በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በሐዋርያት
ስብከት ቤተ ክርስቲያን ስትስፋፋ በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ተስበው ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱ ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች መሬታቸውንና ጥሪታቸውን በመሸጥ ያላቸውን ሀብት
አንድነት በማድረግ በኢየሩሳሌም የአንድነት ኑሮን ይኖሩ ነበር፡፡ በኅብረትም የሐዋርያት ትምህርትን በመስማትና በጸሎት ይተጉ
እንዲሁም ማዕድን በመባረክ በጋራ ይመገቡ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም “አንድ ልብና አንዲት
ነፍስ አላቸው
በማለት (የሐዋ.4፡32) ስለአንድነታቸው ፍጹምነት ይነግረናል፡፡
ነገር
ግን በቁጥር እየበዙ ሲመጡ በመካከላቸው በማዕድ ምክንያት ልዩነት ተፈጠረ፡፡ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ክርስቲያኖች በምግብ ክፍፍል ወቅት ከግሪክ የመጡትን ይጸየፉዋቸው፣ በተለይ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ስለነበር በማኅበሩ መካከል አለመስማማት ሆነ፡፡ ይህም በሐዋርያት ዘንድ ተሰማ፡፡
ሐዋርያትም
“የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም” (የሐዋ.6፡2) በማለትም ማዕዱንና በውስጥ ያለውን አገልግሎት ያስተናብሩ ዘንድ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ የክርስቲያኑን ኅብረት ጠየቁ፡፡ ምዕመናኑም በአሳቡ ደስ ተሰኝተው መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ክርስቲያኖችን መረጡ፡፡ ሐዋርያትም እጆቻቸውን ጭነው ረድእ ይሆኑዋቸው ዘንድ ዲያቆናት አድርገው ሾሙአቸው፡፡
ከእነዚህም
ዲያቆናት መካከል በቅድስና ሕይወቱ ለክርስቲያኖች አብነት የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይገኝበታል፡፡ እስጢፋኖስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “አክሊል” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግእዝ በኋላም ወደ አማርኛ የመለሱት ሊቃውንት
አባቶች በቀጥታ የግሪኩን እስጢፋኖስ የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ምንም እንኳ ስሙ የግሪክ ስም ቢሆንም በትውልዱ ግን
አይሁዳዊ ነው፡፡ ወላጆቹ ይህንን ስም ሊሰጡት የቻሉት በፍልስጤም ጠረፋማ ከተሞች ይኖሩ ስለነበር የግርክ ባሕልና ቋንቋ ተጽእኖ አድሮባቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
ቅዱስ
እስጢፋኖስ በሐዋርያት ጥበቃ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ከአምላኩ ዘንድ ባገኘው የማስተማርና የፈውስ ሀብት ያገለግል ነበር፡፡ በእርሱም ታላላቅ ተኣምራት ይፈጸሙ ነበር፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ከፊት ይልቅ እጅግ እየበዛና በትምህርት እየጠነከረ መጣ፡፡ አይሁድም ይህን ተመልክተው በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ በቅናትና በጠላትነት ተነሡበት፡፡ ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘው ጥበብና ኃይል እነርሱን በቃልም በድርጊትም ይቃወማቸው ነበርና ሊረቱት አልተቻላቸውም፡፡ ስለዚህም “እግዚአብርሔርንና ሙሴን ሲሳደብ ሰምተነዋል፤
ሙሴ የሠራልንን
ሥርዐት ይለውጣል፤ በዚህ ቤተ መቅደስና በሕጉ ላይ የስድብን ቃል ይናገራል፤ ይህንንም ቤተ መቅደስ የናዝሬቱ ኢየሱስ አፍርሱ ብሎአል” እያለ ያስተምራል እያሉ ሕዝቡን፣ ሽማግሌዎችንና ጸሐፍትን በማናደድ ይዘው ከሸንጎ ፊት አቆሙት፡፡
ቅዱስ
እስጢፋኖስን በሸንጎ ፊት ባቆሙት ጊዜም ፊቱ ልክ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ በርቶ ነበር፡፡ እርሱም ለተከሰሰበት ነጥብ መልስ ሰጠ፡፡ ከአብርሃም ጀምሮ
እስከ ክርስቶስ ለእነርሱ የተሰጣቸውን በረከት በመቃወማቸው ከተስፋ ቃል ርቀው እንደተወገዱ ገለጠላቸው፡፡ ክርስቶስንም ባለመቀበላቸው ወቀሳቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በቁጣ ተነሣስተው ከከተማ ውጭ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡
ቅዱስ
እስጢፋኖስ ግን
አይሁድ በድንጋይ እየወገሩት ሳለ ሰማያት ተከፍተው ክርስቶስን በአብ ቀኝ ቆሞ ተመለከተ፡፡ ይህንን ራእይም የክርስቶስን ትንሣኤን ለማይቀበሉት አይሁድ አሰምቶ ተናገረ፤ እነርሱ ግን
ከፊት ይልቅ በእርሱ ጨከኑ፤ በድንጋይም ወገሩት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታውን ክርስቶስን መስሎ ነበርና ልክ እንደ መምህሩ ክርስቶስ “አቤቱ ይህን ኀጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ሰጠ፡፡
በቤተክርስቲያን ታሪክም ስለ
ክርስቶስ መስክሮ
ሰማዕትነትን የተቀበለ የመጀመሪያው ዲያቆን ሆነ፡፡
በደማስቆ
መንገድ ላይ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ሳውል በኋላም ቅዱስ ጳውሎስ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው ሐዋርያ ቅዱስ እስጢፋኖስ
በድንጋይ በሚወግሩበት ወቅት በእርሱ ሞት ተስማምቶና ድንጋይን በእስጢፋኖስ ላይ ያነሡትን የአይሁድ ልብስ ይጠብቅ የነበረ ብላቴና ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ከሆነ በኋላ የእስጢፋኖስን ቤተሰቦች አጥምቆአቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ድንቅ ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም ይህን ቅዱስ የመታሰቢያ ቀን በመስጠት ጥቅምት 17 የድቁና
ማዕረግን በአንብሮተ ዕድ በሐዋርያት የተቀበለበትን፥ ጥር 1 ደግሞ
ዕረፍቱን ታስባለች፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ከቅዱስ እስጢፋኖስ በረከትና ረድኤት ይክፈለን
አሜን፡፡
(ጽሑፉ
ከማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር የተወሰደ ነው)
|
No comments:
Post a Comment