Thursday, July 2, 2015

የንስሐ አባቴ ኃጢአቴን ቀለል አድርገው ስለሚነግሩኝ ንስሐ ለመግባት እቸገራለሁ፡፡ ምን ላድርግ?



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችሁ? ዛሬም ከአንባብያን ከተላኩልኝ ጥያቄዎች መካከል አንዱን መርጬ በአበው ካህናት የተሰጠውን ምላሽ ይዤላችሁ ቀርቢያለሁ፡፡ ዛሬም መልሱን የሚሰጡን በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል እንዲሁም መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ ለአባታችን ተናጋሪ አንደበት ለእኛም ሰሚ እዝነ ልቡና ያድለን፡፡ አሜን!!!
ጥያቄ፡-  “ውድ የመቅረዞች አዘጋጆች! እንዴት አላችሁ? የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባቢ ነኝ፡፡ ከምእመናን የምታስተናግዱት ጥያቄ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እኔም ከንስሐ አባት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለካህናት እንዲህ አደረግኩ ብዬ ስናገር፡- ‘ምንም ችግር የለውም፡፡ ይህቺ’ማ ምን አላት?’ እያሉ በተደጋጋሚ ስለሚነግሩኝ ሌላውን ለመናገር ቸገረኝ፡፡ ምን ላድርግ?”
አንዳርግ ነኝ ከቺካጎ

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡-  ይህ በካህናት አባቶቻችን ዘንድ ይከሰታል፡፡ “ይኼ’ማ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ይኼ’ማ ቀላል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ኃጢአት ነው እንዴ?” በማለት ኃጢአታችንን ቀለል አድርገው ሲነግሩን ከዚያ በኋላ ሌላውን ለመናገር ድፍረት፣ ብርታት አይኖረንም፡፡ አንዳንድ ጊዜም ኃጢአትን የበለጠ የመደፋፈር ነገር ሊፈጥርብን ይችላል፡፡
ጠያቂው ኃጢአትን ለመናዘዝ ወደ ካህናት መሔዳቸው በራሱ በጣም የሚበረታታና መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፡- “ራስህን ለካህን አሳይ” ብሎ ባዘዘው አምላካዊ ቃል መሠረት /ማቴ.8፡4/ ኃጢአትን ለመናዘዝ፤ “ካህኑ እግዚአብሔር ይፍታሕ ሲለኝ ምሕረት አገኛለሁ፤ በንስሐ የሕይወት ለውጥ ንጽህና ሥርየተ ኃጢአትን አገኛለሁ” ብሎ ማመንና ይህን ለመተግበር መዘጋጀታቸው በራሱ በጣም የሚበረታታና የመንፈሳዊ ሕይወት መገለጫ ነው፡፡
እንግዲህ ወደ ጥያቄው ስንመለስ “ካህናቱ እንዲህ የሚሉን ከምን አንጻር ነው?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያት ብዙ ሊኾን ይችላል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-
1.  እንዳንርቅ፡፡ ለንስሐ የመጡት ምእመናን ደንግጠው ድጋሜ ለመምጣት እንዳይፈሩ፣ በሠሩት ነገር ወዲያውኑ ቅስፈት መዓት የሚወርድባቸው መስሎ እንዳይታያቸው፣ የእግዚአብሔርን ቸርነት ርኅራኄ ረስተው ከባድ ቁጣ የሚያመጣባቸው እንዳይመስላቸውና የንስሐ ልጆቻቸው እንዳይርቁ ከሚል እይታ አንዳንድ ካህናት ነገሮችን የማቅለል ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡
2.  ካለመገንዘብ፡፡ ይኸውም መጻሕፍትን ጠንቅቀው ካለማወቅ፣ በንባብም ኾነ በተለያየ ነገር ብንዳብርም ደግሞ ኃጢአትን ማቅለል ሰዎች ኃጢአትን ይበልጥ እንዲደፋፈሩት የሚያደርግ መኾኑን፣ ሌላውን ኃጢአት ላለመናገር የሚያደፋፍር መኾኑን፣ የተነሳሕያንን የኑሮ ኹኔታና የተለያዩ ገጽታዎችን፣ መክረን ገሥጸን ወደ ቀጣዩ ሕይወት እንዴት ማሸጋገር እንዳለብን ካለመገንዘብ የተነሣ ኃጢአታችንን አቅልለው የሚያዩ ካህናት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
3.  ከቸልተኝነት፡፡ ይህም ከዕውቀት ማነስ፣ በክህነት አገልግሎት በቂ ልምድ ያለ ማግኘት ወይም በሌላ ተያያዥ ምክንያት የተነሣ ሊኾን ይችላል፡፡ በአንዳንድ አባቶች ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት፣ በሰዓታቱ በማኅሌቱ በቅዳሴውና በሌላው አገልግሎት ብርቱ ሲኾኑ ልጆቻቸውን ቸል የማለት ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህም ተያይዞ ግድየለሽነት፤ ነገሮችን እንዲሁ በጣም የማቅለል፣ መክሮና ገሥጾ ወደ ቀና መንገድ ለመመለስ ቸል ከማለት የተነሣ ቸል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ምንደኛ ከመኾንም የሚመጣውን ጉዳት ካለማስተዋል (ከቸልተኝነት) ነገሮችን በማቅለል ወደ መፍትሔ እንዳይሔዱ የሚያደርጉ ይኖራሉ፡፡
“ታዲያ ምን ይሻላል?” ወደሚለው ስንመጣ፡-
1.  ከንስሐ ላለመራቅ መወሰን ያስፈልጋል፡፡ በንስሐ ሒደት ውስጥ የሚገጥሙን ነገሮች ኹሉ በጎና የበረከት ገጽታ እንዳላቸው ኹሉ ፈተናም አላቸው፡፡ አንድ ሰው በመንፈሳዊ ኑሮ ውስጥ ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፣ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት ሲጓዝ በየማዕረጉ ፈተናው እየጨመረ ነው የሚሔደው፡፡ ክርስትና ግን “እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ኹን፤ የሕይወትንም አክሊል አቀዳጃሃለሁ” ተብሎ እንደተነገረ /ራእ.2፡10/ እስከ ሞት ድረስ እየጸኑ እየታገሉ ፈተናን ድል እየነሱ የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ እስከ ሞት ድረስ ፈተናም አይቋረጥም፡፡ በከተማም ብንኖር፣ በዓት አጽንተን በገዳምም ብንኖር ፈተናው አለ፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎችና በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች የሚመዘኑበት መንገድ እንደሚለያይ ኹሉ በመንፈሳዊ ሕይወትም፡- “ማደግህ በነገር ኹሉ ይገለጥ ዘንድ ይህንን ዘወትር አስብ” እንዲል ደረጃውን የሚመጥን ፈተና አለ፤ መመዘኛ አለ፡፡ ከሚመጡ ፈተናዎች አንዱ በራሱ በንስሐ የሚመጣ ፈተና ሊኾን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ያ ወደኋላ እንድንል፣ እንድንፈራ፣ ጠንከር ያለና መናዘዝ የሚገባንን ኃጢአት ቸል ብለን የኃጢአት ልምምድን እንድናዳብር የሚያደርጉ ፈተናዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ “እርሳቸው ካሉኝማ …” በሚል አጉል ሐሳብ ሳናስብ የንስሐ ጉዳይ የእግዚአብሔር ሕግ ነውና ምንጊዜም ከንስሐ ላለመራቅ መወሰን ይገባናል፡፡ ስለ መፍትሔ እያሰቡ ወደ ቀጣይ ለመሸጋገር እንጂ “ይኼ ኾኗልና ምንም ማድረግ አልችልም” ብሎ ጉዳዩን በቤት ማቈየት አያስፈልግም፡፡
2.  የኃጢአትን ጉዳት በማስተዋል ከኃጢአት መራቅ፡፡ “እርሳቸው ስላቀለሉት ምንም ችግር የለውም፡፡ አይዞህ/ አይዞሽ ብለዉኛልና ደግሜ ባደርገውም ችግር የለውም፡፡ ይኼን ይኼን ኃጢአት ሠርቼ በሚቀጥለው ጊዜ ሔጄ ንስሐ እገባለሁ” ብሎ ማለት እንደነ ኤልዛቤል ለንስሐ ሳይበቁ መጥፋት አለ፡፡ እንደነ ፈርዖን የእግዚአብሔር ቁጣ ሊያመጣብን ይችላል፡፡ እጠገናለሁ ብሎ መሰበር እንደማያመች ኹሉ ንስሐ እገባበታለሁ ብሎ ኃጢአት መሥራትም ራስን ማታለል ነው፡፡ አባቴ ሐኪም ነውና ከሕንፃ ከዳገት ላይ ልውደቅ አይባልም፤ ለመውደቅ ሲያስቡ መሞትም አለና፡፡ በመኾኑም የንስሐ አባቶቻችን ኃጢአታችንን ስላቀለሉብን የበለጠ ወደ ኃጢአት ከሔድን ድክመቱ የእኛ ነው፡፡ ለኃጢአታችን ደረጃ እየሰጠነው ከሔድን በመንፈሳዊ ሕይወታችን መዛልን ከዚያም ሞትን ነው የሚያስከትልብን፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ሲበረታ በጸጋ ላይ ጸጋ እንደሚጨመርልን ኹሉ ኃጢአት በሠራን ቁጥርም በአንዱ ኃጢአት ላይ ተጨማሪ ኃጢአትን እየሠራን ነው የምንሔደው፡፡ አንድ ትንሽ ቁስለ ሥጋ በጊዜው ካልታከሙት እስከ ካንሰርና ሞት እንደሚያደርስ ኹሉ በእኛ እይታ ትንሽ ነው የተባለው ኃጢአትም በጊዜው አስፈላጊውን መፍትሔ ካልወሰድንበት እስከ ሞት ድረስ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ሥጋ ምግብ፣ ውኃ ካጣ ይዝላል፡፡ ነፍስም እንደዚሁ በየጊዜው በንስሐ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ምግብ ካልተመገበች ትዝላለች፤ ውድቀትም ይመጣል፡፡ በመኾኑም ኹልጊዜ ይህንን ጉዳት በማሰብ፣ የኃጢአት ፍጻሜው ሞት መኾኑን በማስተዋል ልንኖር ይገባናል፡፡ ከላይ እንደተናገርን ለኃጢአታችን ደረጃ ልንሰጠው አይገባንም፡፡ አንድ ልጅ ወቅቱን ጠብቆ የሚወለደው መጀመሪያ ፅንስ ኾኖ ነው የሚፈጠረው፡፡ ኃጢአትም እንዲህ በልቡናችን ነው የምንፀንሰው፡፡ ገና እዚህ ደረጃ ማለትም ኀልዮ ላይ እያለ መፍትሔ ካልወሰድንበት ነገ ከነገ ወዲያ በቃልም በገቢርም እንወልዷለን፡፡ ኃጢአታችንን ገና በኀልዮ እያለ ካቀለልነው ነገ ሞት እንደሚወልድብን በማሰብ ልንለማለስ ይገባናል፡፡
3.  ካህኑ ተገቢውን ቀኖና እንዲሰጡን በፍቅር ማናገር፡፡ ካህናት አባቶቻችንን “እንዲህ አድርጉ” ብሎ ማዘዝ ቢከብድም እንደ ልጅነታችን ግን “እንዲህ አድርጉልኝ” ማለት እንችላለን፡፡ ድካማችንን እንዲረዱልን ማድረግ እንችላለን፡፡ “አለመገሠጼ፣ አለመደንገጤ የበለጠ ላይጠቅመኝ ይችላልና ቢገሥጹኝ ይሻላል፡፡ አታድርጊ ይበሉኝ፡፡ አታድርግ ይበሉኝ፡፡ ቃለ እግዚአብሔር እንደሚናገረው አድርገው ይገሥጹኝ” ማለት በጣም የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ የሠራነው ኃጢአት ከሌላ ሰው ጋር ተነጻጽሮ ትንሽ የሚመስል ቢኾንም ለኃጢአት ደረጃ ባለማውጣት እንዲመክሩን እንዲገሥጹን በፍቅር፣ በትሕትና መጠየቅ ይቻላል፤ ይገባልም፡፡ “ብዙዎች በገቢር ስለወደቁ የአንተኮ በኀልዮ ነው” ብለው ቢያቀሉብንም ተገቢውን ቀኖና፣ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጡን በአክብሮት መጠየቅ አለብን፡፡
4.  እነዚህን ነገሮች አድርገን ምናልባት ኃጢአት የማቀለሉን ነገር ከቀጠሉ ግን እርሳቸውን ተሰናብቶ ወደ ሌላ አባት በመሔድ መናዘዝ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እዚያም ሔደን፡- “እኚህ አባት እንዲህ አደረጉኝ” ማለት ሳይኾን “በደንብ እንድገሠጽ እፈልጋለሁ፡፡ ስሕተቴን በደንብ እያወቅኩ እንድታረም አፈልጋለሁ” በማለት የንስሐ ሕይወቱን መቀጠል ይገባል፡፡          
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

3 comments:

FeedBurner FeedCount