Thursday, February 27, 2014

ዘወረደ ዘዐርብ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
 
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 21 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ 

 የጽዮን አምሳያ ለሆነችው ቤተክርስቲያን እንዲህ ይላል ቅዱስ አባት ዜመኛው ኢትዮጵያዊጎሕ ጎሐ ወኮነ ጽባሐ ንሳለማ ለጽዮን ምክሐ እምነ በሀ - ሌሊቱ ነጋ ጠዋትም ሆነ መመኪያችን እናታችን ጽዮን እንሳለማት፡፡” እኔም በቤተክርስቲያን ጡቶች ያደግሁ ከእርሷ በሚሆን ወተት ላደጉና ለኖሩ ምዕመናን እናታችን ለምትሆን ለቤተክርስቲያን ዜመኛው በሰጣት ሰላምታ የጽዮን ልጆች ሆይ ሰላም ለእናንተ ይሁን ሰላማችሁ ይብዛ፡፡ ትናንት በቅኔ ማሕሌት እንደተኛው ከበሮ (ከበሮ አገልግሎት በዚህ ወቅት አይሠጥም) ሳይሆን የድካም የሆነ ወዝ (ላብ) ከማይታይበት ከላይ ታች፣ ከግራ ቀኝ፣ ወደፊት ወደኋላ በሚለው መቋሚያ እየታገዝን ዜማውን በቤተክርስቲያን ስለቤተክርስቲያን ሠምተናል፡፡ ዛሬም እንዲሁ ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን (ጽዮን) እና ቅዱስ መስቀል በመሃልም መልካም ቃለ እግዚአብሔር እንሠማለን፣ የአባታችን አምላክ ከመላእክቱ ጋር ያሰልፈን፡፡


 ቅዱስ ያሬድ ሰላማዊቷን ቤተክርስቲያን አይኖችሽን አንሺ ዙሪያሽንም ተመልከቺ እግዚአብሔር ይቅርታውን ባንቺ አድርጓል ክብርሽንም ለሌላ አልሰጥም እያለ ይነግረናል፡፡ በደሙ ያከበራትን ቤተክርስቲያን ክብርሽና ጌጥሽ እኔ ነኝ፡፡ እኔን የሚያከብር አንቺን ያከብራል፡፡ አንቺን የሚያከብር ደግሞ በቤቴ የሚገባውን የጾም ሥርዓት ይፈጽማል፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ይላል ዜመኛው፡- በቤተክርስቲያኔ በሥርዓቴ የሄደውን ይህን ድፍረት እሰጠዋለሁ፡፡ በማይሠማ ጩኸት ሳይሆን በሚደነቅ ዜማእኔ ወደ እግዚአብሔር እጠጋለሁ ብወድቅም እነሳለሁ ወደ ጨለማ ብሄድም እግዚአብሔር ያበራልኛል በእግዚአብሔር ታምኛለሁና፡፡” “የከበረች ኦሪት የበደለ ቢኖር ለሞትም ቢያደርሰው በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ ግደሉት በእንጨት ላይ የተሠቀለ የተረገመ ነውና ትላለች፡፡ ስለዚህም ነገር ለኦሪት በበደል ሳይሆን በመሠቀል ወደ ኦሪት ርግማን ገብቶ በመሰቀል ርግማኗን ሁሉ ፈታ (መጽሐፍ ምስጢር)፡፡ ቅዱሱም ያሬድ ስለዚህ እንዲህ አዜመልንየፍጹማን ብርሃን ለታረዙት ልብስ ለተቸገሩት የሚረዳ ዕውራንን የሚመራ ይኸውም መስቀል ነው፡፡ ሙሴ በትሩን አነሳ ባሕሩንም መታ የመስቀሉም ኃይል ለሁሉ ያበራል” (1ኛቆሮ1:18)፡፡ እኔ ፍጹም ነኝ እንደ እኔ ሁኑ ያለን ክርስቶስ የወደደንን እስከ መጨረሻው የወደደን በመስቀሉ ብርሃን ነው፡፡ ፍጹማኑ ከመስቀል ብርሃን ውጪ ሁሉም ጨለማቸው ነው፡፡ በኃጢአት ለተራቆቱት አዳምና ልጆቹ የመስቀል ሞት የቀድሞ ልብሳቸውን የሚመልስላቸው ነው፡፡ የተቸገሩት በመስቀሉ ፊት ያለአዚህም የተሠቀለውን አይተው ይጽናናሉ፡፡ ዕውራነ ልብ ከፊታቸው ያለውን ባሕርና ጨለማ በመስቀሉ በትርነት ከሙሴ ጋር ይከፍሉታል፡፡ እነዚህምአቤቱ እንደ አንተ ይቅር ባይ ማነው? ጨለማን አስወግደህ ብርሃንን የምታወጣ ይቅር በለን በደላችንን አታስብብንእያሉ ያዜማሉ፡፡

 ስለጾም መናጋሩን አልረሣውም፤ አላማው ልባችንን በቤቱ እና በመስቀሉ ፍቅር መትቶ የተሠበረው ማንነታችን ለጾምና ፍቅር እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እንደተለመደንጹም ጾመ. . . - ጾምን እንጹም ወንድማችንንም እንውደድ” ይላል፡፡ ድንቅ የቃላት እና የፍቅር ማረፊያ ናቸው፡፡ በንጹህ ልብ ለልዑል ምሥጋና እናቅርብ በትዕዛዝህ እንድንሄድ እርዳን ምግብን ባልበላ አንደበታችን ብቻ ሳይሆን ኃጢአት ባላደለበው ሰውነታችን ፍቅር በጠገበች ነፍሳችን አንተን እንድናከብር እርዳን፡፡

 ያቺ ጾም ለሰነፎች ሐዘን ለጠቢባን ደስታ ናትጾም ትረዳለች ምግባርም ታሰለጥናለች ሐይማኖትና ምጽዋት ደግሞ መንግስተ ሠማያት ያደርሳሉ፡፡ይገርማል፡፡ በጾም ርዳታ ባለስልጣን እንሆናለን፡፡ ስልጣን አባ አባት የምንልበትን የልጅነት ስልጣን ነው፡፡ ዜመኛው ጾም ለዚህ ትረዳለች፡፡ ከዚያም ከምግባር ጋር ታሠለጥናለች በልጅነት የሠለጠነ ደግሞ የአባቱ ሁሉ የእርሱ ነውና በኃይማኖቱ ሁሉን መጽውቶ የአባቱን መንግስት ለዘለዓለም ይወርሳል መንግታችን በዚህ አይደለም፡፡

 ቅዱስ ያሬድ ይላል፡በምድር ያለን ነገር የለም ሁላችንም ወደ ሰማይ እናስባለን . . . ልጄ ሆይአቤት አትሉምልጄ ሆይ ራስህን አታኩራየፆመኛ ሰው ሕይወት እንዲህ ነዋራስህን አታኩራ ትዕቢት ባለበት ውርደት አለ ወደ መንግስተ ሠማያት እንድትገባ አይፈቀድልህምተመልከቱ በጾም ምግባር፣ ሐይማኖትና ምጽዋት ወደ መንግስቴ የምትገቡት ከትዕቢትና ከኩራት ስትርቁ ነው እያለ በነፍስ ዜማ በዝማሜ ይነግረናል፡፡

 በመጨረሻም እንደ ጠቢባን እንጂ እንደ ሰነፎች ያለ ሕይወት እንዳንኖር መክሮን ወደ ቤታችን ወደ ልባችን ይሸኘናል፡፡ጥበቡ ለሁሉ የሆነ የእግዚአብሔርን ተስፋ ደጅ ጥኑ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ታውቁ ዘንድ ሃሳባችሁን ወደ እርሱ መልሱ ልባችሁን ጥበበኛ አድርጉ፣ ትዕዛዝህን እየጠበቅን ነፍሳችን እየተደሰተች ሥጋችን ጤነኛ እያለች በሰላም እንግባ፡፡”

 በቤተክርስቲያን ሠላምታ እንደጀመርኩ እኔም ዜማው ተሠምቶ የማይጠገበውን የአባቴን ድርሰት ኃይል በሌለው ቃል ጽፌ እንድጨርስ እኛም አብረን እንድናዜም ስለረዳን በጌታ በሚሆን የዚህ ዓለም ባልሆነ ሰላም ይጎብኘን ብዬ እፈጽማለሁ፡፡

 ደካማ ስሆን ስላልተገባኝ ነገር ስለፃፍኩ ስለ እኔ ጸልዩልኝ አሜን፡፡ በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን በረከቱን ያሳድርብን አምላክ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount