስውሩ) እኔ ነኝ” አላቸው። እነርሱም መልሰው፡-“(እንዴ!) ታድያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱልህ?” አሉት።  እርሱም መልሶ፡-ኢየሱስ የሚባለው ሰው በምራቁ ጭቃ ለውሶ አይኖቼን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም መጠመቂያም ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ (እኔም) ሄጄ ታጠብኩ እነሆም አሁን አያለሁ” ብሎ በግልጽ ነገራቸው። እነርሱም፡-“ ሰው አሁን የት አለ?” አሉት።አላውቅም” አላቸው /ቁ.8-12፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 503/።
   ከዚህ በኋላ (አሁን አላወቅም ብለህ ብትደብቀን እነርሱ ሳትወድ በግድ ያናግሩህ የለ? ብለው ለማስፈራራት) ወደ አለቆቻቸው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ጌታችን ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን (እንደተለመደ) ሰንበት (በእነርሱ ቅዳሜ) ስለ ነበር ነው። ከወሰዱት በኋላም ፈሪሳውያን እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት፡፡ በውስጠዘ ግን “በሰንበት ዐይንህ እንዲያይ ያ ኢየሱስ የምትለው ሰው ምን አደረገ?” ማለታቸው ነበር። እርሱም መልሶ፡- “(መጀመርያ) ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ (ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብም አለኝ) ታጠብሁም፤ (እነሆም) አያለሁ” ብሎ እውነቱን ሳይሸፋፍን በግልጽ ነገራቸው ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፡- “ይህ ሰው (ክርስቶስ) ሰንበትን አያከብርምና (ይሽራልና) ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ግማሾቹ ግን፡-ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል (ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው እንዴት ሊያድነው ይችላል)?” አሉ። በዚህም ምክንያት በመካከላቸው መለያየት ሆነ /ቁ.13-16/። ልብ በሉ! አስቀድመን ቀዳማዊነቱን በገቢር (በሥራ) ያስረዳቸው ዘንድ ወደደ ያልነውን እዚህ ተፈጸመ፡፡ ምክንያቱም ይህን ተአምር በግልጽ እነርሱ እንደሚያስቡት ዕሩቅ ብእሲ ሊያደርገው እንደማይችል ጥያቄ ፈጥሮባቸዋልና /ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ፣ ዝኒከማሁ/፡፡
  ፈሪሳውያኑም ከማመን ይልቅ ዕውሩን፡-አንተ ዓይኖችህን (በሰንበት) ስለ ከፈተ ስለ እርሱ (ስለ ክርስቶስ) ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም ገና በአምላክነቱ አላወቀውም ነበርና፡-ነቢይ ነው” አላቸው። እንዲህ ቢልም እነርሱን ሳይፈራ መመለሱን እናስተውል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ “ሰንበትን አያክብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም” ቢሉም እርሱ ግን “ነቢይ ነው (ከእግዚአብሔር የተላከ ነው)” አላቸው፡፡ ፈሪሳውያኑ ግን ወላጆቹ እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም  አላመኑም፡፡ ወላጆቹ ተጠርተው ከመጡ በኋላም፡-እናንተ! ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል?ብለው ሦስት ጥያቄዎች አከታትለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም፡-ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል” በማለት ሁለቱንም መልሰው አንዱ ግን ልጃቸው ራሱ እንዲመልስላቸው ነገርዋቸው። ወላጆቹ ሦስተኛውን ጥያቄ ያልመለሱት ፈሪሳውያኑን ስለ ፈሩአቸው ነው ምክንያቱም እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት (አይሁድ) ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። ስለዚህ ወላጆቹ፡-ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት” አሉ። ከዚህ በኋላልጃችን አይደለም፤ ዕውርም አልነበረም ብላችሁ ውሸት ተናገሩ” እንዳይሏቸው ከበዳቸውና ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠሩት፡፡ ጠርተውም፡-እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። የሚደንቀው ግን ጌታ አስቀድሞ “ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?” ሲላቸው ዝም ነበር ያሉት /8፡46/፡፡ አሁን ግን ስለ እግዚአብሔር ክብር ተጨንቀው ሳይሆን ልጁን ያደናግሩት ዘንድ እንዲህ አሉ /ቁ.18-24፣ St. John Chrysostom, Homily 58/፡፡
  ልጁ ግን ፈሪሳውያኑ በሚነግሩት ማደናገሪያ ሐሳብ ምንም አልተደናገረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዱላቸውን ስንኳ ሳይፈራ፡-እኔ ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ነገር ግን ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ” አላቸው። ከእነርሱ ግማሾቹም ቢሆኑ አስቀድመው ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል?” ብለው ስለነበር /ቁ.16/ ይህ አጠያየቃቸው እንደማያዛልቃቸው አስተዋሉና እንደ አዲስ መጠየቅ ፈለጉና ደግመው፡-ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ?” አሉት። እርሱም እንደ ረታቸው ብቻ ሳይሆን አጠያየቃቸው ማወቅ ስለ ፈለጉ ሳይሆን ስሕተትን ፍለጋ እንደሆነ አስተዋለ፤ እንደገና በዝርዝር ሊነግራቸውም አልወደደም፡፡ ስለሆነም፡- “(ፈሪሳውያንና አለቆች ሆይ!) አስቀድሜ ነገርኋችሁ (ሆኖም ፍላጎታችሁ ሌላ ስለሆነ) አልሰማችሁኝም፤ (ታድያ) ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? (ወይንስ) እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁ?” አላቸው /ቁ.25-27/። ተወዳጆች ሆይ! እንዲህ እያለ ለአለቆችና ምሁራነ ኦሪት ነን ለሚሉት ረበናት የሚነግራቸው በእነርሱ ዐይን “የተናቀው ለማኙ” እንደሆነ ታስተውላላችሁን? ዕጹብ ድንቅ! ለካስ እውነት እንዲህ ብርቱ ያደርጋል?!/St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
  በዚህም ጊዜ፡-“አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን (ፊት ለፊት) እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው የዕውር ስድብ ሰደቡት (ጠንባሳ፤ ዕውር እንደማለት) የሚደንቀው ግን እነርሱ ራሳቸውን ለማጽደቅ እንዲህ አሉ እንጂ የሙሴ ደቀመዛሙርትም አልነበሩም፡፡ የሙሴ ደቀ መዛሙርትስ ቢሆኑ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለመሆን ምንም ባልከበዳቸውም ነበር፤ ሙሴ ስለ ክርስቶስ ጽፏልና /5፡46/፡፡ ሰውዬው ግን እንዲህም ሲል መለሰላቸው፡-ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ (ብቻ ሳይሆን የማታውቁትን መሳደባችሁ እጅግ) ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን፡፡ በሌላ አገላለጽ እናንተ ‘ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን’ ብትሉም እግዚአብሔር ፈቃዱን የማያደርጉትንና ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን /ኢሳ.1፡15/፡፡ ስለዚህ እናንተ እንደምትሉት ኢየሱስ ኃጢአተኛ አይደለም። ምክንያቱም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደ ኋላም ዓይኑ ያየ ከቶ ተሰምቶ አያውቅም፤ ይህ ሰውም ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም (የዓይን ምልክት እንኳን ባልነበረው ግናባሬ ዓይንን) ሊያደርግ (ሊፈጥርልኝ) ባልቻለ ነበር” /ቁ.28-33፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 504-505/፡፡
   ፈሪሳውያንም የሚሉት አጡና መሳደብ ጀመሩ፡፡ ክርስቶስን ይክዳል ብለው ሲጠብቁት ጭራሽ ደቀ መዛሙርቱ ይሆኑ ዘንድ ሲጋብዛቸው በጣም ተበሳጩ፡፡ ስለሆነም፡-አንተ ሁለንተናህ (በሥጋህም በነፍስህም) በኃጢአት ተወለድህ (ስትሆን) እኛን ታስተምረናለህን?” ብለው ከቤተ መቅደሱ ወደ ውጭ አወጡት /ቁ.34/። ትዕቢት ክፉ ነው፡፡ ትሑት፣ ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ግን እንኳንስ ከሕጻናት ራሳቸውን ከማያውቁ ዐብዳንም ይማራል! የሰውዬው እምነት በእውነት በጣም አስደናቂ ነው! ይህች ፍጥረታዊት ፀሐይን ስንኳ አንድ ቀን አይቷት የማያውቅ ይህ ሰው ከእርሷ አልፎ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ለዘላለም የማይጠልቅ ፀሐይ” ብሎ ስለሚጠራው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥብዐት ሲመሰክር የእግዚአብሔር አሠራር እንዴት ግሩም ነው ያስብላል፡፡ ምን ያደርጋል? ምድራዊ ክብርን ፍለጋ የሚጨነቁት እንዚህ ፈሪሳውያን ወደማይጠልቀው ብርሃን ከመውጣት ይልቅ በጨለማ መኖርን መረጡ፡፡
 ስለዚህም ወደ ውጭ አወጡት፡፡ ከማኅበራቸው ለዩት፡፡ ወላጆቹ እንኳን ሳይቀሩ ከምኩራብ እንዳይለዩ ብለው የረበናቱን ትእዛዝ ፈርተው ልጃቸው ሲገፋ ዝምታን መረጡ፡፡ ለተገፉት መጠጊያቸው፣ አሳዳጊ ለሌላቸውም አሳዳጊያቸው የሚሆን አምላኩ ግን አገኘው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ሲገፋ የሚወድቀው በእግዚአብሔር መዳፍ ላይ ነው፡፡ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ ሆኖም የቤተ መቅደሱ ባለቤት ተቀበለው፡፡ መዳናቸው ከሚገፉት ማኅበር ተለየ፤ የደኅንነት ምንጭ የሚሆን ጌታም አገኘው፡፡ ንቀው፣ ዘልፈው፣ ሰድበው አባረሩት፤ ጌታ ግን በክብር በልዕልና በፍቅር ተቀበለው፡፡ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወትም እንዲህ ናት፡፡    
  ሰውዬው እስከዚያች ደቂቃ ድረስ ያዳነው ኢየሱስን በዐይነ ሥጋው አይቶት አያውቅም፡፡ አሁን ግን ከፊቱ ቆመ፡፡ ጌታችንም፡-አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም እንደ አዳነው እንዲሁም ደግና ከእግዚአብሔር የተላከ ሰው እንደሆነ እንጂ ከዚያ በላይ በትክክል አያውቀውም ነበርና፡-ጌታ ሆይ፥ አምንበት ዘንድ ወልደ እግዚአበሔር ማን ነው?” ብሎ በትሕትና ጠየቀው። ጌታም፡-የምታየው ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው (ማለት እኔ ነኝ)” አለው። እርሱም፡-ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ” ብሎ አሰምቶ ተናገረ፤ ይህን ይመሰክር ዘንድም ወድያው በፍጹም ልቡ ሰገደለት /ቁ.35-38/።
  ከዚህ በኋላ ጌታችን፡-የማያዩ እንዲያዩ (አላዋቂዎች እንዲያውቁ) የሚያዩም (አዋቂዎች ነን የሚሉትም በራሳቸው ፈቃድ) እንዲታወሩ  (አላዋቂዎች እንዲሆኑ) እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ (ለመፈራረጃ) መጣሁ” ብሎ ተናገረ። ከእርሱ ጋር የነበሩት ፈሪሳውያንም ይህን ሰምተው፡-እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው፡- “(የሥጋ) ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት (ዕዳ፣ በደል) ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን (ሳታውቁ እናውቃለን) ትላላችሁ /ምዕ.8፡55/፤ ስለዚህ ኃጢአታችሁ ይኖራል (አይሠረይላችሁም)” /ቁ.39- ፍጻሜ፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/።
  የማትጠልቅ የጽድቅ ፀሐይ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በበደላችን ምክንያት ወድቀን አንተን ማየት ቢሳነንም በልዩ እይታ አይተህ ስለጐበኘኸን እናመግንሃለን፡፡ አስቀድመህ ከምድር አፈር ንጹሓን አድርገህ ፈጥረኸን ሳለ በምክረ ሰይጣን ተታለን ራሳችንን አቆሸሽን፡፡ አንተ ግን ዳግመኛ መጥተህ ፈጠርከን፡፡ በቅዱስ ደምህም አጠብከን፡፡ አቤቱ እናመሰግንሃለን! ስምህንም እንጠራለን! ተኣምራትህንም ሁሉ እንናገራለን /መዝ.75፡1/! ቅዱስ አባት ሆይ! ሁለንተናውን በፈወስክለት ጊዜ ፈሪሳውያን እንዳሳደዱት ሰው ዛሬም ነፍሳችንን የሚያሳድዷት ብዙዎች ናቸውና አትራቀን፡፡ ቅዱስ ቃልህን ሁል ጊዜ በውስጣችን እንድናኖር የጨለማ አበጋዞችም እንዳይሰለጥኑብን አንተ እርዳን፡፡ ከፈወስከው ሰው ተምረን ስደትን እንዳንፈራ፣ እንደ ገላትያ ሰዎች የማናስተውል እንዳንሆን፣ ይልቁንም መቼም መች ዐይናችንን ከቀራንዮ እንዳናነሣ ደግፈን፡፡ በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በወዲያኛውም ዓለም እንደዚያ እንፈወስከው ሰው በፍጹም ልባችን በፍጹምም ሐሳባችን እንድናመሰግንህ፤ እንድንሰግድልህ፤ እንድንገዛልህም እርዳን አሜን! 

3 comments:

  1. የዮሐንስ ወንጌል የ41ኛ ሳምንት ጥናት ጀምሮ ያሉትን ማግኘት አልቻልኩም የት ለይ ነው ያሉት

    ReplyDelete
  2. የዮሐንስ ወንጌል የ41ኛ ሳምንት ጥናት ጀምሮ ያሉትን ማግኘት አልቻልኩም የት ለይ ነው ያሉት

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount