የዮሐንስ ወንጌል የ38ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.8፡21-47)
በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
(ከቻሉ
ጸልየው ይጀምሩ)
ልበ
ስሑታን የሆኑ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ጌታችንን ለመግደል፣ ከሕዝቡ ልብ ለማውጣት ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልፈለጉበት ስሕተት
የለም፡፡ ሆኖም ንጹሐ ባሕርይ ነውና ይህን ያገኙበት ዘንድ አልተቻላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ነውና በልባቸው የሚያመላልሱትን
ስለሚያውቅ ኃጢአታቸውን አውቀው ፍቅሩን እንዲረዱለት፤ የታመሙትን (እነርሱን) ፍለጋ እንደመጣ እንዲያውቁለት በጥበብ፣ በኃይል
እንዲሁም በሥልጣን ይነግራቸው ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሚያስፈራሩ ቃላት ሌላ ጊዜም በሚጋብዙ የትሕትና ቃለት ያምኑበት ዘንድ
ይጠራቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን ይህን እንዳያውቁ በምርጫቸው ልባቸውን አደንድነውታልና ይገድሉት ዘንድ ፈለጉ፡፡
ሆኖም በአባቱ ፈቃድ፣ በራሱ ፈቃድ፣ ማኅየዊም በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚሞትባት ሰዓት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ከሣ ቤዛ የሚሆንባት ደቂቃ ገና ናትና ይህን ማድረግ (ጌታችንን መግደል) አልተቻላቸውም (ይህን የበለጠ ለማንበብ እዚህ ይጫኑhttp://mekrez.blogspot.com/2012/09/blog-post_16.html)፡፡
ሆኖም በአባቱ ፈቃድ፣ በራሱ ፈቃድ፣ ማኅየዊም በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚሞትባት ሰዓት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ከሣ ቤዛ የሚሆንባት ደቂቃ ገና ናትና ይህን ማድረግ (ጌታችንን መግደል) አልተቻላቸውም (ይህን የበለጠ ለማንበብ እዚህ ይጫኑhttp://mekrez.blogspot.com/2012/09/blog-post_16.html)፡፡
የፍቅር አባት ጌታ ኢየሱስ አሁንም
ፍርሐት ተሰምቶአቸው እንዲመጡ “እኔ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ
ሆኖም
አታገኙኝም፡፡ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና
እኔ
ወደምሄድበት
እናንተ
ልትመጡ
አትችሉም” ይላቸዋል /ቁ.21/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ከእናንተ ተለይቼ የምሄድበት ሰዓት ይመጣል ፡፡ ያኔ (ኢየሩሳሌም
በሮማውያን ስትፈርስና በዕለተ ምጽአት) ሁላችሁም መሲሑን ተከትለነው (አምነንበት) ቢሆን ይህ ሁሉ መከራ ባልደረሰብን
ነበር ብላችሁ ትሹኛላችሁ፤ ሆኖም አታገኙኝም፡፡ ሕዝቅኤል ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች እንዳለ /ሕዝ.18፡20/
ሞት በሚገባው ኃጢአት የሞተ ሰው /1ዮሐ.5፡16/ ተድላ መንግሥተ ሰማያትን ማየት የሚቻለው አይደለምና እኔ ወዳለሁበት ተድላ መምጣት
አይቻላችሁም” /Augustine: On the Gospel of
St. John, tractate 38:2/፡፡
አይሁድ ግን፡- “እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ” አሉ /ቁ.22/። ከዚህ በፊት በአሕዛብ ዘንድ ተበትነው
ወደሚኖሩት አይሁድ ሂዶ ሊያስተምር ነውን? ይሉ ነበር /ምዕ.7፡34/፡፡ አሁን ግን ጌታችን ስለሞቱ እንደተናገረ አውቀው ክብር
ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና እንደ አንድ ተራ ሰው አይተዉት ከዚያም በላይ ራሱን ሊገድል ነው ብለው ለማስወራት እንዲህ
ተነጋገሩ፡፡
ጌታችንም እንዲህ አላቸው፡- “እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ግን ከላይ ነኝ፤ እናንተ
ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። እንግዲህ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ እላችኋለሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ ከእነ ኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና” አላቸው /ቁ.23-24/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “እንዲህ (ራሱን
ይገድላል) ብላችሁ ማሰባችሁ የሚደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም እናንተ ምድራውያን (ዳግም ያልተወለዳችሁ) አስተሳሰባችሁም እንዲሁ
ሥጋዊ ደማዊ ነውና፡፡ እኔ ግን እም ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቴ የተወለድኩ እንጂ ከዚህ ዓለም የተገኘሁ አይደለሁምና እንዲህ
እንደምታስቡት የማደርግ አይደለሁም፡፡ ከዚህ ዓለም የተገኘሁ አይደለሁም ስላችሁም የእናንተን ባሕርይ ባሕርይ አላደረግኩም ማለቴ
አይደለም፡፡ እንደነገርኳችሁ አምላክ ወልደ አምላክ ነኝ ማለቴ እንጂ፡፡ እንኳንስ እኔ በእኔ የሚያምንም ከዚህ ዓለም አይደለም
ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ /ምዕ.15፡19/፡፡ ስለዚህ እነግራችኋለሁ እኔ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ የመጣሁ በግ (መሲሑ)
እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአት እንደተያዛችሁ ይቅርታን ሳታገኙ ትሞታላችሁ” /ምዕ.3፡18፣ St. John
Chrysostom: Homily 53 /፡፡
እነርሱም
መልሰው፡- እንዲህ የምትለን “አንተ ማን ነህ?” አሉት /ቁ.25/። ኢየሱስም፡- “ከመጀመሪያ አንሥቶ ለእናንተ
የተናገርሁት ነኝ። ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ” አላቸው /ቁ.26/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡-“ማን እንደሆንኩ
ለማወቅ የተዘጋጃችሁ የተገባችሁ አይደላችሁም እንጂ እኔስ ገና ከዘመነ ብሉይ ከጥንት አንሥቶ ለእናንተ የተናገርኩ ነኝ
/ዘጸ.3፡16/፡፡ ያው ነኝ እንጂ አልተለወጥኩም፡፡ ትምህርቴን ከመስማት ይልቅ ልትገድሉኝ ትሻላችሁ እንጂ እኔስ ገና አባታችሁ
አዳም እንደበደለ የእባቡን ራስ ይቀጠቅጣል የተባልኩ መሲሑ (ክርስቶስ) ነኝ /ዘፍ.3፡16/፡፡ ልታምኑብኝ አልወደዳችሁም እንጂ
እኔስ የአባቶቻችሁ የእነ አብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ጋሻቸው እምነታቸው ነኝ፡፡ ልትቀበሉኝ አልፈቀዳችሁም እንጂ የዘመኑ
ፍጻሜ ሲደርስ እናንተን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ሁሉ ለማዳን ስል ሰው ሆኜ የመጣሁ የነቢያት ትንቢት ፍጻሜአቸው ነኝ /ገላ.4፡4/፡፡
እናንተ ገፋችሁኝ እንጂ እኔስ አባቶቻችሁ (ከግብጽ ባርነት ወጥተው) ገና በበረሀ ሳሉ መንፈሳዊ መብል መጠጥም የሆንኳቸው ነኝ
/1ቆሮ.10፡4/፡፡ አይሁድ ሆይ! ፍቅሬን ብትረዱስ እኔ አዳኙ (ኢየሱስ) ነኝ /ማቴ.1፡21/፡፡ የምወቅስባችሁ የምፈርድባችሁ
ብዙ ነገር አለኝ፤ ሆኖም አሁን እፈርድባችሁ ዘንድ ፈቃዴ አይደለም፤ አባቴም አድናችሁ እፈውሳችሁ ዘንድ እንጂ እፈርድባችሁ
እወቅሳችሁ ዘንድ አልላከኝም /ምዕ.3፡17/፡፡ የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእርሱ በሕልውና የሰማሁትን ለእናንተ እናገራለሁና
የእውነት ልጅ እውነተኛ ነኝ፡፡ ይህን ሁሉ የምላችሁም እንድትድኑልኝ ስለምወድ ስለምሻ እንጂ እናንተን ለመውቀስ አይደለም” /St. John
Chrysostom: Ibid/፡፡
እነርሱ ግን “የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ” ሲላቸው “ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም” /ቁ.27/ ነበርና መልሶ እንዲህ አላቸው፡-“እንገድለዋለን ብላችሁ የሰውን ልጅ (ክርስቶስ) ከፍ
ከፍ አድርጋችሁ
በሰቀላችሁት (በሰቀላችሁኝ) ጊዜ ከጥንት ጀምሮ የተናገርኳችሁ እኔ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ ፀሐይ
ብርሃኗን መስጠት ባቆመች ጊዜ፣ ጨረቃ ደም በለበሰች ጊዜ፣ ከዋክብት በረገፉ ጊዜ፣ ሙታን በተነሡ ጊዜ እኔ (አምላክ ወልደ
አምላክ) እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ በዚህ ብቻም አይደለም፤ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳልል በራሴ ሥልጣን ከሙታን
ተለይቼ በተነሣሁ ጊዜ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ ያኔ እኔ ከራሴ ብቻ አምጥቼ እንዳላስተማርኩ
(ከአባቴ የተለየ ፈቃድ እንደሌለኝ) ብቻ ሳይሆን እናንተ እንደምታስቡት ከአባቴ ጋር የተካከልኩ እንጂ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ
እንዳልሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ ይልቁንም ይህን (ዕሩይነታችንን) የማትቀበሉት እናንተ አባቴ በቁጣው ሲናገራችሁ እናመልክበታለን
የምትሉት ቤተመቅደስም በሮማውያን በ70 ዓ.ም እንዳልነበረ ሲሆን /ማቴ.24፡1-22/ ያኔ የአባቴ ተቃዋሚ እንዳልሆንኩ
ታውቃላችሁ /መዝ.2፡5/፡፡ የአባቴ ተቃዋሚ ብሆን፣ የሌለኝን አምላክነት ለራሴ ገንዘብ የማደርግ ብሆን አባቴ እንዲህ በእናንተ
ባልተቆጣ ነበር /ማቴ.21፡41/፡፡ ስለዚህ እላችኋለሁ! ተሰቀል ሙት ብሎ የላከኝ አባቴ (መንፈስ ስለሆነ አታዩትም እንጂ)
አሁንም በሕልውና ከእኔ
ጋር ነው፡፡
እናንተ እንደምታስቡት የእርሱ ተቃዋሚ ብሆን፣ በፈቃድ አንድ ባንሆን ኖሮ ከእኔ ጋር ባልሆነ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔም ደስ የሚያሰኘውን ፈቃዱን ዘወትር
አደርጋለሁና (እናንተ ሰንበትን ሻረ ብትሉኝም የእናንተ ዓይነቱ የሰንበት አከባበር መሻርም
ደስ ያሰኟልና) አብ
ብቻዬን አይተወኝም” አላቸው /ቁ.28-29፣ /St. John
Chrysostom: Ibid/።
ይህንን
ባለ ጊዜ ብዙዎች በእርሱ አመኑ /ቁ.30/።
ጌታም ያመኑበትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፡- “እናንተም በእኔ ማመናችሁ
ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቃሌ፣ በትምህርቴ፣ በሕጌ እስከ መጨረሻ ጸንታችሁ ስትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቶቼ (ያመናችሁ)
ትባላላችሁ እንጂ፡፡ ወተአምርዋ ለጽድቅ- እውነትን ታውቋታላችሁ (እውነት እኔ ነኝና እኔን በትክክል ታውቁኛላችሁ)፡፡ ታድያ
እውነትን ማወቃችን ምን ረብሕ አለው? ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኔም እላችኋለሁ፡- እውነት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ነጻ (አርነት) ታወጣችኋለች
(አወጣችኋለሁ)፡፡ ምክንያቱም እውነት የሌለው ሰው (አምኖም ቢሆን ሕጌን የማይጠብቅ ሰው) ሕሊናው ስለሚወቅሰው፣ ይህን
ሠርተሀል ይህን አድርገሻል እያለ ስለሚዘልፈው ሲባዝን ሲባንን ይኖራልና፡፡ ከውጭ ሲያዩት ነጻ ቢመስልም ውስጡ በኃጢአት
የተተበተበ ነውና ነጻነት (አርነት) የለውም፡፡ የኃጢአት ባርያ ነው፤ የኃጢአት ተገዢ ነው፤ እናንተ ግን (እንዳመናችሁብኝ በቃሌ
በትምህርቴ በሕጌ ብትጸኑ) ከዚህ ዘለፋ አርነት ትወጣላችሁ” /ቁ.31-32፣ የቃል መረጃ ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ፣ መቐለ/፡፡
አይሁድም መለሱ፡- “እኛስ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ከሆነ ጀምሮም ለማንም
ለማን ተገዝተን አናውቅም፤ እንዴትስ ነጻ ትወጣላችሁ ትለናለህ?” አሉት /ቁ.33/፡፡ ይህን ያሉት የላይ የሥጋ ነጻነትን
የነገራቸው ስለመሰላቸው ነው፡፡ ሆኖም ትምክሕት እያነቃቸው ነው እንጂ በሥጋም ቢሆን ነጻ አልነበሩም፡፡ ትዝ አልላቸው ብሎ
ወይም ደብቀውት ካልሆነ በቀር በባቢሎን 70 ዘመን፣ ጡብ እየረገጡ የግብጻውያን ባሮች ሆነውም ለ430 ዓመታት ተገዝተዋልና
/ዘጸ.12/፡፡ ስለዚህ ይህን ሁሉ ረስተው “እንዴት ነጻ ትወጣላችሁ ትለናለህ?” ማለታቸው ከንቱ ፉከራ ነበር ማለት ነው፡፡ የፍቅር
አባት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ይህን (በሥጋ ባርያ መሆናቸውን) አላስታወሳቸውም፡፡ ለምን ቢሉ አፍረው እርሱን ከማመን
ይዘገያሉና፡፡ እንዴት ግሩም ጥበብ ነው?!
ስለዚህ ከዚያ (በሥጋ ባርያ ሆነው እንደሚያውቁ ከመናገር) ይልቅ አሁን
ሊነግራቸው የፈለገው ሌላ ነውና፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአትን የሚሠራ ሰው ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው፡፡ ባርያ
በጌታው ቤት ለዘላለም አይኖርም፡፡ ባስፈለገ ጊዜ ሊያወጣው፣ ሊያባርረው ባስ ካለም (በጥንቱ
አስተሳሰብ) ሊሸጠው ይችላል፡፡ ልጅ ግን ወራሽ ነውና በአባት ቤት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡ እንግዲያውስ እናንተም
ልጅ (ወልድ) ነጻ ካወጣችሁ (ካመናችሁበት፣ ሥርየተ ኃጢአትን ካገኛችሁ፣ በቃሉ ጸንታችሁ ከኖራችሁ) በእውነት ነጻ የወጣችሁ
ናችሁ፤ አለበለዝያ ግን በወልድ ነጻ ካልወጣችሁ ነጻ ወጥተናል ልትሉ አትችሉም፤ ሁል ጊዜ የኃጢአት ባርያዎች ናችሁ እንጂ”
አላቸው /ቁ.34-36/፡፡ የአብርሃም ዘር ነን ብለውት ነበርና፡- “አአምር ከመ ዘርአ አብርሃም አንትሙ- የአብርሃም ዘር
የአብርሃም ወገን መሆናችሁንስ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌ ሕጌ በእናንተ ዘንድ ጸንቶ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትሻላችሁ፡፡ እናንተ
ከአባታችሁ ያገኛችሁትን ያያችሁትን ትሠራላችሁ፤ አባታችሁ ሰይጣን ነውና፡፡ እኔ ግን ከአባቴ በሕልውና ያየሁትን ያገኘሁትን
እናገራለሁ፤ አስተምራለሁ” አላቸው /ቁ.37-38/፡፡
አይሁድም መልሰው፡- “ለእኛስ አብርሃም አባታችን ነው” አሉት፡፡
ጌታም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- “የአብርሃምስ ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን
ሥራ በሠራችሁ ነበር፤ ከእግዚአብሔር ወይም ከአብ ዘንድ በሕልውና ያየሁትን የሰማሁትን እውነቱን የምነግራችሁ እኔን ልትገድሉኝ
ትሻላችሁና፡፡ አብርሃም እንዲህ አላደረገም፤ ነፍስ አልገደልም፡፡ መግደልስ ይቅርና ልጁን ነው ለእግዚአብሔር የሠዋው፤ ነፍስስ
መግደል ይቅርና የወጣው የወረደውን፣ ያለፈው ያገደመውን እንግዳ ነበር ሲቀበል የነበረው፡፡ እንኳንስ እንዲህ ያለ ትምህርት
አግኝቶ ነግረውት አስተምረውት አላምንም ማለት ይቅርና ወጥቶ ወርዶ ነበር ፈጣሪውን ያገኘ፡፡ ስለዚህ እናንተ ልትገድሉኝ
እንደምትሹ አባታችን የምትሉት አብርሃም እንዲህ አላደረገም፡፡ በዚያም ላይ ደግሞ ባስተምራችሁ አልተቀበላችሁኝም፡፡ ስለዚህ
የአባታችሁኝ የሰይጣን ሥራን ትሠራላችሁና አባታችሁ አብርሃም አይደለም” አላቸው /ቁ.39-41፣ የቃል መረጃ፣ ሊ/ሊ. ያሬድ
ካሣ/፡፡
አይሁድም እንዲህ ሲሉ መለሱ፡- “እኛስ ከዝሙት (በአምልኮተ ጣዖት ከነበሩ
ሰዎች) አልተወለድንም፤ አንድ አባት አለን እንጂ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከአብርሃም በዲቃላ የተወለድን
ሳይሆን ከእውነተኛይቱ ሚስቱ ከሣራ የተወለድን ነንና የምናመልከው አንድ እግዚአብሔር አለን” አሉት፡፡
ጌታችንም፡-
“እግዚአብሔርስ አባታችሁ ቢሆን እኔን በወደዳችሁኝ ነበር፤ ቃሌንም በጠበቃችሁ ነበር፡፡ እስመ አነ እምኀበ እግዚአብሔር ወጻእኩ
ወመጻእኩ- እኔ ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘምእባሕርይ ተወልጄ መጥቻለሁና፤ እኔ በራሴ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን
በአባቴም ፈቃድ መጥቻለሁና፡ አባቴም ውረድ ተወለድ ሙት ተሰቀል ብሎ ልኮኛልና በወደዳችሁኝ ነበር፤ ቃሌንም በጠበቃችሁ ነበር፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር አባታችሁ ከሆነ ቃሌን እንደምን አታምኑም? እፎ እንከ ተአምኑ ቃልዬ- ሕጌን ትምህርቴን እንደምን
አታምኑም? የእኔን ነገር ለመስማት እምቢ ብላችኋልና ቃሌን ስለምን አታምኑም? እውነትን የምትጠሉ መሆናችሁ አይደለምን? ስለዚህ
እውነት ብነግራችሁ ከመራራ ቅንዓት ተነሥታችሁ ልትገድሉኝ ትሻላችሁና እናንተ የአባታችሁን የሰይጣንን ሥራ ትሠራላችሁ፤ አባታችሁ
ሰይጣን ነው፡፡ ወፍትወቶ ለአቡክሙ ትፈቅዱ ትግብሩ- የአባታችሁ የሰይጣንን ምኞት የእርሱን ፈቃድ ልትፈጽሙ ትወዳላችሁና
አባታችሁ ሰይጣን ነው፡፡ እርሱ ከጥንት ጀምሮ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ ቃኤል ሰውን መግደል ያስተማረው ሰው አልበረም፡፡ ሰይጣን
ግን ነፍሰ ገዳይ ስለሆነ በቃኤል አድሮ ግደለው ግደለው ብሎ ኮርኩሮ ኮርኩሮ አቤልን አስገደለው፡፡ አዳምንም ያሳተው እርሱ
ነው፡፡ ስለዚህ ከጥንት ጀምሮ ነፍሰ ገዳይ ነውና ኢይቀውም በጽድቅ- በእውነት ጸንቶ አይኖርም፡፡ ሐሰት በተናገረ ጊዜ ከራሱ
አመንጭቶ ይናገራል፡፡ እስመ ሐሳዊ ውእቱ- ውሸተኛ ነው፤ ወአቡሃ ለሐሰት- የሐሰት የውሸት ነቅዋ፣ መገኛዋ፣ አባትዋ፣ መነሻዋ ነው፡፡
ሔዋንን ሲያስት ያስተማረው አልነበረም፤ ይህን በበላችሁ ጊዜ አምላክ ትሆናችሁ ብሎ ውሸትን ከራሱ አመንጭቶ ተናገረ እንጂ፡፡
በአጠቃላይ የኃጢአት ጓዝ በሙሉ መገኛዋ ዲያብሎስ ነው፡፡ ገና በዓለመ መላእክት አምላክ ነኝ ብሎ ሲታበይ ማንም ያስተማረው
አልነበረም፡፡ በመጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 12 ላይ ዓመጻ ወጽአት እመዛግብቲሃ- ክፉ ሥራ (ዓመጻ ሁሉ) ከምንጯ፣ ከሳጥንዋ፣
ከመገኛዋ፣ ከሰይጣን ወጣች እንዲል መራራ ቅንዓት፣ ምቀኝነት ሁሉ፣ ወኵሉ ምግባረ እከይ- ክፉ ሥራም ሁሉ ኢኮነት እምኀበ
እግዚአብሔር- ከላይ (ከእግዚአብሔር) የተገኘች አይደለችም፤ አላ እምድር እንተ እም ነፍሰ አጋንንት- ከዚህ ዓለም ከአጋንንት
ባሕርይ ነቅ የመጣች ናት እንጂ /ያዕ.3፡14-15/፡፡ እስመ ቀዳሚ ሰይጣን አበሰ- ቀድሞ ከመጀመርያው የበደለው ሰይጣን ነውና
ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ ከጋኔን የተማረ ነው፤ ጽድቅን የሚሠራ ግን ከእግዚአብሔር የተማረ ነው፡፡ የጋኔን ልጆችና የእግዚአብሔር
ልጆችም በዚህ ይታወቃሉ /1ዮሐ.3፡8/፡፡ እናንተም እንደነገርኳችሁ አባታችሁ እግዚአብሔር አይደለምና እውነት ባስተምራችሁ (የውሸት
አባታችሁን ሰይጣንን ስለምትሰሙ) አታምኑብኝም፡፡ መኑ እምኔክሙ ዘይዘልፈኒ በእንተ ኃጢአት- እስኪ ከእናንተ ወገን ስለ ኃጢአት
የሚወቅሰኝ ማን ነው? በነቢብም ይሁን በገቢርም ይሁን በኃልዮም ይሁን ኃጥእ ነህ የሚለኝ ማን ነው? ታድያ እንዲህ ከሆነ
የምትጣሉኝ ስለምንድነው? እኔን ለመግደል የምተከሱበት ምክንያታችሁስ ምንድነው? ትምህርቴ ነውን? ወይስ ተአምራቴ ነውን? ከእግዚአብሔር
የተወለደ፣ ከእግዚአብሔር የተማረ፣ እግዚአብሔር አባቱ የሆነለት ግን ቃለ እግዚአብሔርን ይሰማል፡፡ ወአንትሙሰ ኢትሰሙዑኒ-
እናንተ ግን ከእግዚአሔር ያልተማራችሁ ናችሁና አትሰሙኝም፤ ጀሮዎቻችሁም ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት የፈዘዙ ናቸውና አትሰሙኝም”
አላቸው /ቁ.42-47፣ የቃል መረጃ፣ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ/፡፡
አባት ሆይ! አንተ በእውነት የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ነህ፡፡
በራሳችን ኃጢአት ተሰነካክለን ወድቀን ሳለ ስለ እኛ መዳን ብለህ ባሕርያችንን ባሕርይ አድርገህ መጥተህ አባ አባ የምንልበትን
የልጅነት መንፈስ እንዲሁ ሰጠኸን፡፡ የኃጢአት ባሮች ሳለን የአብርሃም ልጆች ነን ብለን ስንመካ የመንፈስ ፍሬ ሳይኖረን ወደቅን፤
አንተ ግን የባርነት ደብዳቤአችንን ቀደድክና ወደ ነጻነት፣ ከምንመላለስበት የጨለማ ሕይወትም ወደሚደነቅ ብርሃን አወጣኸን፤ ዳግመኛም
የአብርሃም ልጆች አሰኘኸን፡፡ ቅዱስ አባት ሆይ! የሥጋ ፈቃዳችንን ተከትለን ይህን ልጅነታችንን ሳናቆሽሽ እስከመጨረሻ
እንድንጠብቅ አንተ እርዳን?! ክብርና አለቅነት አምልኮትና ውዳሴ ለአንተ ይሁን እስከ ዘለአለሙ ድረስ አሜን!
አሜን
ReplyDelete