Sunday, May 20, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ አንደኛው ሳምንት ጥናት!!!


  (ከቻሉ በጸሎት ጀምረው በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት!)
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታችን ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ አሁን ግን እንዲህ የሚላት ምንም እንኳን ልጇ ወዳጇ ቢሆንም በአምላክነቱ ሰው የሚያዘው አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀን የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 22/፡፡ እመቤታችንም ይህንን ስለምታውቅ፡- “ልጄ ወዳጄ! አንተ ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ እንደሆንክ አውቃለሁ፤ ሁሉም በጊዜው ውብ አድርገህ የምትሠራ ኤልሻዳይ መሆንህንም አላጣውም፡፡ ልጄ ወዳጄ! አሁን የምለምንህ ወገኖቼን ከሐፍረት እንድትታደጋቸው እንጂ በአምላክነትህ ለማዘዝ አይደለም፤ ከባቴ አበሳ አምላክ መሆንህን አሳምሬ አውቃለሁና፡፡ ልጄ ሆይ! ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆነህ የመጣህ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እንደሆንክማ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ቃል አውቃለሁ፤ በሕግ በአምልኮ ለሚቀርቡህ ግን ሰማዔ ጸሎት ነህና እባክህን ራራላቸው” ብላ በአራኅርኆ ማለደችው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም፡- “እናቴ ሆይ! አንቺ ሴት የምልሽ ኃይለ አርያማዊት እንዳልሆንሽ ለመግለጽ ነው፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ተብሎ የተነገረልሽ የአዳም ልጅ መሆንሽን ለማስገንዘብ እንጂ ውኃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ” ብሎ መለሰላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ፡-  “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
“አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እኔህን ጋኖች ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው” /ቁ.6-7/። ወንጌላዊው “አይሁድ የማንጻት ልማድ የሚያደርጉባቸው የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ” የሚለን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ምክንያትን የሚፈልጉ ከሐድያን “ጠጁ አላለቀም ነበር፤ ቀርቶ የነበረውን አበርክቶ ሰጣቸው እንጂ” ብለው ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሪቱ ሕግ መሠረት ጋኖቹ ለማንጻት የሚጠቀሙባቸው ጋኖች ከሆኑ ለመጠጥ የሚሆን ወይን ጠጅ ፈጽሞ አይቀዳባቸውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ቀጥሎም “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ዶኪማስ ብሎ ጠራው። ሰው ሁሉ አስቀድሞ ሸሎውን፣ በርዳዳውን፣ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ ተራውን፣ መናኛውን ያጠጣል፡፡ አንተ ግን ሸሎውን፣ በርዳዳውን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” /ቁ.8-10/። አንዳንድ ልበ ስሑታን “ሠርገኞቹ ሁሉም ሰክረው ስለ ነበር የወይኑን ጣዕም ሊያውቁ አይችሉም፤ ስለዚህ የጠጡት የተለወጠው መልካሙን ወይን ሳይሆን መናኛውን ነው” ብለው ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ ወንጌላዊው ግን የእነዚህን ነቀፋ አስቀድሞ ስለሚያውቅ “መጀመርያ ሠርገኞቹ ሁሉ ቀመሱት” አላለንም፡፡ አስቀድሞ የቀመሰው ያልሰከረው ሊሰክርም የማይችለው አሳዳሪው ብቻ ነው፡፡ እንደውም ወንጌላዊው ትንሽ ቆየቶ፡- “ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወደ አደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ” በማለት ወይኑ በተአምራት የተለወጠ መሆኑን ነግሮናል /ምዕ.4፡46፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡  
 “ኢየሱስ በሦስት ዓመት ከሚያገርገው ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ቁ.11/። አስተውላችሁ ከሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወይን ለማድረግ ሲጸልይ ወይም ሲለምን አንመለከተውም፡፡ ይልቁንም ሠራተኞቹ ለአሳዳሪው እንዲሰጡት ነገራቸው እንጂ እስኪ ልቅመሰው እንኳን አላለም፡፡ እኛ እንደምናውቀው ተራ ወይን ሳይሆን እጅግ መልካም የሆነ ወይን እንደሰጣቸው ያውቃልና፡፡ በዚህም ጌትነቱን ገለጠ፤ ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አሳየ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት፡፡
ወንድሞቼ ሆይ! ዛሬም እግዚአብሔር እንደ ውኃ ጣዕም ያጣው ሕይወታችንን ወደ መልካም ወይንነት ፍጹም ሊለውጠው ይፈልጋል፡፡ እንግዲያስ እንደ ውኃ የቀዘቀዘው፣ የደከመው ማንነታችን ወደ እርሱ እናቅርበውና ፈቃዳችንን ተመልክቶ ወደ ወይን ይቀይርልናል፡፡ ከዚያ በኋላ በቃና እንደሆነው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የደስታ ምክንያት እንሆናለን፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግ እንደ ነነዌ ሰዎችም እንድንለወጥ እግዚአብሔር ይርዳን!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ10ኛው ሳምንት ጥናት!!


“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ”/ቁ.3/፡፡ ሰርጉ የሆነው የይሁዳ ዕጣ ከምትሆን ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ነብዩ “የአሕዛብ ገሊላ” ባላት በቃና ነው /ኢሳ.9፡1/፡፡ ጌታ በዚያ መገኘቱ የአይሁድ ምኵራብ አማናዊውን ሙሽራ እንዳልተቀበለችው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ግን በደስታ እንደተቀበለችው ያሳያል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ Commentary on the Gospel of John 2:1/፡፡ ይህም የሆነው ከተጠመቀ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ የመጀመርያው ቀን እንድርያስና ዮሐንስን የጠራበት ቀን ሲሆን ሁለተኛው ቀን ደግሞ ፊሊጶስና ናትናኤልን የጠራበት ቀን ነው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:2:1/፡፡ አንድም ጌታ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት እንደ አንድ ቀን ተቆጥሮ ነው፡፡
“እመቤታችንም ቤተ ዘመድ ናትና በዚያ ነበረች፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ” /ቁ.2/፡፡ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን እንግዲህ ሰው አይለየው” እንደ ተባለ ፈጣሪ በፍጥረት መጀመርያ በአዳምና በሔዋን የመሠረተውን የጥንቱን ሥርዓተ ጋብቻ በአዲሱ የምሕረት ኪዳን በኪዳነ መንፈስ ቅዱስም መጽናቱንና መቀደሱን ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው አንዴ ብቻ በተገኘበት በዚሁ ሠርግ አረጋግጦልናል /ቅዱስ ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ክብር ይልቅ ስለ ሰዎች መልካምነት የሚገደው ነውና በዚያ ተገኘ፡፡ የባርያዎቹን መልክ ለመያዝ እንኳን ያላፈረ ጌታ በባሮቹ ሠርግ መገኘት አላሳፈረውም፤ እንኳንስ ከዚህ ቅዱስ ጋብቻ “ከኃጢአተኞች” ጋር እንኳን ሳያፍር ለመመገብ ተቀምጧል /ፊል.2፡7፣ማቴ.9፡13 ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 20፡1/፡፡
 ከዚያ በኋላ የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ እመቤታችንም “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ቁ.3/፡፡ ይህንንም ያደረገችው ልጇ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ስለምታውቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያች ቀን በፊት ሁሉንም በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ “የአምላክ እናት ነኝ፤ እርሱም አምላክ ነው” እያለች ራሷን ከፍ ከፍ አታደርግም ነበር፡፡ በዚሁ ሰዓት ግን የሆነው ነገር አሳፋሪ ነውና ሁልንም ለሚችል ልጇ በቀስታ አናገረችው፡፡ ከራሷ ፍላጎት ይልቅ ስለ ምእመናን የምትጨነቅ እናት መሆኗንም ያመለክታል፡፡ ልመናዋም “ሊያደርግ ይችል ይሆናል” በሚልና ጥርጣሬ በተሞላበት አኳኋን ሳይሆን በእርግጠኝነት እንደሚያደርግላት በማመን ነበር፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱን ልብ ይፈልጋል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡
ሌለው የምረዳው ነገር ደግሞ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ራሱን ለሕዝቡ መግለጥ ስለ ነበረበት ይህ ተአምር የአስተርእዮ አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የተገለጠው የእርሱ አምላክነት ብቻ ሳይሆን የእናቱ እመ አምላክነትንም ጭምር ነበር፡፡
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታ ኢየሱስ ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ እዚህ ቦታ ግን ለእመቤታችን እንዲህ የሚላት በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ እንደሌለበት ለማጠየቅ ነው፤ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀትር የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና፡፡ ይህ ቢሆንም ግን “እመቤታችን ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ትላቸዋለች” /ቁ.5/፡፡ ልጇ ምን ያህል እንደሚያከብራት ደግሞም የጠየቀችውን እንደሚያደርግላት ታውቃለችና /ቅ.ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ይቆየን!!

የዮሐንስ ወንጌል የ9ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.1፡44-ፍጻሜ)!!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምለካ አሜን!!
“በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው” /ቁ.44/፡፡
 ጌታ በወርቃማው ስብከቱ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የሚፈልግ እርሱ ያገኛል” /ማቴ.7፡8/፡፡ እውነት ነው! ፊልጶስ የተዘጋጀና እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ስለ ነበረው እነ እንድርያስ ከመጥምቁ እንደተማሩት ከማንም ሳይማር ጌታ “ተከተለኝ” ስላለው ብቻ ተከትሎታል፡፡ ቀጥለን እንደምንመለከተውም ሲያነበው የነበረው ትንቢት ሲፈጸምለት ስላየ በጣምኑ ተደስቷል፡፡ በእርግጥም ጌታ ይህንኑ ልቡን አይቶ ተከተለኝ ብሎታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily on John 20፡1/፡፡
ይህ ፊልጶስ አስቀድመው ዮሐንስ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ሲል ሰምተው ከተከተሉተ ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ (የዓሣ ከተማ) ነበረ /ቁ.45/። ፊሊጶስ እንደ ናትናኤል ባይሆንም ከነብያትና ከሙሴ መጻሕፍት በትንሽ በትንሹ ያነብ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በኦሪት የጻፈለትን ነቢያትም ስለ እርሱ ትንቢት የተናገሩለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል” የሚለው፡፡ እዚህ ጋር ናትናኤልም የሕግና የነብያትን መጻሕፍት ያውቅ እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ናትናኤል ግን መልሶ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” ብሎታል /ቁ.47/፡፡ ለምን እንዲህ አለው? ስንልም ገሊላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖር ማኅበረሰብ የሚኖርባት፣ ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ብዙም ግድ የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አከባቢ እንደሆነች እንመለከታለን፡፡ ስለዚህም በሌሎቹ የአይሁድ ሕዝብ ዘንድ የተናቁ ነበሩ፡፡ አይሁድ ለኒቆዲሞስ “ነብይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” ማለታቸውም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናክራል /ዮሐ.7፡52/፡፡ ፊልጶስ ናትናኤል ከሚለው ሐሳብ ተቃራኒ የሆነ ነገር ተደርጐ ስላየና ተከራክሮ ማስረዳት ባይቻለው “የእኔ ንግግር ካላሳመነህ ጌታ ራሱ ያሳምንህ ዘንድ መጥተህ እይና ተረዳ” አለው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:1:46/።
 ናትናኤልም አሁን የፊሊጶስን ንግግር ለማረጋገጥ መጣ፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፡- ክዳት ተንኰል የሌለበት በእውነት እስራኤላዊ እነሆ አለ” /ቁ.48/፡፡ የሚገርም ነው! ናትናኤል “ከገሊላ መልካም ነገር ይወጣልን?” በማለቱ እንደሰው አስተሳሰብ መወቀስ ሲገባው ተመሰገነ፤ በውዳሴ ከንቱ ሳይሆን በአውነት በጌታ አንደበት ተወደሰ፡፡ እንዴትስ አልተወቀሰም ስንልም የናትናኤል ንግግር ከተንኰል የመነጨ ሳይሆን የፊሊጶስ ንግግር ከነብያቱ ትንቢት ጋር የተጋጨ መስሎት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ናትናኤል ከመጻሕፍት ሲያነብ ያገኘውና የተረዳው ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም እንጂ ከናዝሬት እንደማይመጣ ነውና /ሚክ.5፡2/፡፡ ስለዚህ ናትናኤል እንደዚያ ማለቱና ክርስቶስም “ተንኰል የሌለበት ማለቱ” ትክክል ነበር፡፡ መጻሕፍትን አንዳንዶች እንደሚያደርጉት በራሱ ፈቃድ ለመተርጐም አለመሞከሩ ደግሞ የበለጠ ቅንነቱን ያሳያል /ቅ.ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatian’s Diatessaron 4:14/፡፡
 የናትናኤል ቅንነት የበለጠ ግልጽ የሚሆነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጌታ “ተንኰል የሌለበት” ሲለው “ከወዴት ታውቀኛለህ?” ማለቱም ጭምር እንጂ። “ኢየሱስም መልሶ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” በማለት የበለጠ ያምን ዘንድ የነበረበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን ጊዜውም ጭምር ነገረው /ቁ.49፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ በምሥጢራዊ አነጋገር ግን “አባትህ አዳምና እናትህ ሔዋን በወደቁበት ዕጸ በለስ ስር ወድቀህ በኃጢአት ተጐሳቁለህ ሳለህ በመለኰታዊ ባሕርዬ አውቃሃለሁ፤ አይቻሃለሁ” ማለቱ ነበር /ቅ.አምብሮስ/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ ከዚሁ የበለስ ግልድም አላቅቆ ጸጋውን ያለብሰን ዘንድ እኛን የጠፋነውን ለመፈለግ መጥቷል /አውግስጢኖስ/፡፡
 ከዚህ በኋላ ክርስቶስ የልቡን ስለነገረው ምንም ሳይጠራጠር እምነት ጨመረና “መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ፡፡ በዚህ ሰዓት ፊልጶስ እንደነገረው ከማመን፣ ከመረዳት፣ ከመደነቅ፤ በሐሴት ከሞመላትና ለክርስቶስ እጅ ከመስጠት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም /ቁ.50/፡፡ “ኢየሱስም መልሶ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? በል በዚህ ብቻ አትደነቅ! ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ /ቁ.51/። እኔ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) ስላይደለሁ ገና ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት እኔን ለማገልገል ሲወጡና ሲወርዱ ታያለህ” በማለት አባቱ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያየውን ራዕይ መፈጸሙን ይነግረው ነበር /ቁ.52/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ እንደተናገረው ናትናኤል መላእክት ክርስቶስ ፈታኙን ድል ሲያደርግ /ማቴ.4፡11/፤ ሲሰቀል፣ ከሙታን ተለይቶ ሲነሣ፣ ሲያርግ መላእክት ሲያገለግሉት አይቷል፡፡ ናትናኤል ባያይም ይህ ክስተት በቤተልሔም ግርግምም “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰበእ ሃሌ ሉያ” ሲሉ ተመልክተናል፡፡
አስተውላችሁ ከሆነ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ከነገረው በኋላ ናትናኤል አንዲትም ቃል መልሶ አልተነፈሰም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ላላመኑት እንደ ናትናኤል “ረቢ አማን አንተ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር- መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚል ቀና ልብ ይስጥልን፤ እኛንም በተዋሕዶ ያጽናን አሜን!!!!!!

Saturday, May 19, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የ8ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.1፡35-42)!!

“በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስን ሲሄድ አይቶት፡- እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።” /ቁ.35-36/
 የሰው ልጅ በባሕርይው ሐዋርያው፡- “ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ አይታክተኝም፤ እናንተን ያበረታችኋልና” እንዳለው ተደጋግሞ ካልተነገረው በቀር ተሎ አይገባውም /ፊል.3፡1/፡፡ ለዚህም ነው መጥምቁ ከዚህ በፊት የተናገረውን ቃል መልሶ የሚነግራቸው፡፡ ሲነግራቸውም መንደሩ እየዞረ ሳይሆን ሁሉም ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ እንዲመጡ በማድረግ ነበረ፡፡ “ለምን እንዲህ አደረገ?” ብለን ስንጠይቅም አንደኛ ሌሎች እርሱን የሚመስሉ ሐሰተኞች ዮሐንሶች በተነሡ ነበር፤ ሁለተኛ ሕዝቡ ሁሉም በተሰበሰበበት ሁኔታ “እነሆ የነገርኳችሁ በግ” ቢላቸው የበለጠ ታማኝነትን ያገኛል፤ ሦስተኛ ምስክነቱ እውነት እንደሆነ (ከዝምድናው የተነሣ እንዳልሆነ) አብም መንፈስ ቅዱስም ሲያረጋግጡት ሕዝቡ የበለጠ ያምናል፤ አራተኛ አይሁድ ክርስቶስ ሕግ አፍራሽ ነው ብለው ላለማመናቸው ምክንያት እንዲያጡ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ነበረበት፡፡ ነብያትን መታዘዝ ጽድቅ ነውና፡፡ ስለዚህ ሚዜው ሙሽራይቱን ከሙሽራው ጋር ለማገናኘት አሁንም ከወንዙ ዳር ቆሞ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ በግ” እያለ ይጮኽ ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐ. ወንጌል ትርጓሜ ድርሳን 18፣ ድርሳን በእንተ ጥምቀት/፡፡
  ከዚህ በኋላ ሁሉም ሳይሆኑ “ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።” /ቁ.37/ እውነት ነው! ፀሐይ ከወጣች በኋላስ የሻማ ጥቅሙ ምንድነው? የዮሐንስ ጥምቀትስ የክርስቶስ ጥምቀት ከመጣች በኋላ ምን ረብሕ አላት? /ቅ.ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatians Diatessaron 4:17/፡፡
ክርስቶስም ሲከተሉት አይቶ በልባቸው ምን እንደሚፈልጉ ስለማያውቅ ሳይሆን ፈቃደኝነታቸውን ለመጠየቅ “ምን ትሻላችሁ?” አላቸው /ቁ.38/፡፡   እነርሱም “ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?”  በማለት የሚፈልጉት እንዲያስተምራቸው እንደሆነና ወዴት እንደሚኖር በግልጽ ነገሩት፡፡ እርሱም “መጥታችሁ እዩ” አላቸው። መጥተውም ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች ማረፍያ ጐጆ እንዳላቸው ክርስቶስ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት እንደ ሌለው አዩ፤ በዚያም ቀን እስከ አሥር ሰዓት ድረስ በእርሱ ዘንድ ሲማሩ ዋሉ /ቁ.39፣ ሉቃ.9፡58/፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ሆነው ሄደውም እስራኤል ዘነፍስ ተባሉ /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:1:38/፡፡
 “ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ” /ቁ.40/፡፡ ምንም እንኳን ስሙ የተጠቀሰው እንድርያስ ብቻ ቢሆንም ሁለተኛው ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ራሱ ነበር፡፡ “እንዴት ይታወቃል?” ቢሉ ወንጌሉን ሲጽፍ የተለያየ ቦታ ስለ እርሱ የሚነገሩትን “ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር” ይላል እንጂ በሙሉ ስለ ትሕትና ብሎ ስሙን አይጠቅስምና /ዮሐ.19፡26፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ ዝኒ ከማሁ/፡፡
“እንድርያስም አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፡- መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው” /ቁ.41/፡፡ የሚገርም ነበር! ሰብአ ሰገል “የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ብለው ጠይቀው ለራሳቸው አግኝተውት ስለሄዱ አሁን እንድርያስ ሲያገኘው በጣም ነበር የተደሰተው፡፡ ምክንያቱም መጥምቁ የሚጠበቀው መሲሕ እርሱ መሆኑን ነግሮዋቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስ ሲመሰክር አይተዋል፡፡ ክርስቶስም እርሱ ማን እንደሆነ ነግሮታል፡፡ እንድርያስ ያልተማሩና የተናቁ የገሊላ ሰዎች በመሆናቸው መሲሑን ሲያገኘው በጣም ተደስቷል፡፡ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን ወጣለት” የሚለው የነብዩ ቃል ሲፈጸምለት በዓይኑ አይቷል /ኢሳ.9፡1/፤ “ምናምንቴዎችን መረጠ” የሚለው ቃል ሲፈጸምለት የማይደሰትስ ማን ነው? /1ቆሮ.1፡27፣ ኤፍሬም ሶርያዊ ዝኒ ከማሁ/፡፡ የሚደንቀው ደግሞ እንድርያስ እዚያ ተቀምጦ አልቀረም፤ ወንድሙን ይጠራ ዘንድ ተፋጠነ እንጂ፡፡ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተምሮና አምኖ “መሲሕን አግኝተናል” እያለ ወንድሙን ለመስበክ ተቻኮለ፡፡ በጣም በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበረም ያመለክታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 19/፡፡
 “ኢየሱስም ስምዖንን ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው” /ቁ.42/፡፡ ጴጥሮስ ለመጀመርያ ጊዜ ስሙ የሚቀየረው በዚሁ ሰዓት ነው፡፡ ጴጥሮስ ማለት ዐለት ማለት ነው፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን መሠረት ጽኑ እና የማይነዋወጥ መሆኑን ያመለክታል /ማቴ.7፡24፣ ማቴ.16፡18፣ አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ 7፡14/፡፡
 “ክርስቶስ ለአንዳንዶቹ ሐዋርያት ስማቸውን የሚቀይርላቸው ለምንድነው?” ብለን ስንጠይቅም በብሉይ ኪዳንም አብራምን አብራሃም፣ ሦራን ሣራ፣ ያዕቆብን እስራኤል ያለ አምላክ እርሱ እንደሆነ እንገነዘብ ዘንድ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ሳንወደው ለወደደን ከዲያብሎስ መንጋጋ አላቅቆም ወዳጆቹን ላደረገን ለእግዚአብሔር ዛሬም ዘወትርም ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን!!

FeedBurner FeedCount