ከመጀመርያ ጀምሮ መልካም ነገርን መምረጥ ክፉ አይደለም፤
በመልካምነት አለመቀጠል ግን ብዙ ወቀሳን ያመጣል፡፡ የብዙ ሰዎች ክፉ መሆን በዚሁ የሚመደብ ነው፤ ብዙዎች ሕይወታቸውን በመልካም
ጀምረው በኋላ ግን በክፋት መርዝ ተጠምቀው ሲሰክሩ ተመልክቻለሁና፡፡
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ወደ ክፋት ጥልቅ ወርዳችሁ
ቢሆንም “ከዚሁ ተመልሰን መነሣት አይቻለንም፤ መለወጥም አይሆንልንም” በማለት ተስፋ የምትቈርጡ አትሁኑ፡፡ እናንተ ስትፈቅዱ እግዚአብሔርም
ሲረዳችሁ ከክፋት ዐዘቅት መውጣት በእጅጉ ቀላል ነውና፡፡
ከሁሉም በላይ አመንዝራ ተብላ በከተማው ዘንድ ትታወቅ የነበረችውን ሴት በመልካምነቷ
እንዴት እንደምትወደስ አልሰማችሁምን? እየነገርኳችሁ ያለሁት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ስለተጠቀሰችው ሴት አይደለም፡፡ በእኛ ዘመን
ስላለችውና ፍኒሳ ከተባለችው ጋጠ ወጥ ከተማ ስለተገኘችው ሴት እንጂ፡፡ ይህች ሴት አስቀድማ በመካከላችን በአመንዝራነቷ ትታወቅ
ነበር፡፡ በክብር ቦታ ሁሉ የመጀመርያን ስፍራ የምትይዝ ሴት ነበረች፤ ስሟ በሀገሩ ሁሉ የገነነ ነበር፤ በእኛ ከተማ ብቻ ሳይሆን
በሲልስያ እና በቀጰዶቅያም ጭምር እንጂ፡፡ ይህች ሴት ብዙ ከተሞችን አፍርሳለች፤ የብዙ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ንብረት በልታለች፡፡
ብዙዎችም “መተተኛ ናት” ይሏታል፤ ውበቷን ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ጭምር ትጠቀም ነበርና፡፡ ከዚሁ የተነሣ በአንዱ ቀን የንግሥቲቱን
ልጅ እስከ ማማለል ደርሳለች፡፡ ጭካኔዋ የክፉ ክፉ ነበር፡፡
ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ግን ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ሆኖም ግን በዓይኔ ፍጹም
ተለውጣ ራሷን በእግዚአብሔር የጸጋው ዙፋን ፊት ድፍት አድርጋ ስታለቅስ አየኋት፡፡ አሁን የቀድሞ ክፉ ሥራዎቿን ሁሉ እርግፍ አድርጋ
ትታለች፤ በእርሷ ላይ ከነበሩት የአጋንንት ጭፍራ ተፋትታ አሁን የክርስቶስ ሙሽሪት ሆናለች፡፡
በእውነት ከእርሷ የሚከፋ ሰው በዐይኔ አላየሁም፡፡ በኋላ ግን ራሷን ከእንደዚህ
ዓይነቱ ክፉ ሥራ ከለከለች፡፡ ከዚህ በፊት ስትለብሳቸው የነበሩት የምንዝር ጌጦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ
በእርሷ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህን ሁሉ አወላልቃ ጥላ ለእግዚአብሔር በሚገባ የማቅ ልብስ ለብሳ ራሷን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር
አድርጋለች፡፡ ይህችን ሴት ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ለመመለስ የሀገሪቱ መኳንንት ከዙፋናቸው ወርደው ለምነዋት ነበር፤ ወታደሮች ትጥቃቸውን
ታጥቀው በመምጣት አስፈራርተው ሊወስዷት ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ሊመልሷት አልተቻላቸውም፤ ከተቀበሏት ደናግላን
በዓት ሊያስወጧት አልተቻላቸውም፡፡
ይህች ሴት ከዚያ አስነዋሪ ሕይወቷ ተመልሳ ለቅዱስ ቁርባን በቅታለች፤ ለእግዚአብሔር
ጸጋ የተገባ ሆና ተገኝታለች፤ ኃጢአቷን ሁሉ በጸጋው አጥባለች፤ ከተጠመቀች በኋላ ራሷን መግዛት ችላለች፡፡ ይህች ሴት የቀድሞ ሕይወቷን፣
ገላዋን ለብዙ ወዳጆቿ ያሳየችበትን ሕይወት “የእስር ቤት ሕይወት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ በእውነት “ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም
ኋለኞች ይሆናሉ” የሚለው የከበረው የጌታ ቃል በእርሷ ሲፈጸም አየነው፤ መለወጥ ከፈለግን እኛን ማሰናከል የሚቻለው ኃይል እንደሌለ
አወቅን ተረዳን፡፡
እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ዐዘቅት ሰምጠን የምንቀር
አንሁን፡፡ ከእኛ መካከል በጽድቅ በረሀነት የሚኖር ማንም አይገኝ፡፡ ፊተኛ ነኝ የሚልም ከቶ አይኑር፤ ብዙ አመንዝሮች እርሱን አልፈዉት
ሊሄዱ ይችላሉና፡፡ ማንምም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ፤ ከልቡ ከተጸጸተና ከተመለሰ ፊተኛ መሆን ይቻለዋልና፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- “ይህም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ
ትመለሳለች ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተመለሰችም፡፡ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች” /ኤር.3፡7/፡፡ ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ
የቀድሞ ኃጢአታችንን አያስበውም፤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ በእውነት እርሱ በቀድሞ ኃጢአታችን የሚወቅሰን
አይደለም፡፡ እርሱ እንደ ሰው አይደለምና፡- “እስከ አሁኑ ሰዓት ወዴት ነበርክ?” የሚለን አይደለም፡፡ ብቻ እኛ እንመለስ እንጂ
እርሱ እንዲህ ያለ አምላክ አይደለም፡፡
ይህን እንደናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ
ይርዳን አሜን!!
No comments:
Post a Comment