Monday, July 16, 2012

ጌታ ሆይ ከአንተ ወደ ማን እንሄዳለን?-የዮሐንስ ወንጌል የ31ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡53-ፍጻሜ)!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
   ስለ ሰማያዊ ነገር፣ ስለ መንፈሳዊ ቃል በምንናገርበት ጊዜ አፍአዊ ምድራዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን ሁሉ ከእኛ ዘንድ የራቁ መሆን ይገባል፡፡ ወደ አንድ ምድራዊ ንጉሥ በቀረብን ጊዜ ሐሳባችን ልባችን ሁሉ በምንም ነገር እንደማይባክን መንፈስ ቅዱስ ሲናገረንም ከዚሁ በበለጠ በአርምሞና በአንቃዕዶ ሆነን ልንቀርብ ልናደምጥ ይገባናል፡፡ ዛሬ የምንማማረው ትምህርትም ይህን የመሰለ ልብ የሚጠይቅ የሚፈልግ ነው፡፡ የአይሁድ ሰዎች አቀራረባቸው ሁሉ እንዲህ አፍአዊ፣ ሥጋዊና ደማዊ ስለ ነበረ ጌታችን በሚነግራቸው የሕይወት ቃል ግራ ሲጋቡ፣ ሲጨቃጨቁ፣ ሲያንጐራጕሩ እንመለከታቸዋለን፡፡ “ይህ ሰው ሥጋዉን እንበላ ዘንድ እንደምን ሊሰጠን ይችላል? አንዳንድ ጉርሻስ እንኳ ይደርሰናልን? ደግሞስ ዕሩቅ ብእሲ ሥጋዉን ቢበሉት ደሙንም ቢጠጡት ደዌ ይሆናል እንጂ ሕይወት ይሆናልን?” እያሉ ሲታወኩበት፣ ሲከራከሩበት እናስተውላቸዋለን /ቁ.52/፡፡ ጌታችን ግን “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ” በማለት  ሥጋዉን ሊበሉት ደሙንም ሊጠጡት መስጠት የሚቻል ብቻ ሳይሆን ይኸን ሰማያዊ መብል ይኸን ሰማያዊ መጠጥ አለመብላት አለመጠጣትም ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሳጣ እንደሆነ ይነግራቸው ያስረዳቸው ነበር /ቁ.53/። ንግግሩንም በዚህ ያበቃ አይደለም፤ ጨምሮም፡-ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት የሌላት የማታልፍ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል፥ እኔም በመጨረሻው ቀን በዕለተ ምጽአት በክብር አስነሣዋለሁ፤ አድነዋለሁ” አላቸው እንጂ /ቁ.54፣ St. John Chrysostom, Hom.47./ 

   ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ገና ወንጌሉን ሲጀምርልን “ቃልም ሥጋ ነሣ” በማለት ነገሩን ያቆመ አይደለም፡፡ ፍጹም ተዋሕዶአቸውን ለማሳየት “ቃልም ሥጋ ሆነ” አለን እንጂ /ዮሐ.1፡14/፡፡ ይህን ሲልም ከእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቀዳማዊ ቃል ባሕርይውን ለውጦ ሥጋ ሆነ ማለቱ አይደለም፡፡ ሥጋም ወደ መለኰትነት ተለወጠ አላለንም፡፡ ቃል የቃልነት ባሕርይውን ሥጋም የሥጋ ባሕርይውን ይዞ በፍጹም ተዋሐደ እንጂ፡፡ ሕይወትን ላጡ ፍጥረታት ሕይወትን የሚሰጥ ቀዳማዊ ቃል የሰው ልጆች ሊረዱት ሊመረምሩት ከሚችሉት በላይ በሆነ በተዋሕዶ ምሥጢር የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ፡፡ ለሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ሰጠው፡፡ ሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ፡፡ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ የነበረውን ሞት በእርሱ ባሕርይ አጠፋልን፤ ሥጋ በባሕርዩ ሕይወት የሆነ ቃልን ተዋሕዷልና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን የሚበላ ክቡር ደሙን የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” በማለት ተናገረ፡፡ ሆኖም ግን “ሥጋዬ ያስነሣዋል” አላለም፤ “ሥጋዬን የበላውን ደሜንም የጠጣውን ሰው አስነሣዋለሁ” እንጂ፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ የለምና፡፡… ስለዚህ ምንም እንኳን ሞት የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙርያችን ቢዞርም ሥጋችንንም ልናስወግደው ወደማንችለው መበስበስ ሊቀይረው ቢሞክርም ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ከሆንን ግን በእርግጠኝነት (ለክብር ለሕይወት) እንነሣለን፡፡ ሥጋው እስራኤል ዘሥጋ ጊዜአዊ የሥጋን ረሀብ እንዳስታገሰላቸው መና ያይደለ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚያድል እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሙም እስራኤል ዘሥጋ በገዳም ጊዜአዊ የሥጋ ጥማቸውን እንዳረካላቸው ውኃ ያይደለ እውነተኛ መጠጥ ነውና /ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ በዲ/ን ታደለ ፈንታው ገጽ 154/፡፡ 

    ስለዚህም ነው በሰዋዊ አመክንዮ ሲታወኩ ለነበሩ አይሁድ፡- ሥጋዬ እውነተኛ (የማያልፍ፣ የማይሻር፣ የማይለወጥ )መብል ነው፤ ደሜም እውነተኛ (የማያልፍ፣ የማይሻር የማይለወጥ) መጠጥ ነው፡፡ የዚህ ዓለም መብል እውነተኛ አይደለም፡፡ ማታ ተበልቶ ጧት ይርባልና፤ ጧት ተበልቶ ማታ ያስፈልጋልና፡፡ ኃላፊ ጠፊ ስለሆነም በቀን ብዙ ጊዜ ይበላል፡፡ እኔ የምስጣችሁ መብል፣ እኔ የምሰጣችሁ መጠጥ ግን በኃጢአት ካላሳደፉት በቀር ቀዋሚ ዘላለማዊ ነው፡፡ በአሚን በንጽሕ ሆኖ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ ግን በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ (በልግስና በጸጋ) ተዋሕጄው እኖራለሁ” የሚላቸው /ቁ.55-56/። አዎ! ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ብቻ ሳይሆን ከውጪ ያሉትንም በክርስቶስ አምነውና በስሙ ተጠምቀው ወደዚሁ ቅዱስ ምሥጢር እንዲቀርቡ እንዲቀበሉትም የምታበረታታቸው ስለዚሁ ነው፡፡ መዝሙረኛው እንደተናገረ፡- “ደሙ የሰውን ነፍስ ደስ የሚያሰኝ መጠጥ፣ ሥጋዉም ኃይለ ነፍስን የሚያፀና መብል ነውና” /መዝ.104፡15 ትርጓሜው፣ Saint Ambrose, On the Mysteries 9:55, 58. /፡፡

  ጌታችን አሁንም ከማር የጣፈጠ ሕይወትም የሆነ ቃሉን ይቀጥልና እንዲህ ይላቸዋል፡- “ሕያው አብ (ለተዋሕዶ) እንደ ላከኝ እኔም ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ስለተወለድኩ ሕያው ነኝ፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ (በጸጋ ስለምዋሐደው) ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። አባቶቻችሁ መናውን በገዳም በልተው እንደ ሞቱ ያይደለ ከሰማይ የወረደ ኅብስት ይህ ነውና (ሥጋዬ ነውና)፡፡ ይህን እንጀራ የሚበላም ለዘላለም ሕያው ሆኖ ሞተ ነፍስ (ትንሣኤ ዘለሐሳር) ሳይኖርበት በተድላ በደስታ በሕይወት ይኖራል”/ቁ.57-58፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታው ገጽ 488/፡፡

  ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው ይህ የአይሁድ ዓይነት ቁርባን ያይደለ ንጹሕ የዘለዓለምንም ሕይወት የሚሰጥ ቁርባን ነው /ሚል.1፡10-11,St. Irenaeus Adv. Haer. 4:17:5, 6./፡፡

    በነቢዩ ኢሳይያስ “በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም” /ኢሳ.45፡19/ እንዳለ በቅፍርናሆም ባለ በምኵራብ ሲያስተምራቸው ይኸን (በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ እውነተኛ ሥጋዬ ነው፤ እውነተኛ ደሜ ነው እያለ ስለ ሥጋወደሙ) ነገራቸው፤ አስተማራቸው” /ቁ.59/ ተወዳጆች ሆይ! ሥጋዉንና ደሙን ምሳሌ አለማለቱን እናስተውል፡፡ አምሳል አምሳል እንጂ እውነተኛ አይደለምና፡፡ አንድ ሰው መታሰብያን ብቻ ተቀብሎ ለዘለዓለም በሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር አይችልምና፡፡ ለአማናዊው የክርስቶስ ጥምቀት ምሳሌ የነበረችው የኦሪት የውኃ መታጠብ የዘለዓለም ድኅነት መስጠት የማትችል ይልቁንም ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ የምታስቀር እንደሆነች ሁሉ “ሥጋውና ደሙ እውነተኛ መብል አይደለም፤ ምሳሌ መታሰብያ እንጂ” የሚሉም የዘለዓለም ሕይወት የሌላቸው ይልቁንም ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ የቀሩ የወጡ ናቸው፡፡

  ጌታችን ስለ ሁለት ምክንያት በምኵራብ አስተማራቸው፡፡ አንደኛ ብዙ ሕዝብ ባለበት ቦታ በማስተማሩ ምክንያት ብዙዎች በእርሱ ያምናሉና፡፡ ሁለተኛ እርሱ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ጋር ፍጹም ተቃርኖ እንደሌለው እነርሱም (አይሁድም) እንደሚያስቡት እርሱ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ እንዳልሆነ ያስረዳቸው ዘንድ በምኵራብ አስተማራቸው /St.John Chrysostom, Ibid/፡፡

   ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች ይኸን (የምሥጢረ ቁርባኑን ትምህርት) በሰሙ ጊዜ ረቀቀባቸው ራቀባቸውና፡-ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ማንስ ልብ ሊለው ይችላል? የሰው ሥጋስ እንደምን ሕይወትን ሊሰጥ ይችላል?አሉ /ቁ.60, St. Augustine,On the Gospel of St. John, tractate 27:1./። ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን የሚያውቅ /ዕብ.4፡12/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ምክንያት እንደታወኩ በልቡ አውቆ፡-ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ ወልደ እጓለ እመሕያው (የሰው ልጅ- ክርስቶስ) ቀድሞ ወደ ነበረበት (ያስተውሉ! እንዲህ ማለቱ ሥጋ ከጥንት ነበረ ከሰማይም ይዞት ወረደ ማለት ሳይሆን ቀዳማዊ ከሆነው ቃል ጋር በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ አንድ አካል መሆኑን መግለጽ ነው!)ሲያርግ ብታዩ እንደምን ደንቃችሁ ይሆን?  ሥጋዬ ሕይወትን እንደሚሰጥ በነገርኳችሁ ጊዜ ልባችሁ ከታወከ ሳርግ ብታዩኝ ‘ማ ምን ልትሉ ነው? ዕሩቅ ብእሲ ሲሆን እንደምን እንደ ወፍ ወደ ላይ ሊበር ሊወጣ ቻለ ልትሉ ነውን? ይህ ግን ለዕሩቅ ብእሲ የማይቻል ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን አፈር የነበረው ሥጋ እንዲህ በተዋሕዶ አክብሬ የባሕርይ አምላክ እንዳደረግኩት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ያደረኩትም እኔ ነኝ፡፡ የእኔን ሰው የመሆን ምሥጢር (ምሥጢረ ተዋሕዶን) በመረመራችሁ ባስተዋላችሁ ጊዜ ሰው የሆንኩት እኔ የሚያድን መለኰት እንደሆንኩ፤ ዕሩቅ ብእሲ ግን አንዳች እንደማይጠቅም (ሕይወትን እንደማይሰጥ) ትገነዘባላችሁ፡፡ ስለዚህ እኔ የነገርኋችሁ ቃልም መንፈስ (ረቂቅ) ነው፤ ሕይወትም ነውና በግዙፍ አእምሮ (እኔን ወልደ ዮሴፍ በሚል ልቡና) ሳይሆን በውስጣችሁ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ተረዱት፤ በእምነትም ተቀበሉት። ይህ ሥጋ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ሕይወት የሆንኩትን እኔን (ዮሐ.1፡5) ተዋሐዷልና ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡ ነገር ግን ከእናንተ ይህን የማያምኑ አሉ” አላቸው /ቁ.61-63፣ St.Cyril Of Alexandria, Ibid/።

  ጌታችን የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ (አይሁድ ፈሪሳውያን እንደሆኑ) አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ (ይሁዳ እንደሆነ) ከጥንት ጀምሮ ያውቅ ነበርና እንዲህ አላቸው /ቁ.64፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 489/።

  አሁንም ጨምሮ እንዲህ አላቸው፡- እስራኤል ዘሥጋ ባለማመናቸው ምክንያት ዕረፍተ ፍልስጥኤምን ሳይወርሱ እንደቀሩ ሁሉ አንድ ሰው በልቡ ፈቅዶ ወዶ ከዚያምዕውቀቱ ከአባቴ (ረድኤተ እግዚአብሔር) የተሰጠው ካልሆነ በቀር ወደ እኔ ሊመጣ በእኔም ማመን የሚቻለው የለም፤ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን መውረስን አይቻለውም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ”። እንዲህ ስላላቸውም ከሕዝቡ ወገን ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። በጌታ ማመን ምርጫቸው አልነበረምና “ጽድቅ በዕድል ከሆነስ እንግዲያ ምን ያደክመናል?” በማለት የራሳቸውን አመክንዮ በመስጠት ጌታን ከመከተ ቀሩ /ቁ.65-66/፡፡ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ከብርሃን ይለቅ በጨለማ መቀመጥን ይወዳሉ፤ ዓይነ ልቡናቸው ከማመን የታወሩ ሰዎችም ከፀሐይ ከክርስቶስ ርቀው በጨለማ መኖርን ይመርጣሉ /ቅ.ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ ዝኒ ከማሁ/፡፡

   ጌታችንም ሰዎቹ በፍቃዳቸው ወደ ኋላ እንደተመለሱ አይቶ ለአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ (ያለፈቃዳቸው ይነዳሉ የሚል ነገር እንዳይኖርና ወደው ፈቅደው ሊከተሉት እንደሚገባ ሲያስረዳቸው)፡-እናንተም ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” አላቸው /ቁ.67፣ Cyprian the Martyr Letter 59 to Cornellius: 7./። ስምዖን ጴጥሮስ ግን፡-ጌታ ሆይ! የዘላለም ደኅንነት የሚሰጥ ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደ ማን እንሄዳለን? ከሕይወትስ ወጥተን ወዴት እንሄዳለን?  እኛስ አንተ የሕያው እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ እንደ ሆንህ አምነንብሃል፤ የዘላለምን ሕይወትም በቅዱስ ሥጋህና በክቡር ደምህ ልትሰጠን እንደመጣህ አውቀናል ተረድተናልም” ብሎ መለሰለት /ቁ.68-69፣ Saint Augustine,27:9/። ጌታችንም፡-እናንተ እንድታውቁት ብዬ እንጂ አሥራ ሁለታችሁንማ እኔስ ከፍጹም ፍቅሬ የተነሣ የመረጥኋችሁ አይደለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ የእኔን ፍቅር ያላስተዋለ ሰይጣን (መስተቃርን መስተጻርር) ነው” ብሎ መለሰላቸው /ቁ.70/።

 ይህን ነገር (እስከሚያሲዘው ድረስ በግልጽ ሳይሆን በምሥጢር) የተናገረ ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ነው፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና /ቁ.71/፡፡ ጌታችን እንዲህ ስላለም ከሁሉም ይልቅ ጴጥሮስ በእጅጉ ታውኮ ነበር /ዮሐ.13፡24/፡፡ ይህም የሆነው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ አስቀድሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! መከራ መስቀል ከቶ አይሁንብህ” ሲለው “ወደኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን” ብሎት ስለነበር አሁንም ከእናንተ አንዱ ሰይጣን ነው ሲል “እኔ እሆንን?” በማለት ነበር /St.John Chrysostom, Ibid/።

   ወዬ አባት ሆይ! በሲና በረሐ ምድራዊ መብልን በልተው ምድራዊ መጠጥንም ጠጥተው እንደሞቱ እንደነዚያ እንዳንሞት ሰማያዊ መብል ሰማያዊ መጠጥ ሆነህ መጥተህ ሳይገባን ስለ ሰጠኸን እናመሰግንሃለን፡፡ ከመጀመርያው አዳም ጋር እንዳንሞት ይልቁንም ከሁለተኛው አዳም (ከአንተ ጋር) የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረን ራስህን መብልና መጠጥ አድርገህ ስለሰጠኸን እናመሰግንሃለን፡፡ እንግዲያውስ አባት ሆይ! ከምድራዊ መብል ጋር ስንታገል ካዘጋጀህልን ሰማያዊ ማዕድ (ከቅዱስ ሥጋህና ከክቡር ደምህ) የራቅን እንዳንሆን ይልቁንም በፍርሐትና በረዐድ ሆነን እንድንቀርብ እንድንቀበል እርዳን፡፡ ይህን ሥጋህን በልተን ይህንንም ደምህን ጠጥተን አንተ በእኛ እኛም በአንተ እንድንኖር እንድትዋሐደን እርዳን፡፡ አባት ሆይ! ሕይወት የሆነውን፣ ደኅንነትም የሚገኝበትን ቃልህን ሰምተናል፡፡ መድኃኒታችን ሆይ! ታድያ ከአንተ ወዴት እንሄዳለን? ፍቅር ከሆንከው ከአንተ ርቀንስ ምን ሕይወት አለን? ቅዱስ አባት ሆይ የቸርነትህን ሥራ ሥራልን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!


Thursday, July 12, 2012

.......ብርሃናተ ዓለም......





ማነው በሁለት እግሩ ዓለምን የዞረ
ጽፎ ተናግሮ ዘክሮ ወንጌል የነገረ?
ይህች አለት ናት የቤቴ መሠረት
በሷ ቤቴን ሰራሁ ኮኩሐ ሐይማኖት

አባቴ ዼጥሮስ ...
እስኪንገረኝ...
የቱ ይበልጣል?
መረብ በባህሩ መወርወር
ወንጌል ለዓለሙ መናገር ?
ዓሣን ....ማደን
ሕዝብን ማዳን?
የቱ ይበልጣል አባቴ ...?
በጀልባ መዋሉ
ጌታን ማገልገሉ?

ተወው ዼጥሮስ ...
ለካ እኔ ሞኙ
ያልገባኝ ምስጢሩ
የበለጠውን በተግባር ነግረኸኝ
ዓለምን ተፍተህ ሞተህ አሳየኸኝ

ወዮ!......ወዮ!...
ወዮልሽ ሮም!
የኒሮን ዓለም
የቄሳሮች ሃገር
የግፍ ድንበር
የደም ባህር

ወዮልሽ ሮም ...
የዼጥሮስ ስቅለት ክስ ይሁንብሽ
የቅዱሱ ችንካር ምስክር ይጥራብሽ
በእጇ ያለ ወርቅ
............ሮም አልደመቀችበት

Wednesday, July 11, 2012

በዓለ ዕረፍቶሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በታናሽ ኤስያ እየዞረ በቃሉ እያስተማረ በመልእክትም እየጻፈ ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ በመከራም እንዲታገሱ እየመከረ ካጽናናቸው በኋላ በሮሜ ለክርስቶስ መስክሮ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ዘመኑ ሲደርስ በ67 ዓ.ም ወደ ሮሜ ገብቶ ያስተምር ጀመር፡፡

ኔሮን ቄሳርም በዚያ ዘመን በክርስቲያን ላይ የሚቃጠለው የቁጣ እሳት ገና አልበረደለትም ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ አሰረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በምሴተ ሐሙስ ጌታው በተያዘ ጊዜ ስለ ደረሰበት ፈተና ጌታዉን አላውቀዉም ብሎ መካዱ ብቻ ትዝ እያለው ያዝን ነበር እንጂበመታሰሩ አላዘነም ነበር፡፡…

ኔሮን ቄሳርም ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ ካሰረው በኋላ ወደ አካይያ ዘምቶ ነበርና በዘመቻው ድል አድርጎና ደስ ብሎት ወደ ሮሜ ሲመለስ አረማውያን የሆኑ መኳንንቱን ደስ ለማሰኘትና አማልክቱን ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ሁሉ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስም ሞት በመስቀል እንዲሆን ታዘዘ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን ወአመሰ ልሕቅ ባዕድ ያቀንተከ ሐቄከ ወይወስደከ ሀበ ኢፈቀድከ ብሎ የነገረው ቃል ትዝ አለውና አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡

የሚቀልበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከግዞት ቤት አውጥተው ሲወስዱት ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ እኩል እንዳልሆን ራሴን ወደ ታች ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ ብሎ ለመነ፡፡

በሮማውያን ሥርዓት ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሮሜ ተወላጅ የሆነ እንደሆነ የወንጀሉ ትልቅነት እየታየ ግርፋት ወይም ሞት ይፈረድበታል እንጂ በአንድ ወንጀል ሁለት ቅጣት አይፈረድበትም፡፡
የውጭ ሀገር ወንጀለኛ እንደሆነ ግን ቅጣቱ ግርፋት እንደሆነገርፈው እስራት ይጨምሩበታል፡፡ ቅጣቱ ሞት እንደሆነ ግን አስቀድመው ገርፈው በኋላ በመስቀል ወይም በሌላ መሣርያ ይገድሉታል፡፡…

ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስንም እንደ ሥርዓታቸው አስቀድመው ገርፈው በኋላ ራሱን ወደ ታች እግሩን ወደ ላይ አድርገው ሰቅለው ገደሉት፡፡ የተሰቀለውም በሐምሌ 5 /68 ዓ.ም ነው፡፡

ከሞተም በኋላ መርቄሎስ የሚባለው ደቀ መዝሙሩ ከመስቀል አውርዶ እንደ ሀገሩ ልማድ ሬሳውን በወተትና በወይን አጥቦ ሽቱ ቀብቶ በነጭ ልብስ ገንዞ ማር በተመላ ሣጥን ውስጥ አግብቶ አሁን ዛሬ ቫቲካን በሚባለው ሥፍራ ቀበረው፡፡
በረከቱና ረድኤቱ አይለየን!
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ቅዱስ ጳውሎስና ኔሮን ቄሳር በማናቸውም ነገር የማይስማሙ አጥፊና ጠፊ ነበሩ፡፡ ኔሮን ቄሳር ክፉና ዐመጸኛ ነበር፤ ቅ/ጳውሎስ ግን ደግና ፈቃደኛ ነበር፡፡ ኔሮን ቄሳር ከሐዲና ጨለማ በቃኝ የማይልንፉግ የሰይጣን ማደርያ ነበር፤ ቅ/ጳውሎስ ግን ሃይማኖታዊና ብርሃን በቃኝ የሚል ቸር የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለቱ ተጻራሪዎች በተገናኙና በተያዩ ጊዜ አንዱ የአንዱን ነገር አያስተውለውም ነበር፡፡ ስለዚህ ቅ/ጳውሎስ ወደ ፍርድ ሸንጎ ከቀረበ በኋላ ይፈታ ወይም ይቀጣ ሳይባል ወደ ግዞት ቤት መለሱት፡፡

ነገር ግን በሮሜ ከተማ ቅ/ጳውሎስ አስቀድሞ ያሳመናቸው ክርስቲያኖች እየበዙ ትምህርታቸውም እየበዛ መሔዱ በቅ/ጳውሎስ ምክንያት መሆኑን ኔሮን ቄሳር ስለተረዳው ይልቁንም ከቤተ መንግሥቱ ሹሞች ወገን ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ስለ አሳመነበት የቤሮን ቄሳር ቁጣው ተመለሰበትና ጳውሎስን እንደገና ወደ ፍርድ ሸንጎ አቅርቡት ብሎ

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል አራት!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ውድ ክርስቲያኖች! የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም ይብዛላችሁ! አሜን!
በክፍል ሦስት ትምህርታችን ወደ ስድስት የሚሆኑ ነጥቦችን አይተን ነበር፡፡ ለዛሬም ቸሩ አምላካችን በፈቀደልን መጠን ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡
1. መሥዋዕትን አንዴ (አንድ ጊዜ) ያቀረበ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ለኃጢአት ሥርየት የሚያቀርቡት መሥዋዕት ፍጹም ድኅነትን ስለማይሰጥ ዕለት ዕለት ይሠዉ ነበር፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አንድ ቀን ስለ ዓለም ሁሉ መዳን በቀራንዮ ላይ መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ የዓለምን ኃጢአት ስላስወገደ በእርሱ ያመነ ሁሉ ተረፈ ኃጢአት (የማይደመሰስ ኃጢአት) ስለማይኖርበት በየጊዜው ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ አያስፈልገውም፡፡ ዓለም ሁሉ በእርሱ ካመነ በዕለተ ዐርቡ መሥዋዕት ይድናል እንጂ ሌላ ተጨማሪ መሥዋዕት አይቀርብለትም፡፡ የኃጢአተኛ ተለዋጭ ሆኖ የቀረበው የመሥዋዕቱ በግ ክርስቶስ አንድ ነውና /ዕብ.7፡27-28/፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ አምነን ተጠምቀን የክርስቶስ ማደርያ ከሆንን በኋላ ክፉ ሐሳብ ወደ ራሳችን ሰብስበን ወይም ደግሞ ሰው አገብሮን ተጋፍቶን በገቢር ብንበድል (ሃይማኖታችንን  ክደን ቆይተን ብንመለስ እንኳን) ዳግመኛ ንስሐ ገብተን እንመለሳለን እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ ሁለተኛ ጥምቀት ሁለተኛ መሥዋዕት አይቀርብልንም፤ ወልደ እግዚአብሔርንም ዳግመኛ ተሰቀልልን መከራ ተቀበልልን የለምንለው አይደለም /ዕብ.10፡26/፡፡
2. በአብ ቀኝ የተቀመጠ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ወደ ምድራዊቱ ቅድስት ሥፍራ በዓመት አንድ ጊዜ በብዙ ፍርሐትና ረዐድ ይገቡ ነበር፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንዲህ አልገባም፡፡ ሐዋርያው፡- “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፡፡ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፡፡ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት” እንዲል /ዕብ.8፡1-2/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ እንደ ወረደ ግልጽ ነው /ዮሐ.3፡13/፡፡ ሆኖም ግን “ወረደ” የሚለው አገላለጽ ለምልዓተ መለኰቱ ወሰን ለሌለው ለመለኰታዊ ቃል የሚስማማ አይደለም፡፡ ሰው ሆኖ፣ ሥጋ ለብሶ፣ ባጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ ለድኅነተ ዓለም መገለጡን፤ ለሕማም፣ ለሞት፣ ለመሥዋዕትነት መምጣቱን የሚገልጽ እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ሲናገር፡- “ወልድ ዋሕድ እንደ መላእክት ቦታውን የለቀቀ አይደለም፤ በአንድ ፈቃድ ከአባቱ ጋር እያለ ነው እንጂ፡፡ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ በተላከ ጊዜ እንደ መላእክት ቦታውን ለቆ የሄደ አይደለም፤ እነዚያ በተላኩ ጊዜ ቦታቸውን ለቀው ይሄዳሉና፡፡ በምልዓት ሳለ እንደ መላእክት ቦታውን ሳይለቅ ሥጋን ተዋሐደ እንጂ” ይላል /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድር.3፡153-158/፡፡ ልክ እንደዚሁ “ተቀመጠ” የሚለው ቃልም ሥራዉን መጨረሱን፣ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን፣ ድኅነተ ዓለም መፈጸሙን የሚያመለክት እንጂ እንደተናገርነው ለምልዓተ መለኰቱ ቦታ ተወስኖለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም ይህን ሲያመሰጥሩት፡- “ጌታ ከምልዓተ መለኰቱ የተወሰነበት ወቅት ኑሮ መንበረ ክብሩን ተቆጣጠረ ወይም ከመለኰታዊ ክብሩ ተራቁቶ ኑሮ ወደ መለኰታዊ ክብሩ በተመለሰ ጊዜ መለኰታዊ ክብሩን ተቆጣጠረ ማለት ሳይሆን ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ሰማያዊ ያልነበረውን (ክብር የለሽ የነበረውን) የሰውን ባሕርይ ማክበሩንና በእርሱ ክብር መክበራችን፣ በክብር ቦታ መቀመጣችን፣ የሰው ልጅ ሁሉ በክርስቶስ መክበሩን ነው” ይላሉ /ኤፌ.2፡6-7/፡፡ “በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉ ይሁን” አሜን /ራዕ.5፡14/፡፡
3. በገዛ ደሙ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉዩ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ የዚህ ዓለም (አፍአዊ) ወደ ሆነችው መቅደስ ይገባ ነበር፡፡ አገልግሎቱም ሁሉ ምድራዊ ዓለማዊ ነበር፤ ሥጋን እንጂ ነፍስን መቀደስ የማይቻለው ነበር /ዘሌ.16፡3/፡፡ እንደ ወንበዴ ከወንበዴዎች ጋር የተሰቀለው፣ የተናቀው፣ ገሊላዊ፣ የዓለምንም ኃጢአት ያስወገደው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንደተጻፈ በደመ በግዕ በደመ ላህም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባ አይደለም፡፡ ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ ተወካፌ መሥዋዕት (መሥዋዕት ተቀባይ)፣ ራሱ ይቅር ባይ ሊቀ ካህናት አስታራቂ መሥዋዕት አቅራቢ ሆኖ ገባ እንጂ /ዮሐ.1፡29, St. Augustine, On Ps. 65./፡፡ ሐዋርያው፡- “ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን የዘለዓለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም” እንዲል /ዕብ.9፡11-13/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጠቀም ብሎ ሳይሆን ቅዱሳንን ሊያገለግል ደሙን ይዞ የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን ማን ናት? “ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ በምትበልጠውና በምትሻለው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በዘር በሩካቤ ባልተከፈለች  /ማቴ.1፡20/ በሥጋው መሥዋዕት በኵል /ዕብ.10፡20/ ስለ እኛ ይታይ ዘንድ፣ እንደ አይሁድ ሐሳብ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅድ  መስቀል ላይ በሠዋው አንድ መሥዋዕት ከራሱ ከባሕርይ አባቱና ማኅየዊ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታርቀን ዘንድ የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን እዝነ አብ (የአብ ጀሮ) ገጸ አብ (የአብ ፊት) ናት” /St.John Chrysostom, Homily on the Epistle Of Hebrews, Hom.15፣ ዕብ.9፡24/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ጌታችን ወደ እዝነ አብ ወደ ገጸ አብ አቀረበን ስንል (በሥላሴ ዘንድ ተከፍሎ ስለሌለ) የታረቅነው ከሥላሴ ጋር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ መሥዋዕት ተቀባዩ አብ ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንትም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይህን ክፍል በተረጐሙበት አንቀጽ፡- “ለምትመጣው ሕግ ለወንጌል ሊቀ ካህናት ሆኖ የመጣው ክርስቶስ ግን በምክንያተ ዘርዕ ያይደለ እንበለ ዘርዕ ወደተገኘች ወደ ደብተራ ርእሱ፣ በሰው ፈቃድ ያይደለ በእርሱ ፈቃድ ወደ ተተከለች ደብተራ መስቀል ደመ ላህም፣ ደመ ጠሊን ይዞ የገባ አይደለም፤ ደሙን ይዞ አንድ ጊዜ ወደ እዝነ አብ ወደ ገጸ አብ ገባ እንጂ” ብለዋል /የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነትርጓሜው፣ ገጽ 441/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! አንድ ፍጹም ልንረሳው የማይገባ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ እርሱም ምን እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይነግረናል፡- “የጌታችን አገልግሎቱ እዚህ ምድር በመስቀል ላይ የተፈጸመ ቢሆንም እንደ ቀደሙት ሊቃነ ካህናት ምድራዊ አገልግሎት አልነበረም፤ ሰማያዊ እንጂ፡፡ ለምን ቢሉ ምእመናን በእርሱ አምነን መጠመቅን ገንዘብ አድርገን የሰማያውያን ሥራ እየሠራን የእርሱ ልጆች እንሆናለንና፡፡ ሐሳባችንም ሀገራችንም መንግሥተ ሰማያት ነውና፡፡  ምስጋናችንም ከመላእክት ጋር ኅብረት አንድነት ያለው ሰማያዊ ነውና፡፡ መሥዋዕታችንም እንጨት ማግዶ እሳት አንድዶ የሚቀርብ የላም የበግ ደም ሳይሆን ሰማያዊው መሥዋዕት (ክርስቶስ) ነውና፡፡ ሕጉም (ወንጌሉም) ክህነቱም ሰማያዊ ነውና፡፡ መሥዋዕታችን እንደ ቀደመው ኪዳን መሥዋዕት አመድና ጢስ እንዲሁም መዓዛ ሆኖ የሚቀር ሳይሆን ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ የሚሆን ክብር ነውና፡፡ ይህን የምናከናውንበት ሥርዓተ ቅዳሴአችንም ሰማያዊ ነውና” /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድር.14፡58-77/፡፡ የስነ መለኰት ምሁራንም እንዲህ ሲሉ ይህን የቅዱሱ ሐሳብ ያጐለሙሱታል፡- “ምንም እንኳን በምድራዊቷ ድንኳን (ቅድስት ቤተ ክርስቲያን) ብንሆንም ክርስቲያኖች ወደዚሁ ቅዱስ መሥዋዕት (ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ) በምንቀርብበት ሰዓት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንገባለን፤ ማንነታችን ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ /Kairos/ ይሆናል፡፡ እዚህ ሆነን የመንግሥተ ሰማያትን ኑሮ እንለማመዳለን፡፡ ከመለኰታዊ ባሕርይ ተካፋይ እንሆናለን፡፡ ትላንት፣ ዛሬና ነገ ከሚለው ማንነታችን /Chronos/ ወጥተን “አሁን” /Kairos/ ወደሚለው ማንነታችን እንቀየራለን፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገ የሚሉ አገላለጾች የሉምና፡፡ ወደ ፊት ደግሞ (ዓለም ሲያልፍ) ከጊዜ መፈራረቅ ውጪ ሆነን ለዘለዓለሙ ወደዚሁ ማንነታችን (ወደ Kairos) እንለወጣለን፡፡ ወደ ቅዱስ ቁርባን ስንቀርብ ከጠብና ከበቀል የራቅን እንሁን የሚባልበት ምሥጢርም ማንነታችን ከዚህ ምድር ስለሚለይ ነው፡፡ በሰማያዊ ሕይወት ጠብና በቀል የለምና፡፡ እነዚህን ሳናስወግድ ስንቀርብ ግን ያው እላይ መሆናችን ቀርቶ እታች ነን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የተቀበልን መስሎንም ሳንቀበል እንቀራለን፡፡ ሳይገባን ይህን እንጀራ ስለበላን ወይም የጌታን ጽዋ ስለጠጣንም ዕዳ ይሆንብናል” /1ቆሮ.11፡27/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! ሳምንት ይቀጥላል!!

FeedBurner FeedCount