Saturday, May 14, 2016

የትዳር አንድምታው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ መጽሐፍ በገበያ ውሏል

በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመውየትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮለአምስተኛ ጊዜ ታትሟል።
          በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መልስ የሚያገኙባቸው ነጥቦች፡-
እግዚአብሔር በትዳር ውስጥ ያለውን ድንቅ ፈቃድ፤
ሚስት ለባሏ ትገዛየመባሉ ምክንያትና አተረጓጎም፤
የባልና የሚስት እኩልነትና አንድ አካል ስለ መኾናቸው የተሰጡ ድንቅ ማብራሪያዎች፤
ባልና ሚስት በየበኩላቸው ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ ምግባራት፤
ለትዳራቸው ስኬት የሚጠቅሙን ሰማያዊ ፍልስፍናዎችና መንፈሳዊ ጥበባት፤
ኢአማኒ የትዳር ጓደኛ ቢኖረን ምን እናደርግ ዘንድ እንደሚገባን፤
ስለ ባርነት ትርጉም፤
አሳፋሪና አስፈሪ ትእዛዛት ስላሏት ጨካኝ እመቤት ማንነት፤
ስለ ትክክለኛው ድንግናዊ ሕይወት፤
ትኩረት ስላልተቸራቸው ነገር ግን ለብዙዎች ትዳር መፍረስ ዋና ምክንያት ስለኾነውመከልከል

Wednesday, May 4, 2016

ባሎች ለሚስቶቻቸው ሊያሳዩአቸው የሚገባ ፍቅር

   ☞ (በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመችውና ከአራት ዓመት በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ታትማ ግንቦት አንድ ቀን በገበያ ከምትውለው - የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ - መጽሐፍ የተቀነጨበ፣ ገጽ 17-19)

☞ … ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡
አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “But He for one who turned on Him and hated Him” “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡
ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው?

Saturday, April 30, 2016

የጌታችን ትንሣኤ



በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ወንጌላውያን ሁሉ ጽፈውታል፡፡ ከጥቃቅን ልዩነቶች በስተቀር የአራቱም ወንጌላውያን አጻጻፍ እርስ በርስ የተስማማ ነው፡፡ ልዩነቱም ቢሆን አንዱ የገለጠውን ዝርዝር ነገር አንዱ ባለመጨመሩ እንጂ የሚለያይ ወይም የሚጋጭ ነገርን በማካተቱ አይደለም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በበኩላቸው የትንሣኤውን ነገር መሠረት አድርገው ያስተማሩት ትምህርት፣ የሰበኩት ስብከት፣ እንዲሁም የተመስጧቸው ፍሬና የትርጓሜ ሐሳቦቻቸው እጅጉን የበዙ ሲሆን ከዚያ ውስጥ በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት ጥቂቱን መርጠን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ለትምህርቱ እንዲመቸን በዋናነት የሉቃስን ወንጌል እንያዝና የተቀሩትን ምንባባት እንደ አስፈላጊነታቸው ከየወንጌላቱ እንጨምራለን፡፡

Thursday, April 28, 2016

ደም ለበሰች

ያቺ ውብ ጨረቃ በጣም የደመቀች
                ውቢቷ ጨረቃ፤
ደም ለበሰች አሉኝ
             በኃይል ተጨንቃ፡፡
እርቃኑን ሲያስቀሩት የዓለም ፈጣሪ
    ከላይ ተመልክታ ከልቧ አዘነች፤
ይህን አላደርግም ድምቀቴ በሱ ነው
                ብላ ራሷን ጣለች፡፡
ደሙ ሲፈስ አይታ፤
ህመም ግርፋቱን እሷም ተመልክታ፤
ጌታ ሲንገላታ፤
አይ አይሆንም አለች
          አይኖቿን ጨፈነች፤
የጭንቀቷ ብዛት
         እሷም ደም ለበሰች፡፡

FeedBurner FeedCount