Friday, September 13, 2013

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር - ክፍል 3 (የመጨረሻው ክፍል)



ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም 3 ቀን፥ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
 በዚህ ክፍል በአንዳንድ ምእመናን የሚጠየቁትን አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
 ጥያቄ አንድ፡ - የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ከአውሮፓውያን የዘመን አቈጣጠር ስለምን 7 ወይም 8 ዓመት ወደኋላ ይዘገያል?

ምላሽ፡- የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንቱ እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያና የአውሮፓ የዘመን አቈጣጠር የ7 ወይም የ8 ዓመት ልዩነት የለውም፡፡ ልዩነቱ ያለው የአውሮፓ ሐሳበ ዘመን ከጌታ ልደት ብቻ ዠምሮ ዘመኑን የሚቈጥር ስለሆነ አበቅቴ ወርኅ የሚገኝበትን 2013 ዓመተ ወርኅን ቈጥሮ ያስረዳል እንጂ አበቅቴ ፀሐይ የሚገኝበትን 2006 ዓመተ ፀሐይ ቈጥሮ አያስረዳም፡፡ ስለዚህ የ8 ዓመቱ ልዩነት በፀሐይና በጨረቃ የዘመን አቈጣጠር መካከል ያለ ልዩነት እንጂ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ሐሳበ ዘመን መካከል አይደለም /አቡሻኽር አንቀጽ 26፣ ባሕረ ሐሳብ በአለቃ ያሬድ ፈንታ ገጽ 71/፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አውሮፓውያን ራሳቸው የኢትዮጵያ የፀሐይና የጨረቃ አቈጣጠር ትክክል መሆኑን መናገር ጀምረዋል፡፡ ለዚህም አምና ማለትም 2005 ዓ.ም. ላይ በፈቃዳቸው ከመንበራቸው የወረዱት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፖፕ የነበሩት በነዲክት 16ኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ጥያቄ ሁለት፡ - የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ዓመትን የምትጀምረው እንደ አውሮፓውያኑ ጥር ላይ ሳይሆን መስከረም ላይ መሆኑ ስለምድነው?
ምላሽ፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐዲስ ዓመት ስለ ሦስት ምክንያት መስከረም ላይ ይዠምራል፡፡
ሀ. የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት) የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜን ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ይጀምራሉ፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ትክክል (እኩል) ነው፡፡ መስከረም አንድ ቀን የሚነበበው ስንክሳርም “የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርዕስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው” ይላል፡፡ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሊቃውንቱ፥ ዐዲስ ዓመት በመስከረም ወር እንዲጀምር አድርገዉታል፡፡
ለ. ቅዱስ መጽሐፍ ለእሥራኤል ዘሥጋ ሲናገር፡- “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ” ይላል /ዘጸ.12፡2/፡፡ በዚህ ወር በዓለ ፋሲካን ያከብራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዐዲስ ዓመትን የሚያከብሩት “በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” ተብሎ በተሰጣቸው የሮሽ ሖሻና (በዓለ መጥቅዕ) በዓላቸው ላይ ነው /ዘሌ.23፡24/፡፡ ለምን በዚህ ወር እንደሚያከብሩት ሲናገሩም “በዚህ ወር ኖኅ ከመርከብ የወጣበት ወር በመሆኑና የዐዲስ ዓመት መዠመርያ ተደርጎ መከበር በመዠመሩ ነው” የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም ይህን በቀጥታ ወስደው ዐዲስ ዓመት በመስከረም ወር እንዲዠምር አድርገዉታል፡፡ የኢትዮጵያ ልጃገረዶች በዚህ ዕለት አበባና ለምለም ሳር መያዛቸው ርግቢቱ ለኖኅ ካመጣችው ቄጤማ ጋር ተያያይዞ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ሐ. ጠቢቡ ሰሎሞን በምሥጢር የኵነኔ ዘመን፣ የፍዳ ዘመን ማለፉን በርሱም ፈንታ ዘመነ ሐዲስ መተካቱን ሲናገር፡- “እነሆ ክረምቱ አለፈ፤ ዝናቡም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥” ይላል /መኃ.2፡11-12/፡፡ ሊቃውንቱ ይህን ሲተረጕሙት “እነሆ 5500 ዘመን አልፏልና ዝናበ መከራም ወደ ዲያብሎስ ተመልሷልና ጽጌ ክርስቶስ ተገለጠ፡፡ ሥጋዉን ደሙን የምንቀበልበት ጊዜም ደረሰ፤ ዲያብሎስ የሚሻርበት ጊዜ ደረሰ” ይላሉ /አንድምታዉን ይመልከቱ/፡፡ ሊቃውንቱ ከዚሁ ቅዱስ ቃል መነሻ በማድረግ የክረምት ክፈለ ዘመን የብሉይ ኪዳንን ምሳሌ አድርገዉታል፡፡ መስከረም እንደ ስሙ የክረምት፣ የጭቃ፣ የጭጋግ ወራት ማለፉን ስለሚያስረዳ፤ ዓመተ ኵነኔ ዓመተ ፍዳ አስቸጋሪው ዘመንም በጽድቅ ፀሐይ በክርስቶስ ማለፉን ለማሰብ ዐዲስ ዓመት በዚህ ወር እንዲዠምር አድርገዉታል፡፡
ጥያቄ ሦስት፡- ዐዲስ ዓመት ዕንቍጣጣሽ መባሉ ከምን ጋር የተያያዘ ነው?
ምላሽ፡- ይህ ስያሜ ከንግሥተ ሳባ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት እንደ ሔደች የጠገብነው ታሪክ ነው፡፡ ንግሥቲቱ በሰሎሞን ቤተ መንግሥትና በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚገኙትን እጅግ በጣም የከበሩቃዎችን አስጎብኝቷት ሲያበቃእንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቍ እንዳበረከተላትና፤ ይህ ዕንቍም ከሌሎች ንዋያት ሁሉ የሚበልጥና ወደር የማይገኝለት በጨለማ የሚያበራ ከመሆኑም በላይ ብርሃኑም እስከ አራት ዓይነት እየለዋወጠ የሚያሳይ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጐብኘት ሔዳ ቀዳማዊ ምኒሊክን ፀንሳ መጥታለች፡፡ በወለደች ጊዜም ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ ብሎ ዕልል እያለ “አበባ ዕንቊ ጣጣሽ” እያለ ገጸ በረከት ለንግሥቲቱ አቀረበ፡፡ ከዚያን ጊዜ ዠምሮ ዕንቊ ጣጣሽ ተባለ፡፡ በጥያቄ ቍጥር ሁለት ከገለጽነው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ልጃ ገረዶች አበባን በሥጦታ መልኩ በዚሁ ወራት መስጠታቸው ከዚሁ ታሪክ ጋርም የተያያዘ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡  
ጥያቄ አራት፡- ዐዲስ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ መባሉ ስለምንድነው?
ምላሽ፡- መጥምቁ ዮሐንስ አንገቱ ተቀልቶ ሰማዕት የሆነው ስንክሳሩ እንደሚነግረን መስከረም 2 ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጥምቁ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ላይ የነበረ ከነቢያት የመጨረሻ፣ ስለ ክርስቶስ በመስበክም የመጀመርያ እንደነበረ ሁሉ፥ ሊቃውንትም ክረምቱን በዘመነ ብሉይ በመመሰል፣ መስከረምን (ዐዲስ ዓመትን) ደግሞ በዘመነ ሐዲስ በመመሰል መጥምቁ በዚሁ ጊዜ እንዲታሰብ ወስነዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ጌታ ባረገ በ180 ዓ.ም. ላይ በእስክንድርያ መንበር ሊቀ ጳጳስ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ዲሜጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ባሕረ ሐሳብን ሲደርስ በዮሐንስ ጀምሮ ደርሶታል፡፡ በመሆኑም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ - የዓመት በዓላት ራስ ዮሐንስ ጊዜ መቀመሪያ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ አንተ ነህ” እያሉ ይዘምሩለታል፡፡  
ጥያቄ አምስት፡- በኢትዮጵያና በአውሮፓ አቈጣጠር የቀናት አቈጣጠር ልዩነት መነሻው ምንድነው?
ምላሽ፡- በኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር መስከረም አንድ ሲሆን በምዕራባውያኑ አቈጣጠር መስከረም ዐሥር አንድ ይሆናል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በ1582 ዓ.ም. የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበረው ፖፕ ጐርጐርዮስ በፊት ይቈጠርበት የነበረውን አንድ ዓመት 365 ቀናት ከ6 ሰዓት የሚለውን ቀይሮ 365 ቀናት ከ5 ሰዓት እንዲሆን ስለ ወሰነ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ከጉባኤ ኒቅያ (ከ325 ዓ.ም.) ዠምሮ በመቍጠርና እንደርሱ ሐሳብ በዓመት አንድ ሰዓት የተጨመረውን በመደመር ዐሥር ቀናት አድርሶታል፡፡ በዚህም ጥቅምት 5 ቀን የነበረውን ጥቅምት 15 እንዲሆን በማወጁ የ10 ቀን ልዩነት ሊፈጠር ችሏል፡፡  ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ዋቢ፡- - “ባሕረ ሐሳብ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምሥጢር” በአለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ
-         የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ
ልዩ ምስጋና፡-መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፤ ለመምህር ሔኖክ ያሬድ ፈንታና ወ/ት ማኅደር ታፈሰ እግዚአብሔር ዐስበ አገልግሎታቸውን እግዚአብሔር ይክፈልልኝ፡፡

2 comments:

  1. ስለምን እናንተ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ትጠቀማላቹ?

    ReplyDelete
    Replies
    1. ላንተ ጥያቄ እኔም መልስ እፈልጋለሁ ::

      Delete

FeedBurner FeedCount