መንፈሳዊ ጸጋቹ በዛሬው ዕለት በእኛ ላይ በምላት ወርዷልና መንፈስ ቅዱስን
በመንፈሳዊ ጣዕመ ዝማሬ ከፍ ከፍ እናድርገው፡፡ ምንም እንኳን ያገኘነውን የጸጋ ታላቅነት ለመግለጽ የእኛ ቃላት በጣም ደካሞች ቢሆኑም
እንደ አቅማችን ኃይሉንና ሥራውን ከማመስገን አንከልከል፡፡
እያከበርን ያለነው የጴንጤ ቆስጤ በዐል ነው፤ የርደተ መንፈስ ቅዱስ ቀን፣
ተስፋ ፍጻሜ ያገኘበት ቀን፣ መጠበቅንና የመዳንን ናፍቆት ያበቃበት ቀን፣ ጸሎተ ሐዋርያት መልስ ያገኘበት ቀን፣ ዐስበ ትዕግሥትን
ያየንበት ቀን፡፡ የዛሬው ዕለት በዔቦር ዘመን ቋንቋን የደበላለቀ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የእሳት ላንቃዎችን ሲያሳይ የተመለከትንበት
ነው /ዘፍ.10፡25/፡፡ በዔቦር ዘመን አስወቃሹንና አሳፋሪውን የሰው ልጅ ፈቃድ ለመግታት ቋንቋቸውን የደበላለቀ መንፈስ ቅዱስ
ዛሬ ግን ደቀመዛሙርቱ ሁሉም በአንድ ቤት ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ንፋስ መጥቶ ቤቱን ሲሞላው፤ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖችም
ሲያሳያቸው፤ በፈቃዱም የሰባኪነትን ልሳን ሲሰጣቸው አየን፡፡
ይህ ቅዱስ መንፈስ በሥነ ፍጥረት መጀመርያ በውኃ ላይ ሲሰፍ አየነው፤ በኋላ
በዘመነ ሐዲስም በጌታችን ራስ ላይ ሲያርፍ አየነው፡፡
ይህ በርግብ አምሳል በጥፋት ውኃ ላይ በርሮ የንፍር ውኃ መጉደሉን ለኖኅ ያበሰረ
መንፈስ ቅዱስ በኋላም በርግብ አምሳል በዮርዳኖስ ውኆች ላይ በመታየት ሲጠመቅ የነበረውን በግ ለዓለም ሁሉ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ
ልጅ መሆኑን ሲገልጥ ሲመሰክር አየነው፡፡
ዳዊት ይህን ቅዱስ መንፈስ ፈልጐ ወደ አምላኩ ሲጸልይ፡- “ጌታ ሆይ ከፊትህ
አትጣለኝ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድብኝ” አለ /መዝ 50፡11/፡፡
በእርግጥም ቅዱስ መንፈስ በሌለበት ሁሉ የክፋት ወረርሽኝ ዓይነት ይገባል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ከሳኦል ሲለይ ክፉ መንፈስ ወደ እርሱ እንደ ገባ፡፡ ስለዚህም ዳዊት “ቅዱስ መንፈስህን ከእኔ አትውሰድብኝ” ሲል
ይጸልይ ነበር፡፡
ነቢያትን የለያቸው፣ ሐዋርያትን የመራቸው፤ ሰማዕታትን ያሚያበረታቸው ይህ ቅዱስ
መንፈስ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ ኢሳይያስን አንጽቶታል፤ ሕዝቅኤልን አስተምሮታል፤ ትንሣኤ ሙታንንም ገልጾለታል፡፡ “የእግዚአብሔር
እጅ በላዬ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ” እንዲል /ሕዝ. 37፡1/፡፡
ይህ
ቅዱስ መንፈስ ኤርምያስን በእናቱ ማኅፀን ሳለ መረጠው፤ ዳንኤልንም ሶስናን ያድናት ዘንድ አነሳሣው፡፡ “ይገድሏትም ዘንድ ሲወስዷት
እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ወጣት አነሳሣ” ተብሎ እንደተጻፈ /ዳን. 13፡44-45/፡፡
ዳዊት ይህ ቅዱስ መንፈስ ከእርሱ ጋር ሆኖ ያድነው ዘንድ ስለወደደ ወደ እግዚአብሔር
እንዲህ ሲል ጸለየ፡- “ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ” /መዝ. 142፡10/፡፡
ይህ ቅዱስ መንፈስ ያድርባት ዘንድ ወደ እመቤታችን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም መጣ፤
ኃይለ ልዑል ወልድም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ እንዲወለድ በማድረግ ወላዲተ አምላክ አደረጋት፡፡ በዚሁ ቅዱስ
መንፈስ ውስጧ የተመላ ቅድስት ኤልሳቤጥ በድንግል አማካኝነት ጌታ ወደ እርሷ እንደ መጣ ተረዳች አወቀች፡፡ ስለዚህም፡- “የጌታዬ
እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ?” አለች /ሉቃ.1፡43/፡፡
የዮሐንስ አባት ዘካርያስም በዚሁ ቅዱስ መንፈስ ሲመላ ከእርሱ የሚወለደው ሕፃን
የልዑል ነቢይ እንደሚሆን፤ መንገዱንም እንደሚጠርግ ጮኾ ተናገረ /ሉቃ.1፡76/፡፡
ጌታንም ደቀመዛሙርቱን ሲያስተምራቸውና በሚደርስበት ጸዋትወ መከራ እንዳያዝኑ
ያጽናናቸው ነበር፡፡ “እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም” እንዲል /ዮሐ.16፡7/፡፡
ስለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት የዚህን ቅዱስ መንፈስ ኃይል ከላይ እስኪያገኙ
ድረስ ጠበቁ፤ ይህን ኃይል ከአርያም እስኪለብሱ ድረስም ቆዩ፤ ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞዘቸው ነበርና፡- “እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ
ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” /ሉቃ 24፡49/፡፡
እንደ ተባለውም፡- “በዓለ ሐምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ
ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማያት ድምጽ መጣ፤ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው፤ እንደ
እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩዋቸው” /ሐዋ.2፡1-3/፡፡
በአብና በመንፈስ
ቅዱስ የተሰጣቸውን ተስፋ ከተቀበሉ በኋላም ኃይልን አገኙ፤ ተቀብለውም የወልድ እግዚአብሔር ጸጋዉንና ሥልጣኑን ለዓለም ሁሉ ገለጡት፡፡
ሐዋርያት እጃቸውን ሲጭኑበት ይህን ቅዱስ መንፈስ የተቀበለና የተመላው ሊቀ ዲያቆናት ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በሕዝቡ መካከል ታላላቅ
ምልክቶችንና ተአምራትን አደረገ፡፡ ይህን ቅዱስ መንፈስ ሲመላ የሰማያት ደጅ ተከፍተው ሥግው ቃል በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ቆሞ
ተመለከተ፡፡
ጳውሎስ በዚሁ ቅዱስ መንፈስ ተመልቶ የመለኰታዊ ምስጢር ሰባኪ ሆነ፡፡ ሐናንያ
እንዲህ ብሎ እንደ ነገረው፡- “ጌታ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ አዳኝ /ኢየሱስ/ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ
ወደ አንተ ላከኝ” /ሐዋ.9፡17/፡፡ ጳውሎስም ይህን ሲያስረግጥ፡- “እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል”
አለ /1ቆሮ.7፡40/፡፡
ይህ ቅዱስ መንፈስ ወደ ቆርኔሌዎስና ከእርሱ ጋራ መጠመቅ ወደ ነበረባቸው ሰዎች
መጣ፡፡ እያንዳንዳቸውም በጳውሎስ ቋንቋ በመናገር እግዚአብሔርን ገለጡት፡፡ ይህ ቅዱስ መንፈስ ይጠመቅ ዘንድ ወደ ውኃ ወደ ወረደው
ወደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መጣ፡፡ ጃንደረባው በዚህ መንፈስ ሲመላ ሐሴት አደረገ፤ ደስ ብሎትም መንገዱን ሔደ፡፡
በነቢያት አንደበት የተናገረው፣ ለሐዋርያት ማስተዋልን የሰጣቸው፣ ለሥጋ ለባሽም
ሁሉ የተናገረው ይህ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ መንፈስ ጌታችን ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፤ ተቃዋሚዎቻቸው ግን ይህን መንፈስ መቃወምም
ሆነ መቀበል አልተቻላቸውም፡፡ “በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩት እናንተ አይደላችሁም” እንዲል /ማቴ.10፡20/፡፡
ይህ ቅዱስ መንፈስ ቀሳውስትን ይሾማል፤ አብያተ ክርስቲያናትን ይቀድሳል፤ መናብርትን
ያነጻል፤ ምሥዋዕን ፍጹም ያደርጋል፤ የሰውንም ሁሉ ኃጢአት ያስተሠርያል፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ያድራል፤ ጻድቃንን ያበረታል፤
ነገሥታትንም ይመራል፡፡
ይህ ቅዱስ መንፈስ የጌታን መሲሕ ሳይመለከት እንዳይሞት ቃል የተገባለት ስምዖን
የሞትን ሕግ ሽሮና ዕድሜውን አስረዝሞ የሕይወትና የሞት ቤዛ የሆነውን ኢየሱስ እስኪመለከት ድረስ አቆየው /ሉቃ.2፡25-26/፡፡
ለኤልያስ ብርታትን የሰጠው ይህ ቅዱስ መንፈስ ነው፤ ኤልሳዕም ይሰጠው ዘንድ
ኤልያስን የጠየቀው ይኸን መንፈስ ነው፡፡ “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ” እንዲል /2ነገ.2፡9/፡፡
ይህ መንፈስ ቅዱስ ዓይነ ልቡናን ያበራል፤ ሁለንተናንም ይቀድሳል፡፡
በሐዋርያት ላይ የወረደውና በመለኰታዊ ጥበብም የሞላቸው ይኸው መንፈስ ቅዱስ
ነው፡፡ የእርሱን ስጦታዎች ከተቀበሉ በኋላ ሁሉም በእግዚአብሔር እውቀት ተሞሉ፡፡ የተሰጣቸውም መለኰታዊ ዕውቀት ብቻ አልነበረም፤
መንፈሳዊ ስጦታዎችም ጭምር እንጂ፡፡
ሲሞን መሰሪ ለዚሁ ቅዱስ መንፈስ እንግዳ ቢሆን ወደ ሲዖል ተጣለ፡፡ ጴጥሮስ
እንዲህ እንዳለ፡- “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” /ሐዋ.8፡20/፡፡
እንግዲያውስ ተወዳጆች ሆይ! አዲስ ሰውነትን ያገኘ ሰው፣ የዚሁ ቅዱስ መንፈስ
ቤተ መቅደስ የሆነ ሁሉ እውነተኛ የዲያብሎስ አሸናፊ ነውና ሁለንተናችንን እንቀድስ፡፡ ለዚህ ያልተገባን ስንሆን በዚሁ ቅዱስ መንፈስ
አማካኝነት ለሲሞን የተነገረው ዕጣ በእኛ ላይ ሊደርስ ይችላልና፡፡ ልጅነታችንን ሳናረክስ ቅድስት ሥላሴን በማመስገን እንጽና፡፡
ምስጋና ይሁን አንድ አምላክ ለሆነ ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን!!
አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ
እየሱስ አማላጅ ነውን?
ከአንድ በላይ ሚስት ለምን
ካህናተ ደብተራ
የዮሐንስ ወንጌል የ10ኛ ሳምንት ጥናት
No comments:
Post a Comment