Saturday, June 23, 2012

“የታመነ፣ የከበረና የተመሰገነ ስለሚሆን ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ!” ቅዱስ ኤራቅሊስ

የታመነ፣ የከበረና የተመሰገነ ስለሚሆን ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፡፡ እርሱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሚፈጸመውን ምሥጢር አላወቀምና፡፡
አገልጋይ የሆነለት ምሥጢር ምን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ለእርሱ ከታጨችለት ከድንግል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገሩለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ዘር እንዲወለድ አላወቀም፤ በነቢይ እንደ ተናገረ ሕፃን ያለ አባት ከድንግል እንዲወለድ አላወቀም፡፡ /ኢሳ.714 96-7 ዮሐ.146/
ከንጹህ ዘር የተፈጠረች ድንግል የእግዚአብሔር ማደርያ እንድትሆን አላወቀም፤ ዘላለም መለወጥ የሌለበት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ ድንግልና ካላት ገነት እመቤታችን እንዲገኝ አላወቀም፡፡ /ዘፍ.927 መኃ.412/
ፍጡራንን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ያለ ዘር እንዲወለድ አላወቀም፤በምድራችን ታየተብሎ በነቢይ እንደ ተነገረና ዳግመኛም ምድር ፍሬን ትሰጣለች ተብሎ እንደ ተነገረ፡፡ ኢሳ.321-2 ዮሐ.14 ቆላ.115-18/
የድንግል ሆድዋ ገፋ፤ ያለ ዘር የፀነሰች የድንግልን የሆድዋን መግፋት ባየ ጊዜ የዮሴፍ ልቡ አዘነ፤ የንጽህት እመቤታችንን ምሥጢሯን ፈጽሞ መረመረና በማያውቀው ምሥጢር ፀንሳ ቢያገኛት በጽኑ ሐሳብ በማውጣት በማውረድ ተያዘ፡፡
ፀንሳ አገኛት፤ በዘር የፀነሰችም መሰለው፤ ከእርሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና አንተም እንደምትጠራጠረው አይደለምና ዮሴፍ አትፍራ ብሎ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ እስኪነግረው ድረስ፡፡
ዮሴፍም ይህን በሰማ ጊዜ ለድንግል ሰገደ፤ ንጽህናዋንም አመነ፤ ነቢዩ አሳይያስ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙም አማኑኤል ይባላል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው ብሎ የተናገረላት ድንግል እርሷ እንደ ሆነች አወቀ፡፡ /ማቴ.118-25 ሉቃ.126-39 ኢሳ.714/
(
ምንጭ፡ ሃይማኖተ አበው.4829-35)

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount