Wednesday, September 4, 2013

“ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” - የዮሐንስ ወንጌል የ48ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.13፡1-19)

ገ/እግዚአብሔር ኪደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ነሐሴ 29 ቀን፥ 2005 ዓ.ም.)፡- የነገረ መለኮት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ከዚህ ከ13ኛው እስከ 17ኛው ምዕራፍ ያሉት የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፎች ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ያደረጋቸውን የፍቅር ድርጊቶችንና ትምህርቶቹን አጠቃልለው ስለያዙ “የፍቅር ወንጌል” ብለው ይጠሩዋቸዋል፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች ብቻ ወንጌላዊው “ፍቅር” እያለ 20 ጊዜ ጽፏል፡፡ የፍቅር ግብር ምሥጢረ ትሕትና የበለጠ የተገለጠው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የፍቅር ማዕድ ምሥጢረ ቁርባን የተመሠረተው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የምሥጢረ ጸሎት ትምህርትም በስፋት በጌቴ ሴማኒ የአታክልት ስፍራ የተማርነው በዚህ ዕለት ነው፡፡  እኛም ለዛሬ ከወንጌላዊው ጋር በሕፅበተ እግር ስለተገለጠው ስለ ምሥጢረ ትሕትና እንማማራለን፡፡ ምሥጢሩን ይግለጥልን!

  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሎ አስተምሮ ነበር /1ኛ ቆሮ.11፡1/፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ያደረገው ስለዚሁ ነው፡፡ የእኛን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ የመጣው በምግባር በትሩፋት እንደምን ማጌጥ እንዳለብን ያስተምረን ዘንድ ነው፡፡ ሐዋርያው “እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ … ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ” ይላል /ሮሜ.8፡3/። ጌታችንም፡- “ከእኔ ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥” ብሏል /ማቴ.11፡29/፡፡ ጌታችን ይህን ያስተማረው በቃል ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን፣ ካህናት ሊቃነ ካህናት አንዳንድ ጊዜ “ሳምራዊ ነው”፤ አንዳንድ ጊዜ “ጋኔን አለበት”፤ በሌላ ጊዜም “አሳች ነው” እያሉ ድንጋይ ይወረውሩበት ነበር፡፡ አንዳንዴ ይዘው ያመጡት ዘንድ አገልጋዮቻቸውን ይልኩበታል፤ በሌላ ጊዜም በኅቡዕ ይሰልሉትና አደጋ ይጥሉበት ዘንድ ሰላዮችን ይልኩበታል፡፡ እነርሱም ራሳቸው ያለመሰልቸትና ያለማቋረጥ ይሰድቡት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢኾንም ግን ጌታ ደግ ነገር ማድረግን አላቋረጠባቸውም፡፡ እንደተናገርን በቃል ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ ለምሳሌ ከሎሌዎች አንዱ በጥፊ ሲመታው “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ስለ ምን ትመታኛለህ?” ብሎ የመለሰለት ይህን የሚያስረግጥ ነው /ዮሐ.18፡23/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! “ስለምን ትመታኛለህ?” እያለ ያለው ለገዛ ጠላቶቹና ይገድሉት ዘንድ ለተሰበሰቡ መኾኑን ታስተውላላችሁን?
 እስኪ አሁን ደግሞ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይ ደግሞ አሳልፎ ለሚሰጠው ለይሁዳ ምን እንዳደረገለት እንመልከት፡፡ ከአፍአ ስንመለከተው ይህ ሰው (ይሁዳ) ከጌታ ደቀ መዛሙርት ይልቅ አብልጦ ለመጠላት ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ደቀ መዛሙር ሲኾን፣ አብሮ ማዕዱን ተካፍሎ፣ ጌታ ያደረጋቸውን ገቢረ ተአምራት ተመልክቶ፣ ለሐዋርያነት መዓርግ ተመርጦ ሳለ ከማንም ሰው በላይ ክፋትን ተሞልቷልና፡፡ ክፋቱንም የገለጠው ድንጋይ በመወርወር አልያም በመሳደብ አልነበረም፤ ይሞት ዘንድ አሳልፎ በመስጠት እንጂ፡፡ ጌታችን ደግሞ ምን ያህል እንዳፈቀረው አስተውሉ፡፡ ከላይ ከገለጥናቸው በተጨማሪ እግሩን አጠበው፡፡ ይኽንንም የሚያደርግለት ከክፋቱ ተመልሶ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው ወድዶ ነው፡፡ ፍሬ እንዳላገኘባት በለስ ማድረቅ፣ እንደ ድንጋይ ለሁለት መሰንጠቅ፣ እንደ እላቂ ጨርቅም ቆራርጦ ይጥለው ዘንድ በተቻለው ነበር፤ ይሁዳን፡፡ ሰው አፍቃሪው ጌታ ግን፥ ይሁዳ በምርጫው ከገባበት ግብረ እከይ በኀይል ያወጣው ዘንድ አልወደደም፤ ጐንበስ ብሎ፣ ተንበርክኮ እግሩን በማጠብ ወደ ዕቅፉ ይጠራው ነበር እንጂ፡፡ ሐፍረት ቢሱ ይሁዳ ግን በዚህም አልተመለሰም /St. John Chrysostom, Homily LXX/፡፡   
 “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ፋሲካ አስቀድሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አወቀ” /ቁ.1/፡፡ አወቀ ሲባልም ከዚህ በፊት የማያውቀውን ነገር ድንገት አሁን አወቀ ማለት አይደለም፤ ከጥንት አንሥቶ የሚያውቀውንና በመለኮታዊ ዕቀዱ ውስጥ የነበረውን የሰው ልጆችን የሚያድንበት አሁን በሰዓቱ አደረገው ማለት ነው እንጂ፡፡ “በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹንም እስከ መጨረሻ (ፈጽሞ) ወደዳቸው፤ እሰቀልላችኋለሁ አላቸው፤ ልጅነትን እሰጣችኋለሁ አላቸው፡፡” ተወዳጆች ሆይ! እንግዲህ በአካለ ሥጋ ከእነርሱ ተለይቶ የሚሔድበት ሰዓት እየቀረበ በሔደ ቊጥር ጌታ፥ ፍቅሩ እንደምን እየጨመረ እንደሔደ ታስተውላላችሁን?
 “እስከ መጨረሻ (ፈጽሞ) ወደዳቸው” ሲልም መጠንና ልክ የሌለው መውደድ፤ ደግሞም በዚህ ጊዜ ይቆማል ወይም ይቀንሳል ተብሎ የማይታሰብ መውደድን ወደዳቸው ሲል ነው፡፡ ከእናንተ መካከል “ይህን ለምን ከመጀመርያ አንሥቶ አላደረገውም?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ሲል ይመልስለታል፡- “በርግጥ ገና በክበበ ትስብእት ተገልጦ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ታላላቅ ነገሮችን አድርጓጐላቸዋል፡፡ ነገር ግን የፍቅር ጣርያ አድርጐ ራሱን የሰጠላቸው ግን አሁን በመጨረሻ ነው፡፡ ይኸውም ከፈጣሪያቸው (ከእርሱ ከራሱ) ጋር ያላቸውን አንድነት ይበልጥ ይጠነክር ዘንድ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ አሁን በአካለ ሥጋ ተለይቷቸው ስለሚሔድና እነርሱም ስለ ወንጌል ብለው ከዐላውያን ነገሥታት እጅግ ብዙ መከራን ስለሚቀበሉ፥ በተጋድሎአቸው መኻል ፍጹም ሊፈሩና ሊጠራጠሩ እንደማይገባ ሊያስረዳቸው ፈልጎ ነው” /ዕብ፣12፡2፣ Ibid/፡፡
 አሁንም ከእናንተ መካከል “በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን… ሲልስ ምን ማለቱ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- እንደ ሊቃውንቱ አተረጓጐም ይህ ኹለት ዓይነት ትርጉም አለው፡፡ ይኸውም፡-
፩ኛ) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በዚህ ዓለም የሌሉት ይልቁንም በእደ እግዚአብሔር በሲዖል ውስጥ ያሉትን እነ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ሌሎችም ቅዱሳን ሲያመለክት ነው” ብሎ ይተረጕሟል፡፡ “በዚህም በምሥጢራዊ መንገድ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላከ ብሉይ ወሐዲስ መኾኑን እየተናገረ ነበር ማለት ነው” ብሎም ይጨምራል /Ibid/፡፡
፪ኛ) ቅዱስ ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ ደግሞ “ይህ አነጋገር በጠቅላላ ደቂቀ አዳምን የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም ወገኖቹ የሚኾኑ ሌሎች ሰማያውያን ኃይላት፣ ሊቃናት፣ ሥልጣናት እና ሌሎች ቅዱሳን መላእክት አሉትና፡፡ ብፁዕ ጳውሎስ እንደተናገረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ የመላእክትን ባሕርይ ገንዘብ አላደረገም /ዕብ.2፡16/፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር ያለውን መተካከል እንደ መቀማት ሳይቈጥረው አርአያ ገብርንም የነሣው ለመላእክት አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ለምንኖር ለእኛ (ለደቂቀ አዳም) ነው እንጂ” በማለት ይተረጕሟል /Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel of John, Book IX/፡፡
 እራትም ሲበሉ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ ዲያብሎስ የአስቆሮት ሰው በሚኾን በስምዖን ልጅ በይሁዳ አደረበት /ቁ.2/፡፡ “ተለይቶት ያውቃልን?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ አይደለም፤ እንደ ባለቤት ኹኖ ገብቶ ሥራ አሠራው ለማለት ነው እንጂ /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 522/፡፡ ዲያብሎስ የይሁዳን ልብ ሲጠቀም የወልደ እግዚአብሔርን ፍቅር ያጨናገፈ መስሎት ነበር፤ ብርሃን ክርስቶስን አጥፍቶ ዓለሙን በጨለማ አገዛዙ የሚያቆይ መስሎት ነበር፡፡ የጥበብ ምንጭ እግዚአብሔር ግን የዲያብሎስን ክፋት ለእኛ ጥቅም አደረገው፡፡
  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ አብ ኹሉን በእጁ ጭብጥ በእግሩ እርግጥ አድርጎ እንደ ሰጠው፥ ከእግዚአብሔር እንደ መጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሔድ አውቆ ከእራት ተነሣ /ቁ.3-4/፡፡ ወንጌላዊው ይህን ኹሉ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ወንጌላዊው ይህን ኹሉ የሚለው ታላቅ መደነቅ ይዞት ነው፡፡ አዎ! ታላቅ መደነቅ! ታላቅ መገረም! ለምን? ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ ምንም ልዑለ ባሕርይ ቢኾንም፣ ምንም ከባሕርይ አባቱ አንድነት ሳይለይ ለድኅነተ ዓለም ብሎ ዝቅ ብሎ የመጣ ደግሞም ዳግም ወደርሱ የሚሔድ ቢኾንም፣ የፍጥረተ ሰማይ ወምድር ገዢ እርሱ ብቻ ቢኾንም፣ ምንም ኪሩቤልና ሱራፌል ያለማቋረጥ ተንበርክከው ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት አምላክ ቢኾንም፥ ራሱን ዝቅ አድርጐ እንደ ባርያም ኾኖ አደግድጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ነውና፥ ወንጌላዊው መደነቅ ያዘው!
 ተወዳጆች ሆይ! አንድ ነገርን ልብ እንል ዘንድ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድም በጠቀስነው ድርሳኑ ላይ ይመክረናል፡፡ ምንድነው እርሱ? “አብ ሰጠው ሲባል እንዲሁ ሰዋዊ የኾነ ዓይነት መስጠትንና መቀበልን ልናስብ አይገባንም፡፡ አብ ሰጠው ሲባል የባሕርይ ዕሩይነታቸውን (ትክክል መኾናቸውን) መናገር ነውና፡፡ እንዲያስ ባይኾን ማለትም አብ ሰጠው ስለተባለ ብቻ ወልድ ከአብ ያንሣል ካልንስ፤ ወልድም ሰጥቶታልና አብ ከወልድ ያንሣል ያሰኝብናል /1ኛ ቆሮ.15፡24/፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይደለም፤ እንደተናገርኩ ዕሩይነታቸውን (መተካከላቸውን) መናገር ነው እንጂ፡፡”
  እራት ለመብላት ከተቀመጡ በኋላ ጌታችን ልብሱን አኑሮ ተነሣ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፡፡ ቀጥሎም በመታጠቢያው (በኵስኵስት) ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግርያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ እያበሰ ያደርቅ ጀመረ /ቁ.5/። ተወዳጆች ሆይ! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትሕትናውን የገለጠው እንደምን እንደኾነ አስተውሉ፡፡ ጌታችን የተነሣው ኹሉም ከተቀመጡ በኋላ ነው፡፡ ቀጥሎም ዝም ብሎ ውኃዉን ቀድቶ አላጠባቸውም፡፡ መጀመርያ ልብሱን አኖረ፡፡ በዚህም አላቆመም፤ አደገደገ እንጂ፡፡ አሁንም በዚህ አልረካም፤ ኵስኵስቱን እርሱ ራሱ በውኃ ሞላው እንጂ፡፡ ሌላ ሰው ይሞላው ዘንድ አላዘዘም፤ እርሱ ራሱ ሞላው እንጂ፡፡ ይህን ኹሉ የሚያደርገው ለምንድነው? እንዲህ ያለ ነገርን ለወንድሞቻችን ስናደርግ ለይስሙላ ሳይኾን በፍጹም ትጋት ልናደርገው እንደሚገባን ሲያስተምረን፡፡ በአይሁድ ባህል እጅ የሚያስታጥበው ወይም እግር የሚያጥበው ባርያ ተብሎ የሚታሰበው ሰው ነው፡፡ ባርያ ከሌለ በዕድሜ ወይም በክብር ትንሽ ነው ተብሎ የሚታሰበው ሰው ያስታጥባል (ያጥባል)፡፡ በምሴተ ሐሙስ ግን ጌታችን ይህን አደረገ፡፡ ለባሮች ካሣ እየከፈለ ነበር ማለት ነው፡፡ ዓምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ፡- “ምንም እንኳን የባሕርይ አምላክ ቢኾንም ያለ ልክ ዝቅ ዝቅ አለ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር እስከ ማጠብ ደረሰ፡፡ ለምን? እርስ በርሳችን እንዲህ እንዋደድ ዘንድ፤ የፍቅራችን አርአያ (ሞዴል) እርሱን እናደርግ ዘንድ፡፡ ፍቁራን ሆይ! እንኪያስ የትዕቢት ልቡናን ትተን ትሑታን እንኹን፡፡ ምንም ያህል ባለጸጐች ብንኾንም በዚህ ፈጽመን ልንታበይ አይገባንም” ይላል /Book IX/፡፡
  ከዚህ በኋላ አስቀድሞ የይሁዳን እግር አጠበ፡፡ ለምን? የጌታን ፍቅር ተመልክቶ ንስሐ ይገባ ዘንድ /ሕዝ.18፡23/፡፡ ቀጥሎምስምዖን ጴጥሮስ ዘንድ ደረሰ፡፡ ኾኖም ግን ጴጥሮስ፡-ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” ይለው ጀመር /ቁ.6/። ጴጥሮስ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ጌታ ሆይ! በእነዚህ ብሩካን እጆችህ የዕዉራንን ዐይን አበራህ፤ ለምጻሞችን አነጻሕ፤ ሙታንን አነሣህ፡፡ ታዲያ ቆሻሻ እግሬን ትነካ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” ጌታስ ምን አለው? እኔ ዛሬ የምሠራውን አንተ አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ (ታውቀዋለህ)” /ቁ.7/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ጴጥሮስ ሆይ! ከዚህ የሚገኘው ረብሕ (ጥቅም) ምን ያህል ታላቅ እንደኾነ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ሰውን ኹሉ ወደ ትሕትና የሚመራው ይህ ትምህርት እንደኾነ ታስታውሰዋለህ፡፡” ጴጥሮስ ግን አሁንም ከለከለው፤ እንዲህም ይለው ነበር፡- “አቤቱ አንተ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም።” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲህ ሲል ይጠይቋል፡- “ጴጥሮስ ሆይ! ምን እያልክ ነው? ጌታህ ከዚህ በፊት ምን እንዳለህ አታስተውስምን? ‘አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም’ ባልከው ጊዜ፡- ‘ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል’ ብሎ የነገረህን ዘነጋኸውን?” /ማቴ.16፡22-23፣ St. John Chrysostom, Homily LXX/፡፡
 ሐዋርያው ጴጥሮስ በፊልጶስ ቂሳርያ “አይሁንብህ” ብሎ የተናገረው ለጌታ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ አሁንም በዚህ ቦታ “አታጥበኝም” የሚለው ያው ለጌታ ካለው ፍቅርና አክብሮት የተነሣ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጴጥሮስ በሚበልጥ ፍቅር ፡- “እኔ ካላጠብኩህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ (አንድነት) የለህም ብዬ በእውነት እነግርሃለሁ” በማለት የሚመልስለት /ቁ.8/። አቤት! ጴጥሮስ ከፍቅሩ የተነሣ አልታጠብም ብሎ ከጌታ ጋር ዕድል ፋንታ (ጣዕመ መንግሥተ ሰማያት) እንደሌለው ከተነገረው፥ ኹለንተናችን በትዕቢት የተያዝን እኛ ዕድል ፈንታችን ጽዋ ተርታችን እንደምን ይኾን?  
 ጴጥሮስስ ምን አለ?ጌታ ሆይ፥ ከአንተ ጋራ ዕድል ፋንታ ከሌለኝስ እግሬን ብቻ አታጽበኝም፤ እጄንም እራሴንም ነው እንጂ” /ቁ.9/። ከእናንተ መካከል “ጴጥሮስ እንዲህ ለጌታችን ካለው ፍቅር የተነሣ አልታጠብም ካለ፥ ጌታችን እንዲህ የሚያስፈራራ ቃላትን የሚነግረው ስለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ጌታ እንዲህ ከአፍአ ሲታይ የሚያስፈራራ የሚመስል ነገር ግን ያይደለ ቃል ባይናገረው ኖሮ ጴጥሮስ አይሆንም ብሎ በእንቢታው በጸና ነበር፡፡ ጌታችን እንዲህ ጠንከር አድርጎ መናገሩ ግን፡- “አንተ ጴጥሮስ! ይህንን የምልህ ትሑት እንድትኾን ነውና እሺ በል፡፡ ደግሞም እኔ አንተን በማገልገሌ ከክብሬ ዝቅ እንደምል አድርገህ አታስብ” ማለቱ ነበር፡፡
  “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ሲለውስ ምን ለማለት ነው? ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይመልስለታል፡- “አጋንንትን በስሜ ስታወጣ፤ በርቀ’ት ሳይኾን በርሕቀት ወደ ሰማያት እያረግሁ ስታየኝ፤ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ የነገርኩህን ሲያስታውስህ፤ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ በአብ ቀኝ (ዕሪና) እንደተቀመጥኩ ሲነግርህ፤ የዚያን ጊዜ አሁን የነገርኩህን ያስታውስሃል፡፡ አንተም ታስታውሳለህ፤ ታውቀዋለህ” /Ibid/፡፡ አንድም ደግሞ “በኋላ ማለትም እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስኾን እግራችሁን ካጠብኳችሁ፥ እናንተም የወንድማችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። አብነት ኹኛችኋለሁና እናንተም እኔ እንዳደረግሁላችሁ ታደርጉ ዘንድ ይገባል ብዬ ስነግርህ ይገባሃል” ማለቱ ነው /ቁ.13-15/፡፡
   ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፥ ከአንተ ጋራ ዕድል ፋንታ ከሌለኝስ እግሬን ብቻ አታጽበኝም፤ እጄንም እራሴንም ነው እንጂ” ካለ በኋላስ ጌታ ምን ብሎ መለሰለት? “ፈጽሞ ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ነው እንጂ ሌላውን አካሉን ሊታጠብ አይሻም ሌላው አካሉ ንጹሕ ነውና፤ እናንተ ግን ንጹሐን ናችሁ፡፡ ነገር ግን ንጹሐን ናችሁ ማለቴ ለሁላችሁ አይደለም” /ቁ.10/። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሁላችሁም ንጹሐን አይደላችሁም” ማለቱ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳ እንደኾነ ያውቅ ስለ ነበር ነው /ቁ.11/። አስተሳሰቡ ኹሉ ንጹሕ አይደለምና እንዲህ አለው፡፡
 ወደ ክፋት ዐዘቅት መስመጥ እጅግ አደገኛ ነው፤ እንዲህ የወደቀ ሰውን እንደገና ማደስ አስቸጋሪ ነውና፡፡ እንኪያስ ወገኖቼ! ወድቆ ከመነሣት ይልቅ አስቀድሞ ከመውደቅ መጠንቀቅ ይቀላልና እንዳንወድቅ የተቻለንን ያህል ልንጣጣር ያስፈልጋል፡፡ ይሁዳን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ኃጢአት ከወደቀ በኋላ ምንም እንኳን እጅግ ብዙ ርዳታ ቢደረግለትም ፍጹም መነሣት አልተቻለውም፡፡ ክርስቶስ “ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” ብሎታል /ዮሐ.6፡71/፤ ዳግመኛም “ከእናንተ የማያምኑ አሉ” /ዮሐ.6፡64/፤ “ስለ ሁላችሁ አልናገርም”፤ “እኔ የመርጥኳቸውን አውቃለሁ” /ዮሐ.13፡18/ ቢለውም ፍጹም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እንደተናገርን አንድ ጊዜ ወደ ክፋት ዐዘቅት መስመጥ እጅግ አደገኛ ነውና፡፡
 ከእናንተ መካከል “ደቀ መዛሙርቱ ንጹሐን ከነበሩ ታድያ ስለምን አጠባቸው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ትሕትናን እንማር ዘንድ፡፡ ለዚህም ነው’ኮ ጌታ ሌላውን የሰውነታቸውን ክፍል ትቶ ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች አንጻር ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚታሰበውን (እግር) ዝቅ ብሎ ያጠበው /1ኛሳሙ.25፡41/፡፡ የታጠበ ሲልስ ምን ማለቱ ነው? ንጹሕ የኾነ፡፡ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ባልተሻረበት ኹናቴ፣ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም ቅዱስ ሥጋዉን እስካልቈረሰ ቅዱስ ደሙንም እስካላፈሰሰ ድረስ፣ የዕዳ ደብዳቤ ባልተቀደደበት ኹናቴ “ንጹሐን ናችሁ” ሲላቸው ምን ለማለት ፈልጐ ነው? ጌታችን እየተናገረ ያለው በዚህ መልኩ አይደለም፡፡ እንዲህ እንዳልሆነ ለማመልከትም፡- “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤” ሲል ጨምሯል /ዮሐ.15፡3/፡፡ ከዋለበት ይውላሉ፤ ካደረበት ያድራሉ፤ ብዙ ነገርን ትተው ተከትለውታል፤ ንጹሕ እምነት ነበራቸው፤ ጌታን እጅግ ይወዱታል፡፡ ከጨለማ (ከድንቁርና) ወደ ብርሃን (ዕውቀት) ተሻግረዋል፤ ከአይሁድ ስሕተት ወጥተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ደቀ መዛሙርቱ ንጹሐን ናቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥” ብሎ የተናገረውም ይህን የመሰለ ነው /ኢሳ.1፡16/፡፡ እንዲህ ከክፋቱ የታጠበ ሰው ንጹሕ ነውና ጌታ ደቀ መዛሙርቱን “ንጹሐን ናችሁ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ክፋትን ኹሉ ከሰውነታቸው ስላራቁ፥ በንጹሕም ሕሊና ስለ ተከተሉት፥ እንደ ነቢዩ ቃል “የታጠበ … ሁለንተናው ንጹሕ ነው” ተባሉ፡፡ ይሁዳ ግን ነቢዩ እንደተናገረው በአይሁዳውያን እንደሚደረገው የውኃ “መታጠብ” ሥርዓት ሳይኾን ክፋትን ከሕሊናው ያላጠበ ነበር፤ ውስጡ በዲያብሎስ ሐሳብ የተመረዘ ነበር፤ ንጹሕ አልነበረም፡፡

 እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ኹለተኛ ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ /ቁ.12/፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው በዚህ ሰዓት መታጠቂያውን ለዮሐንስ ወንጌላዊ ሰጥቶታል፡፡ ዮሐንስም ጌታ በታጠቀበት ቢታጠቅ ሕገ ሥጋ ጠፍቶለታል /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 523/፡፡
 ኹለተኛ ከእነርሱ ጋር ከተቀመጠ በኋላ ጌታችን እንዲህ አላቸው፡-ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህራችንና ጌታችን ትሉኛላችሁ፤ መምህራችሁ ጌታችሁም ነኝና ትክክል ናችሁ እንኪያስ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስኾን እግራችሁን ካጠብኳችሁ፥ እናንተም የወንድማችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። አብነት ኹኛችኋለሁና እናንተም እኔ እንዳደረግሁላችሁ ታደርጉ ዘንድ ይገባል” /ቁ.13-15/፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ይህንን አስመልክተው፡- “ኢትትሐከይ ኀፂበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትሐሠሦሙ ለእለ ያፀርእዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳት እስመ እግዚአብሔር ሐፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ አዘዞሙ ይግበሩ ከማሁ - ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፥ ይህችን ሥራ ቸል የሚልዋትን ስለዚህ ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና፤ ምንም ኤጲስ ቆጶሳትም እንኳ ቢኾኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና” ብለው አስተምረዋል /ሃይ.አበ.20፡29/፡፡ ዳግመኛም የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ልዑለ ባሕርይ የሚኾን ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ፣ ከዚህ በላይ ደግሞ የይሁዳን እግር፥ የሌባውን እግር፥ ከክፋቱ መፈወስ የማይችለውን ሰው ካጠበ፥ ከማዕዱ እንዲካፈል ካደረገ እኛማ እንዴት? እኛማ እንዴት ይህን ከማድረግ እንከለከላለን? የሠራተኞቻችንን እግር ብናጥብ ምንድነው ክፋቱ? የአሠሪና የሠራተኛ ልዩነት የቃላት ልዩነት ብቻ አይደለምን? እኛስ ሁላችን ዕሩቅ ብእሲዎች ነን፡፡ እርሱ ግን የባሕርይ አምላክ ነው፤ ኾኖም የባሮቹን እግር ዝቅ ብሎ ከማጠብ ምንም አልተጠየፈም፡፡ ለዚህም ነው ‘እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስኾን እግራችሁን ካጠብኳችሁ፥ እናንተም የወንድማችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል’ ያለን፡፡ … ጌታችን እንዲህ ራሱ አድርጐ ካሳየን በኋላ እኛ አናደርግም ብንል በዚያች ቀን የምንመልሰው መልስ ምን ይኾን? … ይህን ከማድረግ ተከልክለን በትዕቢት የምንያዘውስ እኛ ምንድነን? እንደምን ያለ ስንፍናስ ቢይዘን ነው? ሰው ሆይ! በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው እርሱ ዝቅ ብሎ የይሁዳን እግር ካጠበ፥ አፈርና ትቢያ የምትኾን አንተ ራስክን ከፍ ከፍ ታደርጋለህን? ለዚህ ትዕቢትህስ እንደምን ያለ ፍዳ ይጠብቅህ ይኾን? ወዳጄ ሆይ! ከፍ ከፍ ማለትን ትወዳለህን? እንኪያስ ና! እንዴት ከፍ ከፍ እንደምትልም አሳይሃለሁ፡፡ እንደ ጌታህና እንደ መምህርህ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ራስህን ዝቅ አድርግ፤ የዚያን ጊዜም ከፍ ከፍ ትላለህ” በማለት በተለይ በአሁኑ ዘመን የያዘንን ትዕቢት በወርቃማው ስብከቱ ይንደዋል /St. John Chrysostom, Homily LXXI/፡፡    
 ጌታችን ንግግሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ፡- “አማን አማን እብልክሙ አልቦ ገብር ዘየዓቢ እምእግዚኡ ወአልቦ ሐዋርያ ዘየዓቢ እምዘፈነዎ - እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከጌታው የሚበልጥ ባሪያ፥ ከላኪውም የሚበልጥ መልእክተኛ የለም።” ጌታ ሆይ! ይህን እኮ እናውቀዋለን፡፡ የምናውቀውን ነገር የምትነግረን ለምንድነው? “ማወቅስ ታውቁታላችሁ፡፡ ነገር ግን ንዑዳን ክቡራን የሚያሰኛችሁ አውቃችሁ ብትሠሩት እንጂ ማወቃችሁ ብቻ አይደለም። የጌታውን ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባርያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል /ሉቃ.12፡47-48/፡፡ አይሁዳውያን ከእናንተ በላይ ቃለ እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ ነገር ግን አያደርጉቱምና ንዑዳን ክቡራን አይደሉም /ቁ.16-17/፡፡
 ጌታችን “እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከጌታው የሚበልጥ ባሪያ፥ ከላኪውም የሚበልጥ መልእክተኛ የለም” ብሎ ሲናገር ደቀ መዛሙርቱን ከራሱ ጋር እያነጻጸረ ሲያስተምራቸው ነው፡፡ አንድ ምድራዊ ንጉሥ ባሮቹን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙታል፡፡ አልታዘዝም ቢሉ ምን እንደሚጠብቃቸው ግልጽ ነው፡፡ እኛም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከኾንን ልንታዘዘው ይገባል፤ ፈርተን ሳይኾን ወድደን፡፡ ሰው ወይም መልአክ ሳይኾን እርሱ ራሱ ዝቅ ብሎ አስተምሮን ሳለ፥ ዝቅ የማይል ወይም ለማለት የማይፈቅድ ልቡና ካለን ግን፥ “እኛ ከአንተ እንበልጣለን” እንደማለት ይቈጠርብናል፡፡
  ጌታ አሁንም ይቀጥላል፤ እንዲህ በማለት፡- “ይህን የምናገር ስለ ሁላችሁ አይደለም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁና” /ቁ.18/፡፡ ይሁዳ ቃሉን ያውቋል፤ አውቆ ስለማይሠራው ግን እንደሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ንዑድ፤ ክቡር” አልተባለም፡፡ ይኸውም መጽሐፍ፡-እንጀራዬን የሚመገብ አንድም እህል ትምህርቴን የሚበላ ይሁዳ በእኔ ላይ ሰኰናውን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው” /መዝ.40፡9/።
 ከእናንተ መካከል፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ይሁዳ ሰኰናውን እንደሚያነሣበት ማለትም አሳልፎ እንደሚሰጠው እያወቀ ስለምን ለሐዋርያነት መረጠው? ሌባ እንደኾነ እያወቀስ ስለምን ገንዘብ ያዥ አደረገው? አስቀድሞ ነቢዩ ዳዊት ስለ ይሁዳ ይህን የመሰለ ትንቢት ከተናገረስ ይሁዳ ተጠያቂ የሚኾነው ስለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ያለ መንፈስ ቅዱስ ርዳታ፣ ያለ ሊቃውንት ትርጓሜ እንዲሁ መረዳት አይቻልም የምትለው ዝም ብላ አይደለም፡፡ ይህን ለመሰሉ ጥያቄዎች ለመረዳት ረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ መሰል ትችት የሚያነሣ ሰውም ርዳታ ካልተደረገለት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በእያንዳንዷ ገቢረ እግዚአብሔር ጥያቄ አዘል ትችት ያነሣል እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅርም በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ይጀምራል፡፡ እንዲህ ርዳታ ያልተደረገለት ሰው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሣቱ አይቀርም፡- “እግዚአብሔር ሆይ! ለአንተ የማይገዛ ኾኖ ሳለ ሳኦልን በእሥራኤል ንጉሥ አድርገህ የሾምከው ስለምንድነው? አንተ ኹሉንም ነገር የምታውቅ ከኾነ ሰውን ከምድር አፈር ስለምን ፈጠርከው? አንተ ማእምረ ኅቡአት ከኾንክ አዳምና ልጆቹ እንደሚበድልና ትእዛዝህን እንደሚያፈርስ እያወቅክ ስለምን ፈጠርከው? ምን ይኼ ብቻ፤ ሳጥናኤልስ ቢኾን እንደሚስት እያወቅክ ስለምን ካለ መኖር ወደ መኖር አመጣኸው?” እያለ ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው መልሱን በራሱ አረዳድ ለመመለስ የሚሞክር ከኾነ አንዳች ረብሕ አያገኝም፤ እንደውም እጅጉን ይጐዳል እንጂ፡፡ የሚጠይቀው በቀና ልቡና ከኾነ ግን እንደተናገርን የመንፈስ ቅዱስ ርዳታ ያስፈልጓል፤ ይህ ለምን እንደኾነ መምህራንን መጠየቅ ይገባዋል፡፡ አሁን ወደ ምላሹ እንመለስ! የእግዚአብሔር አስቀድሞ ኹሉን የማወቅ ባሕርዩ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ከመፍጠር አይከለክለውም (አልከለከለውም)፡፡ እግዚአብሔር ሰውንና መላእክትን ሲፈጥራቸው ከነጻ ፈቃዳቸው ጋር አብሮ ነው፡፡ በመኾኑም እነዚህ ፍጥረታት ወደ መረጡት መሔድ ይችላሉ፡፡ መልካሙን የመረጡ ወደ ሕይወት መንገድ ይሔዳሉ፡፡ ማንም የማይቀማቸውንም ሰላም ያገኛሉ፡፡ በራሳቸው ፈቃድ የክፋትን መንገድ የመረጡትም ወደ ጥፋት ይሔዳሉ፡፡ ነገር ግን በምርጫቸው ነውና ለጥፋታቸው ደመወዛቸውን ይቀበላሉ፡፡ በዓለመ መላእክት ጥርጣሬ ሲገባ “ንቁም በበህላዌነ - በያለንበት እንቁም” ያሉት እነ ቅዱስ ገብርኤል ነጻ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው እንጂ ማንም አስገድዷቸው አልነበረም፡፡ ከሰማይ ስፍራ ያልተገኘላቸው ሠራዊተ መላእክትም ወደ ጥልቁና ወደ ጨለማው የወረዱት አስፈሪውንም የፍርድ ቀን የሚጠብቁት በራሳቸው ምርጫ ነው፡፡ የመጀመርያው ሰው አዳምም ጥንቱን ለሞት የተፈጠረ አልነበረም /ጥበብ.1፡13/፡፡ ገና እንደተፈጠረ በ40ኛው ቀኑ ወደ ገነት ገባ፤ በታላቅ ሐሴትም ይኖር ነበር፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ክብር እያየ ይኖር ነበር፡፡ በራሱ ምርጫና ፈቃድ ባይስት ኖሮም እንዲህ በደስታ ይቀጥል ነበር፡፡ ሳኦልም በእሥራኤል ከመንገሡ በፊት መልካም ሰው ነበር፤ የተቀየረውና በራሱ ፈቃድ ክፉ የሆነው ወደ ዙፋኑ ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይሁዳን ለሐዋርያነት የመረጠው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ይሁዳ የዲያብሎሰን ተንኮል ድል ማድረግ አልቻለም፡፡ ሰይጣን ስግብግብነትን ወደ ልቡ ሲያስገባበት አሜን ብሎ ተቀበለው፡፡ አምላኩን አሳልፎ ለመስጠት ሐሳብን ወደ ልቡ ሲያስገባ አሜን ብሎ ተቀበለው፡፡ ስለዚህ ችግሩ፥ ለሐዋርያነት የመረጠው ጌታችን ሳይኾን፥ የራሱ የይሁዳ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ሕይወቱን ማዳን ይችል ነበር፡፡ ንስሐ ከመግባት ይልቅ ራሱን የገደለው በራሱ ምርጫ ነው፡፡ ነቢያቱም ቢኾኑ ስለ ይሁዳና ስለሌሎች ሰዎች አስቀድመው ትንቢት የተናገሩት እንዲሁ እንዳልኾነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያስ ከኾነ መጽሐፍ ቅዱስ የኀጢአት አገልጋይ ይኾንብናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በነቢያቱ አፍ ያናገረውና ያስጻፈው ሰዎቹ በራሳቸው ፈቃድና ምርጫ የሚመርጡትን መንገድ አስቀድሞ ስለሚያውቅ እንጂ ሰዎቹን ለዚያ ስለወሰናቸው አይደለም፡፡
…ተመስጦ…

 ወዮ አባት ሆይ! ፍቅርህ እንዴት ግሩም ነው? እኛን ያለ ልክ ከፍ ከፍ ታደርግ ዘንድ፣ ኃጢአታችንን በሥጋ ትኰንን ዘንድ ያለ ልክ ዝቅ ብለህ መጥተሃልና መውደድህ እንደምን ጥልቅ ነው? እኛን ላለማዳን ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አንተ ግን አፍቃሪ አባት፥ ምሕረት ማድረግ ባሕርይህ ነውና እስከ መጨረሻወደድከን፡፡ ያለ ልክ አፈቀርከን፡፡ ክብርህን እንደ መቀማት ሳትቈጥረው አርአያ ገብርን ነስተህ መጣኽልን፡፡ ኪሩቤል ሱራፌል ያለማቋረጥ ተንበርክከው ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑህ ልዑለ ባሕርይ ኾነህ ሳለ ራስክን ዝቅ አድርገህ እንደ ባርያም ኾነህ ጐበኘኸን፡፡ ኹለንተናችን የተዳደፈ እኛን ትወለውለን ዘንድ፥ የባርነታችን ደብዳቤ ትቀድልን ዘንድ የባርያን መልክ ይዘህ ጐበኘኸን፡፡ ጌታ ሆይ! ይህን ሁሉ ታደርግልን ዘንድ እኛ ማን ነን? ለዚህ የምንከፍለው ውለታስ ምን አለን? ቅዱስ ሆይ! ዛሬም ቢሆን እንዲያ ካነጻኸን በኋላ እንደ ይሁዳ የስግብግብነት አረም የተዘራብን ብዙዎች ነን፡፡ እንደ ይሁዳ ለታላቅ ማዕረግ መርጠኸን ሳለ እምነት የጐደለንና ሌቦች የሆንን ብዙዎች ነን፡፡ ስለ ገንዘብ ብለን አንተን የሸጥንህ ብዙዎች ነን፡፡ ኹለንተናችን በትዕቢት የተመላ ብዙዎች ነን፡፡ ተመልሰን ወደ ክፋት ዐዘቅት የወደቅን ብዙዎች ነን፡፡ አንተ ግን ከኃጢአታችን ጋር ተስማምተህ ሳይሆን እንመለስ ዘንድ እንደ ይሁዳ ስማችንን ደብቀኸዋል፡፡ አባት ሆይ! በፍዳ ከመመርመራችን በፊት ፍቅርህ እንዲገባን እርዳን፡፡ የቆሸሸው ኹለንተናችን በቅዱስ ደምህ እንታጠብ ዘንድ ርዳን፡፡ እንደ ነቢዩም ቃል የሥራችንን ክፋት ከዓይንህ ፊት አስወግደን፤ ክፉ ማድረግንም ትተን ወደ አንተ እንመለስ ዘንድ ርዳን፡፡ አሜን!!!

1 comment:

  1. my dear brother ገብረ እግዚ ለምን መጽሃፉን ለማህበረ ቅዱሳን አቅርበህ እንዲያሳትሙልህ አታረግም ...ይሄ ትምህርት በመጽሃፍ መልክ ለሁሉ እንዲደርስ ካለኝ ጉጉት ነው!

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount