Monday, July 30, 2012

በግብዝነት አትፍረዱ- የዮሐንስ ወንጌል የ33ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.7፡11-24)!!


   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
   ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በሚመላለስበት ጊዜ ሥግው ቃልነቱን ብቻ ያስተማረን ያስረዳን አይደለም፡፡ አስቸጋሪ ጊዜአትን እንዴት ማለፍ እንዳለብን አርአያ በመሆንም ራሱ አድርጎም ጭምር አስተማረን አስረዳን እንጂ፡፡ ለምሳሌ ፍጹም አምላክ እንደ መሆኑ መጠን ሊገድሉት በሚፈልጉት አይሁድ መካከል ምንም ሳያደርጉት ያስተምራል፤ ይገስጻል፤ ይዘልፋል /ቁ.25/፡፡ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ደግሞ “ወደ በዓል ከእናንተ ጋር አልወጣም” ብሎ ለወንድሞቹ ለደቂቀ ዮሴፍ ይነገራቸዋል /ቁ.8/፡፡ ወንጌላዊውም በገሊላ ቀረ አለን /ቁ.9/፡፡ “ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ” ግን “እርሱም በግልጥ በይፋ ያይደለ በስውር፣ ሰውን ሳያስከትል፣ ከወንድሞቹ ጋር ያይደለ ብቻውን ወጣ” /ቁ.10/። አስቀድሞም ቢሆን ጭራሽ አልወጣም ሳይሆን ከእናንተ ጋር አልወጣም ነበርና ያላቸው (ወንድሞቹ ጠይቀውት የነበረው ምድራዊን እንጂ እውነተኛውን ክብሩ እንዲያሳይ አልነበረምና)፡፡ ስለዚህ አስቀድመን እንደተናገርነው በዚህ ምልልሱ ጌታችን በአስቸጋሪ ጊዜአት እንዴት በዘዴ በጥበብ ማለፍ እንዳለብን አስተማረን፤ አስረዳን /St. John Chrysostom, Hom 49. /፡፡

 ከዚህ በኋላ ማለትም በግልጥ በይፋ ያይደለ በስውር፣ ሰውን ሳያስከትል፣ ከወንድሞቹ ጋር ያይደለ ብቻውን ወደ በዓሉ ከወጣ በኋላ አይሁድ በበዓል እንይዘዋለን የሚል ምኞት ነበራቸውና /ዮሐ.11፡56/ በንቀት አነጋገር ወዴት ነው?” እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር /ቁ.11/። ተወዳጆች ሆይ! የክፋታቸውን ብዛት የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ ጌታችንን ፍጹም ከመጥላታቸው የተነሣ ስሙን እንኳን መጥራት አልፈለጉምና፡፡

  በዚያን ጊዜም በሕዝቡ መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዶቹአረ ደግ ሰው ነው” አሉ፤ ሌሎች ግንአረ ደግ ሰው አይደለም፤ ሕዝቡን ያስታል እንጂ የምን ደግ ሰው ነው?” ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን (መሪዎቹን) ስለ ፈሩ ውስጥ ለውስጥ አጉረመረሙ፣ በማጉተምተም ተነጋገሩ እንጂ ማንም ስለ እርሱ ገልጦ በይፋ የተናገረ የለም /ቁ.12-13/። ለምን ቢሉ በክርስቶስ ያመነ ሰው ቢኖር ከምኩራብ ይባረር ይሳደድ ብለው አዋጅ ነግረው ስለነበር በተለይ ደግነቱን ደፍሮ በይፋ ገልጦ የተናገረ የለም /ዮሐ.9፡22፣ Saint Cyril the Great/፡፡

  አይሁድ ይህን የዳስ በዓል የሚያከብሩት ሰባት ቀን ሙሉ እንደ አንድ ቀን ነውና /ዘሌ.23፡34/ በበዓሉ እኩሌታ ማለትም በአራተኛው ቀን ጌታችን ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመረ /ቁ.14/።

  ሲያስተምራቸውም አይሁድ፡-ይህ ሰው ያስተማረው ሳይኖር እንዴት መጻሕፍትን ያውቃል?” ብለው ትምህርቱን ያደንቁ ነበር። ነገር ግን ሁሉም አይደሉም፡፡ ግማሾቹ አደነቁለት (የበጎ አንክሮ) ገሚሶቹ ደግሞ አደነቁበት (የነቀፋ) /ቁ.15፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 491/፡፡

  ከዚህ በኋላ ማለትም ግማሾቹ የበጎ አንክሮ ግማሾቹ የነቀፋ አንክሮ ካደነቁና እንዴት ሳይማር መጻሕፍትን ያውቃል ካሉ በኋላ ጌታችን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ትምህርቴስ ሙት፣ ተሰቀል፣ ውረድ፣ ተወለድ ብሎ ከላከኝ ከባሕርይ አባቴ ከአብ የተገኘች ናት እንጂ ከእኔ ብቻ አይደለችም (በሥልጣን በአገዛዝ አንድ ናቸውና፤ ፈቃዳቻው የማይለያይ ነውና እንዲህ አለ)፤  ፈቃደ እግዚአብሔር ሊያደርግ ሊፈጽም የሚወድ ቢኖር፥ ውስጡ እኔን ለመግደል በቅንዓት በቁጣ ሳይቃጠል በትሕትና በአንቃዕዶ የሚመጣ ቢኖር፣ ትንቢተ ነቢያትን በመመርመር የሚቀርብ ቢኖር እርሱ ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ ብቻ (እናንተ እንደምታስቡት ከአባቴ ተቃራኒ) የምናገር ብሆን ያውቃል። መንፈስ ቅዱስ ያድርበታልና ምድራዊ መምህር እንዳላስተማረኝ ይልቁንም የባሕርዬ እንደሆነ ይረዳል፤ ያውቃል፡፡ ከራሱ ብቻ አንቅቶ የሚያስተምር የሚናገር ሰው የራሱን ክብር ተድላ ደስታ ይሻል ይፈልጋል፡፡ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን፣ ላኪውን ደስ ሊያሰኝ የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ በእርሱ ዓመፃ የለበትም፤ ሐሰተኛ አይደለም፡፡ እኔም ከባሕርይ አባቴ ጋር የተለየ ፈቃድ የለኝምና የራሴን ክብር ተድላ ደስታ ብቻ የምሻ አይደለሁም (ይህን የሚላቸው በቀላሉ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ያምኑበት ዘንድ ነው!)። ሙሴ ሕግን የሰሰጣችሁ አይደለምን? እናንተስ “እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን” ያላችሁ አይደላችሁምን? /ዘጸ.24፡4/፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፡- በከንቱ ትመጻደቁባታላችሁ እንጂ ከእናንተ አንድ ስንኳ  ሕግን ኦሪትን የሚያደርጋት የሚፈጽማት የለም። እርሷን የምትፈጽሙ ብትሆኑስ “እውነተኛውን በሐሰት አትግደል” ትላለችና ልትገድሉኝ ባልፈለጋችሁ ነበር፡፡ አብ አባቴ ነው ብዬ ብነግራችሁ፤ ከአባቴ ጋር የተካከልኩ መሆኔን በእውነት ያለ ሐሰት ብነግራችሁ፤ ወደ እውነት (ወደ ራሴ) ልመልሳችሁ ብመጣ ባልተቆጣችሁ ባልተናደዳችሁ ነበርአላቸው /ቁ.16-19፣  St. John Chrysostom,Ibid/፡፡

  እነርሱ ግን ቁጣቸው በዛ፤ ፍቅሩን ከማየት ይልቅ ስድብን ለመናገር ፈጠኑ፡፡ ስለዚህም ፡- “ጋኔን አድሮብሃልን? ማንስ ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት /ቁ.20/።

  ጌታችንም መልሶ እንዲህ አላቸው፡-አንድ ሥራ ሠራሁ (ሕሙማንን ፈወስኩ)፤ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። አይ ሥራ! አይ ተአምራት! ትላላችሁ፡፡ ደግሞም በዚያ አሳብባችሁ በዓል ሰንበት ሻረ ብላችሁ ልትገድሉኝ ትሻላችሁ፡፡ እናንተ በበዓል ምንም አይደረግም ብትሉም ሙሴ መገረዝን ሥርዓት ሰጣችሁ፡፡ ይህም ከአባቶቹ ከእነ አብርሃም ያገኘው የወረሰው ነው እንጂ ከራሱ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ሕግ የሰጣችሁን “ሙሴን ሰንበትን ሻርክ” አላላችሁትም፤ ይህ ብቻ ሳይሆን እናንተም ራሳችሁ በሰንበት ሰውን ትገርዛላችሁ፤ ጥንቃቄ የላችሁም፡፡ በዓል መሻር ማለት እንዲህ ከሆነ በሰንበት የተወለደውን ልጅ በሰንበት መግረዝም በዓል መሻር ነው፡፡ ምክንያቱም ምላጩ ይለመጣል/ይሳላል፤ ከዚያም የልጁ ደም ይፈሳል፤ ጅማቱ ይበጠሳልና፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ ማድረጋችሁ “የሙሴ ሥርዓት” ተብሎ በዓል እንደመሻር አልተቆጠርባችሁም፡፡ ታድያ እኔ በሰንበት ቀን ሰውን ሁለንተና ሥጋውን በተአምራት፣ ሁለንተና ነፍሱን በትምህርት ጤናማ ባደርገው ስለምን ትቈጡኛላችሁ? ስለምን በዓል ሻረ ትሉኛላችሁ? /ቁ.21-23፣ Saint Cyril the Great /፡፡ ስለዚህ እላችኋለሁ፡-ከሙሴ የበለጠ ግርዛትን ብፈጽም፣ ሰው ሁለንተናውን ጤናማ ባደርገው ቅን እውነተኛ ፍርድ ፍረዱ እንጂ በሐሰት የምትፈርዱ አትሁኑ፡፡ በእውነት ፍረዱ እንጂ በመልክ በግብዝነት አትፈረዱ፡፡ የምትመጻደቁበት ሕግም ቢሆን በጽድቅ ፍረዱ ትላለችና” /ቁ.24፣ ዘዳ.1፡17፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡

 ወዮ አምላክ ሆይ!ቃልህ ለአይሁድ ብቻ የተነገረ አይደለም፡፡ ዛሬም ላለነው ለሁላችን እንጂ፡፡ እንግዲያውስ ካስተማርከን ጥበብ ካስተማርከን ምግባር የምንማር አድርገን፡፡ ከክፋት ሁሉ የራቅን ክፋትን ሁሉ የምንጸየፍበት ዓቅም ብርታት አድለን፡፡ አንተን ከሚነቅፉ ወገን ሳይሆን አንተን ከሚያመሰግኑ ባለ ማቋረጥም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ከሚያመሰግኑህ ጻድቃን ወገን የምንሆን አድርገን፡፡ ሁል ጊዜም በትሕትናና በአንቃዕዶ ሆነን ፈቃድህን የምንፈጽም አድርገን፡፡ ብሩክ አባት ሆይ! በተሰማራንበት ሁሉ በምንውልበት ሁሉ በጉዞአችን ሁሉ በቅንነት እንድናገለግል አድርገን፡፡ መዝሙረኛው እንደተናገረ ጽድቅን የምትወድ ነህ፡፡ ዓመፃን የሚወዳትም ነፍሱን ይጠላታል /መዝ.11፡7፣5/፡፡ እንግዲያውስ ባለማወቅ ጎዳና ተጉዘን አንተን ከማየት ተከልክለን ዓመፃን ከሚወድዋት ነፍሳቸውንም ከሚጠልዋት ወገኖች እንዳንሆን ደግፈን፡፡ አንተን እንዳናሰድብ፣ በግብዝነት እንዳንፈርድ፣ ደሀን እንዳንበድል፣ ፍትሕ እንዳናጓድል፣ ጽድቅን እንድንከታተላት፣ ከሕግህም ፈቀቅ ያልን እንዳንሆን አጋዥ የሚሆነን ቅዱስ መንፈስህን ላክልን፤ አሳድርብን፡፡ አሜን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!! 

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount