Tuesday, May 12, 2015

“ከካህናት ጋር አብሬ ስለማገለግል ንስሐ መግባት ከበደኝ፡፡ ምን ላድርግ?”



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ ግንቦት 4 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችኁ? ዛሬም ከአንባብያን ከተላኩልኝ ጥያቄዎች መካከል አንዱን መርጬ በአበው ካህናት የተሰጠውን ምላሽ ይዤላችኁ ቀርቢያለኁ፡፡ ዛሬም መልሱን የሚሰጡን በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙርና የዘንድሮ ተመራቂ የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ ለአባታችን ተናጋሪ አንደበት ለእኛም ሰሚ እዝነ ልቡና ያድለን፡፡ አሜን!!!
ጥያቄ፡-  “ውድ መቅረዞች! እንዴት አላችኁ? የመቅረዝ አንባቢ ነኝ፡፡ ከምእመናን የምታስተናግዱት ጥያቄ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኔም ከንስሐ አባት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አለኝ፡፡ እኔ በምኖርበት አከባቢ ከካህናት ጋር አብሮ የመሥራትና የመቀራረብ ነገር አለ፡፡ ይኽም ለእኔ ብቻ ሳይኾን የሀገሩ ጠባይ የፈጠረው ነው፡፡ እናማ ባለን ቅርርብ በቤተ ክርስቲያን ጕዳይ አለመግባባት ሲፈጠርም ኾነ በሌላ ጕዳይ በአካልም ኾነ በስልክ እንደ ልብ ስለምናወራ የሰው ስም እያነሣን ስናማ፣ ስናወግዝ አብረን ስለምንውል እንዴት መናዘዝ እችላለኁ?”
አንዳርግ ነኝ ከቺካጎ

ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  ምእመናንና ካህናት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መቀራረባቸው በራሱ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የኹሉም ናት፡፡ ቃለ ዓዋዲውም ምእመናን በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ ይደነግጋል፡፡ በቅዳሴአችን ጊዜም ይ.ካ. (ይበል ካህን) እንዲል የካህኑ ድርሻ አለ፤ ይ.ዲ. (ይበል ዲያቆን) እንዲል የዲያቆኑ ድርሻ አለ፤ ይ.ሕ. (ይበል ሕዝብ) እንዲልም የምእመናን ድርሻ አለ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሥጋው ሥጋ መለኮት፣ ደሙ ደመ መለኮት የሚኾነው በኹላችንም ጸሎት ነው፡፡ ተሳትፎው፣ ከአባቶች ጋር ያለው ቀረቤታ መቀጠል አለበት፡፡ ነገር ግን፡-
1.  በአገልግሎታችን ውስጥ ወደ ሌላ ከመሔዳችን በፊት ድርሻችንን ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ በምእመንነት ያለን እንደየዕድሜአችን “ድርሻዬ ምንድነው?” ብለን ልንጠይቅ ያስፈልጋል እንጂ “ስለ እነ እገሌ ስለምናወራ” ብለን ልንርቅ አያስፈልግም፡፡ አካሔዳችንን፣ አቀራረባችንን ነው ማስተካከል ያለብን፡፡ ከዚኽ አንጻር ስለ አገልግሎት ግንዛቤ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በቅዳሴአችን የካህኑ፣ የዲያቆኑ እና የምእመኑ ድርሻ ተለይቶ የተቀመጠ ነው፡፡ “ሰላም ለኵልክሙ” ማለት የካህኑ እንጂ የምእመናን ድርሻ አይደለም፡፡ የምእመናን ድርሻ “ምስለ መንፈስከ” ማለት ነው፡፡ በሌላው አገልግሎትም እንደዚኹ ነው፡፡ ቃላ ዓዋዲው ያስቀመጠው የኹላችንም ድርሻ ለይቶ ነው፡፡ ስለዚኽ ሌላ ችግር ውስጥ ላለመግባትና ከመስመር አልፈን የማይገባንን ነገር እንዳናወራና እንዳንሠራ ድርሻችንን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ 
2.  በስጦታችን ለማገልገል ዝግጁ መኾን፡፡ በክህነትም ያለን በማኅበረ ምእመናንም ያለን ስጦታችንን ለይተን ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ የመዘመር ስጦታ ሳይኖረኝ “ልዘምር” ብል አገልግሎቱን እያደናቀፍኩ እንጂ እየጠቀምኩ አይደለም፡፡ ልክ እንደዚኹ እያንዳንዳችን “የትኛው ነው ስጦታዬ? በማስተባበር ነውን? በጽሑፍ በማገዝ ነውን? በመምከር ነውን? በማስተዳደር ነውን? ከዘመናዊው ትምህርት በቀሰምኩት መሠረት በሙያዬ ነውን?” ብለን ልንጠይቅና በዚኹ ስጦታችን ለማገልገል ዝግጁ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡
3.  በዓቅማችን፡- ዓቅም ሲባልም የዕውቀት፣ የገንዘብ፣ የጉልበት ወይም የጊዜ ዓቅም ሊኾን ይችላል፡፡ የእኔ ዓቅም በስብሰባው ላይ ተገኝቼ አስተያየት መስጠት ከኾነ ጕዳዩ እዛው ያበቃል፡፡ ከስብሰባው ውጪ ላወራ አይገባኝም፡፡ ይኼ ዓቅምን አለማወቅ ነውና፡፡ ከዓቅማችን በላይ በምናደርጋቸው ነገሮች ደግሞ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው በእጅጉ ያመዝናል፡፡ ለሐሜትና ለሌላ ኃጢአት የምንዳረገው ዓቅማችን የቱ ጋር እንደኾነ ለይተን ካላወቅነው ነው፡፡ ስለዚኽ “የእኔ ዓቅም የቱ ጋር ነው?” ብለን በአግባቡ ልንለየው ያስፈልጋል፡፡
ይኽን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን ጠያቂው እንዳነሡት ወደ ሐሜት ይወስደናል፡፡ ሐሜት ማለትም ባለቤቱ በሌለበት በስልክም ኾነ በአካል ስሙንና ግብሩን ማጥላላት፤ መንቀፍ፤ መስደብ፤ መናቅ፤ ማቃለል፤ ማስነወር፤ መዝለፍ ማለት ነው /ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ከደስታ ተክለ ወልድ፣ ገጽ 874/፡፡ በገላትያ መልእክት ከተጠቀሱት የሥጋ ሥራዎችም አንዱ ሐሜት ነው /ገላ.5፡22/፡፡ ሐሜት በአንደበት መሳት ነው፡፡ ሐሜት ትዕቢትን፣ ክፋትን ያሳያል፡፡ ሐሜት ፍቅር አልባ መኾንን ያሳያል፤ “ወንድሙን የሚጠላ ቢኖር ርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው” እንዲል ሃይማኖት የሚገለጠው በፍቅረ ቢጽ ነውና፡፡ ስለዚኽ ወንድማችንን የምንወደው ከኾነ የታመነበት ስሕተት በሠራ እንኳን፡-
1.  ብንችል ለዚያ ስሕተት ሠርቷል ለምንለው ሰው ስሕተቱን እንዲያርም በግልጽ መንገር፡፡
2.  ጠብ ተፈጥሮ እንደኾነ ይቅርታ መጠያየቅ፡፡
3.  ባንችልና ቀጥታ የመናገር ዓቅም ባይኖረን ደግሞ በሽማግሌና በሌላ ማስገሠጽና ማስመከር ያስፈልጋል፡፡
እንዲኽ መኾን ሲገባው ግን “እገሌ እንዲኽ በማድረጉ፣ እገሊት እንዲኽ በማድረጓ” በማለት ያንን አካል በክፋት ጐዳና ማንሣት እግዚአብሔር የሚጸየፈው ተግባር ነው፡፡ ከካህን ጋርም ይደረግ፣ ከምእመናንም ጋር ይደረግ፣ ከቆራቢ ጋርም ይደረግ ሐሜት ሐሜት ነው፡፡ 
ወደ መፍትሔ ሐሳቦች ስንመጣም፡-
1.  ከሐሜት ራስን ማግለል፡፡ “ራስህን አድን” /ዘፍ.19፡17/ የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ አንድ ክርስቲያን ከኃጢአት መራቅ የሚዠምረው ከራሱ ሕይወት ነው፡፡ ለቤተሰብም ለሌላም አካል እየበረታን የምንሔደው በግላችን በእምነትም በምግባርም ስንተጋ ነውና፡፡ ስለዚኽ ከራሳችን ስንዠምር በቀና መንገድ ብቻ መነጋገርን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ካህናት አባቶቻችንን እኛው ራሳችን እያሰናከልናቸው እንደኾነስ? ይኼን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
2. ባለቤቶቹ ባሉበት መነጋገርን መለማመድ፡፡
3. ለሐሜት ከሚገፋፉ ነገሮች መራቅ፡፡
4. ሐሜት ሲነሣ ሐሜቱ እንዳይቀጥል የማቋረጥ ዘዴዎችን መጠቀም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው መጥቶ “እንዲኽ አድርጎ፤ እንዲኽ አድርጎኝ” ቢለን በቀና መንገድ ተርጉመን “ባያውቅ ነው፤ ባያስተውሉ ነው” ብንል፡፡ ወይም ደግሞ “እስኪ ባሉበት እናወራለን” ብንል ወሬው ተቋረጠ ማለት ነው፡፡ ያ ሰው ከዚያ በኋላ እንደዚኽ ዓይነት ወሬዎችን ከእኛ ጋር አያወራም፡፡ እንደዉም “የሰው ሐሜት አይወድም” ብሎ ተምሮ ነው የሚሔደው፡፡ ወይም ደግሞ “ይኼን ሌላ ጊዜ እንነጋገራለን” ብለን በሌላ አጀንዳ ወሬውን ብንቀይረው ሐሜቱ ይቋረጣል፡፡
5. ለአገልግሎትና ለንስሐ ብቻ አባቶችን ማግኘት፡፡ “የካህናትና የንስሐ ልጆች ግኑኝነት እስከምን ድረስ ነው?” የሚለውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከዚኽ አንጻር “ከንስሐ አባቶቼ ጋር የሚኖረኝ ግኑኝነት ምን መምሰል አለበት? እስከ ምን ደረጃ ነው?” ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ ከንስሐ አባቶች ጋር ስለ አገልግሎት፣ ስለ ቃለ እግዚአብሔር፣ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ማውራት፡፡ ጠያቂው እንዳነሡት በአገልግሎት ዕንቅፋት የሚፈጥሩ ሰዎች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ እነዚያን ማማት ማውገዝም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲኽ ሊኾን አይገባም፡፡ ባይኾን ከንስሐ አባቶቻችን ጋር ስንገናኝ “እንደዚኽ ዓይነት ችግሮች ተፈጥረዋል፤ ምን እንድርግ? የእኛ ድርሻ ምንድነው?” ብለን መነጋገር አለብን፡፡ “እናስወግደው፣ ሕዝቡን እናነሣሣበት” ዓይነት ግን መኾን የለበትም፡፡ ከዚኹ በተጨማሪ ከንስሐ አባቶቻችን ጋር ማኅበራዊ ጉዳዮችን ልንነጋገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን የምንነጋገርበት ርእሰ ጉዳይ ካህናት አባቶቻችንን የሚመለከታቸው ብቻ ሊኾን ይገባል፡፡ ለምሳሌ ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ሥራ በምክር፣ በሐሳብ፣ በጸሎት እንዲያግዙን ሊኾን ይችላል፡፡ ከዚኽ ውጪ ግን ንስሐ አባቶቻችንን የምንፈልጋቸው ስለ ፖለቲካዊ ጉዳይ፣ ስለ ገበያ መውጣትና መውረድ፣ ወይም ስለ ታተመው መጽሔትና ጋዜጣ፣ ወይም ስለ ሌላ አጀንዳ አይደለም፡፡ ምናልባትም’ኮ ከላይ እንደጠቀስኩት እርሳቸውን እያሰናከለ ያለው እኛ ይዘነው የምንሔው አጀንዳ ሊኾን ይችላል፡፡ በአጭሩ ከካህናት ጋር የምንገናኝበት ጊዜም ኾነ የምናወራበት አጀንዳ ውሱን ሊኾን ይገቧል፡፡ እንደዚኽ የማናደርግ ከኾነ ግን ጠያቂው እንዳነሡት ንስሐ ለመግባት ብርታት አናገኝም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ) ካህናት አባቶቻችንን ማሳጣት ሊመስለን ይችላል፡፡ ኹለተኛ) በጊዜ ሒደት ግኑኝነታችን ተበላሽቶ “ዐወቅኩሽ ናቅኩሽ” የሚል ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡ ሦስተኛ) ከርሳቸው ጋር አብረን ያወራነውን ወሬ መልሰን ብንነግራቸው “ይኽቺማ ምን አላት?” ብለው ኃጢአታችንን ሊያቃልሉብን ይችላሉ፡፡
6. እነዚኽን ኹሉ አድርገን ካልተስተካከለ ግን ሌላ ንስሐ አባትን መያዝ ያስፈልጋል፡፡   
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount