Thursday, July 26, 2012

ከእናንተ የሚፈለገው… በቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ!


 
… ይህ ቃል (“ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” የሚለው ቃል) በየወቅቱ ሊነገር የሚገባው እንጂ ለአይሁድ ብቻ ተነግሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ብርሃን ከወጣልንና /ዕብ.6፡4/ ከብዙ ደዌዎቻችን ከተፈወስን በኋላ መልሰን ወደ ከፋ ዐዘቅት እንገባለን፡፡ ስለዚህም የሚያገኘን መከራ ከድሮ ደዌአችን በጣም የባሰ ነው፡፡ ጌታ ሽባውን ከፈወሰው በኋላ “ናሁኬ ሐየውከ- እነሆ አሁን ከደዌህ ድነሀል፤ ዑቅ ኢተአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይረክበከ- ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአትን አትሥራ” ነበር ያለው /ዮሐ.5፡14/፡፡ 38 ዓመት ሙሉ ለተሰቃየው መጻጕዕም እንደዚሁ ነግሮታል /ዮሐ.5፡14/፡፡ ከእናንተ መካከል “ከዚህ የሚብስ ምን ያገኟል?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ የባሰ እማ አለ እንጂ፡፡ ደዌ ነፍስ ይቅርና በዚህ ምድር እንኳን ሊቋቋመው የማይችል ደዌ ሥጋ ሊያገኘው ይችላል፡፡ አያድርስብን እንጂ መቋቋም የምንችለው መቋቋም የምንችለውን ብቻ ነው፡፡…

 ጌታ ኢየሩሳሌምን ሲወቅሳት እንዲህ ብሎ ነበር፡- “በአብርሃም አድሬ ወዳንቺ መጣሁ  በደመ ጣዖትም ተበክለሽ አየሁሽ፣ በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ…ወሐጸብኩኪ በማይ- በውኃም አጠብሁሽ፣ወአጽረይኩ ደመኪ- ከደምሽም አጠራሁሽ፣ ወቀባእኩኪ በዘይት- በዘይትም ቀባሁሽ…ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር…ወዘመውኪ ምስለ ውሉደ ግብጽ አግዋርኪ እለ ዐብይ ሥጋሆሙ- ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ ወአብዛኅኪ ዝሙትኪ ከመ ታምዕዕኒ- እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ” /ሕዝ.16፡6፣9፣14፣26/፡፡ አዎን! ሁል ጊዜ በኃጢአት ተለውሰን ለምንኖር ለእኛም ወቀሳው ይህን የመሰለ “አሌ ለክሙ” ነው፡፡

…ትላንት ወደ ሠራነው ኃጢአት ስንቴ ተመለስን? ስንቴስ የባሰ ነገር አገኘን? ወንድሞቼ! ይህን ሁሉ የምላችሁ እንድትማሩበት እንጂ ተስፋ እንድትቆርጡ አይደለም፡፡ ፎርዖንን ታስታውሳላችሁ አይደል? እርሱ ከመጀመርያው መቅሰፍት ተምሮ ቢሆን ኖሮ ከነሙሉ ሠራዊቱ ጋር በባሕረ ኤርትራ ሰጥሞ የዓሳ ቀለብ ሁኖ ባልቀረ ነበር፡፡ እኛ እኮ አሁን ከፊታችን የምንሻገረው ቀይ ባሕር የለንም፤ ነገር ግን በዓይነቱም ይሁን በመጠኑ የቀይ ባሕርን የሚያክል ሳይሆን በጣም ግዙፍና ሙቀቱ ኃይለኛ የሆነ፣ ማዕበሉም ታይቶ የማይታወቅ አስጨናቂ የእሳት ባሕር ነው፡፡ በዚህ እንጦርጦስ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ ስቃይ አለ፡፡ በዚህ የእሳት ባሕር ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ እንደ አረመኔ የበረሀ አውሬ በቅጽበት የሚዞር ወላፈን አለ፡፡ እኛ የምናውቀው የዚህ ዓለም እሳት እንኳ ከሩቅ የነበሩትን የናቡከደነጾር መልእክተኞች ለመፍጀት ኃይለኛ ከሆነ /ዳን.3፡22/ ይህ እሳት ያውም ወደ ራሱ የተጣሉለትንማ ምን ያህል ይፈጃቸው ይሆን?
…ወንድሞቼ ያኔ ከዚህ እቶን እንኳንስ ሊያድነን ቀርቶ ምላሳችንን የምናርስበት የውኃ ጠብታ ሊሰጠን የሚችል ማንም የለም፡፡…አሁን ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ መለመን ከፍርድም ነጻ መሆን ይቻላል፡፡ ያኔ ግን ጌታ ይህን ስለማይፈቅድ በሚያንገበግብ እሳት እየተጨነቁ ቃላትም ሊገልጹት በማይችሉ እሳትና ጭንቅ መጣል ብቻ ነው፡፡ አሁን በዚህ ዓለም ወደ እሳት የሚጣሉትና የሚቃጠሉት ቃጠሎ ቃላት አይገልጸውም አይደል? ይህ ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ “እንዴት?” ብትሉኝ ከጊዜ አንጻር ሲታይ በጣም አጭር ነውና፡፡ በዚያ ያለው ቃጠሎ ግን መጨረሻ የለውም፡፡…

 በምነግራችሁ ነገር እያበሳጨኋችሁና እያሳመምኳችሁ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ግን ምን ላድርግ? እኔም እናንተም በምግባር በሃይማኖት የታነጽን እንሆን ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም እናመልጥ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ከመጨማለቃችን የተነሣ እንዴት አድርጌ ላሳምማችሁ እችላለሁ? ብትሰሙኝና ብተለወጡስ እኔም ማረፍ እንኳን በቻልኩ ነበር፡፡ ስለዚህ እስካልተለወጣችሁ ድረስ እናንተን መገሰጼና መምከሬ አላቆምም፡፡… ስለ ገሀነመ እሳት ተደጋግሞ ሲነገር የሚበሳጭ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን “ከዚህ በላይ አስደሳች ትምህርት የለም” እለዋለሁ፡፡ “እንዴት ይህ አስደሳች ትምህርት ነው ትለናለህ?” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም “ወደዚያ መጣል ከደስታ ሁሉ የራቀ ነውና” ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ስለዚህ ነፍሳችን ከመታሰሯ በፊት የነቃን እንሆን ዘንድ ይህን ደጋግሜ እነግራችኋለሁ፡፡…

 እንግዲያውስ ማንም ለራሱ ንስሐ ይግባ እንጂ እንደተወቀሰ አያስብ፤ በንግግሬም የሚቆጣ አይሁን፡፡ ሁላችንም ወደ ጠባቢቱ መንገድ እንግባ፡፡ እስከ መቼስ በስፍና አልጋ እንተኛለን? ዛሬ ነገ ማለት አይበቃንምን? ሰማያዊ ቪላችንን ቀና ብለን ብንመለከት እኮ በዚህ ምድር ይህንን ለመሥራት ባልደከምን ነበር፡፡ እሰኪ ንገሩኝ! ሩጫችን ስንጨርስ ከሬሳ ሳጥንና ከመግነዝ ጨርቅ ውጪ ይዘነው የምንሄድ ነገር አለን? ታድያ ለምን እንከራከራለን?

ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ ከዛሬ ጀምረን አዲስ ሕይወትን እንጀምር፡፡… አሕዛብ ምን ያህል በረከት እንደራቃቸው እናሳያቸው፡፡ በእኛ ዘንድ መልካምነትን ካዩ መንግሥተ ሰማያትን በእኛ ውስጥ ያይዋታል፡፡ አዎ! ጨዋ ስንሆን፣ ከክፋት፣ ከክፉ ምኞት፣ ከቅናትና ከጠበኝነት ርቀን ሲመለከቱን፡- “እነዚህ ክርስቲያኖች ገና እዚህ ምድር እያሉ መላእክትን ከመሰሉ ወደዚያኛው ዓለም ሲሸጋገሩ ወደ እውነተኛው ሀገራቸው ሲሄዱ ምን ይመስሉ ይሆን? በእንግድነት ዘመናቸው እንዲህ ብርሃን ከለበሱ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲሄዱማ እንዴት ይሆኑ ይሆን?” ይላሉ፡፡ በእኛ ምክንያት እነርሱ ይለወጣሉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ የተነሣ ይከብራል /2ተሰ.3፡1/፤ ወንጌል ከሐዋርያት ዘመን በላይ ይፋጠናል፡፡ ሐዋርያት አሥራ ሁለት ብቻ ሆነው ዓለምን ከለወጡ ከእነርሱ በቁጥር የበዛን እኛማ በመልካም ምግባራችን አስተማሪዎች ብንሆን እግዚአብሔር ምን ያህል ሊወደስ ሊቀደስ እንደሚችል አስቡት፡፡ አሕዛብ ራስን ከመግዛት በላይ ሙት ማስነሣትን አይማርካቸውም፡፡ ምክንያቱም ሙት ሲነሣ ይገረማሉ፤ በመልካም ምግባራችን ግን ይጠቀማሉ፡፡ ሙት ሲነሣ የአንድ ጊዜ ክስተት ነው፤ መልካም ምግባር ግን ሁል ጊዜ ከነፍሳቸው ጋር ተዋሕዶ የሕይወት ልምድ ይሆንላቸዋል፡፡

 ስለዚህ እነሱንም እናመጣ ዘንድ እንፍጨርጨር፡፡ ደግሞም እኮ ከባድ ነገር አልተናገርኳችሁም፡፡ አትጋቡ አላልኳችሁም፤ ከሰው ተለይታችሁ ከማኅበራዊ ኑሮ ራቁም አላልኳችሁም፤ ከእነርሱ ጋር ሆናችሁ መልካምነትን አሳዩ እንጂ፡፡ አዎ! በከተማ መሀል ሆነው መልካም ምግባርን የሚያሳዩ ክርስቲያኖች በገዳም ካሉ መነኰሳት ይበልጣሉ፡፡ ምክንያቱም በከተማ ያሉት ሊሰወሩ አይቻላቸውም፤ መብራታቸውንም አብርተው ከእንቅብ በታች ሊያኖሩት አይችሉም /ማቴ.5፡15፣ ሉቃ.11፡33/፡፡

 ስለዚህ ከዛሬ ጀምረን ለመብራታችንን ዘይት እንጨምርበት፤ በጨለማ ላሉትንም ከስሕተታቸው ይወጡ ዘንድ ምክንያት እንሁንላቸው፡፡ “ትዳር አለኝ፤ ልጆችን አሳድጋለሁ፤ የቤት አባወራ ስለሆንኩኝ ይህንን ማድረግ አልችልም” አትበሉኝ፡፡ ከእናንተ የሚፈለገው ፈቃዳችሁ ብቻ ነውና፡፡ ዕድሜም ቢሆን፣ ባለጸግነትም ቢሆን፣ ማጣትም ቢሆን ሌላም ቢሆን ይኸን ሁሉ ከማድረግ አይከለክላችሁምና፡፡ ምክንያቱም ሽማግሌዎችም፣ ወጣቶችም፣ ሚስቶችም፣ ሕፃናት አሳዳጊዎችም፣ ዕደ ጥበቦኞችም፣ ወታደሮችም ይህን ሁሉ ፈጽመውታልና፡፡ ዳንኤል ወጣት ነበር፤ ሠለስቱ ደቂቅ ሕፃናት ነበሩ፤ ዮሴፍ ባርያ ነበር፤ ሉቃስ ሐኪም ነበር፤ ሊድያም ሐር ሻጭ ነጋዴ ነበረች፤ ጳውሎስንና ሲላስን በወኅኒ ሲጠብቅ የነበረውም ፖሊስ ነበር፤ ቆርነሌዎስ ደግሞ አሥራ አለቃ ነበር፤ ጢሞቴዎስ በሽተኛ ነበር… ነገር ግን ይኸን ከማድረግ የከለከላቸው አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁሉ እንደ እኛ ሴቶች፣ እንደ እኛ ወጣቶች፣ እንደ እኛ ሽማግሎች፣ እንደ እኛ ነጋዴዎች፣ እንደ እኛ አሠሪዎች፣ እንደ እኛ ሠራተኞች፣ ወታደሮችና ሲቪል ነበሩ፡፡

 እንግዲያስ መልካም ፈቃድ ይኑረን እንጂ ከንቱ ሰበብን የምናበዛ አንሁን፡፡ ምንም ዓይነት ማንነት ይኑረን ፈቃደኞች ከሆንን ከእግዚአብሔር ጋር መልካምነትን መያዝ እንችላለን፡፡ ይህንን ሁሉ እንድናደርግና በቸርነቱ መንግሥቱን እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!



Tuesday, July 24, 2012

የቁልቢ ገብርኤል አመሠራረት- በዲ/ን ዳንኤል ክብረትና ቀሲስ ከፍያለው መራሒ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 461 ኪ/ሜ. ርቀት ላይ በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጋራ ሙለታ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የዚህን ደብር አመሠራረት በተመለከተ በብዙ ሊቃውንት የሚተረከው የሚከተለው ነው፡፡

በዘጠነኛው መ/ክ/ዘ. ዮዲት ጉዲት ተነሥታ አብያተ ክርስቲያናትን ስትመዘብር፣ ክርስቲያኖችን ስትገድልና መጻሕፍትን ስትቆነጻጽል ንጉሥ አንበሣ ውድም በአኩስምና በአከባቢዋ የነበሩ ታቦታትንና ንዋያተ ቅዱሳትን በመያዝ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ዝዋይ መጣ፡፡

ከ40 ዓመታት ስደት በኋላ አንበሣ ውድም ወደ አኵሱም ሲመለስና የንዋያተ ቅዱሳት ቆጠራ ሲደረግ ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል በዝዋይ መቅረቱ ታወቀ፡፡ ከኤርትራ ደብረ ሲና ማርያም የመጡና አባ ሌዊ የተባሉ አባት ታቦቱን ለማምጣት ከንጉሡ አስፈቅደው ወደ ዝዋይ መጡ፡፡

አባ ሌዊ ከሰባት ቀን ሱባኤ በኋላ ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን ይዘው ወደ አኵሱም ሲጓዙ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ “እኔ ወደማሳይህ ቦታ ታቦቱን ይዘህ ሂድ” አላቸው፡፡ አባ ሌዊም ታቦቱን ይዘው ተከተሉት፡፡ በመጨረሻም ቁልቢ ደረሱ፡፡ ለአባ ሌዊም የተፈቀደላቸው ቦታ ይሄ መሆኑን ታቦቱም በኋላ ዘመን ለሕዝቡ ድንቅ ሥራ እንደሚሠራ ቅዱስ ገብርኤል ነግሯቸው ተሠወረ፡፡ አባ ሌዊ በቦታው ለ130 ዓመታት ያህል አገልግለው በንጉሥ ግርማ ሥዩም ዘመነ መንግሥተ ታኅሳስ 14 ቀን ዐርፈዋል፡፡

ግራኝ አሕመድ ኢትዮጵያን ሲወርር ብዙ ካህናት ከሰሜን ኢትዮጵያ ታቦታትንና ንዋያተ ቅዱሳትን ይዘው ሲጓዙ ቁልቢ ደረሱ፡፡ መልአከ ገነት መብረቁ፣ መምህር የማነ አብ፣ አባ ተከስተ ሥሉስ የተባሉ ካህናት ከተነጠፈ ድንጋይ ላይ የተጻፈ ነገር ያገኛሉ፡፡ ጽሑፉም ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል በሥዉር መቀመጡን፣ ልዩ ልዩ ተአምራት እንደሚፈጸምበት፣ ወደ ፊትም ታላቅ ቤተ መቅደስ እንደሚሠራበት፣ እንዴት አባ ሌዊ ታቦቱን ወደዚህ ቦታ እንዳመጡት የሚገልጽ ነበር፡፡ እነርሱም ይህን ታሪክ ይዘውት በነበረው መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ ሕዳግ ላይ ጻፉት፡፡ ወደ ዝዋይ ደሴት ሲደርሱም መጽሐፉን በዚያ አኖሩት፡፡

ልዑል ራስ መኰነን ከዝዋይ ደሴት መጽሐፈ ቀሌሜንጦስን አስመጥተው ሲያነቡ የቁልቢ ገብርኤልን ታሪክ በማግኘታቸው የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ተነሡ፡፡ ልዑል ራስ መኰንን በአከባቢው የአየር ንብረት ተማርከው በሥፍራው ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ልዑል ራስ መኰንን ቁልቢ ገብርኤልን ከመትከላቸው በፊት ቦታው የአከባቢው ጎሳዎች የግጭት መነሃርያ ነበር፡፡ ሰላምን በአከባቢው ከመሠረትህ በቦታው በስምህ ቤተ ክርስቲያን እሠራልሃልሁ ብለው እንደተሳሉም ይነገራል፡፡

የተሳሉት በመፈጸሙ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት የት እንዳለ ሲያፈላልጉ ቡልጋ ውስጥ ከአዠጉጉ ካህናተ ሰማይ ጋር አባ ዱባለ የተባሉ ካህን ያስቀመጡት ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል መኖሩ ተነገራቸው፡፡ ልዑል ራስ መኰንን ለአባ ዱባለ መልእክት ስለላኩባቸው ከሐረር በተላኩ ካህናት አማካኝነት የቅዱስ ገብርኤልን ታቦት ላኩ፡፡ ልዑል ራስ መኰንንም ከነሠራዊቶቻቸው ሸንኮራ ድረስ ሄደው ታቦቱን በመቀበል የካቲት 21 ቀን 1884 ዓ.ም ታቦቱ ቁልቢ ገባ፡፡

የመቃኞው ሥራ በ1883 ዓ.ም ተጀምሮ ፍጻሜ አግኝቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው ሐምሌ 19 ቀን 1884 ዓ.ም ነው፡፡ በዚሁ ዕለት የዋናው ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ የመሠረቱ ድንጋይ ተጥሎ ታኅሳስ 19 ቀን 1888 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተፈጽሞ በአቡነ ማትያስ ተባረከ፡፡ ቦታውን ከባለ አባቶች የገዙት በአርባ የቁም ከብት ነው፡፡ ራስ መኰንን መጋቢት ዘጠኝ ቀን 1889 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ እዚህ ቦታ ላይ በድንገት ስለታመሙ በዕለቱ ሥጋወደሙ ተቀብለውበታል፡፡ በመጀመርያ ሲተከል በገጠር ቤተ ክርስቲያን ሥሪት ሲሆን በኋላ ግን በስእለት ሰማኢነቱ በመላ ኢትዮጵያ እየታወቀ ስለ መጣ ደብር ሆኗል፡፡

የቅዱስ ገብርኤል ምልጃና በረከት አይለየን!!

(ምንጭ፡ የቤተ ክርሰቲያን መረጃዎች- በዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ Saints and Monastries in Ethiopia, by Kesis Kefyalew Merahi)    

Monday, July 23, 2012

ጊዜዬ ገና አልደረሰም -የዮሐንስ ወንጌል የ32ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.7፡1-9)!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  በእነዚህ ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገብቷልና ከቅንዐትና ከምቀኝነት የባሰ ክፉ ነገር የለም፡፡ “በዲያብሎስ ቅንዐት ሞት መጣ፤ ወደዚህ ዓለምም ገባ” ተብሎ እንደተጻፈ የሰው ልጅ በክብርና በልዕልና ቢያየው ዲያብሎስን ቅንዐት ውስጥ ከቶታል፤ እርሱን ለመመቅኘትም ዓቅሙን ሁሉ ተጠቅሟል /ጥበብ 2፡24/፡፡ ይህ ቅንዐት በሰው ልጆችም ተመሳሳይ ፍሬ ሲያፈራ እናስተውላለን፡፡ ከቅንዐት የተነሣ አቤል ተገድሏል፤ ዳዊት ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ ሌሎች ብዙ ንጹሐን ቅዱሳንም መከራ ተቀብለውበታል፡፡ በዚሁ ቅንዐት አይሁድ ክርስቶስን ገድለውታል፡፡ ወንጌላዊው ይህን ሲያስረዳ፡- “ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር” ይላል /ቁ.1/። ይህን የሚያደርገው ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና ፈርቶ አይደለም፡፡ የሚሰቀልበት የሚሞትበት ጊዜው ስላልደረሰ እንጂ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም! ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለማመልከት ለማስረዳትም አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው ይሄዳል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገለል ይላል፡፡ አሁንም ተናድደውበት ነበርና ገለል አለ፤ ወደ ምድረ ይሁዳም ሊሄድ አልወደደም /St. John Chrysostom, Hom 48/፡፡  

 የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር /ቁ.2/። አይሁድ ከየአሉበት ዓለም ተሰባስበው በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ የሚያከብርዋቸው ሦስት ታላላቅ በዓላት አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ይህ የዳስ በዓል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከየቤቶቻቸው ወጥተው በቤተ መቅደሱ ዙርያ አጠገብ፣ በከተማው ዋና ዋና አደባባይ፣ በየቤታቸው… ድንኳን ይተክላሉ፡፡ ከግብጽ ወጥተው በበረሐ በድንኳን ውስጥ ያሳለፉትን መከራና ስቃይም ያስታውሱበታል /ዘሌ.23፡29-43/፡፡

 ወንድሞቹም (ደቂቀ ዮሴፍ) ይህን ይዘው (በዓል እንደቀረበ አይተው) ጌታን እንዲህ አሉት፡- “(በምድረ ይሁዳ ያሉት) ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ (ተአምራትህን) እንዲያዩ  አይተውም አምላክ መሆንህን እንዲያምኑብህ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፡፡ ምክንያቱም ራሱን ሊገለጥ እየፈለገ፣ ሥራው እንዲታይለት ወዶ ሳለ በስውር በድብቅ የሚሠራ የለምና። አንተም ሥራህ እንዲገለጥልህ እንዲታይልህ ትወዳለህና እነዚህን አድርገህ ራስህን ለዓለም ግለጥ፤ አምላክነትህን ለሁሉ አሳይ” አሉት /ቁ.3-4፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 490/። እነዚህ ደቀቂ ዮሴፍ ጌታችን የሚያደርጋቸው ተአምራት ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተነሣ እንደሆነ አላወቁም፤ ከማመን የዘገዩትን ሰዎች ለማቅረብ ያደረገው መሆኑን አልተረዱም፤ እንዲያው ለታይታ እንዲያው ለውዳሴ ከንቱ ያደረገው ይመሰላቸው ነበር እንጂ፤ ስለዚህ አሁን የተናገሩትን ተናገሩ፡፡ የበለጠ ይታይ ዘንድ ይህን ለገቢረ በዓል በወጣው ሕዝቡ መካከል ያደርገው ዘንድ ተናገሩት፡፡ ወንጌላዊው እንደነገረን ይህን ያሉት እነርሱ ራሳቸው ገና በጥርጥር ተይዘው ስለ ነበር ነው፡፡ የሚመጣው መሲሕ እርሱ መሆኑን ስላላመኑበት ነው፡፡ ስለዚህ በሌላ ሰው አስመስለው ይህን ተናገሩ እንጂ እናምንብህ ዘንድ ተአምራትህን አሳየን ማለታቸው ነበር /ቁ.5/፡፡

 ጌታችንስ ምን አላቸው?፡- “በገሃድ ወደ በዓል የምወጣበት ጊዜዬ፣ በይፋ መከራ መስቀል ምቀበልበት ጊዜዬ (አይሁድ ያለ ጊዘው ይገድሉት ዘንድ ይሹ ነበርና)፣ እንናንተ የምትሉት ሳይሆን እውነተኛው ክብሬ በግልጥ የሚታይበት ጊዜዬ ገና አልደረሰም፡፡ የእናንተ ጊዜ ግን የሚከለክላችሁ የለምና ለበዓለ ፋሲካውም ለበዓለ መጸለቱም ዘወትር ለመውጣት የተዘጋጀ (የተመቸ)ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውምና፡፡ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና፤ ስለዚሁም እዘልፈዋለሁና፤ የተሰወረ ተንኰሉም እገልጥበታለሁና፤ ሌባዉን ሌባ ሲሉት አይወድምና እኔን ይጠላኛል፤ ሊገድለኝም ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔ ግን በገሃድ በይፋ የምወጣበት ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ አይሁድ በተናደዱበት በዚህ ጊዜ ወደዚህ በዓል ገና (ዛሬ) አልወጣም” ብሏቸው በገሊላ ቀረ /ቁ.6-9/፡፡

ከእናንተ መካከል “ጌታችን ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም ብሏቸው ሳለ ስለምን ቀይቶ ወደ በዓሉ ሄደ” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ጌታችን ወደ በዓሉ ጭራሽ አልሄድም ያለ አልነበረም፡፡ ገና (አሁን) አልሄድም እንጂ፤ አሁን ከእናንተ ጋር የምሄድ አይደለሁም እንጂ፡፡ በኋላ ወደ በዓሉ የወጣውም መከራ እንዲያደርሱበት፣ እንዲሰቅሉት፣ እንዲገድሉት ሳይሆን ያስተምራቸው ዘንድ ነው /St. John Chrysostom, Ibid/፡፡

  ተወዳጆች ሆይ! ከቅንዐት ተነሣስተው ጌታን ሊገድሉት ሊወግሩት ሊሰቅሉት ከሚፈልጉት ከአይሁድ ሳይሆን ከመምህራችን ከክርስቶስ ትሕትናን፣ ጥበብን፣ ትዕግሥትን የዋህነትን የምንማር እንሁን /ማቴ.11፡29/፡፡ ብዙ ሰዎች እኛን ለመጕዳት በቁጣ ነደው ይመጣሉ፤ በትሕትና እናሸንፋቸው፡፡ ብዙ ሰዎች እኛን ለመተናኰል ይመጣሉ፤ በፍቅርና በትዕግሥት እንዲሁም በጥበብ እንጠብቃቸው፡፡ ክፉው በእኛ እንዳይሰለጥን እነዚህን የከበሩ የጠቢቡ ቃላት ደጋግመን ለራሳችን እንናገራቸው፡- “እንግዲህ ትቢያና አፈር የሚሆን በሕይወትም ሳለ ሰውነቱ የሚተላ ሰው ለምን ይታበያል /ሲራክ.10፡9/፡፡ በተቈጣ ጊዜ መከራ ይመጣበታልና ቁጡና ዐመፀኛ ሰው መጽደቅ አይችልም /ሲራክ.1፡22/፡፡ በእውነቱ ከቁጣ የባሰ ክፉ ነገር የለም /ምሳሌ.11፡25/፡፡ ስለዚህ ጊዜዋን እስክታሳልፍ ድረስ ቁጣን ታገሣት፤ ኋላም ደስ ታሰኝሃለች /ሲራክ.1፡23/፡፡”
 ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!

FeedBurner FeedCount