Wednesday, September 4, 2013

« ርኢኩ ሰብዐተ መላእክተ እለ ይቀውሙ ቅድመ እግዚአብሔር » ራዕ 8÷2


                                                                             በክፍለ ሥላሴ 

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጳጉሜ 1 ቀን፣ 2005 ዓ.ም.)፡-  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
መግቢያ
     ቅዱስ መጽሐፋችን «የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፣ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው፡፡ እንዳይዘልፉህ ደግሞም ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር» (ምሳ.30÷6) ይላል፡፡ ሰማያዊውን ወንጌል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል መንፈሳውያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሪነት መረመሩት፣ አመኑት አልፈውም ታመኑበት የጠላትን የክህደት ጦር ይመክቱበት ዘንድ ጋሻ ሆናቸው፡፡ ፈቃዳቸው እና የልባቸውም ሃሳብ የሚመራቸው ግን በገዛ መንገዳቸው ቃሉን ፈትነው የተከደነውን ሊገልጡ የተሰወረውን ሊያወጡ ቢባዝኑ ጥርጣሬን ጸንሰው ክህደትን ይወልዳሉ፣ ሀሰትን ጨምረው ተዘልፈው ይጠፋሉ፡፡ «ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉት ነው»  (1ቆሮ 4÷3)፡፡


    በባህሪው :-
                         …… ያደረገው ዘንድ የሚያቅተው አንዳች የሌለ ሁሉ በፈቃዱ የተከወነ፣
         ……………. ይሰወርበት ዘንድ የተሸሸገ አንዳች የሌለ ሁሉ በፊቱ የተገለጠ፣
       ……..የማይኖርበት ዘመንና ስፋራ የሌለ ሁሉ በእርሱ፣ ለእርሱ በቦታና በበጊዜ የተወሰነ አምላካችን እግዚአብሔር አስቀድሞ መርጦ የወደደችውን ለይቅርታም ያዘጋጃቸውን ቅጣቱን የሚያሳይባቸው፣ ሃይሉን  የሚገልጥባቸው ፍጡራን ቅዱሳን መላእክት መሆናቸውን አስፍቶና አብራርቶ የሚገልጸው ይኸው ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡

መላእክት የሚለው ብዙ ቁጥርን አመላካች ሲሆን በነጠላ መልአክ ይሆናል እንደየአገባቡም የተለያዩ ሁለት ትርጉሞችን ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

መልአክ :-
 1. ተመልአከ ከሚለው የግእዝ ግስ ሲወጣ አለቃ ሆነ በሚለው መሪ፣ አስተዳዳሪ፣ አዛዥ፣ አለቃ የሚለውን ይገልፃል፡፡
(ዮሐ.3÷1) ኒቆዲሞስን « መልአኮሙ ለአይሁድ»  ይለዋል የአይሁዳውያን አለቃ ሲል፡፡ የጌታ ወዳጅ ባለራዕይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም በተደጋጋሚ ራዕዩን ለሰባቱ   የቤተ ክርስቲያን መልአክ እያለ ሲገልጽ በዚህ ትርጉም የገባ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ (ራዕ 1÷20)

         2. ለአከ ከሚለው ግስ ሲነሳ ላከ የሚለውን ስለሚያስገኝ መልእክተኛ ጠባቂ ተብሎ ይፈታል፡፡
ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በቁጥራቸው ሰባት በስፋራም ከእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን መላእክት አየሁ አለ፡፡ አበው ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ ቢሉ ከጥሩ የጠጡት ውኃ ለጤና እንዲስማማ ከሰሩ የሰሙትም ነገር ከልብ ይደርሳልና ነው፡፡ መላአክት ማናቸው የሚለውን ለመመለስ አንዳንዶች «ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈሰ ወለእለይትለአክዎ ነደ እሳት$ (መዝ.103÷4) ያለውን ይዘው ከእሳትና ከነፋስ ተገኝተዋል ይህም« መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም እሳት ነበልባል የሚያደርግ »       በሚለው ታውቋል ይላሉ፡፡ ይሁንና ግን ይህ አገላለጽ ባህሪያቸውን ከእሳትና ነፋስ ጋር በማነጻጸር ያስረዳ መሆኑን እንደሚከተለው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ነፋስና እሳት ረቂቃን፣ ፍጡናን (ፈጣኖች) እዲሁም ፈፃምያነ ፈቃድ (ፈቃድን የሚፈጽሙ) ናቸው፡፡ በተነጻጻሪው  መላእክትም
===>  ረቂቃን ይህም በእግር የማይረጋገጡ በእጅም የማያጨበጡ
===>  ለተልእኮ (ለመታዘዝ) የሚፈጠኑ (መዝ 90÷11) 
===>  የጌታን ፈቃድ የሚፈጽሙ (ሮሜ 9÷22)  ናቸው፡፡
   ከዚህም በተጨማሪ እንደምድራውያኑ ተርበው የማይመገቡ፣ ተጋብተው የማይራቡ በመሆናቸው (ማቴ 22÷30) ያለጾታ መለያና ያለድካም ሳያርፉ ሲያመሰግኑ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ለዚህም ሊቃውንቱ   «ወፈጠረ እግዚአብሔር መላእክተ ዘሲሳዮሙ ቀድሶቱ ወሰብሆቱ ወስቴሆሙ ፍቅረ መለኮቱ ወእሉኬ አልቦሙ ትእምርተ ተባዕት ወአንስት»   እያሉ እግዚአብሔር የፈጠራቸው መላእክቱ እርሱን ማመስገን ምፍግባቸው መለኮታዊ ፍቅሩ መጠጣቸው የሆኑ የጾታም መለያ ምልክት የሌላቸው መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡
ቁጥራቸውን ሰፍሮ ብዛታቸውንም ለክቶ ለማመልከት የማይቻል ነው፡፡ ይህንንም ባለራዕዩ ሐዋርያ « የብዙ መላእክት ድምጽ ሰማሁ ቁጥራቸውንም አእላፋት ጊዜ አእላፋት ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር » (ራዕ 5÷11 … መዝ 66÷17  ) በማለት ያስረዳ ቢሆንም ከእነዚህ የተለዩ ተመርጠው በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ግን  ሰባት    መላእክት እንዳሉ ገልጻል እንዚህም ከኪሩቤል፣ ሱራፌልና ደቂቀ አዳም ውጪ ያሉትን ከመቶው ነገድ በሰማይም ሥርዓት አስር መአረጋት ካላቸው ውስጥ የሰባቱ መዓረጋት አለቆች ናቸው፡፡ እነዚሁም የመላእክት የሊቃናት የመናብርት የአጋዕዝት የሥልጣናት የኃይላትና የመኳንንት አለቆች ናቸው፡፡
ከዚህ ተያይዞ  እጅግ ልናጤነው የሚገባ ሁለተኛው አገላለጽ «በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ$ መባሉን  ነው፡፡ እኛ ሰዎች ልባችን ያልነፃ ከኀጢዓት የማንለይ ቢሆን «ሰው አይቶኝ አይድን ፊቴን ማየት አይቻልህም$ (ዘጸ 33÷20) ተባልን፣ መላእክቱ ግን ለምልጃ እንዲቆሙ ምህረት ፊቱን እንዲያዩ ስልጣን ተሰጣቸው፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተነገረ 
~~~>  «እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ» (ሉቃ1÷19)  
~~~>  «ከእነዚህ ከታናናሾቹ እንዱን እዳትንቁ ተጠንቀቁ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉና»  (ማቴ18÷10)
~~~>  «የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ወጡ  » ኢዮ.1÷7  
 ለካ «እግዚአብሔርን ያየው አንድ ሰው እንኳን የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ተረከው » (ዮሐ.1÷18) ተብሎ መነገሩ የእኛ የከፋ ምግባር ከክብሩ ባያደርሰን ኖሯል፡፡ እገዲህም መላእክቱ በእግዚአብሔር ፊት ሲቆሙ የእነርሱን ንጽሕናና ቅዱስና ስለእኛ ፈንታ ተመኝተን ሥራችን ከእርሱ ከአምላካችን  ፊት የማያቆመን ቢሆን በመላእክቱ ፊት ቆመን እንማጸነዋለን ነቢየ እዚአብሔር ንጉስ ዳዊት «በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ» (መዝ.137÷2) አንዳለ አልፎም ከጥፋት ብንመለስ፤ ተጸጽተንም መልካሙን ሁሉ ብናደርግ ደስታውም በእርሱ ፊት ነው ንሰሀ በሚገባ በአንድ ኃጢዓተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል፡፡

     እንግዲህ ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ ሊቀመናብርት (የመናብርት አለቃ) የሆነበሹመት ፈታሔ ማኅጸን (ማሕጸን የሚፈታከሳቴ እውራን (የእውራንን ዓይን የሚያበራሰደዴ አጋንንት (አጋንንትን የሚያባርርፈዋሴ ዱያን (ድውያንን የሚፈውስ) አቃቤ ኆኅት (የምህረትን ደጁ የሚጠብቅ) ተብሎ የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን እንዲህ በማለት ገለጠ #የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ» (ጦቢ.12÷15)
ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የእብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ ሩፋ ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን ኤል ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው ይህም« መልአኬን በፊትህ አሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ . አታስመርሩት» (ዘጸ.23÷20-22) እዳለው ነው፡፡
ታዲያ ሩፋኤል የሚለው በጥምረት ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ የሚለውን ይተካል «በሰው ቁስል የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው፡» (ሄኖ.6÷3)
ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን
  • ይጠብቃቸዋል(ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) 
  • ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡(ዘካ.1÷12)
  • በፈሪሀ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን ድናቸዋል (ዘፍ.49÷15 መዝ.3÷37)
  « እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የይቅርታ መላእክትን ያመጣል»  (ሮሜ.9÷22)
ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀመናብርትን ድንቅ ገቢር ተአምራቱን ያዩ ምዕመናን

                  ……የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ
                                      ስለተሸመ ከጌታ
                              አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም
                               ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም
                          በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ የባላገር ሴቶች ሁሉ
                        የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ
                        ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ ……
እያሉ ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡


ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ  እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡ በጉልህ ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል ጥቂቶቹን እነሆ
             ~~~>  በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና ክብር አብቅቷቸዋል፡፡
              ~~~>  የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጸድቁ አኖሬዋስም በፈጣሪው ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ ለታናሽ ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡
            ~~~> በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላትዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀመናብርቱ ተማጽነው እርዳን ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጸ ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው
            ~~~>  ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት (መጽሐፍ ጦቢት)
ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

ማጠቃለያ
እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሃይል በቅዱሳኑ መላእክት አድሮ የሚፈጽመውን ሥራ የሚክዱ የአምልኮ መልክ ያላቸው ይህን ቅዱስ መጽሐፍ በምስክርነት የገለጠውን በምልዐት የሰበከውን የቅዱሳን መላእክት አገልግሎትና ክብር ማስተዋል የተሳናቸው የገዛ መንገዳቸውን ስለሚከተሉና ቅዱሱንም ቃል ስለማያደምጡ፣ ለራሳቸው ደስታ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ነው፡፡ « ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ የአምልኮት መልክ አላቸው ሃይሉን ግን ክደዋል» (2 ጢሞ.3÷5)

                በታላቁ ንጉስ በእግዚአብሔር ፊት ለምህረት ለምልጃ የሚቆሙ መላእክቱን መመልከት የሚቻለው እንደሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ መከራን ሁሉ ታግሶ በመጽናት መስቀሉ ስር በመገኘት የሥጋን ፈቃድ አስገዝቶ የነፍስን መንፈሳዊ ኃላል በማጎልበት፣ በቅዱሳን መላእክቱ ረዳትነት እግዚአብሔርን ምህረት በመሻት ነው፡፡
   በሃይማኖት ያለን ጽናት ለተጋድሎ ያለን ትጋት፣ ለቤተክርስቲያን ያለን ፍቅር ለአባቶች ያን ክብር ሳቀንስ ሰማያዊውን ሃይል በታቦት በመስቀሉ መንፈሳዊውን በረከት በእምነት በጠብሉ ተቀብለን መንግስቱን አምላካችን እንዲያወርሰን የሊቀመናብርት ቅዱስ ሩፋኤል ምልጃ በህይወታችን ሁሉ አይለየን፡፡ አሜን!!!

«የቃልህ ፍቺ ያበራል» መዝ118 ÷130
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount