Wednesday, June 27, 2012

መርከቤ- በልዑል ገ/እግዚአብሔር!


የሰማይ መስኮት ተከፈተ
የፀሐይ ውበት ተከተተ
ነጎድጓድ ተደባለቀ
መብረቅ ተባረቀ
የምድር ፍልቅልቂት ፈሰሱ
የውሃ ቆሬዎች ተቸለሱ

እንዴ...
መሬት ከውሃ ነው
..........................
የተሰራች ?
መሠረቷ ግድግዳዋ
......................
ማይ የሆነች!

ግራ ቀኙ ጎርፍ
ላይ ታቹ ዝናመ ዶፍ
አለ ጣይ በረዶው ተኮሰ
ዝርጉ ባህር ተን ተነፈሰ
እምቡቅ እምቡቅ
ማየ አይህ መረቅ

ክምችት የውቅያኖስ ሙላት
ነፈረ ተንተከተከ ምድርን አጋላት

እንጃልኝ....
ከሥጋ ከእፁ ከፍጥረቱ
አንዱም ላይተርፍ ከጥፋቱ

አቤት ቁጣ...
ለምን ሰማይ ጎረፈ
ሙላቱ እስተላይ ሰፈፈ?
ክህደቱ:-
የጠፈሩን ቧንቧ ከፈተው
የእልቂቱን ዝናም አዘነመው
ሀጥያቱ:-
የምድርን ምድጃ ለኮሰው
የረጋውን ውሃውን አጋለው

እንግዲህ...
ክህደት ከሀጥያት ከተራመደ
ጎርፍ ከንፍር ተዛመደ

አይኔ እያየ...
ፍጥረት በውሃ ሲወሰድ
በሞቀባት መሬት ሲነድ

እኔ ግን...
የማትሰጥመውን ተመለከትኩ
የማትበገረውን ተከተልኩ
ጎፈር እንጨት በዙሪያዋ
አልቦ ሽንቁር መለያዋ
በጉርጆች የተሰራች
በለምለሞች የተዋበች

ውብ መርከብ መዳኛ
ስርግው ልሂቅ ተአምረኛ
ጣራ ክዳኗን ዶፍ አልበሳው
ግድግዳዋን ግለት አልበገረው
ነፋስ አውሎው አልቀየሳት
ሞገድ ማዕበል አልሰበራት

ተገረምኩ...
እኔስ:-
አይኔን አላሸሁ
ኋላዬን አላየሁ
ስራዬማ...
አካሌ ዋና አይችልም
ሰውነቴ ንፍር አያልፍም

ተፈሳህኩ ርኢክዋ
ለሐመር የዋህ

ገባሁ...
በታላቋ መርከብ ተከለልኩ
ከስጥመት ከንፍረት ተሰወርኩ

ገረምክኒ...
በጣራዋ ታቅፌ
በአጥሯ ተደግፌ
ወገኔ...
ከውስጥ ሲገቡባት
በክዳኗ ሲጠለሏት
ለካ...
ሐሴት
ድህነት
እናት ናት::

ተደሰትኩ...
ሳይ:-
ከውስጥ ወደ ደጅ
ፍጥረት ሲሰጥም ሲፈጅ

ምስኪን...
'
ዋና እችላለሁ' ያለ
...................
ሲሰጥም አየሁት
'
ንፍር አይበግረኝ' ያለ
...................
ሲቀቀል አየሁት

መርከቢቷ ተንሳፈፈች ቀዘፈች
ውስጧ አይሞላ ለሁሉ ነች::

እኔስ...
በመርከቤ አለሁ
ከጥፋቱ እድናለሁ::
..........=//=.........


(
ሰኔ21/2004..)


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount