Sunday, July 5, 2015

ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ /ዘፍ.19፡11/


በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
"ወደላይ አቅንተን እንለምን ያን ጊዜ የመለኮትን ነገር ከሚናገሩ መጻሕፍት እውቀት ይገለጽልናል" ይህን ቃል ለቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ለጢሞቴዎስ የላከው በአርዮስፋጎስ (መካነ-ጥበብ) የሚያስተምር የአቴናው ኤጲስ ቆጶስና ለቅዱሳን ሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቁ ድዮናስዮስ ነው::(ሃይማኖተ አበው ም.10 ቁ.2)
ለዛሬ ያለውን ትምህርታችንን ከላይ ያነሣነውን መሪ ቃል መነሻ በማድረግ የምናይ ሲሆን ለዚሁም በቸርነቱ ብዛት እውቀትን ጥበብን ምስጢርንና ማስተዋልን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚገልጥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ የተሰወረውን ገልጦና የተከደነውን ከፍቶ የቅዱሳት መጻሕፍትን ጥልቅ ሃሳብ እንድንረዳ ይርዳን!


   አስቀድመን የኃይለ ቃሉን መነሻ ታሪክ ገጸ ንባብ በማስተዋል እንመልከት:- "ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም፦ ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም፦ በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት።እጅግም ዘበዘባቸው ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ።ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት። ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት፦ በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው እንዲህም አለ፦ ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬጥላ ሥር ገብተዋልና።እነርሱም፦ ወዲያ ሂድ አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል -አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት።በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።"(ዘፍ 19:1-11) ይቆየን......

 
       በዘመነ ብሉይ ተፈጽመውና በዚህ የዘልደት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው በወንጌል የተብራሩ በእጅጉ ለነፍስ እርባና ካላቸውና ለመንፈሳዊ ሕይወትም ጥቅም ሰጪ ከሆኑ ታሪኮች መካከል ይኼኛው ክፍል አንዱ ነው:: እንደ መግቢያ እስኪ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከጻፈው ገጸ ንባብ የሎጥን ጽድቅና የሰዶምን ኃጢዓት እንቃኝ፡-

የሎጥ ጽድቅ
ሎጥ ለታራን ልጆቹ የሚሆኑ "አብራም" እና ናኮር የተባሉ ሁለት አጎቶች የነበሩት የካራን ልጅ ነው:: አብርሃምን ተከትሎ ካራንን ጥሎ ከአምልኮ ባዕድ ተነጥሎ የወጣ ኋላም በሁለቱ እረኞች መኃል የተከሰተው ጸብ ወደ ርስት መከፋፈል ቢያመራ ሎጥ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል የሆነችውን ሰዶምን ሲመርጥ "አብራም" ግን በከነዓን ተቀመጠ:: "መጻተኛ ይኖር በአገር ይሰጡት ከድንበር" እንዲሉ አላስጠጉትም፡፡ ያም ቢሆን የሰዶም ሰዎች ኃጢአትን ሲያበዙ ሎጥ ከግብራቸው አልተባበራቸውምና በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር ይለናል፡፡ እንዲያውም ውድቀቱን እያየ በዓመጻ ሥራቸው አልተባበረም ነበር:: ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ "ኀጥኣን ሲበዙ ኃጢአት ትበዛለች፤ ጻድቃን ግን ውደቀታቸውን ያያሉ።" (ምሳ. 29:16) ይልቁንም ጽናቱን ለሁላችን አብነት እያደረገ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የጻድቁን ኑሮ በሚከተለው መልኩ አስተምሮናል፡- "ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና...." (2ኛ.ጴጥ.2:7-8) በቤቱም መላእክትን አስጠለለ፡፡ የቤቱም ደጃፍ በቅዱሳኑ ተጎብኝታለችና ኃጢአተኞች ሊቀርቧትና ሊዳፈሯት እንዳይቻላቸው አይናቸው ተያዘ። ኋላም በአገሪቱ ኃጢአት እርሱም ቤተሰቡም እንዳይጠፉ በቅዱሳን መላእክቱ እርዳታ ወደ ምስጋረ እግር "ሴጎር" ተሻገረ።


የሰዶማውያን ኃጢአት
"የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።" ይለናል የዘፍጥረት መጽሐፍ (ም.13 ቁ.13)፡፡ ተመልከቱ ብጹእ ሰው በክፉዎች ምክር ያልሄደና በኃጢአተኞች መንገድ ያልተቀመጠ ነው:: ክፉ ማለት ነፍሱን ያጎደለ ኃጢአተኛም አምላኩን የበደለ ነውና (መዝ.1:1):: ጻድቅ ሎጥ ግን በመካከላቸው ሲኖር በክፋትና በኃጢአት ሥራቸው ያልተባበረ ብጹእና ጻድቅ ሰው ነበር :: ሰዶማዊነት :- ከእንሰሳዊነት በባሰ አጋንንታዊ ተግባርና እና አምላክን በእጅጉ ያሳዘነ በነዋሪዎቹ ስም የተጠራ ሕሱም ተግባርና የከበደ ኃጢአት የከፋ በደልም ነው (ዘፍ.18:20)::
      ለመሆኑ ዓይነ ሥጋቸው ከማየት የፈዘዘውና ዓይነ ሕሊናቸው ከማስተዋል የደንነዘዘው ሰዶማውያን ወደዚህ ክፉ ሥራቸውና ሕግ መተላለፋቸው እንዲያመሩ ያስገደዳቸው ኃጢአት ምንነበር? ነቢዩ ሕዝቅኤል ምክንያተ ሰዶማዊነትን እንዲህ እያለ ያስቀምጥልናል፡- "የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡- ትዕቢት፣ እንጀራን መጥገብ፣ መዝለልና ሥራ መፍታት" (ሕዝ. 16:49):: እስኪ እነዚህን ነጥቦች ለዓይን መታወርና ደጃፉን ለማጣት እንዴት እንደሚያደርሱ እንመልከት፡፡


1·ትዕቢት( Pride )

እንቆጳዝዮን ሊቁ ልሳነወርቅ ዮሐንስ ትዕቢት የኃጢዓት ሥር ምንጭና እናት ናት እንዳለን (“[Pride is] the root and the source and the mother of sin”) በቅዱስ መጽሐፍም ውስጥ ጥበብና እግዚአብሔርን መፍራት ያላቸው ዝምድና ያህል ትዕቢትና ኃጢዓት እንዲሁ ናቸው:: ተመልከቱ:- "የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥" = "እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው" = "እግዚአብሔርን የመፍራት መጨረሻ ጥበብ ነው" (መዝ. 110:10, ምሳ 1:7, ኢዮ 28:28, ሲራ 21:11 ) በአንጻሩ ደግሞ:- "ትዕቢተኛ ዓይንና ደፋር ልብ የኀጥኣንም እርሻ ኃጢአት ነው።" = "የኃጢአት አበጋዝዋ ትዕቢት ናት" (ምሳ. 21:4, ሲራ. 10:13)፡፡ ትሑታን ከፈጣሪያቸው መልካም ገጸ በረከትን በጎ ዕድልን ሲቀበሉ ትዕቢተኞች ግን ከአምላካችን ተቃውሞ ያገኛቸዋል:: በዚህም የከበሩ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ እያሉ ተባብረውበታል፡- "እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።"~~~>"ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።"(1ኛ.ጴጥ. 5:5,ያዕ. 4:6)::
እመ ትሕትና ብላቴዋ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዓለሙን ሁሉ መድኅን በማህጸንዋ ተሸክማ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል "ወላዲቱ ለወልደ እግዚአብሔር" እያለ ሲያመሰግናት ቅድስት ኤልሳቤጥም "እሙ ለእግዚእየ" ብላ እያጸናችላት ራስዋን ግን እናቱ ሳይሆን አመቱ (ሴት ባርያው) እያለች ገለጸች፡፡ ተመልከቱ ለኛም የሚሻገረውን መልእክት በጸሎትዋ እንዲህ ብላ አስተማረችን "ወገብረ ኃይለ በመዝራእቱ ወዘረዎሙ ለእለ የአብዩ ህሊና ልቦሙ.....በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤" ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም (ሉቃ.1:51):: እንግዲህ ልብ እናድርግ በጉልበቱና በሀብቱ በእውቀቱና በውበቱ የሚመካ ትዕቢተኛን ሰው ክፋትን ያደርጋልና አምላኩ በእጅጉ ያዝንበታል "አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።"(ያዕ. 4:16)

1·1 ትዕቢትና መንፈሳዊ ዓይን

ፍጡር ኃጢአት ሲሠራ ምድራዊ ጊዜአዊ እና ሥጋዊ ዓይኑ ይከፈታል፡፡ በዚያው መጠን ሰማያዊ መንፈሳዊ ዘለዓለማዊ ዓይኑ እስኪታወር ይደክማል:: በተለይ ደግሞ ለዚህ እንደምሳሌ ፈጣሪውን አመስግኖ ክብሩን ለመውረስ የተፈጠረው ሳጥናኤል በትዕቢት ወድቆ ብርሃን የሆነ እውቀት ሲገለጥ ጨለማ በሆነ ድንቁርና የኖረው ተዋርዶ ሲጣልም "እግዚአብሔር ጎየ....እግዚአብሔር ሸሸ" ያለው ስለታወረ ነው:: "አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ: ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።" (ኢሳ 14: 12-15)
ውሳጣዊው መንፈሳዊ ዓይን ረቂቁን እንጂ ደረቁን ለማጤን የተፈጠረ አይደለም:: ይህችን ዓይነ ሕሊን ብርሃነ ልቡና ትሕትናን ቀለብ አድርገው ራሳቸውን ገዝተው የተጠቀሙባት ይከብሩባታል፤ ትዕቢተኞች ግን ይዋረዱባታል "የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች ..... አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።" (ኢሳ.5:15, መዝ.18:27)

1·2 አጭር ምክር:-

እንግዲህ ሁሉም ሰው የትዕቢትን ጨለማ የዓይኑን ቅርፊት የኃጢአት ሰንኮፍ ጳውሎስ እንደተባለ ሳውል በንሰሐ ካላነሣ ወደ ጥልቁ ጨለማ ወደ ዘለዓለም ድንቁርና ይጋዛል:: "ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድኻም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥...እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።" (ራእ. 3:17) ስለዚህ ንሰሐ አጥርቶ ለማየት የሚያግዝ ኩል ለሁሉም የተሰጠ ፍኖተ ጽድቅ በተአምኖ ኃጣውዕ የሚኖሩበት የትሕትና ሥራ ነውና ሁላችን ነገን ለመክበር ዛሬ ሁሉን ከፍ ከሚያደርገው ጌታችን በታች ራሳችንን በትሕትና እናዋርድ፡፡ ሊቀ ሐዋርያት እንዲህ እንዳለ "እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤"1ኛ.ጴጥ. 5:6

2· ጥጋብ (Fullness of food)

ይህ ሁለተኛው የሰዶም ኃጢአት ነው:: ጥጋብ ማለት ይላል ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ "ሰው ቁሳዊ ምልአትን ሲሻ በሚያልፈው ላይ ትውክልቱን ሲያኖር ለመንፈሳዊ እሴቶቹ ትኩረት ሲነፍግ የሚታይ መገለጫ ነው:: "(That is when man seeks material fullness, and leans upon the temporaries; disregarding all spiritual values.) ሐዋርያው ለሁላችን በሚጠቅመን ምክሩ ይህን ብሎናል፡- "ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥አ ንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።" (1ጢሞ. 6:6-8) ደጉ ሰው አባታችን ያዕቆብ የምጠግበውን ከማለት ይልቅ "የምበላውን እንጀራ" እያለ የለመነው (ዘፍ.28:20)  እኛም ጌታችን ባስተማረን ምስጋናና ልመና የምንጠይቀው እንዲህ እያልን ነው:-"ሀበነ ዮም ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ" (ማቴ 6:11)፡፡ ምክንያቱም መብል በሥጋ ለመኖር እጅጉን ጠቃሚ የኑሮ መሠረትና የጉልበት ጽናት ነው፡፡  "እክል ያጸንዕ ኃይለ ሰብዕ .... እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።"~~"የኑሮህ መጀመርያ የምትበላው እህል ...ነው" (መዝ.103:15, ሲራ 29:21) እንዲል:: ነገር ግን ሁሉ በልክ ሊሆን ይገባልና ለቁመተ ሥጋ ጸንቶ ለማገልገል ኃይል የሚሆነውን ካገኙ የቀረውን ያን አጥቶ ለተቸገረው መመጽወት ይገባል:: "አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥" ይላልና (2ኛ.ጢሞ. 4:5)
ነገር ሁሉ ከልክ ያለፈ ቢሆን ግን ከአምላክ ይለያል.... ጥጋብም ሰውን ከፈጣሪው ቤት ያባርረዋል፤ ለሆዱ ያሳድረዋል:: እስራኤል ዘሥጋን ያገኛቸው ይህ ነው፡፡ "ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ ስለዚህ ረሱኝ።"(ሆሴ.13:6) ከዚህም ጋር አካተን አንድ ነገር እንመልከት፡፡ ሰው ሲጠግብ እንኳን ለፈጣሪው ፈቃድ መገዛት ቀርቶ ራሱን መግዛት የማይቻለውና ስሜቱ የሚገዛው ለምኞቱ ተላልፎ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ "በሉ እጅግም ጠገቡ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።" (መዝ.78:29) እንግዲህ ሰው ሲጠግብ የማይረባውን ለማግኘት የሚምስ መልካሙን ወደማየት የማይመለስ ይሆናል፡፡ ይህንንም መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን  እንዲህ ሲል በቁሙ ያሳየናል "የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች ......"(ምሳ. 27:7) ፡፡ ጥጋብን የሚከተል ቢኖር ነገን የሚያኖር እግዚአብሔር መሆኑን የዘነጋ የተቸገረ ወገኑን የማያስታውስና ደስታውን በጊዜአዊ ፈቃዱ ላይ የገነባ በመሆኑ አምላኩ ፈጽሞ የሚያዝንበት እስኪሞትም መተላለፉ የሚያዝበት ከንቱ ሰው ነው:: "እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፡፡ እናንተ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል። ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ። እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር"  (ኢሳ. 22:13-14) 

2·1 ጥጋብና መንፈሳዊ ዓይን

አምላኩን በትዕቢት ክዶ በወረደው ዲያቢሎስ ፈንታ የተፈጠረው የሰው ልጅ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ "ረቂቅ የምትሆን ከነፋስና ከእሳት የተፈጠርክ አንተ ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይክ ጊዜና አንተ በተመካህ ጊዜ ከሰራዊቶችህ ጋር እግዚአብሔርን ክደሃልና እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን አይቶ ሳያጓድል ስሙን እንዲያመሰግን አዳምን ፈጠረ" (3መቃ.2:10)፡፡  ይሁንና ግን ሰው ለሆዱ ማደሩ በጨመረ ቁጥር ሕሊናውን እየሸጠ ወደ መክሰር ተሻገረ:: በልማድ "ሆድ ሲሞላ ጭንቅላት ባዶ ይሆናል" እንደሚባለው:: አዳምና ሴቲቱ በምክረ ከይሲ ተረትተው የተፈጠሩበትን ክብር ገፍተው እጸበለስን በልተው ሥጋዊ ዓይናቸው በተከፈተበ ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናቸው ታወረ:: "እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።" "የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ" (ዘፍ 3:4-5, ዘፍ.3:7)
ተመልከቱ! ጠላት ሰውን ሲጥል በምግብ ይፈትነዋል .....ቀድሞ አዳምና ሔዋን በመብል የጣለው ፈታኝ ኋላ ለወንድሞቹ ስንቅ ለማድረስ የደከመ ዮሴፍን ሲርበው ተጠግቶ ብላባቸው አለው፡፡ ብላቴናው ግን አልተበገረለትም፡፡ ያም አልበቃው ቢል ወደ ጌታችንም ቀርቦ ደንጊያውን ዳቦ ቢያደርግ እንደሚበሉ አወያየው፡፡ ክርስቶስ ግን ተርቦ ሳይሳሳ ተፈትኖ ድል ሳይነሳ አሳፈረው:: ታዲያ ለሆዱ ያደረ ምን ተጠቀመ? ምንስ አተረፈ? የሆዱን ፈቃድ ገፍቶ የተወስ ምን ቀረበት ምንስ አጎደለ? "መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።"(1ኛ.ቆሮ. 8:8)

2·2 አጭር ምክር:-

በልክ የሚበላ የሥጋውን ምኞት ለመከልከል አቅም የማያጣ ለፈጣሪውም ፈቃድ ለማደር ጉልበት የማይከዳው ሰው ምንኛ ብርቱ ሰው ነው:: "እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።" ይለናል (መክ.5:12)፡፡ እስኪ ሁላችን ከጠቢቡ ንጉሥ ጋር ሆነን በጋራ ይህንን እንለምን ፡- "ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ: ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፡፡ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።" (ምሳ. 30:7-9)

3· ግድ-የለሽነት (መዝለልና ሥራን መፍታት) (Unconcern)

መዝለልና ሥራን መፍታት በአንድነት ከትጋት ለመራቅ ለግድ-የለሽነት መገለጫዎች ናቸውና በሦስተኛ ነጥብነት አካተን እንመለከታቸዋለን:: ይህም በንሰሐና መስቀሉን በመሸከም ከመኖር ይልቅ ወደ ጥፋት የሚወስደውን ሰፊ መንገድና የተቀማጠለውን ኑሮ የሚመርጡ ሰዎች መገለጫ ነው:: (They picking out the wide way and the spoiled life, instead that of repentance and of bearing the cross.) እንደነዚህ ያሉቱ ግድ የለሾች በመጽሐፍ እንዲህ ተቀምጠዋል "ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም።"1ኛ. ጢሞ. 5:13) ሰው ጥንቱን ከሥራ ጋር ለሥራ ነው የተፈጠረው፡፡ "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው" እንዲል (ዘፍ.2:15)፡፡ ተግባር ከመፍታቱ የተነሣ የጠላት ቤተ ሙከራ የሆነ አእምሮ አዳዲስ ኃጢአቶችን ሲያቅድና ሲያመርት ይኖራል:: ለዚህም ነው ሰብአ ሰዶም በስማቸው የተጠራ ሰዶማዊነትን ያመረቱት። በሥጋ የደለቡ በነፍስ የተራቡ ሆነው ከሕገ ነፍስ ሕገ ሥጋ ከሕገ መላእክት ሕግ እንስሳ በልጦባቸው በገዛ በደላቸው ጠፉ። ተመልከቱ "ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው።" ~~> "ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣለች፥ የታካችም ነፍስ ትራባለች።" (ምሳ. 12:27,ምሳ.19:15)

3·1 ግድ-የለሽነትና መንፈሳዊ ዓይን

ግድየለሽ የምንለው ሰው ሥራ ፈት፣ ፍሬቢስ፣ ትጋት አልባ ሆኖ በቅርብ ያለውን ምድራዊ ነገር ብቻ በሥጋ ዓይኑ የሚያይ በጥልቅ ያለውን ሰማያዊ ሀብት በመንፈሳዊ ዓይን የማይረዳውን "ዕውር" ነው! ስለዚህም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስቀምጧል፡- "ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።"(1ጴጥ. 1-5-9)

3.2. አጭር ምክር:-
የአልዓዛር ልጅ ሲራክ የተባለ ኢያሱ እንዲህ እያለ እስከ ዐረፍተ ዘመናችን እስከ ጊዜ ሞታችን እንድንተጋ ግድ-የለሽነትን እንድናርቅ ይመክረናል "በጊዜው ጊዜ ዋጋችሁን ይሰጣችሁ ዘንድ ይህ ዓለም የሚያልፍበት ጊዜ ሳይደርስ ሥራችሁን ሥሩ" ሲራ 51:30፡፡

ማጠቃለያ
ብዙዎች በትዕቢት በጥጋብና በግዴለችነት የታወሩ በደለኞች ደጃፎቿን ለማግኘት የደከሙባት ዓይነ ሕሊናቸው ከማስተዋል የደነዘዘ ዓይነ ሥጋቸው ከማየት የፈዘዘ ኃጥአን የከበቧት ይህች ደጅ "ደጀ ሰማይ" ቤተ ክርስቲያንና "ደጀ ሰላም" ድንግል ማርያም ናት:: ይህን ለማለት ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው በአመክንዮ (logic) አቀራርበን የምንጽፍ አልያም በሰው ጥበብ አመሳስለን የምንናገር አይደለም:: ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው መንፈሳውያን መጻሕፍትን የጻፉ ኄራን አበውን አብነት እናደርጋለን እንጂ "መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።"(1ኛ. ቆሮ. 2:13)
በምሳሌነቱም በምስጢር የሚስማማውን የሎጥን ቤት ደጃፍ ብቻ አብነት እንወስዳለን እንጂ ስለ ሰዶም የተነገረ ሁሉ ለዚህ ፍቺ ሆኖ እንደማይገባ ልብ ይሏል:: እንደማሳያም ቅዱስ መጽሐፍ ሰዶምን የቀራንዮ ምሳሌ ያደርጋታል "በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።" ራእ.11:8 ይህም የተመቸውን የአይሁድ አመጻ ሲያነጻጽር ... በሌላም ሥፍራ የሰዶም እሳትና ዲን "እሳት በፊቱ ይነዳል" ለተባለ ንጉሥ የምጽአት ፍርዱ ምሳሌ ሆኖም ተቀምጧል "እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ።የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።" (ሉቃ. 17:28)
ታዲያ የሰዶም እሳት ለፍርድ ቀን እሳት ምሳሌ ከሆነ እስከ ዓለም ማለፍ የቅዱሳን ምዕራፍ የጽድቅ ደጃፍ ቤተ ክርስቲያንንና ድንግል ማርያምን እኛም ደጅ ብለን በዚህ ክፍለ ትምህርት አነሣን።


ቤተ ክርስቲያን (ደጀ ሰማይ)

እንደ ሎጥ ያለ ጻድቅ የሚጠለልባትና ለቤቱ ንጽህና ራሱን አሳልፎ የሚሰጥባት እንደ መላእክትም ያሉ ቅዱሳን የሚጠብቋት ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚመገቡባት መሥዋዕቱን የሚያሳርጉባት መነሻዋ ዓለመ መላእክት ቢሆን ለሰው ፍጥረት መጠለያነት በምድርም የጸናች ሥሯ በምድር ላይ ቅርንጫፎቿ በሰማይ የተባለች ኆኅተ ሰማይ የሰማይ ደጅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ከቤራቤህ ወደ ካራን ሲሄድ ደንጊያ ተንተርሶ በምድር የተተከለ መሰላል ወደ ሰማይ ደርሶ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢመለከት ቤቴል ብሎ ስለጠራው ስፍራ እንዲህ አለ፡- "ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው።"(ዘፍ.28:17)
እንግዲህ ልብ አድርጉ ወዴ ሎጥ ቤት መላእክትና ጻድቅ ሎጥ እንደገቡ  በቤተክርስቲያንም ጻድቃኑ ቅዱሳኑ አይታጡምና ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት "ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።" እንዳለ (መዝ. 117:20) በዚያውም ላይ መላእክት ሎጥን ወደ ቤት አግብተው በሩን እንደዘጉ ምዕመናንም ለነፍስ ወደብ መከራውን መሻገርያ በምትሆን ቤታቸው በቅዱሳን መላእክት ተጠብቀው ይኖራሉና ልዑለ ቃል ነቢይ ኢሳይያስ እንዲህ እንዳለ "ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።" (ኢሳ. 26:20)
ምንም ክፉዎች ቢከቧት እና ይህችን ደጅ ቢታገሏትም በመላእክት አዋጅ ጻድቃን እስኪድኑ የሰዶም ደይን ምሳሌው በሆነ በገሃነም እሳት ኃጥአን እስኪቀጡ ቤተ ክርስቲያን መጠለያችን ናት:: ሊቁ መጋቤ ምስጢር ወርቅነህ ውቤ "ቤተ ክርስቲያን የሥጋ አጥር ናት፤ ከውስጥ ውሻ ከውጪ ጅብ የሚዘነጥላት" እንዳሉት፡ ከውስጥ እንደ ብእሲተ ሎጥ ያሉ ሐሳባቸውን ያላጠሩ (ጨው ለመበደር ወደ መንደር ስትሄድ የእንግዶቹን መግባት ለሰዶማውያን ነግራለችና) የቤተ ክርስቲያንን ፈተና የሚያከብዱ በኋላ ሐውልተ ጼው ሆነው የቀሩ፤ ከውጪ እንደ ሰብአ ሰዶም ቅዱሳኑን ተጋፍተው ደጁን ሊያጠፉ የሚዳክሩትን ኋላ ከሰማይ በዘነበ  እሳትና ዲን  የጠፉትን ታግሣ የምትቆይ ይልቁንም ለክርስቶስ ሁሉን እንዲህ ብላ የምታቀርብ  "አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።" መኃ. 7:14 "ምንም በየዘመናቱ የሚነሳው መከራ ቢያልፍም ቤተ ክርስቲያን ግን አታርፍም" እንዲሉ  ክብርና ጌጧ የቅዱሳን መገፋት የሆነ ሊቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ "ሰማዕትኒ ያሰረግዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ" ብሎ የመሰከረላት ቤት ናት::
በተለይ ዛሬ በዘመናችን ይህችን ደጅ ሲፈልጉ የሚደክሙ ለማፍረስ የሚሰበሰቡ ነገር ግን የወደቁ መሳርያ የሚተክሉ ነገር ግን የማይከናወንላቸው ብዙዎች ናቸው። አጽንቶ የሠራት አስውቦም የሸለማት ፈጣሪዋ ይጠብቃታልና ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ይህን እንዲህ እያለ ያስረዳናል፡-  "እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።....እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ።... በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር" (ኢሳ 54:11-17)
እንግዲህ ተመልከቱ! እንኳን ሥጋን ለብሰው የሚያሴሩ ደካሞች ይቅርና በከንቱ ይደክማሉ እንጂ ይህች ደጅ ኋላም ቢሆን የገሃነም ደጆች የማይችሏት ይህች ደጀ ሰማይ ደጀ ቤተ ክርስቲያን ናትክርስቲያን። "እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። (ማቴ. 16:18)

እመቤታችን (ደጀ ሰላም)

ሁለተኛዋ ደጅ የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገባባት ማደርያው ደጀ ሰላም ድንግል ማርያም ናት:: ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል እንዳሳወቀን፡- "ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር።እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።"(ሕዝ 44:1-3) ይህንንም ሊቁ ማር ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "ኆኅትሰ ድንግል ይእቲ"....ብሎ መድኃኒታችንን የወለደች ድንግል ቅድመ ወሊድ ቢሉ ድኅረ ወሊድ ጊዜ ወሊድም በድንግልና ኖራለችና ደጀ ሰላም ያለው እርሷን ነው ይለናል:: እግዚአብሔር በጸጋ የተገለጸባቸው ብዙ ማደርያ ድንኳኖች ከያዕቆብ ቤት ተገኝተዋል፡፡ ይሁንና ግን  አምባ መጠጊያችን የምትሆነን ድንግልን ለኩነት ማደርያነት መርጧታልና ደጆችዋን ከሁሉ ይልቅ ይወዳቸዋል፡- "ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል።"(መዝ. 86:2)
ዛሬ ግን ትውልዱ የራሱን ጽድቅ ሲመሰክር ለድንግሊቱ ክብር አንደበቱ ሲታሰር ይታያል:: ይህን የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት አምላክ ሳለ አማላጅ የሚል "የሚረግም" ይህችን የሰላም ደጅ ፈጣሪን የወለደች የዓለም እናት ትውልድ ሁሉ ያመሰግነኛል ብላ ሳለች የማይባርካትን ትውልድ ከነቅጣቱ በፈታኂው ንጉሥ መፍቀሬ ጥበብ እንዲህ ተዳኝቶ ተቀምጧል:: "አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ። ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ።"~~>"በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል።" (ምሳ.30:11-13,17)
ይልቁንም በደጃፉ የተጉ ግን ዓይናቸው አንሥተው አምላካቸውን ከእናቱ ጋር ያያሉ "ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥" (ማቴ. 2:11) ከገሀነም እሳትና ደይን አምልጠው ሕይወትንና ሞገስን አግኝተው በብሔረ ተድላ ለዘለዓለም ይኖራሉ "ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው፤ ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።" (ምሳ 8:34)

እንደ መደምደሚያም ቀጣዩን የንሰሐ ጥሪ  ከኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ በማውሳት ትምህርታችንን እንቋጫለን፡-
       “ወናጽምዖ ለዘይጼውአነ እንዘ ስፉህ እዴሁ ኀቤነ እምቅድመ  ኅልፈተ ዕለት ወናፍጥን ወንግድፍ ርእሰነ ቅድሜሁ እንዘ ንብል ናሁ አበስነ በቅድሜከ እግዚኦ ነጽር ኃቤነ ወኢትግድፈነ ዘልሕኩትከ እስመ ግብረ እደዊከ ንህነ እስመ አልቦ በውስተ ሞት ዘይዜከረከ ወበሲኦልኒ መኑ ዘየአምነከ ንትባደር ለንሰሃ.... ዘመናችን ሳይፈጸም እጁን ወደኛ ዘርግቶ የሚጠራንን እንስማው፡፡ ፈጥነን በፊቱ ራሳችንን እናዋርድ፡፡ አቤቱ እነሆ አንተን በድለናል፤ እኛን በዓይነ ምሕረት ተመልከት፤ ፍጥረቶችህን አትጣል፤ የእጅህ ፍጥረቶች ነንና ከሞት በኋላ የሚያስብህ በመቃብርስ ተስፋ የሚያደርግህ ማነው እያልን ፈጥነን ንሰሐ እንግባ” (ሃይ.አበ. ም.37:11)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

3 comments:

  1. ለዚህ ጊዚ አስፈላጊ ነው እግዚአብሐር ይባርክህ

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount