Wednesday, February 26, 2014

ዘወረደ ዘሐሙስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

ወገኖቼ ዛሬ በሐሙስ ዜማችን በእኔ ሳይሆን .ያሬድ ዛሬ ብዙውን ስለሚወራላት ቤተ ክርስቲያ በሰጣት የጅማሬ ሰላምታ በሀክሙ እላችኋለሁ። ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የሆነ ደስ ያላችሁ ሆይ ደስ ይበላችሁ እላለሁ።

ትናንት በረቡዕ ድርሰቱ ራስን መመርመር፣ ጾምን፣ መገዛትን፣ ምስጋናን፣ መውደድን ፣ የተራበን ማጥገብን፣ ለድሃውም መፍረድን መልካም እንደሆን ነግሮን እነዚህን ሁሉ ደግሞ በጾም ወቅት ማድረጉ የበለጠ ተገቢ ነውና ጾማችንን አብረን ቀድሰን እንድንፈጽም በሰላም መንገድ እንድንጓዝ ብሎን ለዛሬ አቀብሎን ነበረ።


 በዛሬ ድርሰቱ ከሞላ ጎደል የሚያዜመው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው። ስለ ጾም ከማዜም አረፍ ያለ ቢመስልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ነገሮችን ብሏል ። ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያዜመውን ልናገር ልቤ ቢለኝም ከሰኞ ጀምሬ በዘወረደ የጾም ቃላት ላይ ስላተኮርኩ ያሉትን ጥቂት የሀሙስ የጾም ቃላት እነሆ፡-“ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ እስመ ከማሁ አዘዘነ ቀደሳ ለጾም በእንቲአነእንደተለመደው አባታችን የፍቅር አገልግሎቱን ፍቅርን በመስበክ ይጀምራል። ወቅቱ ስለሆነ እንጂ እሱስ ከጾም ፍቅር ይቀድም ነበረ። አፍቅሩ ቢጸክሙ - ወንድሞቻችሁን ጓደኞቻችሁን ውደዱ ብሎ መጀመር ይችል ነበረ። ነገር ግን አሁን ታላቅ ዐቢይ ጾም ነውና ጾማችንን በፍቅር እንድናስከትለው ጾሙን አስቀድሞ አዘዘን። ትናንትቀድሱ ጾመጾምን ቀድሱ ብቻ ነበር ያለን ዛሬ ግን በግልጥ ባለቤቱ ቀደሳት ብሎ ነገረን። ወዳጆች! እርሱ ያከበረውን ማን ያዋርዳል? እርሱ የቀደሰውን ማን ያረክሳል? እርሱ ያዘዘውን ማን ይሽረዋል ። በረከት የምንሻ ከሆነ ተባርኮ የተሰጠንን ጾም በትጋት እንጹም፡፡ እንኳንስ ተባርኮ የተሰጠን ቀርቶ አባታችን ያዕቆብ ካልባረከኝ አለቅህም አይደል እንዴ ያለው። ስለዚህ ጌታ ስለ እኛ የጾመውን ጾም እንጾም ዘንድ .ያሬድ አለን።

 ዳግመኛም ያለፉትን ቀናት አብራችሁኝ በመርከቧ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቅ.ያሬድ ጋር ስታዜሙ የነበራችሁ ቀጣዩን ቃል አስተውሉልኝ፡-“በጾምና በጸሎት ፣ በምጽዋትም ኃጢአት ሁሉ ይሰረያል።ባለፈውኮ በጾምና በጸሎት ብቻ ኃጢአት ይሰረያል ብሎ ነበር ያዜመልን። ዛሬ ደግሞ ምጽዋትን ጨመረልን፡፡ ቀስ እያደረገ በየጠቂቱ እንዴት እያሳደገን እንደሆነ ተመልከቱ። እኛ አሁን ተረጋግተን በደንብ ጾሙን ይዘናል ስንል ልክ ጌታ አንዲት ትቀርሃለች እንዳለው ባዕለ ጸጋ ሊቁም መልካም! ጾሙን ጹሙ ይህችን ደግሞ ስለ ትሩፋት እና ኃጢአት መሰረይ ጨምሩባት ምጽዋትግን ብቻዋን እንዳትሆን ተጠንቀቁ። ብቻዋን ከሆነች ግን ከህሊና ጋር ታጣላለች። ወይኔ ባልሰጠሁ ነበር እንዲህና እንዲህ እሰራበት ነበር ታስብላለች። በስጋ ያደኸየች ታስመስላለች። ከፍቅር ጋር ከሆነች ግን ለመንግስተ ሰማያት የተጣለች ዕቁብ እንጂ ኪሳራ አይደለችም። እጣዋን ክፍያዋን በኋላ እናገኘዋለን።

 ጸንተው ታግሰው ጾመው ምህረትን ለምነው ጌታ ይረዳቸዋል ይሰማቸዋል።ጾማችሁ እንደ ፈሪሳውያን አይሁን ጾምን ከትህትና ጋር ኑሯችሁ አድርጉት እንጂ ወረተኛ አትሁኑ። ከምትችሉት በላይ አትጹሙ ከምትችሉት በታችም አትጹሙ ። ቃሉን ልብ በሉት ጸንተው ታግሰው የጾሙት ጾም እና ጸሎት ይሰማልና። ምህረትን፣ ቸርነትን፣ በጎ የልብ መሻትን ያሰጣልና

 በመጨረሻም እንዲህ ብሎ ይሰናበተናልሰላምን ተቀበልን ሰላምንም ተውንላችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁንአሜንሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።ዮሐ 1427 ብሎ በማይሻር ቃሉ የነገረን አምላክ ይህን ሰላም ይስጠን።

 በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽምን። በረከቱን ያሳድርብን አምላከ .ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount