Wednesday, June 6, 2012

የወልድ ፍቅር!!


 
ባሕርይውን ዝቅ ብሎ የታየው ከሁላችንም በላይ ከዘመናት ሁሉ አስቀድሞ የነበረው ነው፤ ይህ ሰው የሆነው ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ነው፡፡ የሆነው ሁሉ በእርሱ የተደረገ ነበር፤ የሆነው ሁሉ የተደረገው በምክንያት ነበር፡፡ ያለ ምክንያት የተደረገ አንዳችም ነገር የለም፡፡ እርሱም ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ዋስትና ሲባል የተደረገ ነው፡፡ እርሱ ከመጀመርያው ያለ ምክንያት ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር ሀልዎትስ ምን ምክንያት ይኖረዋል! ነገር ግን በምክንያት እርሱም የሰው ልጅን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆነ፤ የተፈጸመውም የእኛ ድኅነት ነው፡፡ያዋረድነውን እግዚአብሔርነቱን፣ የናቅነውን መንግሥቱን፣ ያቃለልነውን ወገኖቹ ሊያደርገን ስለዚህ የእኛ ባሕርይን ነሣ፡፡ ሥጋ ዝቅ ያለ ሲሆን እግዚአብሔርን ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም የሰው ልጅ ሆነ፡፡በሥጋ ከድንግል ተወለደ፡፡ አስቀድሞ ግን ከባሕርይ አባቱ ከዘላለም የተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፡፡ ከሴት ተወለደ፤ ነገር ግን ድንግል ነበረች፡፡ የመጀመርያው ሰው ሁለተኛው መለኰት ነው፤ ሁለት ባሕርያት ያሉት አይደለም፡፡ በፍጹም ተዋሕዶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነ እንጂ፡፡ ሰው እንደ መሆኑ አባት የለውም፤ አምላክ እንደ መሆኑ እናት የለውም፡፡ በማሕጸነ ድንግል ተወሰነ፤ በነብያቱ አፍ አምላክነቱ ተመሰከረለት፡፡ ነቢያቱ ብቻ የመሰከሩ አይደለም፤ አብም የምወደው ልጄ ነው አለ፤ እርሱም አባቴ ነው አለ እንጂ፡፡ ሰው እንደ መሆኑ በጨርቅ ተጠቀለለ፤ አምላክ እንደ መሆኑ የተገነዘበትን ጨርቅ ጥሎት ተነሣ፡፡ በበረት

ላይ ተኛ፤ መላእክቱ ግን አመሰገኑት፡፡ ወደ ግብጽ ተሰደደ፤ በዚያ የነበሩትን የሐሰት አማልክተ ግብጽን ግን እንዲሰደዱ አደረገ፡፡ በአይሁድ አለቆች ዘንድ ደም ግባት አልነበረውም፤ በዳዊት ዘንድ ግን ውበቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ እጅግ ያማረ ነው፡፡ … እንደ ሰው ተጠመቀ፤ ኃጢአትን ይቅር የሚል ግን እርሱ ነው፡፡… ተራበ፤ ፍጥረትን የሚመግብ ግን እርሱ ነው፡፡…ደከመ፤ ደካሞችን ከሸክማቸው የሚያሳርፍ ግን እርሱ ነው፡፡ ደክሞት አንቀላፋ፤ እስራኤልን የሚጠብቅና የማይተኛው አምላክ ግን እርሱ ነው፡፡ ግብርን ለቄሳር ከፈለ፤… ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤን የተቀበለ ግን እርሱ ነው፡፡ ሳምራውያን ጋኔን አለብህ አሉት፤ እርሱ ግን አጋንንትን ያወጣል፡፡… አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፤ ነገር ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡ ጸለየ፤ ጸሎትንና ምልጃን የሚቀበል ግን እርሱ ነው፡፡ አለቀሰ፤ የሰዎችን እንባ የሚያብስ ግን እርሱ ነው፡፡ እጅግ ርካሽ በሆነ በሰላሳ ድራም ተሸጠ፤ ዓለምን እጅግ ውድ በሆነ ደሙ የገዛ ግን እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ እውነተኛው የበጎች እረኛ ግን እርሱ  ነው፡፡ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ አፉን አልከፈተም፤ ዓለምን በቃሉ የፈጠረ ግን እርሱ ነው፡፡ …ወንጀለኞችን ይፈውስ ዘንድ ከወንጀለኞች ጋራ ተሰቀለ፡፡ ሞተ፤ ሕይወትን የሚሰጥ  ግን እርሱ ነው፡፡ ወደ ሲዖል ወረደ፤ ነገር ግን ነፍሳትን ይዞ ወጣ፡፡ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ በታላቅ ምስጋና ይመጣል፡፡ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበን፡፡ አሜን!!’’  

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ 

ማን ሊናገረው ይችላል
ምሥጢረ ሥላሴ
 

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount