ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ጳጉሜን 5 ቀን፥ 2005 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
መግቢያ
የሰው ልጅ ሕይወት ከጊዜ ጋር በእጅጉ የተቈራኘ
ነው፡፡ እያንዳንዱ ማኅበረሰብም የራሱ የሆነና ይህን ከሕይወቱ ጋር የተቈራኘውን ጊዜ የሚቀምርበት የዘመን አቈጣጠር አለው፡፡ ሊቃውንት
ሲናገሩ “ለቃለ እግዚአብሔር ጥናት ሰዋስው፥ ለምስጋና ዜማ፥ ለምሥጢራት ቀኖና እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጌታ በዓላትም ባሕረ ሐሳብ
የግድ ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ ሐሳበ ዘመን ማለትም የዘመን አቈጣጠር አላት፡፡ ይህ የዘመን አቈጣጠር
(ሐሳበ ዘመን) የዘመናት፣ የዓመታት፣ የወራት፣ የሳምንታት፣ የዕለታት፣ የሰዓታት፣ የደቂቃዎች፣ የቅጽበትና (የካልዒትና)
የመሳሰሉት ጊዜያት በሐሳብ የሚመዘኑበት፣ የሚሰፈሩበት፣ የሚቈጠሩበት ምድብና ቀመር ተሰጥቶአቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ
እያሰማ የሚጠራበት ትምህርታዊ ውሳኔ ነው፡፡
የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል “ሐሰበ፣ ቈጠረ” ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ሲሆን ትርጓሜውም ቊጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም በባሕር ምሳሌ ነው፡፡ ባሕር ጥልቅና ምጡቅ እንደሆነ ሁሉ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱና ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል /ዕዝ.ሱቱ.2፡37/፡፡
የዘመን አቈጣጠር “ሐሳበ አቡሻኽር” እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ አለ፡፡ ይኸውም የዘመን አቈጣጠር ትምህርትን ካዘጋጁ ሊቃውንት አንዱ ዮሐንስ
አቡሻኽር ስለሆነና በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድም እጅግ ስለሚወደድና በእርሱ ስም ስለሚጠራ ነው፡፡ ዮሐንስ አቡሻኽር ማለት በ13ኛው
ምዕተ ዓመት በእስክንድርያ የኖረ ሊቅ ነው፡፡
በቀጥታ ወደ ትምህርቱ ከመግባታችን በፊትም አንዳንድ በትምህርቱ
የምንጠቀምባቸው ቃላት ለአንባቢ እንግዳ ሊሆኑ ስለሚችሉና ሐሳቡን ሳይረዱ እንዳይቀሩ ትርጕማቸውን በመስጠት እንዠምራለን፡፡
·
መጥቅዕ - ማለት በቁሙ ዐዋጅ ነጋሪት ማለት ነው፡፡ መጥቅዕ
በተመታ ጊዜ ሕዝቡና አሕዛቡ እንዲሰበሰብ በዓለ መጥቅዕም በተገኘ ጊዜ አጽዋማትንና በዓላትን ሰብስቦ ያስገኛል፡፡
·
ቀመር - ቊጥር
·
ታሕታይ ቀመር (ኢይወርድ) - ተዘዋዋሪ የሆኑ የአጽዋማትና
በዓላት የማይሻገሩበት የታችኛው ቀመር መስመር
·
ላዕላይ ቀመር (ኢየዐርግ) - ተዘዋዋሪ የሆኑ የአጽዋማትና
በዓላት የማይሻገሩበት የላይኛው ቀን ወሰን
·
አበቅቴ - ትርፍ ማለት ሲሆን በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር
ያለው የ11 ቀን (365-354) ትርፍ (ልዩነት) ማለት ነው፡፡
·
ዓመተ ዓለም - ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ
አሁን ያለው ዘመን (ለምሳሌ ዘንድሮ 7505)
·
ዕለተ ምርያ - 5ኛ ጳጉሜን ናት፡፡ አጽዋማቱንና በዓላቱን
የምታዟዙር (እንዲዟዟሩ የምታደርግ) ይህቺ ቀን ናት፡፡ ምርያ ማለት መድኀኒት ማለት ነው፡፡ ዕለቲቱ ዕለተ ምርያ መባሏም
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባትን ዕለት ስለምታሳውቅ ነው፤ ማለትም ጳጉሜን 5 በዋለበችበት ዕለተ ልደት
ይውላል፡፡ በዚህም መሠረት ዘንድሮ ጳጉሜን 5 ማግሰኞ ስለዋለች ገና ማግሰኞ ይውላል ማለት ነው፡፡
·
ዕለተ ሠግር - 6ኛ ጳጉሜን፤ ሠግረ ዮሐንስም ትባላለች፥
ዮሐንስ ተሻግሮ የሚውልባት ቀን ማለት ነው፡፡
·
ጥንተ ዕለት - ዕለት የተዠመረበት ዕለት፤ ይኸውም እሑድ
ናት፡፡ አንዳንዶች ግን አዳም በተፈጠረበት ቀን መነሻ በማድረግ በዓርብ ይነሣሉ፡፡
·
ጥንተ ቀመር - ቀመር የተጀመረበት ዕለት (ማግሰኞ)፡፡
መሠረቱ ጨረቃ ማግሰኞ ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ስለተፈጠረች ነው፡፡
·
ጥንተ ዮን - ብርሃናት የተፈጠሩበት ዕለት (ረቡዕ)
አሁን ወደ ዋናው ትምርታችን እንግባ!
የዓመተ ዓለም የዘመን አቈጣጠር ከሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
ይኸውም፡-
፩ኛ) ከአዳም እስከ ልደተ
ክርስቶስ (ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ፣ ዘመነ ብሉይ)፤
፪ኛ) ከክርስቶስ ልደት ወዲህ
ያለውን ጊዜ (ዓመተ ምሕረት፣ ዘመነ ሐዲስ፣ ዓመተ ሥጋዌ) በማለት፡፡
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. አዳም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ልደተ ክርስቶስ የነበረው
ዘመን 5500 ዓመተ ዓለም ነው ብላ ታምናለች፡፡ ለዚህ መሠረቷ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ነው /ዘፍ.3፡16፣ መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ፣
ዕዝ.ሱቱ.4፡1፣ ሲራ.24፡6፣ ገላ.4፡4/፡፡
5500 ዘመን ስንተነትነውም እንደሚከተለው ነው፡፡
ከአዳም እስከ ጥፋት ውሃ
|
2256
|
ከጥፋት ውሃ እስከ አብርሃም 75ኛ ዓመት
|
3463
|
ከአብርሃም 75ኛ ዓመት እስከ ሰሎሞን
|
4587 ከ6 ወር
|
ከሰሎሞን እስከ ዓሥሩ ነገድ ምርኮ
|
4787 ከ6 ወር
|
ከዓሥሩ ነገድ ምርኮ እስከ ባቢሎን ምርኮ
|
4921
|
ከባቢሎን ምርኮ እስከ ብልጣሶር ሞት
|
5183
|
ከብልጣሶር ሞት እስከ መንግሥተ ፋርስ ፍጻሜ
|
5183
|
ከመንግሥተ ፋርስ ፍጻሜ እስከ ልደተ ክርስቶስ
|
5501 ይሆናል፡፡
|
|
|
ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከተፀነሰባት ጊዜ የነበሩ ዘመናት ከላይ እንደተናገርን ዓመተ ኩነኔ፣ ዓመተ ፍዳ፣ ዘመነ ብሉይ
ተብለው ይጠራሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ጊዜ ደግሞ ዓመት ምሕረት፣ የምሕረት ዘመን፣ ዘመነ ሐዲስ፣ ዓመተ ሥጋዌ
ይባላል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በፀሐይ አቈጣጠር 2006 ዓመት ተቈጥሯል፡፡ በጠቅላላ 5500+2006= 7506 ዓመት ይሆናል
ማለት ነው፡፡ ይህም ዓመተ ዓለም መሆኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር የፀሐይና የጨረቃ አቈጣጠርን የተከተለ ነው፡፡
በዓመተ ፀሐይ 365¼ ቀናዊ አቈጣጠር ሲኖር /ኄኖክ 21፡49/፥ በዓመተ ጨረቃ ደግሞ 354 ሌሊታዊ አቈጣጠር አለ /ኄኖክ
29/፡፡ ስለዚህ ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ ዘንድሮ በፀሐይ አቈጣጠር 7506 ዓመት ሲሆን በጨረቃ አቈጣጠር ደግሞ 7736 ዓመት
ከ7 ወር ከ29 ዕለት ነው ማለት ነው፡፡ ዐቢይ ጾምንና የትንሣኤ በዓልን አከባበር በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር የሚገኝ ነው፤
በፀሐይ አቈጣጠር ብቻ አይገኝም፡፡
ለዓመተ ዓለም መቊጠርያ (መስፈሪያ) የሚሆኑ ሰባት አዕዋዳት አሉ፡፡ አዕዋዳት
ማለት እንደ ቀለበት ዙርያ ገጠም እየሆኑ የሚታዩ የጊዜያት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
·
ዐውደ ዕለት፡- ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉ ሰባት ቀናት
የሚመላለሱበት ዙር፤
·
ዐውደ ወርኅ፡- በፀሐያዊ አቈጣጠር ዘወትር በ30 ቀናት፥
በጨረቃ ግን አንዴ 29 ሁለተኛ ላይ 30 እያሉ እየተፈራረቁ የሚመላለሱበት ዙር (መስከረም 29፣ ጥቅምት 30፣ ኅዳር 29፣
…)፤
·
ዐውደ ዓመት፡- የዓመት መመላለስ፡፡ ይኸውም በፀሐያዊ
አቈጣጠር 365 ከ¼፥ በጨረቃ አቈጣጠር ደግሞ 354 የሆኑ ዕለታት ናቸው፡፡
·
ዐውደ አበቅቴ፡- በየ19 ዓመታት የሚመላለስ ዙር፤
·
ዐውደ ፀሐይ፡- በየ28 ዓመታት የሚመላለስ ዙር፤
·
ዐውደ ማኅተም፡- በየ76 ዓመት የሚመላለስ ዙር፤
·
ዐውደ ቀመር፡- በየ532 ዓመት የሚመላለስ ዙር ናቸው፡፡
·
ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ዐውደ ወንጌላውያን የሚባልም
አለ፡፡ ይኸውም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ እያለ በየ4 ዓመቱ የሚመላለስ ነው፡፡
እኛም ለጊዜው የመጀመርያዎቹ ሦስቱን
ማለትም ዐውደ ዕለትን፣ ዐውደ ወርኅንና ዐውደ ዓመትን ብቻ ከዚህ በታች እንመለከታለን፡፡
ዐውደ ዕለት
ዐውደ ዕለት ማለት የሰባቱ ዕለታት ዙር ማለት ነው፡፡ የሚዠምረውም ከጥንተ
ዕለት ከእሑድ ሲሆን ቅዳሜ ላይ ያበቃል፡፡ እነዚህም ወራትንና ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡ በሰባት ዕለት
መመደባቸውም ገና ከጥንት ከሥነ ፍጥረት አንሥቶ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱሳችን የምናገኘው ነው /ዘፍ.2፡2-3፣ ዘጸ.20፡11/፡፡
1. እሑድ፡- እሑድ፣ እሒዶት ከሚለው ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንድ አደረገ (የመጀመሪያ ሆነ) ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን ፍጥረታት መፈጠር ስለጀመሩ እሑድ ተብሏል፡፡
2. ሰኑይ፡- ሰኑይ፣ ሰኑዮት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሁለት አደረገ ማለት ነው፡፡ ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ስለሆነ ሰኑይ (ሰኞ) ተብሏል፡፡
3. ሠሉስ፡- ሠልሶ፣ ሠልሶት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ሦስት አደረገ ማለት ነው፡፡ ማግሰኞ ማለት የሰኞ ማግስት ማለት ነው፡፡ ሦስት መባሉም ለሥነ
ፍጥረት ሦስተኛ ቀን መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
4. ረቡዕ፡- ረብዓ፣ ረብዖት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አራት አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ለሥነ ፍጥረት አራተኛ ቀን መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
5. ኀሙስ፡- ኀምሶ፣ ኀምሶት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን አምስት አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
6. ዐርብ፡- ዐሪብ፣ ዐሪቦት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ፍጥረታት እሑድ መፈጠር ጀምረው ዓርብ መካተታቸውን (ተፈጥረው መፈፀማቸውን) የሚያስረዳ ነው፡፡
7. ቅዳሜ፡- ቀዲም፣ ቀዲሞት ከሚል ንዑስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን ሰንበተ ክርስቲያን ከሆነችው ከዕለተ እሑድ ቀድማ ስለምትገኝ ቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜ) ተብላለች፡፡
የምዕራባውያኑ የቀናት ስያሜ
ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ስለሌለው ትርጕማቸው ለጣዖታት መታሰብያ የተሰጠ ነው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ነው፡-
1.
Sunday – Sun’s Day - የፀሐይ ቀን፣ ፀሐይን
የሚያመልኩ ስለሆነ ለአምላካቸው የሰጡት የመታሰብያ ቀን፤
2.
Monday – Moon’s Day - የጨረቃ ቀን፣ ጨረቃን
የሚያመልኩ ሰለሆነ ለአምላካቸው የሰጡት የመታሰብያ ቀን፤
3.
Tuesday – Tiu’s Day - የቲው ቀን፣ ቲው (የጦርነትና
የጠፈር አምላክ) ለሚሉት ጣዖት የተሰጠ የመታሰብያን ቀን፤
4.
Wednesday – Woden’s Day - የወደን ቀን፣
ወደን (የአደን አምላክ) ለሚሉት ጣዖት የተሰጠ የመታሰብያ ቀን፤
5.
Thursday – Thor’s Day - የቶር ቀን፣ ቶር (የመብረቅ
አምላክ) ለሚሉት ጣዖት የተሰጠ የመታሰብያ ቀን፤
6.
Friday – Freya’s Day - የፍረያ ቀን፣ ፍረያ (የፍትወትና
የውበት አምላክ) ለሚሉት ጣዖት የተሰጠ የመታሰብያ ቀን፤
7.
Saturday – Saturn’s Day - የሳተርን ቀን፣
ሳተርን (የእርሻ አምላክ) ለሚሉት ጣኦት የተሰጠ የመታሰቢያ ቀን ነው፡፡
ሳምንት
ሳምንት “ሰሙን” - ሰባት አደረገ ከሚለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ በሕገ ዑደት መሠረት ዕለት ከተነሣበት ማለትም ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያለው ጊዜ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ያሉት ቀናት እያንዳንዳቸው 24 ሰዓት ያላቸው ናቸው፡፡ እሑድ ማለት “እሑድ፣ እሒዶት” አንድ አደረገ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ስለሆነ ትርጉሙ አንድ ማለት ነው፡፡ ሰኞ ሁለተኛ ፣ ማግሰኞ /የሰኞ ማግስት/ ሦስተኛ፣ ረቡዕ አራተኛ፣ ሐሙስ አምስተኛ፣ ዓርብ ስድስተኛ ፣ ቅዳሜ ሰባተኛ ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን በስድስት ቀናት (ከእሑድ እስከ ዐርብ) ፈጥሮ ያረፈባትና ሰዎችም እንዲያርፉበት ያዘዛት ሰባተኛዋ ቀን በግዕዝ ቀዳሚት ሰንበት ተብላ ትጠራለች፡፡
ዐውደ ወርኅ
በፀሐይ ዘወትር 30 ዕለት ነው፡፡ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29 አንድ ጊዜ 30 ዕለት ይሆናል፡፡ ይህም ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለስ ይኖራል፡፡ ወራቱ በፀሐይ አቈጣጠር ተቀምረው እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው 12 ወራት ሲሆኑ፣ 5 ቀናት ከ¼ ማለትም ከ6 ሰዓት ያላት 13ኛዋ ወር ደግሞ ጳጉሜን (ተረፍ፣ ተውሳክ፣ ጭማሪ) ተብላ ትጠራለች፡፡ በየአራት ዓመቱ ግን በየዓመቱ ያሉት ሩቦች ተደምረው አንድ ቀን ስለሚሆኑ ጳጉሜን በጠቅላላ 6 ቀናት ትሆናለች፡፡ የወራቱ ዘይቤአዊ ትርጓሜም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የወሩ ስም
|
የግዕዝ መገኛው
|
የአማርኛ ትርጕም
|
|
|
|
መስከረም
|
ከረመ
|
ከረመ፥ ምሴተ ክረምት፣ የክረምት መካተቻ
|
|
|
|
ጥቅምት
|
ጠቀመ
|
ጠቀመ፥ ጽጌ መደብ አድርጎ ፍሬ ሲሰጥ
|
|
|
|
ኅዳር
|
ኀደረ
|
አደረ፥ ገበሬ አዝመራዉን ሲጠብቅ ከዱር ስለሚያድር
|
|
|
|
ታኅሳስ
|
ኀሠሠ
|
ፈለገ፥ መረመረ፣ ሰብአ ሰገል ጌታን ፍለጋ በኮከብ
እየተመሩ መምጣታቸውን የሚያስረዳ /ማቴ.2፡1-7/፡፡
|
|
|
|
ጥር
|
ጠየረ
|
መጠቀ፥ ረዘመ፣ ከጥቅመ ሰናዖር ጋር የተያያዘ ነው
/ዘፍ.11፡1-11/፡፡
|
|
|
|
የካቲት
|
ከተተ
|
ሰበሰበ፥ ገበሬ ምርቱን መሰብሰቡን የሚያስረዳ፡፡
|
|
|
|
መጋቢት
|
መገበ
|
መገበ፥ የመዓልትና የሌሊት ምግብና ትክክል (እኩል)
መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
|
|
|
|
ሚያዝያ
|
መሐዘ
|
ሚዝት ፈለገ፤ የሚዛዝት (የሚዜዎች) ወራት፤ ወሩ ጋብቻ
ስለሚበዛበት የተሰጠው ስያሜ፡፡
|
|
|
|
ግንቦት
|
ገነባ
|
ገነባ፥ የባቢሎን ግንብ ሳይወር ሁለቱ መቅደሶች በዚህ
ወር መመሥረታቸውን የሚያስረዳ /3ነገ.6፡1፣ ዕዝ.3፡8-11/፡፡
|
|
|
|
ሰኔ
|
ሠነየ
|
አማረ፥ የማሣው በዘር መሸፈኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
|
|
|
|
ሐምሌ
|
ሐምለ
|
ለመለመ፥ ወሩ የቅጠላቅጠል፣ የልምላሜ ወር መሆኑን
የሚያስረዳ
|
|
|
|
ነሐሴ
|
ነሐሰ
|
ሠራ፥ ጨረሰ፣ የመጨረሻ ወር
|
|
|
|
በምዕራባውያኑ ግን መጽሐፍ
ቅዱሳዊ መሠረት ስለሌለው የወራቱ ስያሜ እንደ ቀናቱ ሁሉ ለጣዖታት መታሰብያ የተሰጠ ነው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1.
January – Janus Month - የጃኑስ ወር፣ የኆኀት
(የደጅ) አምላክ ተብሎ ለሚታሰብ ጣዖት፤
2.
February – Februa’s Month - የፌብሯ ወር፣
ሥርየትን የሚሰጥ አምላክ ተብሎ ለሚታሰብ ጣዖት፤
3.
March – Mars’ Month - የማርስ ወር፣ የጦርነት
አምላክ ተብሎ ለሚታሰብ ጣዖት፤
4.
April – Aphrodite’s Month - የአፍሮዳይት
ወር፣ የፍትወትና የውበት አምላክ ተብላ ለምትታሰብ የሴት ጣዖት፤
5.
May – Maia’s Month - የማያ ወር፣ የስጦታ
አምላክ ተብላ ለምትታሰብ ጣዖት፤
6.
June – Juno’s Month - የጁኖ ወር፣ የጋብቻና
ሴቶችን ጥሩ እንዲሆኑ ታደርጋለች ተብላ ለምትታሰብ ሴት ጣዖት፤
7.
July – Julius’ Month - የጁሊዮስ ቄሳር
መታሰብያ ወር፤
8.
August – Augustus’ Month - የአውግስጦስቀ
ቄሳር መታሰብያ ወር፤
9.
September – Septem - ሰፕተም፣ ሰባት፣ ሰባተኛ
ወር፤
10.
October – Octo - ኦክቶ፣ ስምንት፣ ስምንተኛ ወር፤
11.
November – Novem - ኖቨም፣ ዘጠኝ፣ ዘጠነኛ ወር፤
12.
December – Decem - ዴሰም፣ ዐሥር፣ ዐሥረኛ ወር
በማለት ወራቱን በሙሉ እንደ ቀናቱ ሁሉ ለጣዖታት መታሰብያ አድርገው ይጠሩዋቸዋል፡፡
የወራት ብተት (መባቻ ቀን)
መስከረም በሚብትበት ዕለት ሚያዝያ ይብታል፡፡ ጥቅምት በሚብትበት ዕለት
ግንቦት፣ ኅዳር በሚብትበት ዕለት ሠኔ፣ ታኅሣሥ በሚብትበት ዕለት ሐምሌ፣ ጥር በሚብትበት ዕለት ነሐሴ፣ የካቲት በሚብትበት
ዕለት ጳጉሜን ይብታል፡፡ መጋቢት ግን ተመሳሳይ ወር ስለሌለው ለብቻው ይያዛል፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment