በዲ/ን
ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 6 ቀን
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ስመ እግዚአብሔር
ቀዳማዊ ዘእንበለ ትማልም፤ ወማዕከላዊ ዘእንበለ ዮም፤ ወደኃራዊ ዘእንበለ ጌሰም ፤ብሉየ መዋዕል ዘእንበለ ዓም፤ ፈጣሬ ኩሉ
ዓለም ዘእንበለ ድካም፤ ባህረ ምሕረት ዘእንበለ አቅም፤ ብኁተ ሕሉና እስከ ለዓለመ ዓለም አሜን::
"ወባህቱ ለእልክቱሰ ጸላእትየ እለ ኢይፈቅዱ
እንግሥ ላእሌሆሙ አምጽእዎሙ ዝየ ወርግዝዎሙ በቅድሜየ= ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ
አምጡአቸው ።" ሉቃ.19:27
መግቢያ
(አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው
አትመልስለት። ~~~>ምሳ. 26:4)
ክርስትና ከሰብአዊነት ይልቃል...መንፈሳዊነትም
ከባለአእምሯዊነት ይበልጣል....ሃይማኖትም ከስሜት በላይ ነው::
በቅርቡ ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያን ቅዱሳን ሰማዕታተ ሊቢያ
ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ በተመለክተ ድርጊቱ የእምነቱን መርኅና የቁርአንን አስተምህሮ አይወክልም በሚል ዘውግ ከመሟገትና
ከማውገዝ ይልቅ "መጽሐፍ ቅዱሳችሁም ቢሆን :- ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ
አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። ይላል እኮ" በሚል ቅዱሱን ቃል ጠቅሶ ለመክሰስና ነቅሶ ለማርከስ የሚዳክሩ በዝተዋል::
እንኳን ቁርአኑ መጽሐፍ ቅዱሱም ቢሆን እንዲህ ይላል የሚለው
አንደኛ ቁርአኑ እረዱ ግደሉ ይላል ብሎ ማመን ሲሆን
ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስን ብልጫ ማመናቸውን ያሳየ ነው::
ለኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ልክ ለመሆኑ ማረጋገጫችን የቁርአን ምስክርነት
ወይም የሙስሊሞቹ ቃሉን ማጣቀስ አይደለም ይህንንም ፈጽሞ ከምስክርነትም የምናገባውና ጠቅሰውልናል ብለን የምናመሰግናቸው ዓይደለም::
በአንጻሩ የረከሰውን ሲቀድስና የበደለውን ሲወቅስ ማየቱ፤ በቅዱሳን መጻፉን ተፈትኖ ማለፉንመረዳቱ፤በአዝማናት ጅረት ማለፉንለትውልድ
መትረፉን መመልከቱ ብቻ ለኛ አምኖ መቀበል አክብሮ መከተል በቂ ምክንያት ነው:: በስንፍናቸው ለሚኖሩ እንደድክመታቸውና
በእነርሱ አመክንዮ ቁርአንማ እንዲህ ይላል እያሉ መመለስ ለቤተክርስቲያናችን የሚያቅት አይደለም ሆኖም ከስንፍናቸው ላለመተባበር
የመጡበትንም የጥፋት መንገድ በመናቅ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ብቻ እንናገራለን:: ጠቢቡ እንዲህ ሲል እንደነገረን
"አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።" (ምሳ. 26:4)
እንግዲህ በዓይነ ሥጋ እያነበበ በዓይነ ህሊና መረዳቱን
ለሚሻ ግን በመጀመርያ ቃሉን አብራርቶ ከማስረዳትና ፈቶ ከመግለጥ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በምን መንገድ መረዳት
እንደሚገባ ጥቂት ነጥቦች እናስቀምጥ::
፩. መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት አንብቦ
መረዳት ይገባል?
(ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ
ነው።~~~>2ኛ. ቆሮ. 4:3)
"በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ
ቅዱስ ተነድተው" የተናገሩትን መለኮታዊ ቃል "ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም" (2ኛ
ጴጥ.1:20) እናስተውል መጽሐፍ ቅዱሳችን ሥጋዊና ደማወዊ አሳብ ያልተቀየጠበት ንጹህ የእግዚአብሔር መልእክት የተጻፈበት
እውቀትና እውነት ውበትና ሕይወት የሚገኝበት መንፈሳዊ መአድ የሰማይ መንገድ ስንቅ የነፍስ ቀለብ ነው:: በዘመናችን ብዙዎች
የሚስቱት ዓይነ ሥጋቸው አጥርቶ ከማየት እየፈዘዘና ዓይነ ልቡናቸው ደርሶ ከማስተዋል እየደነዘዘ ተቸግረው ነው:: ወደ መጻሕፍቱ
ምስጢር ራሳቸውን እያስጠጉ በእምነት ከመረዳት ይልቅ ቃሉን ወደ ገዛ ፈቃዳቸው እየሳቡ ያልተጠቀሙበት አያሌዎች ናቸው መጽሐፍ
" ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።" እንዳለ (ዕብ.4:2) ጥንቱንም
በወንጌል ቅዱስ ቃሉን ለግል ሃሳባቸው የሚጠቃቅሱትን እንደ ገዛ ስሜታቸውም የሚፈቱትን ስሁታን የክብር ጌታ አምላካችን እንዲህ
እያለ ወቅሷል "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።"
(ማቴ.22:29) ስለዚህ ለጥፋት የተሰጡ እውነቱን ከማወቅ ፈቀቅ ያሉና የሃይማኖት ጤናቸው የታጎለ እንመርምረው ቢሉ
የማይደርሱበት እንፈትነው ቢሉ የማይረዱት እንግለጠው ቢሉ የማይከፍቱት ሆኖባቸው በከንቱ ሲዳክሩ ይኖራሉ "ወንጌላችን
የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው።" እንዲል ( 2ኛ. ቆሮ. 4:3)
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት አንድ ሁለት ቃል እየመዘዙ ለሚጮኹ
አላዋቂ ሳሚዎች ሊቁ መልአከ ብርሀን አድማሱ ጀንበሬ "በታላቅ
ቅል ውስጥ እንደተከተቱ ሁለት ቅንጣቶች ሁለት ቃላትን እያንኳኳችሁ የዓለምን ጆሮ ከምታደነቁሩ ለምን በባህረ መጻሕፍት ውስጥ
የሚያበራ እንቁ ምስጢራቸውን ለማየት አትጠልቁም?" ሲሉ መክረዋል እኔም ያንኑ ደግሜ በማጽናት ቃሉን ከባህረ መጻሕፍት
አስረጂ በማጣቀስ ወደ ማብራራት እሻገራለሁ ::
፪. ስለመግደል መጽሐፍ ቅዱስ
ክርስቲያኖችን ምን ያስተምረናል?
በምክረ ሰይጣን ተታልሎ በኃጢዓት ተጎሳቁሎ ኃይሉ ደካማ
ጸሎቱ የማይሰማ ሆኖ ሞት ተፈርዶበት በመንጸፈ ደይን የወደቀው የሰው ልጅ ገና በጠዋቱ በህገ ልቡና እያለ ነበር
ቅትለትን(መግደልን) የፈጸመው:: እግዚአብሔር ግን በቅናት ስሜት ወንድሙን ስለገደለው ቃየን ያለው ይህንን ነው
"አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።" (ዘፍ.
4:11) ስለዚህ ማንንም መግደል ያልተደገፈ ይልቁንም የሚያስቀጣ ነውና እንዲህ ትብሎ ተቀምጧልና "የሰውን ደም
የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።" (ዘፍ. 9:6)
ኋላም ከህገ ልቡና ወደ ህገ ኦሪትም ሰውን ሲያሻግረው
በሰጠው የሕይወት መመርያ ውስጥ ኢትቅትል (አትግደል) የሚለውን
የፍቅረ ቢጽ ማሳያ ሕግ አኑሯል::( ዘጸ. 20:13, ዘዳ 5:17)
በፍጻሜው ግን ራሱ ፈጣሪው ያንን ወድቆ የነበረ የአዳምን
ሥጋ ለብሶ በበደለው በደል ኹሉ ክሶ የረከሰውን ቀድሶ ያረጀውን አድሶ የቀደመ ልጅነቱንና ኃይሉን መልሶ ጸሎቱ ተሰሚ መስዋዕቱ
ጉዳይ ፈጻሚ እንዲሆን ከማኅበረ መላእክት ሊጨምረው ወደ ህገ ወንጌል ሲያሻግረው ስለመግደል ከቀደመው ስቦ ይህን ብሎታል
"ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ
ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤" (ማቴ. 5:21-22)
እንግዲህ ተመልከቱ ወንጌል ምንድናት ምንስ ትላለች ለሚል
መጽሐፍ ይህን ይላል "ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም
አድርጉ፥የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን
ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ
ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።"(ሉቃ. 6:27, 32, 35)
ስለዚህ :–
♥...
ክርስትና ከሰብአዊነት ይልቃልና የሚያስተምረን ለሰው ማዘንን ብቻ አይደለም ይልቁንም እግዚአብሔር ከመፍጠር ላልናቀው ሁሉ
መራራትን ጭምር እንጂ "ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።" (ምሳ.
12:10)
♥...መንፈሳዊነትም
ከባለአእምሯዊነት ይበልጣልና የሚያስረዳን አለመግደልን ብቻ አይደለም ትድግናን ጭምር እንጂ "ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ
ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን" (ምሳ. 24:11)
♥...
ሃይማኖትም ከስሜት በላይ ነውና ምስክርነቱም ይህ ነው የምንቀጣው ሌላውን ስለገደልን ብቻ ያይደለ ስለምንጠላም ጭምር እንጂ
"ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።"
(1ኛ.ዮሐ.3:15)
እንግዲህማ በክርስትናችን ጽድቅ የሚገኝ በመጥዎተ ርዕስ
ለቢጽ (ለሌላው ራስን አሳልፎ በመስጠት) ጭምር እንጂ ባለ
መግደል ብቻ አይደለም:: በአንጻሩ ግን
v .ከደም የማይሸሸውን ሰው ደም ይከተለዋል "ደምን ስላልጠላህ ደም
ያሳድድሃል።"ይላልና (ሕዝ.35:6)
v .በሰይፍየሚታመነውምሰይፍይረታዋል "ሰይፍየሚያነሡሁሉበሰይፍይጠፋሉና
..." ተብሎተጽፏል (ማቴ. 26:52)
ስለዚህ በቅድስና ሕይወት ለክርስቶስ መንግሥት ራሳቸውን
ምስክር ያደረጉ ቅዱሳን ትዕግስትና እምነታቸው የተገነባው ራስን በመስጠት ላይ ነው። በሥጋ ሞተው አለፉ ነገር ግን ገዳያቸውን
ረትተው ለሰማይ መንግሥት ተረፉ መጽሐፍም እንዲህ እንዳለ "በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል
ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።" (ራእ. 13:10) ይህንንም ያገኙት ከጌታቸው ከአምላካችን ነው እርሱ
በፍለጋው ይህን አስተምሯልና "እንዘ ይጼእልዎ ኢጸአለ ወእንዘ የሐምምዎ ኢተቀየመ ከመ ያርእየነ ለነ አንቀጸ ትህትና
ፍጹመ = የጠሉትን አልጠላቸውም ያሳመሙትንም አልተቀየማቸውም ፍጹም የሆነውን የትህትናን በር ያሳየን ዘንድ" እንዲል
፫. ታድያ በመጽሐፍ እረዱ ግደሉ ፤
ቁረጡ አቃጥሉ መባሉ ስለምነው?
(እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥
በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።~~~>ራእ.2:16)
አበው "መጽሐፍ ቅዱስ የብረት ቆሎ ነው"
ይላሉ አበላሉን ሳያወቁ ጥርሳቸውን ለሚያደቁ ይህ ጥሩ ምክር ነው:: መለኮታዊ ምስጢር የሆነው የመጽሐፉም ቃል በሰው ጥበብ
አይፈታም በሥጋ ምርምር አይረታም ስለዚህ የራሱ ስልትና ዘይቤ አገባብና ፍቺ ያለው ነው:: ይህን ወደ መረዳት ለመሻገር ደግሞ
መማር... ማንበብ... መመርመር... መጠየቅ... መጸለይ... የሥጋን ፈቃድ ቀጥቶ ራስን በመግዛት ለእግዚአብሔር መገዛት
ያስፈልጋል::
ሁሉም ቃል እንደተገኘ በቁም ንባቡ አይፈታም ለዚህም ነው
እንዲህ ተብሎ የተጻፈው "ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።" (2ኛ.ቆሮ. 3:6)
ለምሳሌ:- ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው እርሱ ሰላማችን
ነውና መለያየትን ሽሮ የጥል ግድግዳን በሥጋው አፍርሶ፤ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ነው (ኤፌ. 2:14-15) ነገር ግን በአንጻሩ
ደግሞ ራሱ "በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን
እንጂ።" (ሉቃ. 12:51) ሲል እናገኘዋለን። እንግዲህ ልብ እናድርግ እኛው ከቃሉ ካልተጣላን እንጂ ሁለቱ መልእክታት
ተቃርኖት የለባቸውም ለመረዳትም አገባቡን በማጤን "እንዴትና መቼ ለማንና በምን ምክንያት ተነገረ?" የሚለውን አካቶ
ማጥናቱ ተገቢ ነውና ።
ከላይ ያየነውን በምሳሌነት ጠቀስን እንጂ መሰል ሃሳቦች
በብዛት እያነሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማሳየት ይቻላል:: በዚህ አጭር ጽሑፍ ግን በርእሱ ያነሳነውን ቃል ብቻ ብናይ ለሌሎቹም
አገባቦችም እንደ ዓይን መግለጫ እንደበር መክፈቻ ሊረዳን ይችላልና ትኩረታችንን ወደቀደመ ነገራችን እንመልስ::
እንግዲህ ቀድሞ መግደል በሰው ዘንድ ምን ያህል አስጸያፊ
ተግባርና እግዚአብሔር የሚጠላው ኃጢዓት እንደሆነ አይተናል በሌላ ቦታ ግን
"ወባህቱ ለእልክቱሰ ጸላእትየ እለ ኢይፈቅዱ
እንግሥ ላእሌሆሙ አምጽእዎሙ ዝየ ወርግዝዎሙ በቅድሜየ= ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ
አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።" (ሉቃ.19:27) የሚለውንና ሌሎች ተመሳሳይ መልእክታትን ያለአገባብና ያለአግባብ
እየጠቀሱ መጽሐፍ እረዱ ግደሉ ፤ ቁረጡ አቃጥሉ ይላል እያሉ የሚስቱና ለማሳት የሚጥሩ ተበራክተዋል።
ይህን ለመረዳት ሦስት ነጥቦች ብቻ እናስቀምጥ
1.
ቃሉ እንዴት ባለ አገባብ ነው
የተነገረው?
ታሪኩ የሰፈረበት
ምንባብ እንደሚያስረዳው ጌታችን አስቀድሞ የጠፋውን ሊፈልግ ሊያድንም እንደመጣ በቃል አስተምሮ ሲያበቃ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት
በምሳሌ ሲያስረዳ ከላይ ያነሳነው ቃል ገልጿል:: እንግዲህ አስተውሉ፡፡ አንደኛ ታሪኩ በምሳሌ የተነገረ ነው፡፡ ያም ብቻ ደግሞ አይደለም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ለራሱም መንግሥት ይዞ ሊመለስ የሔደው መኮንን በመጣ ጊዜ የተናገረው መሆኑም ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ እንዴትና መቼ
ተነገረ የሚለውን በግልጽ ተቀምጧል:: ተመልከቱ ይህን በምሳሌ የተነገረ ቃል ነውና "ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባን ቃልና የተሸሸገውን ነገር
ለማስተዋል" ምን ያስፈልጋል ካልን ጠቢቡ ሰሎሞን መንፈሳዊ ዓይን ፈሪሃ
እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ ይጠይቃል ይለናል (ምሳ.1:6-7)፡፡
ስለዚህ ቃል በቃል
እንደወረደ አይፈታም:: ለነገሩ በምሳሌ የተነገረበት አንዱ አቢይ ምክንያት
የማይረዱትንና ያለአገባቡም የሚተረጉሙትን ለመዝለፍ ነው::
ጌታችን ራሱ በምሳሌም
ለምን እንደሚያስተምር ሲጠየቅ "እንዲህም አላቸው፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት
ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭላሉትግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥እንዳይመለሱ
ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል።"
(ማር. 4:11-12) ይላል:: ስለዚህ ክርስትናችንን አይተው ለማይመለከቱ ሰምተውም ለማያስተሉ
መፋረጃ ሲሆንባቸው ይኖራል:: በመንፈሳዊ መነጽር ይህንን መረዳት ለሚሻ ግን የምሳሌው
ፍቺ የሚያሳየን በኀልቀተዓለም እውነተኛው ዳኛ ለፍርድ ሲመለስ የሚሰጠውን ፍትህ ነው:: ስለዚህ በዚህ የአምላካችን ትምህርት አንደኛ የተነገረበት መንገድ በምሳሌ እንጂ በቁሙ የተነገረ አለ መሆኑንና ሁለተኛ
ደግሞ መቼ እንደሚፈጸም ስንመለከት ስለ ፍጻሜ ፍርድ እንጂ አሁን ስላለ ድርጊትም የሚያስረዳ አለመሆኑን ማጤን ይገባል::
2. እረዱ የተባሉትስ እነማን ናቸው?
በምሳሌ በተቀመጠልን ታሪክ ላይ እንደምንረዳው ያልታመነውን እንዲቀጡ ወይም "እንዲያርዱ" የታዘዙት "በዚያም ቆመው የነበሩትን" እያለ የጠቀሳቸውን ነው:: እነዚህም ቀድሞ ለምልጃ የቆሙ ኋላ በፍርድ ቀን ግን ፈቃዱን የሚፈጽሙ ቅዱሳን መላእክት ናቸው:: እነዚህን በሌላ ቦታ የፍርድ ቀን አጫጆች ይላቸዋል፡፡ "እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤መከሩም የዓለም መጨረሻ
ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው።" (ማቴ.
13:39) ስለዚህም ፍሬን
ከገለባ ስንዴን ከእንክርዳድ ምርቱንም ከግርድ ሊለዩ ታዘው የሚላኩ መሆናቸውን መረዳት ይገባል:: እንዲሁም ደግሞ በሌላ ምሳሌ ወደ እሳት የሚጥሉ የሚያቃጥሉም ተብለው ተገልጸዋል "በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።" (ዮሐ.15:6 ) እንዲል:: ስለዚህ በዓለም መጨረሻ ተልከው ያልታመነውን በምሳሌ እንደተቀመጠው የሚያርዱ የሚያቃጥሉና ከእሳት የሚጥሉ እነዚህ ቅዱሳን
መላእክት ናቸው::
3. ማረድምንድርነው?
ሁላችን እንደምንረዳው እርድ የሚፈጸመው በሰይፍ በጎራዴ አልያም ይህን በመሰለው የስለት መሣርያነው:: ቅዱስ መጽሐፋችን ግን ደጋግሞ የሚነግረን በመጨረሻው ዕለት ቅን ፍርድ እንጂ የሰይፍ እርድ እንደሌለ ነው:: እንግዲህ የምሳሌውን ፍቺና የምስጢሩን አገባብ ማጤን ስለሚገባ በቁሙ ደም ማፍሰስ እንደሚኖር መጠበቅ የለብንም:: ስለዚህ በመጨረሻው ቀን የሚፈጸመውን ፍርድ በእሳት መቃጠል በሰይፍ መታረድ ነው ሲል በጽድቅ ያለ ፈታሂነቱን ርቱዕ የሆነ
ኩነኔውን መግለጹ ነው:: ለዚህም ነው መጽሐፍ ይህን የፍትህ መንገድ የእሳትና የሰይፍ
ብሎ የሚጠራው "እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ
ይፈርዳል" እንዲል (ኢሳ. 66:16)::
ሰይፍ ነፍስን ከሥጋ
እንዲለይ ጻድቃንን ወደኔ ኑ ኃጥዓንን ከኔ ራቁ ብሎ በአፉ ሰይፍ እውነተኛው ዳኛ ይለያቸዋልና የአፉን ፍርድ ሰይፍ ይለዋል "እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም
ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።"(ራእ.2:16)፡፡
በሌላም ሥፍራ "እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።" (ዮሐ. 12:48) ይላልና ቃሉም ሰይፍ እየተባለ ተጠርቷል፡፡ ለዚህም ቅዱስ
ጳውሎስ "የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር
ቃል ነው።" (ኤፌ.
6:17) ይለናል:: መልሶም "የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ሁለትም አፍ
ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥" (ዕብ. 4:12)፡፡ እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ እኛ በምንረዳው ስሜት ፍርዱን
መመርመር ፈጽሞ አይገባም፡፡ ጥንቱን "ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥"
መባሉ ቅሉ ለዚህ
ነውና
(ሮሜ. 11:33):: አስተውሉ ደካሞች በሚሰሩት ድፍረትና በሚናገሩት ስህተት
ሳይጸጸቱ በጥጋብ አውታሯ እንደበጠሰች በቅሎ ፋነው ከገደል እንዳይገቡ
"ነገር ግን እነዚያን
በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።"
መባሉ ስለምን እንደሆነ
እርሱ በረዳን መጠን ፈትተን አይተናል::
ማጠቃለያ
(እንግዲህ የእግዚአብሔርን
ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ
አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ።~~~>ሮሜ. 11:22)
አምላካችን በእድሜ
ዘመናችን በሰጠንም መዋዕል ንሰሃ እንድንገባና እንድንመለስ ፍጹም በሆነ አባታዊ ርኅራኄ ይታገሰናል "ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።" (ያዕ. 5:11) እንደ ሥራችን ቢሆን ዛሬን መትረፍና ለነገም መታሰብ ሳይሆን
ትናንትናን ማለፍ እንኳ የማይገባን ነበርን "ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ" (ኤፌ.2:4) ከነነውራችን በደልን በፊቱ ተሸክመን ስንቆም እርሱ ደብረ
ምህረት ባህረ ትዕግስት ነውና ይምረናል፤ ይታገሰናል፡፡
"አምላካችሁም እግዚአብሔር
ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና"
(ኢዩ.2:13)፡፡ ይሁንና ግን ይህን በፍርድ የማይዛባ ፍቅሩን በመጨረሻው ዘመን የሚገልጠው ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን እንደ ምግባሩ
ልክ በመክፈል ነው:: መልካም ምግባርና በጎ ትሩፋት ያልታየባቸውን ሳያዝን ያጠፋቸዋል፡፡ "እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር
ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ።"
ይለናል (ሮሜ. 11:22) እንግዲህ መቆረጥ መታረድ መቃጠል የተባሉ ኃጥኡን ከጻድቁ የሚለዩ የጽኑ ፍርዱ መገለጫዎች ናቸውና ምግባር አጽንቶ የሚመጣውን
ርስት ደጅም ጥናት ይገባል:: በአንድ ወቅት በክርስትናው ውስጥ የተሰጠውን ፍጹም የፍቅር
ህግ በማድነቅና የአምላኩን ፍትህ በማርቀቅ ባለ ቅኔው እንዲህ ሲል ተቀኘ፡-
"ኮንኖተ ኃጥእ ኢይደልወ ከምንተ
አፍቅሩ ጸላእተክሙ እስመትብል አንተ"
(ኃጥዑን መኮነን ላንተ አይገባህም
.... ጠላታችሁንን ውደዱ
ብለኸናልና)፡፡
በዚህ የቅኔ አገባብ
ምስጢራዊ ፍቺ "ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥"! (ሮሜ.
11:33) እያልን ወደ መደነቅ
መሻገር እንደሚገባን ማስተዋል ይኖርብናል። ይህን ፍርድም እንዲፈጽሙ የሚላኩት ምቅዱሳኑ ለማረድ እንደተላከ
ጦረኛ ይህን ፍትህን በደስታ ይፈጽማሉ፡፡ "ቅዱሳን....የእግዚአብሔር ምስጋና በጕሮሮአቸው ነው፡፡ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው፥በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል
ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ ... የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ።ለቅዱሳን ሁሉ ይህች
ክብር ናት። ሃሌሉያ።" (መዝ.149:5-9)፡፡
ከመጽሐፍ ያልተገኘውን ከገዛ ልባቸው አንቅተው የሚጠቅሱና በምላስ ላይ የተገኘውን የማይጠቅም ከንቱ ነገርን መናገር ልማድ
ለሚያደርጉ "ባርክዎሙ ለእለ ይረግሙክሙ" እንደተባለው የሰው መዳኑን እንጂ መጎዳቱን የማይወድ የቅዱሳን አምላክ ቸር ፈጣሪያችን የአባቶቻችንን ምክር የምንሰማ
በትርኅው ጆሮ የሰማነውን የምናመዛዝንበት ረቂቅ አእምሮ ሰጥቶ ኹላችንንም ይቅር ብሎ ለሰማይ መንግስቱ ለማያልፍ ርስቱ ያብቃን:: አሜን!!!
ስማእትነት የተቀበሉ ግብጻዉያን እና ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው ? ኤርትራውያን ስማእታት ኣልነበሩን?
ReplyDeleteወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው።
ReplyDelete2ኛ. ቆሮ. 4:3)
"በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው" የተናገሩትን መለኮታዊ ቃል "ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም"
(2ኛ ጴጥ.1:20)
እናስተውል መጽሐፍ ቅዱሳችን ሥጋዊና ደማወዊ አሳብ ያልተቀየጠበት ንጹህ የእግዚአብሔር መልእክት የተጻፈበት እውቀትና እውነት ውበትና ሕይወት የሚገኝበት መንፈሳዊ መአድ የሰማይ መንገድ ስንቅ የነፍስ ቀለብ ነው::
betame enamesegenalen
ReplyDelete