(ዮሐ.8፡48-59)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ክፋትን የሚሠራት ሰው በጣም የባሰና አሳፋሪ የሚያደርገው ተሸማቅቆና አፍሮ ራሱን መደበቅ ሲገባው ይባስኑ ለስሕተቱና
ለክፋቱ ምክንያትን እየፈለገ ሲቀጥልበት ነው፡፡ አይሁዳውያንም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
“እናንተ የአብርሃም ልጆች አይደላችሁም፡፡ የአብርሃምስ ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር፤ ከአብ ዘንድ በሕልውና
ያየሁትንና የሰማሁትን እውነቱን የምነግራችሁ እኔን ልትገድሉኝ ትሻላችሁና፡፡ አብርሃም እንዲህ አላደረገም፤ ነፍስ አልገደልም፡፡
መግደልስ ይቅርና ልጁን ነበር ለእግዚአብሔር የሠዋው፡፡ ነፍስስ መግደል ይቅርና የወጣው የወረደውን፣ ያለፈው ያገደመውን እንግዳ
ነበር ሲቀበል የነበረው፡፡ እንኳንስ እንዲህ ያለ ትምህርት አግኝቶ ነግረውትና አስተምረውት አላምንም ማለት ይቅርና ወጥቶ ወርዶ
ነበር ፈጣሪውን ያገኘው፡፡ ስለዚህ እናንተ ልትገድሉኝ እንደምትሹ አባታችን የምትሉት አብርሃም እንዲህ አላደረገም፡፡ በዚያም ላይ
ደግሞ ባስተምራችሁ አልተቀበላችሁኝም፡፡ ስለዚህ የአባታችሁኝ የሰይጣን ሥራን ትሠራላችሁና አባታችሁ አብርሃም አይደለም፡፡ እናንተስ
ከእግዚአብሔር አይደላችሁም” ብሎ ማየት ያቃታቸውን የመረቀዘ ቁስላቸውን ቢያሳያቸው የባሰ ተናደዱ (ይህን የበለጠ ለማንበብ እዚህይጫኑ)፡፡ በቁስላቸው ላይ ጨው ጨመሩበት፤ “አንተ በእውነት ሳምራዊ ነህ (አይሁዊ አይደለህም) የምንልህ ስለዚሁ አይደለምን?
ጋኔን አድሮብሃል፤ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለህም የምንልህስ በዚህ ምክንያት አይደለምን?” ብለው ከወገንነት አውጥተው ከይሁዲነት
አግልለው ሰደቡት /ቁ.48/፡፡ እንደ እነርሱ አስተሳሰብ ሳምራዊ ማለት የተናቀ፣ የሚለውን የማያውቅና እንዲሁ የሚዘባርቅ፣ ከአይሁድ
ጋር የማይተባበር ይልቁንም የአይሁድን እምነት የሚያናንቅ ነው፡፡ በዚህ አነጋገራቸው ጌታችን ጸረ አይሁድ አቋም እንዳለው አስመስለው
ለማቅረብም ሞክረዋል፡፡ አይሁድ ሆይ! ጋኔን ያደረበት ማን ነው? እግዚአብሔርን የሚያከብር ወይስ እግዚአብሔር አብን ያከበረው ወልድን
የሚሳደብ? /St.
John Chrysostom, Homily 55/፡፡
ጌታችን ግን በፍቅር መለሰላቸው፡፡ “ሳምራዊ አይደለሁም” አላላቸውም፡፡ እንደውም የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ በማንሣትም አስተማራቸው
እንጂ /ሉቃ.10፡30-34/፡፡ ስለዚህ “እኔስ ጋኔን የለብኝም (ጋኔን አላደረብኝም)፤ አባቴን አከብራለሁ እንጂ (ትዕቢተኛ ነው
እያላችሁ እንዳትሰናከሉብኝ) ራሴን አላከብርም፡፡ ወአንትሙሰ ታስተሐቅሩኒ- እናንተ ግን ዕሩቅ ብእሲ ነው እያላችሁ ትንቁኛላችሁ፤
ጋኔን አድሮበታል እያላችሁ ታቃልሉኛላችሁ፡፡ እኔም እናንተ አብን ማክበር ከእኔ ትማሩ ዘንድ ነቀፋችሁን፣ ንቀታችሁን ሁሉ በትዕግሥት
እቀበለዋለሁ፡፡ እኔ ራሴን ደስ ላሰኝ አልሻም ማለትም የሌለኝን አምላክነት አምላክ ነኝ ብዬ አላስተምርም፤ የሚመሰክርልኝ የሚያስተምርልኝ
አንድም አምላክ መሆኔን ባታምኑ የሚፈርድልኝ አለ፡፡ ቃሌን፣ ሕጌን፣ በግብር ኑሬ የማሳየውን ትምህርቴን የሚጠብቅ ቢኖር ግን እርሱ
ሳይፈረድበት ለዘላለም ሞትን አያይም፤ በሥጋ ቢሞት በነፍስ አይሞትም፤ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፤ ትንሣኤ ዘለክብር ይነሣል፤ ከእግዚአብሔር
አይለይም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ” አላቸው /ቁ.49-51፣ ወንጌል
ቅዱስ አንድምታ ገጽ 501/፡፡
አይሁድ ግን አሁንም “ሞት” የምትለዋን ቃል ይዘው የሥጋን ሞት የነገራቸው
መሰላቸው፡፡ ስለዚህም እንዲህ አሉት፡- (ሎቱ ስብሐት!) “በእውነት ጋኔን አድሮብህ እንዳለ ዛሬ አወቅን፤ አንተም ይህን በግልጽ
አሳወቅኸን፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙ እነ አብርሃም ሞቱ፤ ነቢያትም ሁሉ ሞቱ፡፡ አንተ ግን ሕጌን የጠበቀ፣ ቃሌን
የጠበቀ ለዘላለም አይሞትም ትለናለህ፡፡ እስኪ ንገረን! አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ከሞተው ከአብርሃም በላይስ
አንተ እግዚአብሔርን አነጋግረኸዋልን? ከሞቱት ከነሙሴስ እንዲሁም ከሌሎቹ ታላላቅ ነቢያት አንተ ትበልጣለህን? እኮ አንተ ራስህን
ማንን ታደርጋለህ? ከማን ጋራስ ታወዳድራለህ?” ብለው ዘበቱበት /ቁ.52-53/፡፡ ይህን የመሰለ የስንፍና ቃልስ (ጋኔን አድሮብሃል
የሚለው) ሳምራይቱ ሴት ስንኳ አልተናገረችውም /ዮሐ.4፡11-12፣ St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
ጌታም መለሰ፤ እንዲህም አላቸው፡- “ይህን አስቀድሜ ነገርኳችሁ፡፡ እንገድለዋለን
ብላችሁ የሰውን ልጅ (ክርስቶስ) ከፍ ከፍ አድርጋችሁ በሰቀላችሁት (በሰቀላችሁኝ) ጊዜ ከጥንት ጀምሮ የተናገርኳችሁ እኔ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡
ፀሐይ ብርሃኗን መስጠት ባቆመች ጊዜ፣ ጨረቃ ደም በለበሰች ጊዜ፣ ከዋክብት በረገፉ ጊዜ፣ ሙታን በተነሡ ጊዜ እኔ (አምላክ ወልደ
አምላክ) እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ በዚህ ብቻም አይደለም፤ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳልል በራሴ ሥልጣን ከሙታን ተለይቼ
በተነሣሁ ጊዜ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ ያኔ እኔ ከራሴ ብቻ አምጥቼ እንዳላስተማርኩ (ከአባቴ
የተለየ ፈቃድ እንደሌለኝ) ብቻ ሳይሆን እናንተ እንደምታስቡት ከአባቴ ጋር የተካከልኩ እንጂ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ እንዳልሆንኩ
ታውቃላችሁ፡፡ ይልቁንም ይህን (ዕሩይነታችንን) የማትቀበሉት እናንተ አባቴ በቁጣው ሲናገራችሁ እናመልክበታለን የምትሉት ቤተመቅደስም
በሮማውያን የጦር አበጋዞች እንዳልነበረ ሲሆን /ማቴ.24፡1-22/ ያኔ የአባቴ ተቃዋሚ እንዳልሆንኩ ታውቃላችሁ /መዝ.2፡5/፡፡
የአባቴ ተቃዋሚ ብሆን፣ የሌለኝን አምላክነት ለራሴ ገንዘብ የማደርግ ብሆን አባቴ እንዲህ በእናንተ ባልተቆጣ ነበርና /ማቴ.21፡41/፡፡”
/ቁ.28/፡፡
ሆኖም “እናንተ ከአባታችሁ (ከሰይጣን) ያገኛችሁትን ያያችሁትን ስለምትሠሩ ቃሌ በእናንተ ዘንድ ጸንቶ አይኖርም፡፡ ስለዚህም ልትገድሉኝ
ትሻላችሁ /ቁ.36/፡፡ እኔ ራሴን ባመሰግን ምስጋናዬ አይረባኝም አይጠቅመኝምም፤ የሚያመሰግነኝና የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን
የምትሉት ግን ደግሞ የማታውቁት አባቴ ነው፡፡ እኔ እንደናንተ አላውቀውም ብል ሐሰተኛ በሆንኩ፤ ሕጉንም ባልፈጽም ሕግ ተላላፊ በተባልኩ፡፡
ሆኖም ግን አውቀዋለሁ፤ ሕጉን እጠብቃለሁ፤ ቃሉንም እፈጽማለሁ (ይህ የትሕትና አነጋገር እነርሱን
ለማቅረብ እንደሆነ ያስተውሉ)፡፡ አባታችን የምትሉት (ሆኖም ግን ያይደለ) አብርሃም እኔን ያይ ዘንድ ተመኘ፡፡ (በተስፋ፣
በትንቢት፣ በራዕይ፣ አንድ ልጁ ይሥሐቅን በመሠዋት፣ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዓ በረከት ከመልከጼዴቅ በመቀበልም አየ፡፡) አይቶም ደስ
አለው” አላቸው /ቁ.54-56፣ የቃል መረጃ ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ
ካሣ፣ መቐለ/፡፡
አይሁድም መልሰው፡-
“እንሆ አብርሃም ከሞተ ብዙ ሺ ዘመን ሆኖታል፡፡ ታድያ ሃምሳ ዓመት ስንኳ በቅጡ ያልሞላህ አንተ እንደምን አብርሃምን አየሁ ትለናህ?”
አሉት /ቁ.57/፡፡ ጌታ ግን መለሰ
እንዲህ አላቸው፡- “በዚህ አትደነቁ! እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ (ሳይፈጠር) እኔ አለሁ (I AM)” አላቸው /ቁ.58/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ኃይለ ቃሉን
በደምብ የምታስተውሉት ሁኑ፡፡ አንደኛ ክርስቶስ እርሱ ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የሌለው ቀዳማዊ እንደሆነ “ነበርኩ- I WAS” ሳይሆን “አለሁ- I AM” ብሎ መናገሩን (በዚህ ትምህርቱ የእነ
አርዮስ እንዲሁም የመሓመዳውያን ትምህርት ገደል ይገባል)፤ ሁለተኛ አብርሃም ሳይወለድ
በመለኮቴ አለሁ ሳይሆን የሥጋ ገንዘብ ለመለኮት የመለኮት ገንዘብም ለሥጋ እንደሆነ በማሳየት በአንድ
አካል በአንድ ባሕርይ በሆነ አገላለጽ “አለሁ” ብሎ እንዳስተማረ በጥንቃቄ እናስተውል (በዚህ ትምህርት የካቶሊክና
የልጁ የፕሮቴስታንት ትምህርት ከንቱ ይሆናል)፡፡
አይሁድም ንዴታቸው
ጫፍ ደረሰና እንደ ሕጋቸው ሊደበድቡት ድንጋይ አነሡ /ዘሌ.24፡16/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተሰውሯቸው በመካከላቸው አልፎ
ሄደ፡፡ ረቂቅ አምላክ መሆኑን ሆኖም ለድኅነተ ዓለም (ሊጣሉት ድንጋይ ላነሡትም ጭምር) ሲል ከምልአቱ ሳይጐድል ሰው ሆኖ የተገለጠ
መሆኑን ያስረዳቸው ዘንድ ተሰውሯቸው በመካከላቸው አለፈ፡፡ ከእነርሱ ጋር ነበር፤ ሆኖም አላገኙትም /ቁ.59/፡፡
ተወዳጆች ሆይ! አይሁድ ምድራዊ ጥቅማቸው ሰዋዊም ክብራቸው ስለቀረባቸው እንዴት በቅንዓት እንደሚከራከሩት ታስተውላላችሁን?
ከሐኪማቸው ጋር ጠብ እንደገጠሙስ ትገነዘባላችሁን? ሽባነታቸውን ሊተረትር ቢመጣ ጋኔን አለብህ አሉት፡፡ አቤት! እልፍ ምልክት ብዙ
ትምህርትም ከአምላኳ እያየችና እየተማረች የማትፈወስ ነፍስ ምንኛ ጎስቋላ ነች? ከቅናት የባሰ ክፉ ነገር የለም፡፡ በቅናት የተያዘች
ነፍስ ሌላውን እመቀኛለሁ ስትል ራሷን ታጠፋለች፡፡ ዓይኗ ሁል ጊዜ እንደ ቀላ ነው፤ በቀን ብዙ ጊዜ ትሞታለች፤ የምታየውን ሁሉ
(ያልበደሏትም ጭምር) በጠላትነት ትመለከታለች፡፡ አውቃም ይሁን ሳታውቅ በሰይጣን ሥራ ሓሴት ታደርጋለች፡፡ እኛ ግን ራሳችንን ከዚህ
እናርቅ፡፡ የክፋት ሁሉ ሥር እርሷ ናትና ክፋትን ሁሉ እናርቅ ዘንድ የሚመጣውንም መንግሥት እንወርስ ዘንድ ከቅናት እንራቅ፡፡ ይህን
እንድናደርግ በቸርነቱም መንግሥቱን እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!
(ይህ ወንጌል ለሌሎች በማካፈል /ሼር በማድረግ/ የበኩልዎን
ድርሻ ይወጡ፡፡ እናመሰግናለን!)
No comments:
Post a Comment