Thursday, May 3, 2012

=+= “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ”=+=

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4 የምናገኛት ሳምራይቱ ሴት ውኃ ልትቀዳ ወደ ያዕቆብ ጕድጓድ እንደመጣች እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን የክብር ንጉሥ፣ የዓለሙ መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ልቧ ሰተት ብሎ ሲገባ “ማድጋዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች”፡፡ መጽሐፍ “ሊከተለኝ የሚወድ እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ” ይላል፡፡ በእውነቱ ሐዋርያት መረባቸውን፣ መንጠቆዋቸውን ትተው የምሥራችን ለዓለም ለመንገር እንደወጡ ይህቺ ሴትም ማድጋዋን ትታ በሐሴት ሠረገላ ተጭና ወንጌሉን ለመንገር ስትሯሯጥ እናያታለን፡፡ “ለሰዎችም ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያለች መላ ከተማውን ጠራርጋ ታመጣቸው ነበር። የሚገርመው ሴቲቱ የምታመጣቸው ሰዎች እንደ እንድርያስ ወይም ደግሞ እንደ ፊሊጶስ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መላ ከተማውን እንጂ፡፡ ትጋቷም ከኒቆዲሞስ በላይ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በወልደ እግዚአብሔር ቢያምንም እንደ እርሷ ግን በግልጥ ለመመስከር አልወጣም፡፡ ሐሳብዋን ብቻ ይግለጥላት እንጂ እንዴት እንደምትነግራቸው የቃላት ምርጫ አታደርግም፡፡ እናም “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” ትላቸዋለች፡፡ ተጠራጥራ አይደለም፤ መጥተው ራሳቸው ለራሳቸው እንዲወስኑ እንጂ፡፡ ስለዚህም “ኑና እዩ፤ አይታችሁም እመኑ” እያለች ከነፍሳቸው እረኛ ጋር እንዲገናኙ ትፈልጋቸው ነበር፡፡ ሰዎቹም የምትነግራቸውን ነገር ለማየት “ከከተማ ወጥተው ወደ ጌታችን ይመጡ ነበር”። ይህች ሴት በጠዋት አዋልደ ሰማርያን ላለማየት ብላ በጠራራ ፀሐይ ውኃን ለመቅዳት የመረጠች ሴት ነበረች፡፡ አሁን ግን እውነተኛው ፀሐይ ሲነካት ሐፍረቷ እንደ በረዶ ተኖ ጠፋ፡፡ ስለዚህም ቀድሞ ወደምታፍራቸው ሰዎች በመሄድ “አንድ ነብይን ትመለከቱ ዘንድ” ሳይሆን “ያደረግሁትን ሁሉ፣ ምሥጢሬን ሁሉ የነገረኝን ሰው ትመለከቱ ዘንድ ኑ” እያለች ሕዝቡን ጠራቻቸው፡፡ እነርሱም መጡ፡፡ ትጋቷ እንዴት ድንቅ ነው? ቅናቷ እንዴት ግሩም ነው? ዛሬ የዚህችን ሴት ዜና መዋዕል ከመናገር በላይ እኛ ምን እንማራለን? ምን ያህል ቀናተኞች እንሆን? የራሳችንን ጨምሮ ምን ያህል ነፍሳት በእጃችን እንዳሉ እናውቅ ይሆን? ወንድሞቼ “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን፤ ያደረግሁትን ሁሉ የፋቀልኝን፤ በነጻ ሥርየተ ኃጢአት የሰጠኝን፤ በነጻ ልጅነት የሰጠኝን፤ በነጻ የራሱን ሥጋና ደም የሰጠኝን… ትመለከቱ ዘንድ ኑ” ብለን የምንመሰክር ስንቶች እንሆን? መክሊታችንን የቀበርን ስንቶች እንሆን? … መጽሐፍ “ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ?” ይላል… ወንድም እኅቶቼ! የምናውቃትን ያህል ከመመስከር ወደኋላ አንበል፡፡ የታመመን ሰው ሕክምና መውሰድ ያለብንን ያህል እንዲሁ ራሳችንን ጨምሮ ብዙዎችን ከመድኃኒተ ነፍሳቸው ጋር ልናገናኛቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህን እንድናደርግ እኛን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን፡፡

Wednesday, May 2, 2012

=+=እናንተ ደካሞች… /በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/=+=

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- “እናንተ ኃጢአት ሸክም የሆነችባችሁ፣ እናንተ ጭንቀት አላኖር አላስቀምጥ ያላችሁ፣ እናንተ ሐዘን የደቆሳችሁ፣ እናንተ ትእዛዛቴን በመተላለፍ ቅስማችሁ የተሰበራችሁ፣ እናንተ በሐፍረት ካባ ተከናንባችሁ የምቆዝሙ፣ እናንተ ከእንግዲህ ወዲህ አበቃልኝ በቃኝ ብላችሁ ያንገሸገሻችሁ፣ እናንተ… እናንተ ለመናገር እንኳን ድፍረት ያጣችሁ… ምንም እንኳን ዝሙት ብትሠሩም፣ ምንም እንኳን ዋሽታችሁ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን ሰርቃችሁ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን መናገር የማትችሉት ከባድ የምትሉት ኃጢአት ብትሠሩም፣ ምንም እንኳን “ከእንግዲህ ወዲህ በቃ እግዚአብሔር ይቅር አይለኝም” ብትሉም የእኔ ፍቅር፣ የእኔ ቸርነት ይህን ሁሉ ኃጢአታችሁ - ይህን ሁሉ ሸክማችሁ - ይህን ሁሉ ሐዘናችሁ - ይህን ሁሉ ከባድ የምትሉትን ነገራችሁ መደምሰስ የሚችል ነውና ኑ፡፡ ኑና ላሳርፋችሁ፤ ኑና ስለ እናንተ የቆሰለውን እጄ ተደገፉ፤ ኑና ፍቅሬን ቅመሱ፤ ኑና ቸርነቴን አጣጥሙ፤ ኑና ሸክማችሁን ሁሉ በእኔ ላይ አራግፉ፡፡ ብቻ እናንተ ፈቅዳችሁ ኑ እንጂ ከእኔ ዓቅም በላይ የሆነ ሸክም የለባችሁምና አትስጉ፡፡ ኑና ሥርየተ ኃጢአትን ልስጣችሁ፤ ኑና ዕረፍተ ነፍስን ሰጥቼ ላሳርፋችሁ፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንኳ እንደ አመዳይ አነጻላችኋለሁ፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ አጠራላችኋለሁ፡፡ ስለዚህ ኃጢአታችሁን እየቆጠራችሁ ከምትቆዝሙ ቀና በሉና ወደ እኔ ኑ፡፡ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ልጆቼ ወደ እኔ ቅረቡ፡፡ እኔም ልቅረባችሁ፡፡ “ቀንበሬን ተሸከሙ” ስላችሁ በሩቁ አትፍሩኝ፡፡ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና፡፡ ደግሞም ይህ ቀንበር አንገታችሁን ለማለዘብ (ለመላጥ) ሳይሆን በቀጭኒቱ መንገድ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ እኔ ወዳዘጋጀሁላችሁ ርስት መንግሥት የምታደርስ ናትና በሩቁ አትፍሯት፡፡ ስለዚህ እናንተ ደካሞች፣ እናንተ ዓቅመ ቢሶች፣ እናንተ ከእኔ ውጪ ምንም ማድረግ የማትችሉ በገዛ ደሜም የገዛኋችሁ ልጆቼ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ማዳን ብቻ ሳይሆን አሳርፋችኋለሁ፡፡”

የጉብዝናን ወራት እንደ ዮሴፍ!!

ብዙዎች እንደሚስማሙት የጉብዝና ወራት የሚባለው ከ20 እስከ 40 ዓመት ያለ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ወራት ደግሞ ብዙዎቻችን በጸረ ክርስትና ፍልስፋናዎች ማለትም ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ኮሙኒዝም፣ ግራ ዘመም እና ቀኝ ዘመም ፖለቲካ የምንያዝበት ወራት ነው፡፡ ሂዩማኒዝም የሚባል የፍልስፍና ዓይነት “የችግሮቻችን መፍትሔ ሁሉ ያለው በእኛ እጅ እንጂ በሌላ አካል አይደለም” ይላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን “አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ” ይላል /ኤር.10፡23/፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ይኸንን ቢያውቅ “ቅዱስ መንፈስህን ከእኔ አትውሰድብኝ” አለ /መዝ.50፡12/፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ ብዙ ወጣቶች ለአላስፈላጊ ግብረ ሥጋ ግንኝነት፣ ለጫት፣ ለሐሽሽ፣ ለስካር ይጋለጣሉ፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ. በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ኰሌጅ ውስጥ ከገቡ ወጣቶች 71% ሳይጋቡ የግብረ ሥጋ ግንኝነት ያደርጋሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይላል፡- “ልጄ ሆይ ስማ ጠቢብም ሁን፤ የልብህን ሐሳብ አቅና፡፡ የወይን ጠጅ ጠጭ አትሁን፤ ለሥጋም አትሣሣ፤ ሰካራምና አመንዝራ ይደኸያል” /ምሳሌ.23፡19-22/፡፡ ወጣቱ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ለብዙዎቻችን አርአያ ሊሆን የሚችል ነውና ከሕይወቱ መማር ያስፈልገናል፡፡ 1. ዮሴፍና የወንድሞቹ ቅናት፡ ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብ ከወንደሞቹ ይልቅ በሥነ ምግባሩ መልካምነት አብልጦ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ይጠሉት ነበር፣ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልወደዱም፡፡ የዮሴፍ ልብ ግን ያው ነበር እንጂ አልተቀየረም፡፡ ወንድሞቹን ይወዳቸው ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሰማያት ተከፍተው እየተመለከተ ወንድሞቹ ሁሉ ለእርሱ እንደሚሰግዱ ሲያይ የነበረው፡፡ ወንድሞቹ ሰማያዊውን መልእክት ከማስተናገድ ይልቅ የገዛ ወንድማቸውን የበለጠ ይጠሉት፤ ይቀኑበትም ነበር፡፡ ዮሴፍ የእነርሱን ቅናት ሳይመለከት በፍጹም ፍቅር ይወዳቸዋልና ከሴኬም ወደ ኬብሮን፣ ከኬብሮንም ወደ ዶታይን እየተቅበዘበዘ በበረሀው ደኅንነታቸውን ይመለከት ነበር፡፡ እነርሱ ግን ከሩቅ ሆነው እርሱን በመመልከት ይገድሉት ዘንድ ይማከሩ ነበር፡፡ ከዚሁ ይልቅ ግን እሱን በመሸጥ የሚያገኙትን ገንዘብ በማየት እንዲሁም ደግሞ በዓይናቸው እንኳን እንዳያዩት ለእስማኤለውያን ሸጡት፡፡ እርሱ እነርሱን በመውደድ ቢመጣም እነርሱ ግን በቅናት ተቃጥለው ጠበቁት፡፡ ቅናት አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታ ላይ ቅናት ስለያዛቸው ቤታቸው እንደ ተፈታ ቀርቷል፤ መዳን ከእነርሱ ቤት ቀርቷል፤ ሐዋርያትን አሳድዷል፡፡ ወንድሞቹ ከቅናታቸው የተነሣ የዮሴፍን ልብስ ደም በመንከር እርሱ እንደ ሞተ በማስመሰል አባታቸውን አሳዝነዋል፤ ለብዙ ቀናት አስለቅሰውታል፤ ይጽናናም ዘንድ አልወደደም፡፡ 2. የዮሴፍ ንጽህና እና የጴጢፋራ ሚስት፡ ምንም እንኳን ዮሴፍ እንደ ባርያ ለእስማኤለውያን ቢሸጥም ልቡ ግን እንደ ባርያ አልነበረም፡፡ ከምንም በላይ ረዳቱ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነውና ጭንቀት የሚባል ነገር አይታይበትም ነበር፡፡ ባርያ ቢሆንም ግብጽን ከረሀብ ታድጓታል፡፡ ምንም ወንድሞቹ በቅናት ወደ ባርነት ቢሸጡትም እርሱ ግን በፎርዖን ቤት ነገሠ፡፡ በፎርዖን ዘንድ ባለሟልነትን አገኘ፡፡ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ የውስጡ ውበት በየዕለቱ ይፈካ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን ልቡ ወደ ትዕቢት አላዘነበለበትም፡፡ በዚሁ ሰዓት ግን ሌላ ፈተና ተጋረጠበት፡፡ የንጉሡ ሚስት ታስነቅፈው ዘንድ ወደደች፡፡ ይህም ቢሆን ግን ምናልባት ልብሱ ትቀድበት እንደ ሆነ እንጂ ልቡን ታቆሽሽበት ዘንድ አልተቻላትም፡፡ ዮሴፍ እንደ ስሙ ጥንካሬ እና ንጽህናን እየጨመረ ሄደ፡፡ ወንደሞቹን እንደወደዳቸውም የጴጢፋራን ሚሰት ይወዳት ነበር፡፡ ስለዚህም ነበር ልብን በሚያቆስል አነጋገር “አንቺ አመንዝራ ሴት ነሽ፤ ከአመንዝራ ሴትም ጋር እተኛ ዘንድ አይገባም” ሳይላት ስለ ራሱ ብቻ ይናገር የነበረው፡፡ እርሷ ንግሥት እርሱ ግን ባርያ እንደሆነም ይነግራት ነበር፡፡ ምንም ወደ ወኅኒ ብትጥለውም አንዳች እንኳን አልመለሰላትም፡፡ እርሷ ግን በተቃራኒው እንኳንስ እርሱን ራሷንም የማትወድ ምስኪን ነበረች፡፡ ምክንያቱም ወዳውስ ቢሆን ኖሮ ወደ እስር ቤት ባልጣለችው ነበርና፤ ራሷንም የምትወድ ብትሆን ኖሮ ንግሥት ሆና ሳለ ይህን የመሰለ አሳፋሪ ሥራ አታደርግም ነበርና፡፡ ስለዚህ እርሷ በፍቅር ሳይሆን በዝሙት የተቃጠለች ሴት ነበረች፡፡ ምንም እንኳን ዮሴፍ አብርሃም እና ይስሐቅን ከመሰሉ ታላላቅ አባቶች የተወለደ ቢሆንም ራሱን ከፍ ከፍ ሳያደርግ ለፎርዖን ይታዘዝ ነበር፡፡ ንጽህናው ለወጣት ወንዶች ሁሉ አርአያ ነው፡፡ አዎ! ወንዶች ከዮሴፍ፣ ሴቶች ከሶስና ደናግላንም ከድንግል ማርያም ንጽህናን መማር ይገባናል፡፡ ይህን ንጽህና እንይዝ ዘንድ ጌታ ይፈልጋል፡፡ ይኸንንስናደርግ አምላካችን ይደሰታል፤ በሕይወታችንም እንደ ዮሴፍ ይባርከናል፡፡ ምንም እንኳን ዮሴፍ ልብሱን ትቶላት ቢሮጥም እንደ አዳም ግን አላፈረም፡፡ ንጽህናው በገነት ውስጥ ሆኖ ከበደለው አዳም ትበልጥ ነበርና፡፡ እንግዲያስ እኛም ወጣቶች ክብራችንን ለማጉደፍ እንቅልፍ ላጣች ዓለም ልብሳችንንም እንኳን ቢሆን ጥለንላት ከዝሙት ግብዣዋ እንራቅ (ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡ ይህንን ስናደርግ በእርግጥም መስቀላችንን ተሸክመናልና የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንባላለን፡፡ ኤልያስ የዚህ ዓለም የሆነውን መጐናጸፍያ በዚሁ ዓለም ትቶት እንደ ሄደ እኛም የዓለም የሆነውን ለራሷ እንስጣት (ቅዱስ ጀሮም)፡፡ 3. ዮሴፍና የማያቋርጥ አገልግሎቱ፡ ከላይ እንደገለጽነው የጴጢፋራ ሚስት የዮሴፍን ልብ መውሰድ ስላልተቻላት ልብሱን ብቻ በመያዝ እርሱን በመክሰስ የባሏን ቁጣ ታነሣሣበት ዘንድ ትጮኽ ነበር፡፡ ለካ የሴፍ ወደ እስር ቤት የተጣለው ለወንጀለኞችም የሚያስተምረው ትምህርት ስለ ነበረው ነው፡፡ አንዳንዴ ለእኛ የማይገባን እግዚአብሔርኛ ክንውኖች በእኛ ሕይወት ውስጥ ይከናወናሉ፡፡ የጴጢፋራ ሚስት ምንም በዙፋኗ ብትሆንም ከወንጀለኛ ሰው በላይ ብስጩ ነበረች፤ ዮሴፍ ግን “በወኅኒም” ቢሆን በወኅኒ ጠባቂው ዘንድ ሞገስን ስላገኘ እጅግ ደስተኛ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ ስለ ነበረ ወኅኒ ቤቱ ገነት ሆኖለታል፡፡ ዮናስ በዓሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ስለ ገባ የባሕሩ ወጀብና ማዕበል አላሰጠመውም፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ውስጥ ቢጣዱም ወላፈኑ ጨርቃቸውን እንኳን አልነካውም፡፡ ጌታ ዛሬም እንደ ዮሴፍ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ እንሆን ዘንድ ይሻል፡፡ እርሱ በእኛ ውስጥ ካደረ የትም ብንሆን አንጨነቅም፡፡ እርሱ ዕረፍታችን ነውና፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ እኛን ለመጉዳት የመጡት ሆኔታዎችም እኛን ይጠቅሙ ዘንድ ጌታ ይቀይራቸዋል፡፡ ጌታ ጠላት ብለን በምናስባቸው ሰዎች እጅ እንኳን ማሳደግ እንደሚችል ከሙሴ ተምረናልና፡፡ ዮሴፍ ወደ እስር ቤቱ ባይገባ ኖሮ ሴትዮዋ አሥር ጊዜ እየመጣች “አብረን እንተኛ፤ ዝሙትም እንፈጽም” እያለች በጨቀጨቀችው ነበር፤ አሁን ግን ወደ ወኅኒ ስለ ጣለችው ይኸ ሁሉ ቀርቶለታል፡፡ በእስር ቤቱ ውስጥ ሆኖም እስረኞቹን እንደ ወንድሞቹ ያገለግላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱ በሄደበት ሁሉ ሁሉንም በትሕትና ያገለግል ነበር፡፡ ለካስ እኛ ወጣቶች ትሕትናን ገንዘብ ስናደርግ ወደ ሕይወት ነው የምንወጣው!! 4. ዮሴፍ እና ሥልጣን፡ ዮሴፍ ከፍቅር ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ማለትም የሚጠሉት ወንድሞቹን፣ የጴጢፋራን ሚስት እንዲሁም እስረኞችን በመውደድ በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ካጠናቀቀ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ክብር ዙፋን አውጥቶታል፡፡ ሲወጣም የመጀመርያ ሥራው የግብጽ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሊፈቱት ያልቻሉትን ሕልም መፍታት ነበር፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ማንም ሊፈታው ያልቻለ ጥያቄ በእኛ በወጣቶች እጅ ይገኛል፡፡ እንደ ዮሴፍ እግዚአብሔርን አጋዥ የምናደርግ ከሆነ በየጊዜው የሚፈታተነን የድርቅ ዘመን በጥጋብ ማለፍ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር በረከት ከእኛ ጋር ትሆናለች፡፡ በየትኛውም የሐላፊነት ቦታ ብንቀመጥም የተበደለውን ደሃ እንረዳለን እንጂ አናስጨንቅም፡፡ 5. ዮሴፍና ይቅርታ፡ የእስራኤል ልጆች ወንድማቸውን ከሸጡት በኋላ በረከት ርቋቸው በረሀብ ተጠቁ፡፡ በረከቱ ከዮሴፍ ጋራ ወደ ግብጽ ሄዷልና፡፡ ወንድሞቹ “ዳግም አናየውም” ያሉትን ዮሴፍ ጌታ በሀገራቸው ረሀብ አመጣ እና ዳግም እንዲገናኙት አደረገ፡፡ ወንደሞቹ ሲመጡ ግን ክፋታቸው ያውቁ ዘንድ አንዳንድ ማንቅያ ድርጊቶችን ከማድረግ ውጪ በፍቅር ተቀበላቸው እንጂ አልተበቀላቸውም፡፡ መጀመርያ ሲገናኛቸውም ስለ ፍቅሩ ለብቻው እየሄደ ያለቅስ ነበር፡፡ ዛሬ ክፉ ላደረጉብን ሁሉ ልናለቅስላቸውና ልናዝንላቸው ይገባል፤ ለእነርሱም እንባችንን እንጂ ቁጣችንን ልንስጣቸው አይገባንም፤ ካደረጉት መጥፎ ነገር የተነሣ ሊያጋጥማቸው ከሚችል ክፉ ሁሉ ይድኑ ዘንድ እንማልድላቸው ዘንድ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እየገፉን ያሉት (እነርሱ እንደዚያ ባያስቡትም) ወደ ክብር አክሊል ነውና፡፡ የዮሴፍ ወንድሞች እርሱን ከመፍራታቸው የተነሣ ፊቱን እንኳን ማየት አልቻሉም፡፡ መልካም ስናደርግ ከቃላችን በላይ ድርጊታችን ይናገራል፡፡ ዛሬ በኃጢአት ምክንያት ከእኛ አውጥተን የሸጥነውን ዮሴፋዊ ማንነታችን “እኔ ነኝ” ሲለን ዳግም በፍቅር ልንቀበለው ያስፈልጋል፡፡ ይኸንን ለማድረግም ፈጽመን አንፍራ፡፡ እግዚአብሔር የሚያየው የትላንቱ ኃጢአተኛ ማንነታችን ሳይሆን የዛሬውን የይቅርታ፤ የንስሐ እና እርሱን የፈለግንበት ልባችንን ነውና፡፡ ዮሴፍ ወንድሞቹ ያደረጉበትን ሳይሆን እግዚአብሔር ለምን ዓላማ ወደዚያ ሀገር እንዳመጣው ይነግራቸው ነበር፡፡ ስለ ተቀመጠበት ወንበርም ዓላማውን ይነግራቸው ነበር እንጂ ከዚያ የተነሣ በወንድሞቹ ላይ ድሮ እነርሱ እንዳሰቡት ክፋትን አላሰበም፡፡ እርሱ የይቅርታ እንጂ የበቀል ልብ የለውምና፡፡ ወንድሞቼ እና እኅቶቼ!! አንድ ነገር ልንገራችሁ? የዮሴፍ አምላክ የእኛም አምላክ ነው፡፡ ከእኛ ፈቃድን ብቻ ይሻል፡፡ እኛን የመለወጥ ኃላፊነት የእርሱ እንጂ የእኛ አይደለም፡፡ ስለዚህ “ጌታ ሆይ እኔ መለወጥ እፈልጋለሁ፡፡ የመለወጥ ኃይል ግን የለኝም፡፡ ስለዚህ ለብዙ ዘመናት ‘ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ’ ያልከኝን ልቤን ውሰድና ያንተው ምርጥ ዕቃ አድርገኝ” እንበለው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋራ መጣበቅን እንውደድ፤ አላስፈላጊ መድሐኒቶችን እና መጠጥን አቁመን ጓደኞቻችንን እንምረጥ /1ቆሮ.15፡33፣ ምሳሌ.13፡20/፡፡ የደስታ ምንጭ መንፈስ ቅዱስ እንጂ እነዚህ ሱሶች አይደሉምና፡፡ ወደ ቤቱ መመላለስን እንለማመድ፡፡ በኋላ በክርስቶስ ፊት ከምናፍር ዛሬ ከእርሱ ጋር ሁነን ደስ ይበለን፡፡ አይዟችሁ እርሱ ከእኛ በላይ ለእኛ ቅርብ ነው፡፡ ሊረዳንም ዝግጁ ነው፡፡ እንበርታ፤ እንጨክን፡፡ እርሱ በእጃችንን ሲይዘን እኛም “አንለቅህም” ብለን እንያዘው፡፡ ዲያብሎስን ግን፡- “ከአሁን በኋላ የጌታየ እንጂ ያንተው አይደለሁም፤ እስከ ዛሬ ድረስ ላታስተኛኝ ተኛ ያልከኝን ይበቃሀል” እንበለው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በጉብዝናችን ወራት ከቅናት የጸዳን፣ ንጽህናን ገንዘብ ያደረግን፣ አገልግሎታችንም ሁሉ በትሕትና እና በይቅርታ የተመላ ያድርግልን፡፡ አሜን!!

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ…!!

እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ሁሉ ከእኛ ሊሰርቅ የሚፈልግ አንድ ጠላት አለን፡፡ የዚህ ጠላት ጦር ግን በዓይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ አይደለም፡፡ ጠላታችን እርሱ ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ በዓይናችን ልናየው አንችልም፡፡ ማየት አንችልም ማለት ግን ሀልዎት የለውም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ጥንተ ጠላታችን እኛን ከእግዚአብሔር ከመለየት በላይ የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡ ሰይጣን በጣም ተንኰለኛ ነው፤ እኛን ከፈጣሪያችን ለመለየት የማይጠቀምበት ዘዴ የማይፈነቅለውም ድንጋይ የለም፡፡ ስለዚህ እርሱን ለመዋጋት ሁሌ መዘጋጀት አለባችሁ እንጂ “እንዲህማ ከሆነ” ብላችሁ ሰይጣንን ልትፈሩት አይገባም፡፡ ይህንን ለማደረግም እንደ ወታደር ትጥቃችሁን ሁሉ ልትታጠቁ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በዚህ ወርሐ ጾም! ጠላታችሁ መንፈስ ቢሆንም እግዚአብሔር ይህን ጠላት ድል የምታደርጉበት መንፈሳዊ ጦር ይሰጣችኋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፡፡ ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ጠበቅ አድርጉት፡፡ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ይወዳችኋል፤ ስለ ኃጢአታችሁ ብሎ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ያፈቅራችኋል! አሁንም ይህ ፍቅርና እውነት የሆነው እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ይህን እውነት ጠበቅ አድርጋችሁ ታጠቁት፤ እንዲህ ስታደርጉም በብርታትና በኃይል ሰይጣንን ድል ታደርጉታላችሁ፡፡ ልባችሁ ይጽና!! የጽድቅ ጥሩርንም ልበሱ፡፡ ሁል ጊዜ መልካም የሆነውን ብቻ አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ ሰይጣን ወደ እናንተ ለመምጣት ወደ ልባችሁም ሾልኮ ለመግባት ዕድል አያገኝም፡፡ እንዲህ ስታደርጉ ሰይጣን እናንተን መጣል ስለማይችል ተደላድላችሁ ትቆማላችሁ፡፡ ቀጥላችሁም እግሮቻችሁ በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት ይጫሙ፡፡ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ይህንን ወንጌል ወደዚህ ቦታና ሰው አድርስ ሲላችሁ ለመሄድ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡ በሁሉም ላይ ጨምራችሁም የሚምበለበሉትን የሰይጣንን ፍላጻዎች ሁሉ ታጠፉ ዘንድ የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነውና በርቱ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋልና ጽኑ! ብቻ እምነታችሁ ሁሉ በእርሱ ይሁን እንጂ ሰይጣን በእናንተ ላይ አንዳች አያደርግም፡፡ የመዳንን ራስ ቁር ያዙ፡፡ አሁን መዳናችሁን ወደ ምትፈጽሙበት የሕይወት ልምምድ ገብታችኋል፤ የእግዚአብሔር የልጅነትን ሥልጣን አግኝታችኋል፤ የሰይጣን ኃይሉ መክኗል፤ ሞትም ድል መንሳቱ ቀርቷል፡፡ ስለዚህ እናንተን ከእግዚአብሔር ለይቶ ሊወስድ የሚችል አካል የለምና ባላችሁበት ጽኑ፡፡ በመጨረሻ የመንፈስን ሰይፍ ያዙ፡፡ አዎ! እግዚአብሔር የሰይጣንን ውሸትና ክስ ድል የምናደርግበት መሣርያ ሰጥቶናል፡፡ የተሰጠን መሣርያም ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰይጣንን ሐሳብ ሁሉ ከንቱ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በዚሁ በጾም ወራት ጌታችን ጠላትን በቃሉ ወደ መሬት ሲጥለው እንደነበር እናንተም በእግዚአብሔር ቃል ሰይፍ ቆራርጡት፡፡ ሁል ጊዜ ይህን ሰይፍ ለመታጠቅ ቸል አትበሉ፡፡ አሁን እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፡፡ ከእጁም ማንም ሊነጥቃችሁ አይችልም፡፡ ብቻ እናንተ ይህን የሰይጣን ፍላጻ ልታጠፉበት የምትችሉበትን የእምነት ጋሻ አንሡ፡፡ ሁል ጊዜ እውነት እውነቱን ብቻ ተናገሩ፡፡ መልካም የሆነውንም አድርጉ፡፡ እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ቸርነት ደግሞም በምን ዓይነት ፍቅር እንደወደዳችሁ ለመናገር ቸል አትበሉ፡፡ ይህን የፍቅር ጽዋ ሌሎች እንዲቀምሱት ጋብዝዋቸው፡፡ እናንተም አሁን ካላችሁበት በላይ ጨምራችሁ አጣጥሙት፡፡ እምነታችሁ ሁሉ በእርሱ ጣሉት፡፡ እግዚአብሔር ስለናንተ ብሎ እስከምን ድረስ እንደደረሰ ሁል ጊዜ ከማሰብ አትቆጠቡ፡፡ ሊይዛችሁ ደግሞም እንዳትወድቁ ቀና ሊያደርጋችሁ ሲፈልግ እጃችሁን ከመስጠት አትቦዝኑ፡፡ ስለዚህ ሰይጣንን እግዚአብሔር በሰጣችሁ ሰይፍ (በቃሉ) ለመቆራረጥ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡ ሰይጣን እግዚአብሔር የሰጣችሁን ነገር ለመንጠቅ በዙርያሁ ይዞራል- ነገር ግን አንዳች ስንኳ አትጨነቁ- እግዚአብሔር አሁንም አብሯችሁ ነው! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል!! እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነውና በርቱ! የተዋሕዶ ልጆች ትጉ! በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ታመሙት፣ ስለ ተሰደዱት፣ ስለታሰሩት፣ ስለ ዝናብ፣ ስለ አዝርእት… ጸልዩ! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል!!

FeedBurner FeedCount