Wednesday, June 13, 2012

ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው- የዮሐንስ ወንጌል የ27ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡1-15)!!


          በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 ተወዳጆች ሆይ! ከክፉዎች ጋር ክፉዎች አንሁን፡፡ ይልቁንም ክፋታቸው በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ጕዳት ሊያመጣ እንደማይችል እንረዳ፡፡ አንድ የሚፈነዳ መሣርያ ድንጋይ ላይ ቢወረወር ተስፈንጥሮ ወደ ወረወረው ሰውዬ ይመለሳል፤ ይጐዳዋልም፤ ባስ ካለም ሕይወቱን ሊያሳጣው ይችላል፡፡ ምናልባት የተወረወረው መሣርያ ለስላሳ መሬት ላይ አርፎ ቢሆን ግን መሬቱ የመሣርያውን ግለት ስለሚያቀዘቅዘው ሰውዬውን ባልጐዳው ነበር፡፡ በእኛ ላይ ክፋትን የሚፈጽም ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ እኛ መልሰን ክፋት የምናደርግበት ከሆነ ክፋቱን ይበልጥ ይገፋበታል፤ እኛ ትዕግሥተኞችና ሰው ወዳዶች ብንሆን ግን ክፋቱን እንዲመለከት መስታወት ስለምንሆነው ከክፋቱ ይቀዘቅዛል፡፡ ይህን የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ጌታችን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርግ በሰሙ ጊዜ በእርሱ ላይ ክፋትን ለመፈጸም ወደ ቃና ዘገሊላ ስለሚሄዱ እንጂ፡፡ ሰው አፍቃሪው ጌታ ግን ይህን ክፋታቸው ስላወቀባቸው እንዳይገፉበትና ራሳቸውን የበለጠ እንዳይጐዱ ስለወደደ እነርሱ ወዳሉበት ወደ ቃና ዘገሊላ አልሄደም፡፡  ይልቁንም “የጥብርያዶስ ባሕር ወደሆነው ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ” እንጂ /ቁ.1/፡፡ ሲሄድም “በበሽተኞች ያደረገውን ምልክቶች አይተው ብዙ ሰዎች ተከተሉት” /ቁ.2፣ ምዕ.5፡9/። እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው “በልሳን መናገር (በአጠቃላይ ተአምራትን ማድረግ!) ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም” እንዳለው ከጌታችን ትምህርት ይልቅ ተአምራቱ ይማርካቸው ነበር፡፡ /1ቆሮ.14፡22፣ Saint John Chrysostom, Homilies on St. John, Hom: 42:1/።
 ከዚህ በኋላ “አስተምራችሁ ገስጻችሁ፣ መክራችሁ ዘክራችሁ የራሳችሁ የሆነ የጽሞና ጊዜ ያስፈልጋችኋል፤ ከጥብብ ምንጭ ከእግዚአብሔር ጋር የምትገናኙበት ልዩ ጊዜ ሊኖራችሁ ይገባል፤ እንዳትታበዩ ሥጋችሁን የምትጐስሙበት ትሕርምት፣ ጾም ጸሎት ያስፈልጋችኋል” ሲልወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ” /ቁ.3/።  ይህም ሲሆን የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር” /ቁ.4/፡፡ ሆኖም ግን ጌታችን ወደዚሁ ገቢረ በዓል አይሄድም፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው በቤተ መቅደሱም ያሉት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን አብዝተው ሊገድሉት ይፈልጋሉና፡፡ ስለዚህ ፈርቶ ሳይሆን ጊዜው ስላልደረሰ፣ አንድም ለክርስቲያኖች መሸሽ ኃጢአት አለመሆኑን ለማሳየት፣ አንድም እነዚህ ሰዎች እርሱን የጐዱ መስሎዋቸው ራሳቸውን እንዳይጐዱ፣ አንድም ነፍሱ በዓላቶቻቸውን እንደጠላች ደግሞም እንዳለፉ ለማሳየት ወደ ገቢረ በዓላቸው አይሄድም /ኢሳ.1፡14፣ Saint John Chrysostom, Ibid /፡፡

    ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተራራው በተቀመጠ ጊዜ፣ ከልጆቹ ጋር መነጋገር በጀመረ ጊዜ ዓይኖቹን አራምዶ አየ፤ ብዙ ሕዝብም ወደ እርሱ ሲመጡ ተመለከተና አዘነላቸው /ቁ.5፣ ማቴ.14፡6/፡፡ አቤት ፍቅር! አቤት ቸርነት! አቤት ርኅራኄ! ወንድሞቼ እስኪ የጌታችንን የፍቅር ፊት በኅሊናችሁ ሣሉት! እስኪ የርኅራኄና ሰው ወዳዱ ፊቱን በልቡናችሁ ቅረጹት፡፡ አያችሁ?! ጌታ እንዲህ ይወደናል! አባታችን እንዲህ ይሳሳልናል! ወዮ አባት ሆይ ስላፈቀርከን እናመሰግንሃለን!!

   ከዚህ በኋላ ኅብስቱን አበርክቶ ሊሰጣቸው እንደሚችል ኃይልና ሥልጣን እንዳለው ቢያውቅም ደቀ መዛሙርቱ ገና በእምነት ያልጠነከሩ ስለነበሩ እምነታቸው ይጨምር ዘንድ በፊልጶስ በኵል፡-“ለእኒህ ሰዎች የምንመግባቸውን እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አላቸው። ይህም እግዚአብሔር ሙሴን ለማሳመን ያደረገውን ተአምር ያስታውሰናል፡፡ ሙሴ እስራኤላውያንን ከፎርዖን አገዛዝ እንዲያላቅቃቸው በእግዚአብሔር ሲታዘዝ
ፍርሐት ነበረበት፡፡ “እነሆ አያምኑኝም፤ ቃሌንም አይሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከቶ (በሐመልማል ዕጽ) አልተገለጠልህም ይሉኛል” ሲል ተናገረ፡፡ ከኃሊው እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር መሆኑን እንዲያምን፡- “ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት?” አለው፡፡ ሙሴም “በትር ናት” አለ፡፡ ከዚህ በኋላ በያዘው በትር እርሱ የአብረሃም፣ የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ መሆኑን እርሱም እንደተገለጠለት ማሳመኛ እንዲሆነው አሳየው /ዘጸ.4፡1-6/፡፡ አሁንም የፍቅር ንጉሥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በእጃቸው ከያዙት ተነሥቶ እርሱ ኤልሻዳይ መሆኑን ያስረዳቸዋል፡፡ “ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ” እንዲል /ቁ.6/፡፡ ደቀመዛሙርቱ ግን፡-መምህር ሆይ! ከአምስት የገብስ እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር ምንም አልያዝንም፡፡ እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? እያንዳንዳቸው አንዳንድ ጉርሻ እንኳ እንዲቀምሱ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም፡፡ ስለዚህ ሰዓቱ አልፏል፣ ቦታውም ምድረበዳ ነውና ወደ መንደር ሄደው ለራሳቸው ምግብ ቢገዙ የተሻለ ነው” ይሉታል /ቁ.7-9፣ ማቴ.14፡15-17/።  ጌታ ኢየሱስ ግን፡- “ይህስ ካለ ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ” አላቸው /ቁ.10/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ልጆቼ! ከእናንተ ጋር ያለው አምጻዔ ዓለማት ነው፤ ከእናንተ ጋር የሚነጋገረው ዓለምን በፍቅሩ የሚመግባት ነው፤ ከእናንተ ጋር የተቀመጠው እስራኤልን በበረሐ መናን እያዘነመ የመገበ ነው፤ ከእናንተ ጋር… አዎ! ከእናንተ ጋር ዝቅ ብሎ የሚነጋገረው… አምላክነቱን እንደመቀማት ሳይቆጥረው የባርያውን መልክ የያዘ ነገር ግን እስራኤልን ከጭንጫ ውኃ እያፈለቀ ያጠጣ ኤ-ል-ሻ-ዳ-ይ ነው /መዝ.77፡16/፡፡ እንግዲያውስ የሕዝቡ ብዛት የያዛችሁትም የእንጀራ ማነስ አያስጨንቃችሁ፡፡ እርስ በእርሳችሁም ምን እንሰጣቸዋለን? እያላችሁ በጭንቀት አትነጋገሩ፤ ሰዓቱ መሽቷልም አትበሉ፡፡  ሕዝቡ ምን እንደሚፈልግ አውቃለሁ፤ የቦታው በረሐማነት እረዳለሁ፤ የጊዜው መምሸት እገነዘባለሁ፤ የሕዝቡን ጭንቀት አስተውላለሁ፤ የማደርገውንም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን ጥሩና በለምለሙ መስክ አስቀምጡልኝ፡፡ መቀመጫቸውን አሰናዱልኝ፡፡ እንጨቱንና ደንጊያውንም አንሡላቸው፡፡”

   ደቀመዛሙርቱም የተባሉትን አደረጉ፡፡ “ወንዶችም በለምለሙ ሣር ተቀመጡ፤ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር።  ጌታ ኢየሱስም  እንጀራውን አንሥቶ ያዘ፥ አመስግኖም ስጧቸው ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች አቀረቡላቸው አንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን” /ቁ.11/። ጌታ እንጀራውም ሆነ ዓሣው ከእዚያ በላይ ማብዛት ዓለምንም እስኪሞላ (አረ ከዚያም በላይ!) ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የጥበቡ ታላቅነት፣ የሥልጣኑ አይነገሬነት ይታወቅ ዘንድ በሥልጣኑ መጠን ሳይሆን በተራቡት ሰዎች መጠን አደረገው፡፡

   በልተው ከጠገቡ በኋላም ደቀ መዛሙርቱን፡-አንድ ስንኳ እንዳይቀር የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ” አላቸው /ቁ.12/። እንዲህም የሚላቸው አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ቍርስራሹን ለድሆች ለመስጠት ሳይሆን የተደረገው ተአምር ምትሐት አለመሆኑን ይረዱ ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፍርፋሪ አምላክ አይደለም፡፡ “ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ” /ቁ.13/። መሰቦቹ የያዙት በትንሽ በትንሽ አይደለም፡፡ እስከ አፍ ገደፋቸው ድረስ ድረስ እንጂ፡፡ ወንድሞቼ! ከአምስቱ እንጀራ የተረፈውና የተነሣው ቍርስራሽስ በሐዋርያቱ መጠን መሆኑን ታስተውላላችሁን?! በእርግጥም ጌታችን የሰራፕታዋን ሴት ማሰሮ እንዲሞላ የረሀብ ዘመኑም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይጐድል ያደረገው የኤልሣዕ አምላክ ነው /Tertullian, Against Marcion 4:21/፡፡


    ሕዝቡም ጌታ ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ፤ ጭው ባለ በረሐ እንደመገባቸው እንዳጠገባቸውም ባስተዋሉ ጊዜ፡-ነቢይ ያነሥእ- እንደ እኔ ያለ ነብይ፤ ባሕረ ኤርትራን ከፍዬ እንደተሻገርኩ በባሕሩ ላይ የሚረማመድ ነብይ፤ በሥጋ መገረዝ ፈንታ የልብን ሳንኮፋ የሚቆርጥ ነብይ፤ በኢያሱ ፈንታ ድንግሉ ዮሐንስን (ጳጳሳትን) የሚሾም ነብይ፤  በኢያሱ ፈንታ በጐቹን ለቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰጥ ነብይ ያስነሣልሃል” ተብሎ የተነገረለት ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው (የአብ የባሕርይ ልጅ ነው) አሉ /ቁ.10-14፣ St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatessaron. 12:4-5/።
  
    ከዚህ በኋላ “ቢራቡ ያመሳል፣ ቢታመሙ ይፈውሳል፣ ቢሞቱ ያስነሣል እንዲህ ያለውን ቢያነግሡት ምን ይብሳል” ብለው ይዘው ሊያነግሡት እንደወደዱ አውቆባቸው ሰው የማያነግሠኝ ልዑለ ባሕርይ ነኝ ሲል ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ /ቁ.15፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 484/።


   ወዮ አባት ሆይ! ከአፍቃሪው እጅህ አንውጣ! ሁሉ ጊዜ ከሚሳሳልን እቅፍህ አንሽሽ፡፡ አንተ ከምትወዳቸው እነርሱም ከሚወዱህ ከቅዱሳንህ ጋር በለምለሙ መስክ (በመንግሥተ ሰማያት!) አሳድረን! የምንጠራበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስም ከሥጋዊ መብል ይልቅ በሰጠኸን አማናዊው መና (ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህ) ሐሴት የምናደርግ እንደንሆን እርዳን! በዚሁ ጸጋህም ጐደሎው መሶባችንን (ሕይወታችንን) ሙላልን፡፡ አሜን አሜን!!



No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount