Tuesday, July 17, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- የመጨረሻው ክፍል (ክፍል አምስት)!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ተወዳጆች ሆይ! እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ለመማማር የጀመርነው ርእስ የሚያልቅ ስላልሆነ እናንተ በይበልጥ ከሊቃውንት ከመጻሕፍት እንድታዳብሩት እየጋበዝኩኝ እኛ ዛሬ እንጨርሳለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
1. ደሙ ከሞተ ሥራ ሕሊናን የሚያነጻ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት መሥዋዕቶች የጊደሮች፣ የኮርማዎች፣ የፍየሎች የሆነ ደመ እንስሳ ነበር፤ የዘመነ ሐዲስ ግን በደመ ክርስቶስ የተደረገ ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ መሥዋዕቶች ያለ ፈቃዳቸው ያለ ውዴታቸው የሚሞቱ እንስሳት ነበሩ፤ የዛሬው ግን ሞት ይሁንብኝ ይደረግብኝ ብሎ ያለ ኃጢአቱ እንደ ኃጢአተኛ ተቈጥሮ በፈቃዱ እስከ ሞት ድረስ የታዘዘ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ የእነዚያ መሥዋዕት ነውርና ነቀፋ ባለባቸው አገልጋዮች የሚቀርብ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ግን ነውርና ነቀፋ በሌለበት በንጹሑ ኢየሱስ የተከናወነ ነው፡፡ የእነዚያ መሥዋዕት ሞት በሚይዛቸው በእንስሳት ደም የሚከናወን አገልግሎት ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት ግን ትንሣኤና ሕይወት በሆነው በክርስቶስ የተከናወነ አገልግሎት ነው፡፡ የመጀመርያው ኪዳን ለጊዜው የሆነ ንጽሕናን የሚሰጥ ነበር፤ የሊቀ ካህናችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ግን ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ (Beyond Time) የሆነ ዘለዓለማዊ ንጽሕናን የሚሰጥ አገልግሎት ነው፡፡ የቀደመው ኪዳን በምሳሌና በጥላ በሆነ በደመ እንስሳ የሚከናወን ነበር፤ የዛሬው ግን አማናዊ በሚሆን በንጹሑ በደመ ክርስቶስ ተደርጓል፡፡ የቀደመው መሥዋዕት እሳት አንድዶ እንጨት ማግዶ የሚሠዋ ነበር፤ የዛሬው ግን በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት የተደረገ ነው፡፡ እንዲህም ስለ ሆነ የእነዚያ መሥዋዕት ደመ ነፍስን (ሥጋን) ብቻ የሚቀድስ ነበር፤ የዛሬው ግን… ደመ ክርስቶስ ግን ሕያው መሥዋዕት ስለሆነ ሁለንተናን ሕያውና ቅዱስ የሚያደርግ ነው፤ ሕሊናን ከሞተ ሥራ የሚያነጻ ልዩ መሥዋዕት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “ደመ ላህም ደመ ጠሊ የጊደርም አመድ ሥጋዊ ኃጢአትን የሚያነጻ ከሆነ፣ በኃጢአት ያደፉትን የሚያከብራቸው ከሆነ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ራሱን ለእግዚአብሔር ነውር ነቀፋ የሌለበት የዘለዓለም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ የኢየሱስ ክርስቶስ ደምማ ከኦሪት፣ ከኃጢአት፣ ከፍዳ፣ ከፍቅረ ንዋይ ልቡናችንን እንደምን ያህል ያነጻ ይኾን?” /የዕብ.9፡13-14 ትርጓሜው፣ገጽ.441/፡፡  ስለዚህ ደሙ ከሞተ ሥራ ሕሊናን የሚያነጻ ሊቀ ካህናት አለን፡፡
2. የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ (ምርጥ) ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው “ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው ይላል /ዕብ.9፡15/፡፡ እውነት ነው! ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማያትም አስታራቂ የሐዲስ ኪዳን ብቸኛው መካከለኛ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ክፍል በተረጐመበት አንቀጽ ምን ማለት እንደሆነ እንዲህ ያብራራልናል፡- “መካከለኛ ማለት ምን ማለት ነው? መካከለኛ መካከለኛ ለሆነለት ነገር ባለቤት (ተጠቃሚ) አይደለም፡፡ ለምሳሌ አማጭ (መካከለኛ) ለሚያገባ ሰው ሚስት ለማግባት አጋዥ ይሆነዋል እንጂ እርሱ የሚያገባ ሙሽራ አይደለም፡፡ በጌታም ዘንድ እንዲህ ነው (የተሠዋው እጠቀም ብሎ አይደለም)፡፡ ወልድ ዋሕድ ጌታ በአባቱና በእኛ መካከል አስታራቂ ሆነ፡፡ አብ በሠራነው ኃጢአት ፈርዶብን መንግሥቱን ሊያወርሰን አልወደደም ነበርና ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የባሕርይ ልጁ በእርሱና በእኛ መካከል አስታራቂ ሆነ፡፡ እርሱንም ደስ አሰኘው፡፡ ከዚያም እኛን ወደ ልጅነት ልጅነትንም ወደ እኛ ጠራ፤ በሞቱ ከአብ ዘንድ መንግሥተ ሰማያትን አስገኘልን፡፡ ሕጉን በማፍረስ በነበርን ጊዜ ሞት ተገባን፤ እርሱ ግን ስለ እኛ በሞተ ጊዜ ሳይገባን ለመንግሥተ ሰማያት የበቃን አደረገን፡፡ አባት ለልጁ እንደሚሰጥ ቀድሞ ልጅነትን ሳንጥር ሳንግር እንዲያው ሰጠን”  /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድር.16፡33-48/፡፡ አዎ! በበደልነው ጊዜ ሕጉ (ኦሪት) እንደ ፍርድ ሆነብን (የሚያስፈርድብን ሆነ)፡፡ ለማዳን የሚሞት አንድ ስንኳ ጠፋ፡፡ ሊቀ ካህናችን ግን ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከራሱና ማኅየዊ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታርቀን ዘንድ የባርያውን መልክ ይዞ (የእኛን ባሕርይ ነሥቶ) ትምክህታችን ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሆነ፤ አምላክ የሆነ ሰው ሰውም የሆነ አምላክ (መካከለኛ) ሆነ፤ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ ሥግው ቃል (Incarnated Word)፣ አምላክ ወሰብእ (መካከለኛ) ሆነ፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በሥግው ቃልነቱ ስለ እኛ ባይሞት ኖሮ ኦሪት ደካማ ከመሆኗ የተነሣ ባልዳንን ነበር፡፡ ስለዚህ እንደ ሰውነቱ ዘመዳችን እንደ መለኰትነቱ ፈጣርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዲስ ሕግ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይ አስታራቂ ሆነ፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ብቸኛ መካከለኛ ሆነ፡፡
3. ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን የሻረ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ደጋግመን እንደተናገርነው የቀደመው ሊቀ ካህናት ብዙ ጊዜ ብዙ መሥዋዕት ሠዋ፤ ሊቀ ካህናችን ግን አንድ ጊዜ ራሱን ሠዋ፡፡ የቀደመው ሊቀ ካህናት ገንዘቡ ባይደለ በሌላ ደም አገለገለ፤ የዛሬው ግን እውነት ገንዘቡ በሚሆን በራሱ ደም አስታረቀ፡፡ ምሥዋዑ እርሱ ነውና፤ የሠዋው እርሱ ነውና፤ የተሠዋውም እርሱ ነውና በራሱ ደም አገለገለ፡፡ ፈቃዱን እንደ ካህን ሥጋው እንደ መንበር አድርጎ ነፍሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ (ኑሮ ኑሮ አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም) ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር (ያጠፋት ዘንድ) አንድ ጊዜ ተገልጦአል” /ዕብ.9፡26/ ተብሎ እንደተጻፈ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት ያስወገደው ራሱን በመሠዋት እንጂ የጊደርና የኮርማ ደም በማፍሰስ አይደለም፡፡
4. ያዳናቸውን ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመውሰድ ሁለተኛ የሚገለጥ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል” /ዕብ.9፡27-28/፡፡ ምን ማለት ነው? ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት እንዲሉ ለሰው ኑሮ ኑሮ ሞት እንዲቆየው ኋላም መቃብር እንዲከተለው ሁላችንም ከፊት የሚጠብቀን አንድ ጊዜ “መሞት” አለ፡፡ ሆኖም ግን ይህ “ሞት” ክርስቲያኖች ለምንሆን ለእኛ ከድካማችን ዕረፍት እንጂ እውነተኛ ሞት አይደለም፤ ሞት የሚሠለጥንብን አይደለም፡፡ ሞትስ ሰው የኃጢአቱን ትብትብ ተሸክሞ ሳለ ሥርየተ ኃጢአትን ሳያገኝ መንግሥተ ሰማያትን ሲያጣ ነውና፡፡ ስለዚህ ከድካም ካረፍን በኋላ የዘለዓለም ሕይወት አለን፡፡ ክርስቶስም የብዙዎችን ሰዎች ኃጢአት ያስተሠርይ ዘንድ ኑሮ ኑሮ አምስት ሺ አምስት ዘመን ሲፈጸም አንድ ጊዜ ራሱን ሠዋ፡፡ አዎ! በአዳም ምክንያት የመጣው ሞት ሁሉን ለማጥፋት መጣ፡፡ ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና ጌታችንም ኃጢአት ሳይኖርበት ስለ እኛ ኃጥእ አሰኘ፡፡ እርሱ ንጹሕ ሲሆን “ከኃጥአን ጋር ተቈጠረ” /ኢሳ.53፡12/፤ የእኛን ኃጢአት የራሱ እንደ ሆነ ቈጥሮ ወደ መስቀል ወጣ /2ቆሮ.5፡21/፡፡ ማመንን ደኅንነትን ለወደዱም አዳናቸው፡፡ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ /ሉቃ.23፡34/ ሥርየተ ኃጢአትን ሰጣቸው፤ ይቅር አላቸው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን የሰውን ኃጢአት ለመሸከም ሳይሆን ያዳናቸውን ወደ አዘጋጀላቸው ርስት ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ ይመጣል፡፡ የዘይት ማሰሮአቸውን ሞልተው ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚጠባበቁት ለሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል፤ ይመጣላቸዋል፡፡ ዓለምን ለማሳለፍ፣ ጻድቃንን ለማወደስ፣ ኃጥአንን ለመውቀስ፣ ሞትንና ዲያብሎስን ወደ ጥልቁ በመጣል ለመደምሰስ፣ መንግሥቱንም ለምእመናን ለማውረስ ይመጣል፡፡ ወንድሜ!... እኅቴ!... የኢየሱስን መምጣት ትጠባበቃለህን/ ትጠባበቂያለሽን? እንግዲያው ከወንጌላዊው ጋር፡- “ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፤ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” እንበል /ራዕ.22፡20/፡፡

      ስናጠቃልለው ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ የሚወድ ደግሞም  የምናመልከው እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ እንዲያድነንና ወደ እውነት (ወደ ራሱ) ሊመራን ቤዛም ሊሆነን በተለየ አካሉ ትምክሕታችን ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋንና ፍጹም ነፍስን ተዋሕዶ የመጣም አንዱ እውነት እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንዲህ ስለሆነም መካከለኛ መባልን ተገባው፡፡ “እግዚአብሔር አባቴ ነው”፤ “በአባቴ ስም መጣሁ”፤ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ የመሰከረውን ምሥክርነት ያልተቀበሉት ባይቀበሉትም በገዛ ዘመኑ (በመዋዕለ ሥጋዌው) ምስክርነቱ ነበረ /1ጢሞ.2፡4-6/፡፡ እኛም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን ይህን እውነት እንናገራለን፤ አንዋሽም፡፡ ብዙዎች ሌላ መካከለኛ እንዳለን አድርገው ቢከሱንም “ከአንዱ ሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ሌላ መካከለኛ የለንም” ብለን እንመሰክራለን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት የመንግሥተ ሰማያትን መንገድ በደሙ የመረቀልን ሊቀ ካህናችን አንድ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል ብለን እንመሰክራለን፡፡ የቅዱሳንን ምልጃ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነውና “ሌላ መካከለኛ” የለንም ብለን እንመሰክራለን፡፡
አኰቴት ወክብር ለሊቀ ካህንነ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስለ አቡሁ ወምስለ መንፈሲሁ እስከ ለዓለም አሜን!! 

1 comment:

  1. በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የሀዲስ ኪዳን መካከለናኛ የሚለውት የንባብ ክፍሎች የአማላጅነትን ወይም የአብ የበላይነትን የወልድ የበታችነትን የሚያሳዩ አይደሉም በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ መካከለኛ ተብለው የተገለጹት ቃላት በሙሉ በእግዙ "ሕሩይ" ተብለው ነው የተገለጹት ሕሩይ የተባለው ስጋ ማርያም ነው ይህም " ብርክት እንቲ እምንእስት አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ"ባለው ይታወቃል ሉቃስ 1፡28 ቅዱስ ጳውሎስም " ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ " ያለው ለሰው ልጅ የተሰጠውን ክብር የባርያውን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ"በማለት ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ ራሱን በዶ ማደረጉን ገልጻል።ፈል 2፡7 አንድ እገዚአብሄር አለን በእግዛብሔርና በሰው መካከል "አራቱ እንሰሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አላቸው በዙራቸውም በውስጣቸውም አይኖች ሞልቶባቸዋል ቅዱስ ቅዱስ ቅዱሰ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ለሊት አያርፉም እንሰሶቹም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ከዘላለም እስከ ዘዓላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎችም ራዕ 8፤11 ፤በልጁ የሚያም የዘላለም ህይወት አለው በልጁ የማያምን ግን እግኢአብሔር ቁጣ በሱ ላይ ይኖራል እንጂ በሕይወት አይኖርም ዬሐ 3፤37 እግዲህ ልናምን የሚገባው በልጁ በመካከለኛው ወይስ በአብ? በልጁ ያላመነ ሕይወት የማያይ ከሆነ "መካከለኛ " የሚለው ቃል ሚስጢራዊ ይዘት እንዳለው ልንገዘብ ይገባል ለምሳሌ ሰላሜን እተውላቸዋለሁ ዬሐ 14፤ 27 ሰላም ቁሳዊ አካል አለመሆኑ መረዳት አለብን ይኸውም እኔ የምሰጣችሁ አለም እደሚሰጣችሁ አይደለም ይላል" መንግስተ ሰማይ በመካከላችሁ ናት ሲል ማመናችንና አለማመናችንን እደሚገልጽ ማለት ነው። በማጠቃለያም፡ የአብ የመንፈስ ቅዱስ መካከኛ ኢየሱስ ክረስቶስ ነው ። በአብ ልብነት የሚታሰበው በመንፈስ ቅዱስ እስተፋስነት የሚወጣው የሚወርደው የሚገለጸው በመልድ ቃልነት ነው" በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለኔ ይመስክራል" እንዲል ዬሐ10፤ 25 የብሉይና የሀዲስ ኪዳናትን ያዋሀዳቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የፈጸማቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የምንድንባቸውን ሚስጢራት አፈጻጸም የሰራልን የወሰነልን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በመስቀል ላይ ተስቅሎ ጥልን በመስቀል ጠርቆ አስወገደልን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ኤፌ2፤14 ስለ አበቱ ተረከል ነገረን ኢየሱስ ክረስቶስ ነው።የሐ1፤18 የት እንደምኖር እንዴት እነደምኖር የነገረን ቃል ገባል ኢየሱስ ክረስቶስ ነው ዬሐ14፤2 እንደ ስራችንም ዋጋ ሚከፍለን ኢየሱስ ክረስቶስ ነው ራዕ 22፤12 ይህ ማለት ግን ወልድ በሚአደርገው አብ የለም ማለት አይደለም አብ በሚያደርገው ደግሞ ወልድ የለም ማለት አይደለም :: ወስበሀት ለእግዚአብሔር ለወላደቱ ድንግል ለመስቀሉ ክብረ አሜን!!!!!!!!!!

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount