Monday, July 16, 2012

ጌታ ሆይ ከአንተ ወደ ማን እንሄዳለን?-የዮሐንስ ወንጌል የ31ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡53-ፍጻሜ)!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
   ስለ ሰማያዊ ነገር፣ ስለ መንፈሳዊ ቃል በምንናገርበት ጊዜ አፍአዊ ምድራዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን ሁሉ ከእኛ ዘንድ የራቁ መሆን ይገባል፡፡ ወደ አንድ ምድራዊ ንጉሥ በቀረብን ጊዜ ሐሳባችን ልባችን ሁሉ በምንም ነገር እንደማይባክን መንፈስ ቅዱስ ሲናገረንም ከዚሁ በበለጠ በአርምሞና በአንቃዕዶ ሆነን ልንቀርብ ልናደምጥ ይገባናል፡፡ ዛሬ የምንማማረው ትምህርትም ይህን የመሰለ ልብ የሚጠይቅ የሚፈልግ ነው፡፡ የአይሁድ ሰዎች አቀራረባቸው ሁሉ እንዲህ አፍአዊ፣ ሥጋዊና ደማዊ ስለ ነበረ ጌታችን በሚነግራቸው የሕይወት ቃል ግራ ሲጋቡ፣ ሲጨቃጨቁ፣ ሲያንጐራጕሩ እንመለከታቸዋለን፡፡ “ይህ ሰው ሥጋዉን እንበላ ዘንድ እንደምን ሊሰጠን ይችላል? አንዳንድ ጉርሻስ እንኳ ይደርሰናልን? ደግሞስ ዕሩቅ ብእሲ ሥጋዉን ቢበሉት ደሙንም ቢጠጡት ደዌ ይሆናል እንጂ ሕይወት ይሆናልን?” እያሉ ሲታወኩበት፣ ሲከራከሩበት እናስተውላቸዋለን /ቁ.52/፡፡ ጌታችን ግን “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ” በማለት  ሥጋዉን ሊበሉት ደሙንም ሊጠጡት መስጠት የሚቻል ብቻ ሳይሆን ይኸን ሰማያዊ መብል ይኸን ሰማያዊ መጠጥ አለመብላት አለመጠጣትም ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሳጣ እንደሆነ ይነግራቸው ያስረዳቸው ነበር /ቁ.53/። ንግግሩንም በዚህ ያበቃ አይደለም፤ ጨምሮም፡-ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት የሌላት የማታልፍ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል፥ እኔም በመጨረሻው ቀን በዕለተ ምጽአት በክብር አስነሣዋለሁ፤ አድነዋለሁ” አላቸው እንጂ /ቁ.54፣ St. John Chrysostom, Hom.47./ 

   ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ገና ወንጌሉን ሲጀምርልን “ቃልም ሥጋ ነሣ” በማለት ነገሩን ያቆመ አይደለም፡፡ ፍጹም ተዋሕዶአቸውን ለማሳየት “ቃልም ሥጋ ሆነ” አለን እንጂ /ዮሐ.1፡14/፡፡ ይህን ሲልም ከእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቀዳማዊ ቃል ባሕርይውን ለውጦ ሥጋ ሆነ ማለቱ አይደለም፡፡ ሥጋም ወደ መለኰትነት ተለወጠ አላለንም፡፡ ቃል የቃልነት ባሕርይውን ሥጋም የሥጋ ባሕርይውን ይዞ በፍጹም ተዋሐደ እንጂ፡፡ ሕይወትን ላጡ ፍጥረታት ሕይወትን የሚሰጥ ቀዳማዊ ቃል የሰው ልጆች ሊረዱት ሊመረምሩት ከሚችሉት በላይ በሆነ በተዋሕዶ ምሥጢር የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ፡፡ ለሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ሰጠው፡፡ ሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ፡፡ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ የነበረውን ሞት በእርሱ ባሕርይ አጠፋልን፤ ሥጋ በባሕርዩ ሕይወት የሆነ ቃልን ተዋሕዷልና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን የሚበላ ክቡር ደሙን የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” በማለት ተናገረ፡፡ ሆኖም ግን “ሥጋዬ ያስነሣዋል” አላለም፤ “ሥጋዬን የበላውን ደሜንም የጠጣውን ሰው አስነሣዋለሁ” እንጂ፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ የለምና፡፡… ስለዚህ ምንም እንኳን ሞት የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙርያችን ቢዞርም ሥጋችንንም ልናስወግደው ወደማንችለው መበስበስ ሊቀይረው ቢሞክርም ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ከሆንን ግን በእርግጠኝነት (ለክብር ለሕይወት) እንነሣለን፡፡ ሥጋው እስራኤል ዘሥጋ ጊዜአዊ የሥጋን ረሀብ እንዳስታገሰላቸው መና ያይደለ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚያድል እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሙም እስራኤል ዘሥጋ በገዳም ጊዜአዊ የሥጋ ጥማቸውን እንዳረካላቸው ውኃ ያይደለ እውነተኛ መጠጥ ነውና /ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ በዲ/ን ታደለ ፈንታው ገጽ 154/፡፡ 

    ስለዚህም ነው በሰዋዊ አመክንዮ ሲታወኩ ለነበሩ አይሁድ፡- ሥጋዬ እውነተኛ (የማያልፍ፣ የማይሻር፣ የማይለወጥ )መብል ነው፤ ደሜም እውነተኛ (የማያልፍ፣ የማይሻር የማይለወጥ) መጠጥ ነው፡፡ የዚህ ዓለም መብል እውነተኛ አይደለም፡፡ ማታ ተበልቶ ጧት ይርባልና፤ ጧት ተበልቶ ማታ ያስፈልጋልና፡፡ ኃላፊ ጠፊ ስለሆነም በቀን ብዙ ጊዜ ይበላል፡፡ እኔ የምስጣችሁ መብል፣ እኔ የምሰጣችሁ መጠጥ ግን በኃጢአት ካላሳደፉት በቀር ቀዋሚ ዘላለማዊ ነው፡፡ በአሚን በንጽሕ ሆኖ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ ግን በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ (በልግስና በጸጋ) ተዋሕጄው እኖራለሁ” የሚላቸው /ቁ.55-56/። አዎ! ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ብቻ ሳይሆን ከውጪ ያሉትንም በክርስቶስ አምነውና በስሙ ተጠምቀው ወደዚሁ ቅዱስ ምሥጢር እንዲቀርቡ እንዲቀበሉትም የምታበረታታቸው ስለዚሁ ነው፡፡ መዝሙረኛው እንደተናገረ፡- “ደሙ የሰውን ነፍስ ደስ የሚያሰኝ መጠጥ፣ ሥጋዉም ኃይለ ነፍስን የሚያፀና መብል ነውና” /መዝ.104፡15 ትርጓሜው፣ Saint Ambrose, On the Mysteries 9:55, 58. /፡፡

  ጌታችን አሁንም ከማር የጣፈጠ ሕይወትም የሆነ ቃሉን ይቀጥልና እንዲህ ይላቸዋል፡- “ሕያው አብ (ለተዋሕዶ) እንደ ላከኝ እኔም ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ስለተወለድኩ ሕያው ነኝ፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ (በጸጋ ስለምዋሐደው) ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። አባቶቻችሁ መናውን በገዳም በልተው እንደ ሞቱ ያይደለ ከሰማይ የወረደ ኅብስት ይህ ነውና (ሥጋዬ ነውና)፡፡ ይህን እንጀራ የሚበላም ለዘላለም ሕያው ሆኖ ሞተ ነፍስ (ትንሣኤ ዘለሐሳር) ሳይኖርበት በተድላ በደስታ በሕይወት ይኖራል”/ቁ.57-58፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታው ገጽ 488/፡፡

  ነቢዩ ሚልክያስ እንደተናገረው ይህ የአይሁድ ዓይነት ቁርባን ያይደለ ንጹሕ የዘለዓለምንም ሕይወት የሚሰጥ ቁርባን ነው /ሚል.1፡10-11,St. Irenaeus Adv. Haer. 4:17:5, 6./፡፡

    በነቢዩ ኢሳይያስ “በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም” /ኢሳ.45፡19/ እንዳለ በቅፍርናሆም ባለ በምኵራብ ሲያስተምራቸው ይኸን (በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ እውነተኛ ሥጋዬ ነው፤ እውነተኛ ደሜ ነው እያለ ስለ ሥጋወደሙ) ነገራቸው፤ አስተማራቸው” /ቁ.59/ ተወዳጆች ሆይ! ሥጋዉንና ደሙን ምሳሌ አለማለቱን እናስተውል፡፡ አምሳል አምሳል እንጂ እውነተኛ አይደለምና፡፡ አንድ ሰው መታሰብያን ብቻ ተቀብሎ ለዘለዓለም በሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር አይችልምና፡፡ ለአማናዊው የክርስቶስ ጥምቀት ምሳሌ የነበረችው የኦሪት የውኃ መታጠብ የዘለዓለም ድኅነት መስጠት የማትችል ይልቁንም ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ የምታስቀር እንደሆነች ሁሉ “ሥጋውና ደሙ እውነተኛ መብል አይደለም፤ ምሳሌ መታሰብያ እንጂ” የሚሉም የዘለዓለም ሕይወት የሌላቸው ይልቁንም ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ የቀሩ የወጡ ናቸው፡፡

  ጌታችን ስለ ሁለት ምክንያት በምኵራብ አስተማራቸው፡፡ አንደኛ ብዙ ሕዝብ ባለበት ቦታ በማስተማሩ ምክንያት ብዙዎች በእርሱ ያምናሉና፡፡ ሁለተኛ እርሱ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ጋር ፍጹም ተቃርኖ እንደሌለው እነርሱም (አይሁድም) እንደሚያስቡት እርሱ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ እንዳልሆነ ያስረዳቸው ዘንድ በምኵራብ አስተማራቸው /St.John Chrysostom, Ibid/፡፡

   ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች ይኸን (የምሥጢረ ቁርባኑን ትምህርት) በሰሙ ጊዜ ረቀቀባቸው ራቀባቸውና፡-ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ማንስ ልብ ሊለው ይችላል? የሰው ሥጋስ እንደምን ሕይወትን ሊሰጥ ይችላል?አሉ /ቁ.60, St. Augustine,On the Gospel of St. John, tractate 27:1./። ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን የሚያውቅ /ዕብ.4፡12/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ምክንያት እንደታወኩ በልቡ አውቆ፡-ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ ወልደ እጓለ እመሕያው (የሰው ልጅ- ክርስቶስ) ቀድሞ ወደ ነበረበት (ያስተውሉ! እንዲህ ማለቱ ሥጋ ከጥንት ነበረ ከሰማይም ይዞት ወረደ ማለት ሳይሆን ቀዳማዊ ከሆነው ቃል ጋር በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ አንድ አካል መሆኑን መግለጽ ነው!)ሲያርግ ብታዩ እንደምን ደንቃችሁ ይሆን?  ሥጋዬ ሕይወትን እንደሚሰጥ በነገርኳችሁ ጊዜ ልባችሁ ከታወከ ሳርግ ብታዩኝ ‘ማ ምን ልትሉ ነው? ዕሩቅ ብእሲ ሲሆን እንደምን እንደ ወፍ ወደ ላይ ሊበር ሊወጣ ቻለ ልትሉ ነውን? ይህ ግን ለዕሩቅ ብእሲ የማይቻል ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን አፈር የነበረው ሥጋ እንዲህ በተዋሕዶ አክብሬ የባሕርይ አምላክ እንዳደረግኩት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ያደረኩትም እኔ ነኝ፡፡ የእኔን ሰው የመሆን ምሥጢር (ምሥጢረ ተዋሕዶን) በመረመራችሁ ባስተዋላችሁ ጊዜ ሰው የሆንኩት እኔ የሚያድን መለኰት እንደሆንኩ፤ ዕሩቅ ብእሲ ግን አንዳች እንደማይጠቅም (ሕይወትን እንደማይሰጥ) ትገነዘባላችሁ፡፡ ስለዚህ እኔ የነገርኋችሁ ቃልም መንፈስ (ረቂቅ) ነው፤ ሕይወትም ነውና በግዙፍ አእምሮ (እኔን ወልደ ዮሴፍ በሚል ልቡና) ሳይሆን በውስጣችሁ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ተረዱት፤ በእምነትም ተቀበሉት። ይህ ሥጋ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ሕይወት የሆንኩትን እኔን (ዮሐ.1፡5) ተዋሐዷልና ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፡፡ ነገር ግን ከእናንተ ይህን የማያምኑ አሉ” አላቸው /ቁ.61-63፣ St.Cyril Of Alexandria, Ibid/።

  ጌታችን የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ (አይሁድ ፈሪሳውያን እንደሆኑ) አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ (ይሁዳ እንደሆነ) ከጥንት ጀምሮ ያውቅ ነበርና እንዲህ አላቸው /ቁ.64፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 489/።

  አሁንም ጨምሮ እንዲህ አላቸው፡- እስራኤል ዘሥጋ ባለማመናቸው ምክንያት ዕረፍተ ፍልስጥኤምን ሳይወርሱ እንደቀሩ ሁሉ አንድ ሰው በልቡ ፈቅዶ ወዶ ከዚያምዕውቀቱ ከአባቴ (ረድኤተ እግዚአብሔር) የተሰጠው ካልሆነ በቀር ወደ እኔ ሊመጣ በእኔም ማመን የሚቻለው የለም፤ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን መውረስን አይቻለውም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ”። እንዲህ ስላላቸውም ከሕዝቡ ወገን ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። በጌታ ማመን ምርጫቸው አልነበረምና “ጽድቅ በዕድል ከሆነስ እንግዲያ ምን ያደክመናል?” በማለት የራሳቸውን አመክንዮ በመስጠት ጌታን ከመከተ ቀሩ /ቁ.65-66/፡፡ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ከብርሃን ይለቅ በጨለማ መቀመጥን ይወዳሉ፤ ዓይነ ልቡናቸው ከማመን የታወሩ ሰዎችም ከፀሐይ ከክርስቶስ ርቀው በጨለማ መኖርን ይመርጣሉ /ቅ.ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ ዝኒ ከማሁ/፡፡

   ጌታችንም ሰዎቹ በፍቃዳቸው ወደ ኋላ እንደተመለሱ አይቶ ለአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ (ያለፈቃዳቸው ይነዳሉ የሚል ነገር እንዳይኖርና ወደው ፈቅደው ሊከተሉት እንደሚገባ ሲያስረዳቸው)፡-እናንተም ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” አላቸው /ቁ.67፣ Cyprian the Martyr Letter 59 to Cornellius: 7./። ስምዖን ጴጥሮስ ግን፡-ጌታ ሆይ! የዘላለም ደኅንነት የሚሰጥ ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደ ማን እንሄዳለን? ከሕይወትስ ወጥተን ወዴት እንሄዳለን?  እኛስ አንተ የሕያው እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ እንደ ሆንህ አምነንብሃል፤ የዘላለምን ሕይወትም በቅዱስ ሥጋህና በክቡር ደምህ ልትሰጠን እንደመጣህ አውቀናል ተረድተናልም” ብሎ መለሰለት /ቁ.68-69፣ Saint Augustine,27:9/። ጌታችንም፡-እናንተ እንድታውቁት ብዬ እንጂ አሥራ ሁለታችሁንማ እኔስ ከፍጹም ፍቅሬ የተነሣ የመረጥኋችሁ አይደለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ የእኔን ፍቅር ያላስተዋለ ሰይጣን (መስተቃርን መስተጻርር) ነው” ብሎ መለሰላቸው /ቁ.70/።

 ይህን ነገር (እስከሚያሲዘው ድረስ በግልጽ ሳይሆን በምሥጢር) የተናገረ ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ነው፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና /ቁ.71/፡፡ ጌታችን እንዲህ ስላለም ከሁሉም ይልቅ ጴጥሮስ በእጅጉ ታውኮ ነበር /ዮሐ.13፡24/፡፡ ይህም የሆነው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ አስቀድሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! መከራ መስቀል ከቶ አይሁንብህ” ሲለው “ወደኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን” ብሎት ስለነበር አሁንም ከእናንተ አንዱ ሰይጣን ነው ሲል “እኔ እሆንን?” በማለት ነበር /St.John Chrysostom, Ibid/።

   ወዬ አባት ሆይ! በሲና በረሐ ምድራዊ መብልን በልተው ምድራዊ መጠጥንም ጠጥተው እንደሞቱ እንደነዚያ እንዳንሞት ሰማያዊ መብል ሰማያዊ መጠጥ ሆነህ መጥተህ ሳይገባን ስለ ሰጠኸን እናመሰግንሃለን፡፡ ከመጀመርያው አዳም ጋር እንዳንሞት ይልቁንም ከሁለተኛው አዳም (ከአንተ ጋር) የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረን ራስህን መብልና መጠጥ አድርገህ ስለሰጠኸን እናመሰግንሃለን፡፡ እንግዲያውስ አባት ሆይ! ከምድራዊ መብል ጋር ስንታገል ካዘጋጀህልን ሰማያዊ ማዕድ (ከቅዱስ ሥጋህና ከክቡር ደምህ) የራቅን እንዳንሆን ይልቁንም በፍርሐትና በረዐድ ሆነን እንድንቀርብ እንድንቀበል እርዳን፡፡ ይህን ሥጋህን በልተን ይህንንም ደምህን ጠጥተን አንተ በእኛ እኛም በአንተ እንድንኖር እንድትዋሐደን እርዳን፡፡ አባት ሆይ! ሕይወት የሆነውን፣ ደኅንነትም የሚገኝበትን ቃልህን ሰምተናል፡፡ መድኃኒታችን ሆይ! ታድያ ከአንተ ወዴት እንሄዳለን? ፍቅር ከሆንከው ከአንተ ርቀንስ ምን ሕይወት አለን? ቅዱስ አባት ሆይ የቸርነትህን ሥራ ሥራልን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!


1 comment:

  1. KHY!! Girum Girum Girum timihirt new! Yesemanewun lehiwot yehuniln! Tsegawun yabzalih wendimachin!!

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount