Wednesday, July 11, 2012

በዓለ ዕረፍቶሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በታናሽ ኤስያ እየዞረ በቃሉ እያስተማረ በመልእክትም እየጻፈ ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ በመከራም እንዲታገሱ እየመከረ ካጽናናቸው በኋላ በሮሜ ለክርስቶስ መስክሮ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ዘመኑ ሲደርስ በ67 ዓ.ም ወደ ሮሜ ገብቶ ያስተምር ጀመር፡፡

ኔሮን ቄሳርም በዚያ ዘመን በክርስቲያን ላይ የሚቃጠለው የቁጣ እሳት ገና አልበረደለትም ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ አሰረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በምሴተ ሐሙስ ጌታው በተያዘ ጊዜ ስለ ደረሰበት ፈተና ጌታዉን አላውቀዉም ብሎ መካዱ ብቻ ትዝ እያለው ያዝን ነበር እንጂበመታሰሩ አላዘነም ነበር፡፡…

ኔሮን ቄሳርም ቅዱስ ጴጥሮስን አሲዞ ካሰረው በኋላ ወደ አካይያ ዘምቶ ነበርና በዘመቻው ድል አድርጎና ደስ ብሎት ወደ ሮሜ ሲመለስ አረማውያን የሆኑ መኳንንቱን ደስ ለማሰኘትና አማልክቱን ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ሁሉ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስም ሞት በመስቀል እንዲሆን ታዘዘ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት መፈረዱን በሰማ ጊዜ ጌታችን ወአመሰ ልሕቅ ባዕድ ያቀንተከ ሐቄከ ወይወስደከ ሀበ ኢፈቀድከ ብሎ የነገረው ቃል ትዝ አለውና አላውቀውም ብዬ መካዴን ሳያስብብኝ በዚህ ፍጹም ይቅርታ ያደርግልኛል በማለት እጅግ ደስ አለው፡፡

የሚቀልበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከግዞት ቤት አውጥተው ሲወስዱት ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ እኩል እንዳልሆን ራሴን ወደ ታች ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ ብሎ ለመነ፡፡

በሮማውያን ሥርዓት ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሮሜ ተወላጅ የሆነ እንደሆነ የወንጀሉ ትልቅነት እየታየ ግርፋት ወይም ሞት ይፈረድበታል እንጂ በአንድ ወንጀል ሁለት ቅጣት አይፈረድበትም፡፡
የውጭ ሀገር ወንጀለኛ እንደሆነ ግን ቅጣቱ ግርፋት እንደሆነገርፈው እስራት ይጨምሩበታል፡፡ ቅጣቱ ሞት እንደሆነ ግን አስቀድመው ገርፈው በኋላ በመስቀል ወይም በሌላ መሣርያ ይገድሉታል፡፡…

ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስንም እንደ ሥርዓታቸው አስቀድመው ገርፈው በኋላ ራሱን ወደ ታች እግሩን ወደ ላይ አድርገው ሰቅለው ገደሉት፡፡ የተሰቀለውም በሐምሌ 5 /68 ዓ.ም ነው፡፡

ከሞተም በኋላ መርቄሎስ የሚባለው ደቀ መዝሙሩ ከመስቀል አውርዶ እንደ ሀገሩ ልማድ ሬሳውን በወተትና በወይን አጥቦ ሽቱ ቀብቶ በነጭ ልብስ ገንዞ ማር በተመላ ሣጥን ውስጥ አግብቶ አሁን ዛሬ ቫቲካን በሚባለው ሥፍራ ቀበረው፡፡
በረከቱና ረድኤቱ አይለየን!
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ቅዱስ ጳውሎስና ኔሮን ቄሳር በማናቸውም ነገር የማይስማሙ አጥፊና ጠፊ ነበሩ፡፡ ኔሮን ቄሳር ክፉና ዐመጸኛ ነበር፤ ቅ/ጳውሎስ ግን ደግና ፈቃደኛ ነበር፡፡ ኔሮን ቄሳር ከሐዲና ጨለማ በቃኝ የማይልንፉግ የሰይጣን ማደርያ ነበር፤ ቅ/ጳውሎስ ግን ሃይማኖታዊና ብርሃን በቃኝ የሚል ቸር የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ነበር፡፡

እነዚህ ሁለቱ ተጻራሪዎች በተገናኙና በተያዩ ጊዜ አንዱ የአንዱን ነገር አያስተውለውም ነበር፡፡ ስለዚህ ቅ/ጳውሎስ ወደ ፍርድ ሸንጎ ከቀረበ በኋላ ይፈታ ወይም ይቀጣ ሳይባል ወደ ግዞት ቤት መለሱት፡፡

ነገር ግን በሮሜ ከተማ ቅ/ጳውሎስ አስቀድሞ ያሳመናቸው ክርስቲያኖች እየበዙ ትምህርታቸውም እየበዛ መሔዱ በቅ/ጳውሎስ ምክንያት መሆኑን ኔሮን ቄሳር ስለተረዳው ይልቁንም ከቤተ መንግሥቱ ሹሞች ወገን ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ስለ አሳመነበት የቤሮን ቄሳር ቁጣው ተመለሰበትና ጳውሎስን እንደገና ወደ ፍርድ ሸንጎ አቅርቡት ብሎ
አዘዘ፡፡

ቅ/ጳውሎስም በኔሮን ቄሳር ፊት በቀረበ ጊዜ በቀኝ እጁ ከሰንሰለቱ ጋራ መስቀሉን ይዞ ሳይፈራ የክርስቶስን ነገር መሰከረ፤ ኔሮን ቄሳርም በቁጣ ቃል ይሞት በቃ ብሎ ፈረደበት፡፡…

የሮማውያን የወንጀለኛ መቅጫ ሕጋቸው አስቀድመን ተመልክተነዋል፡፡ ስለዚህ ቅ/ጳውሎስ በጠርሴስ ተወላጅነቱ የሮማውያን ዜጋ ስለሆነ ስቃዩ ቀርቶለት በአንድ ቅጣት ብቻ በሰይፍ እንዲሞት ተፈረደበት፡፡

በመግደያውም ስፍራ ምናልባት በንግግሩና በተአምራቱ ሌሎችን ሰዎች ወደ ክርስቲያንነት እንዳይመልስ ተብሎ ስለተፈራ ልባቸው ክርስቲያንን በመጥላት እጅግ የበረታ ጥቂቶች ሰዎች ብቻ ተመርጠው መሞቱን ለማየትና ለመመስከር ሔደው ነበር እንጂ ሌሎች አረማውያን በፈቃዳቸው እንዳይሔዱ ተከልክለው ነበር፡፡

ቅ/ጳውሎስም ወደ መሞቻው ሥፍራ ሲወስዱት በንግግሩና ባስተያየቱ ምንም ፍርሐት አልነበረበትም፡፡ እንዲያውም በጦርነት ላይ ድል አድርጎ ገድሎና ማርኮ እየፎከረ በደስታ ወደ ቤቱ የሚመለስ ወታደር ይመስል ነበር፡፡

ፊቱም በደስታ እያበራ ለገዳዮቹ የኃጢአት ሥርየት ይለምንላቸው ነበር፡፡ አስቀድሞም ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈላቸውን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል እየጮኸ ይናገር ነበር፡-
በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና። ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤  በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤  እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤  የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።  የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል። ነገር ግን። አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።  ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።  የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው” /2ቆሮ.4፡6-18/።

ጥቂቶችም ክርስቲያኖች ተከትለውት ሔደው ነበርና እነዚያን ባያቸው ጊዜ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው ያለውን የጌታው ቃል እየጠቀሰ በእውነትና በሃይማኖት ቢጸኑ በኋላ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ይሰብክላቸው ጀመር፡፡

ይህንም ሲናገር የመከራና የስደቱ ሌሊት አልፎ የደስታና የሰላም ቀን መምጣቱ ይታየው ነበር፡፡
ወደ ሩቅ ሀገር ሄዶ ሰንብቶ ወደ ቤቱ የሚመለስ መንገደኛ በአንድ ስፍራ ዐርፎ በቤቱ አጠገብ ያለውን ትልቅ ዛፍ ወይም ተራራ እያየ በደኅና ስለ መድረሱ ደስ እንደሚለው ቅ/ጳውሎስም ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ የእግዚአብሔርን ክብር ይመለከት ነበር እንጂ የሚሞትበትን ሰይፉን ወይም ደሙ የሚፈስበትን መሬቱን አይመለከትም ነበር፤ ይልቁንም የያዕቆብ መሰላል ተዘርግቶ መላእክትና ሰማዕታት ጻድቃንም ሲወጡበትና ሲወርዱበት ይታዩት ነበርና በእነዚያ መካከል ለመሆን ይቸኩል ነበር፡፡

ደግሞ በመጨረሻው ቀንም እኔ አስነሠዋለሁ ያለውን የጌታችን ቃል በጉልህ ጽሕፈት ተጽፎ በፊቱ ይታየው ነበርና የሞት ግርማ አላስፈራውም ነበር፡፡

የገዳዩም ሰይፍ ሲመዘዝ የሞት ጥላ ዙርያውን በከበበው ጊዜ ጌታው የሚሰጠውን የጽድቅ አክሊል ለመቀበልና ጌታውን በአየር ላይ ለመገናኘት ዳግም ምጽአት የደረሰ መስሎት ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ያለ ፍርሐትና ያለ ጭንቀት በደስታ አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ መሞቱን በዚያው ቁመው ሲያዩ የነበሩ ወዳጆቹ ክርስቲያኖች ራሱን ከወደቀበት አንሥተው ከአንገቱ ጋር አጋጥመው ለመቃብር በተፈቀደው ስፍራ ወስደው ቀበሩት፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ቅ/ጴጥሮስና ቅ/ጳውሎስ በአንድ ወር በአንድ ቀን በአንድ ስፍራ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የቅ/ጴጥሮስ ያረፈው በ67 ዓ.ም ነው፤ የቅ/ጳውሎስ ግን በ68 ዓ.ም ነው ብለው ጽፈዋል፡፡

ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ የሚያስመሰግናቸውና በሰማይ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጣቸው ከክርስቶስ ይልቅ ዓለምን ሳይወዱ ስለ ክርስቶስ ፍቅር በሃይማኖት ጸንተው በሰማዕትነት ማረፋቸው ነው እንጂ በአንድ ወር በአንድ ቀን በአንድ ስፍራ ማረፋቸው አይደለምና የሚያከራክር አይደለም፡፡

ስለ በዓላቸውም አከባበር የሆነ እንደሆነ በአንድነትም ቢያርፉ ለየብቻቸውም ቢያርፉ ወሩና ቀኑ አንድ በመሆኑ ጸሐፊዎቹ አልተለያዩበትምና በየዓመተ በሐምሌ 5 ቀን በዓለ ጴጥሮስ ወጳውሎስን ማክበር ይገባናል፡፡

“ሰላም ለቃልክሙ መታሬ እሳት ነዳዲ፣
ሥሉስ ቅዱስ ንዋያተ ዕጹብ ነጋዲ፣
አመ በንስሐ ተወልዱ እምጸጋክሙ ወላዲ፣
ተወፈየ መርሆ ሰማይ የማነ ጴጥሮስ ከሃዲ፣
ወመምህረ ወንጌል ኮነ ጳውሎስ ሰዳዲ፡፡” ቅዱስ ያሬድ

በረከታቸውና ረድኤታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን፡፡
(ዋቢ ድርሳን፡ ነቅዐ ንጹሕ)  

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን በረከታቸውና ጸጋቸው ይደርብን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን በረከታቸውና ጸጋቸው ይደርብን፣ አሜን።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount