Monday, July 2, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል ሦስት!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 በክፍል ሁለት ትምህርታችን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም የሚለይባቸውን ነጥቦች ማሳየት ጀምረን ነበር፡፡ የሚምር ነው፤ የታመነ ነው፤ በሰማያት ያለፈ ነው፤ በድካማችን የሚራራልን ነው ብለን አራት ነጥቦችን አይተናል፡፡ ለዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ቢችሉ አስቀድመው ይጸልዩ!
1. በመሐላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ መሐላ የማይለወጥ ነገርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ይህን አላደርግም እንዲህም አላደርግም ብሎ ከማለ የነገሩን ሓቅነት ያመለክታል፡፡ “ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው (ሎሌ በጌታው፣ ገረድ በእመቤቷ፣ ደቀ መዝሙር በመምህሩ፣ ልጅ በአባቱ) ይምላሉና ለማስረዳትም የሆነው መሓላ የሙግት (የክርክር የጸብ) ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ (አብዝቶ) ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ እግዚአብሔር ሊዋሽ (ሊፈርስ፣ ሊታበል) በማይቻል በሁለት  በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ (በሥጋዌው) በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን (ተስፋችንን አጽንተን ለያዝን ለእኛ ልቡናችን እንዳይነዋወጥ እንደ ወደብ የሚያጸናን ፍጹም ደስታ አለን)፤ እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ (እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሹሞ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት የገባ የዘላለም አስታራቅያችን ፊተውራርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ነው” እንዲል /ዕብ.6፡16-19/፡፡ እንግዲያውስ ከሌዋውያን ክህነት በሚበልጥ ክህነት፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ዘላለማዊ በሆነ ክህነት የተሾመ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ጥሪ የተመረጡ ቢሆኑም አገልግሎታቸው ጊዜአዊ ስለ ነበረ ያለ መሓላ የተሾሙ ነበሩና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከኦሪት ለምትበልጥ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይም አስታራቂ ሆኖአልና በመሓላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያውም ስለዚሁ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እነርሱም ያለ መሓላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሓላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሓላ ካህን እንዳልሆነ መጠን እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል /ዕብ.7፡20-22/፡፡ በዚህም ኦሪት ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስላልቻለች እንደተሻረች ወንጌል ግን ማዳን ስለቻለች፣ ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስለቻለች ሕልፈት ሽረት እንደሌለባት አወቅን፤ ተረዳን፡፡ ካህኑም አገልግሎቱም እንደዚሁ፡፡ ለምን ቢሉ ያለ መሓላ ከተሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ይልቅ በመሓላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ይበልጣልና፡፡  
2. የማይለወጥ ክህነት ያለው ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የቀደሙት ሊቃነ ካህናት ያለ መሓላ ለተሠራችው ሕገ ኦሪት የተሾሙ ስለ ነበሩ አንድም መዋትያን ስለ ነበሩ ካህናት የሆኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመሓላ ለተሠራችው ወንጌል የተሾመ ስለሆነ አንድም ሞትን በሞቱ ገድሎ ተነሥቶ በሕይወት የሚኖር ሥግው ቃል ስለሆነ ወራሽ የሌለው አንድ ነው፡፡ ክህነቱም (ኃጢአት የማሥተስረይ ችሎታውም) የባሕርዩ ስለ ሆነ በሞት (ሞት ሊያሸንፈው ስላልቻለ) አይለወጥም፡፡ የባሕርዩ የሆነውን ለእነዚያ በጸጋ ሰጥቷቸው ነበርና ሥጋ ለብሶ በክህነት ሲገለጥ ባሕርያዊ ሥልጣኑ የማይሻር ሆነ፡፡ ሐዋርያውም ይህን አስመልክቶ ሲናገር፡- “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው አለን /ዕብ.7፡23-24/፡፡
3. ሞትን አሸንፎ በሕይወት የሚኖር ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፡፡ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ካቶሊክ ሳትታሰብ ፕሮቴስታንትም ሳትታለም ከ325 እስከ 389 ዓ.ም የነበረውና የቀጰዶቅያ አውራጃ ለምትሆን የቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲተረጕመው እንዲህ ይላል፡- “ይህ ቃል የሚያመለክተን የጌታችን አስታራቂነቱን ነው፡፡…  ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው  (ሰው ሆኖ ሰውና እግዚአብሔርን ያስታረቀ) ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም (ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ራሱን አሳልፎ ለሞት ለሕማም የሰጠ) ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው /1ጢሞ.2፡5-6/፡፡ አሁንም ይህ ሥግው ቃል ከመቃብር በላይ ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ “በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” እንላለን /1ኛ ዮሐ.2፡1/፡፡ ሆኖም ግን ይህን በአብ ፊት በመውደቅና በመነሣት የሚያደርገው አይደለም፤ በዕለተ ዐርብ በተቀበለው መከራ ባደረገው ተልእኮ እንጂ”  /On The Son, Theological Oration, 4(30):14/፡፡ ከ347 እስከ 407 ዓ.ም የነበረውና የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “የቀደሙት ሊቀነ ካህናት መዋትያን ስለ ነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ እርሱ ግን የማይሞት ሕያው ስለሆነ አንድ ነው፡፡ የማይሞትም ስለ ሆነ እርሱን አምነው የሚመጡትን ሁሉ ሊያድናቸው ይቻለዋል፡፡ እንደምንስ ያድናቸዋል? የሚል ሰው ካለም “በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ነው” ብለን እንመልስለታለን፡፡ በሃይማኖት በንስሐ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን የሚያድናቸው በዕለተ ዐርብ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ በኋላም ጭምር እንጂ፡፡ በወደደበት ጊዜም ለመነላቸው፡፡ ሁል ጊዜ ይለምናል ብሎ የሚያስብስ ከቶ እንደምን ይኖራል? ጻድቃንስ እንኳ አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን የሚያገኙ አይደሉምን?… ሐዋርያውም ሁል ጊዜ ቁሞ የሚያገለግል እንዳያስመስሉት በማሰብ በመትጋት መሥዋዕት አንድ ጊዜ እንደሠዋ አስረዳ፡፡ አንድ ጊዜ ሰው እንደ ሆነ አንድ ጊዜ ተሾመ፤ አንድ ጊዜ እንደ ተሾመ አንድ ጊዜ አገለገለ፡፡ ሰው በሆነ ጊዜ የሰውነትን ሥራ በመሥራት ጸንቶ እንዳልኖረ ሁሉ ባገለገለ ጊዜም በማገልገል ጸንቶ አልኖረም፡፡ አሁን ቢያገለግል ኖሮ ሐዋርያው ቆመ እንጂ ተቀመጠ ባላለ ነበርና፡፡ መሥዋዕቱ ቁርጥ ልመናውን አንድ ጊዜ ወደ እዝነ አብ (በአብ ጀሮ) ወደ ገጸ አብ (በአብ ፊት) የደረሰች ስለሆነች እንደ ቀደሙት ሊቃነ ካህናት ሁል ጊዜ ሊያገለግል አያስፈልገውም” /Homily on the Epistle of Hebrews, Hom.13/፡፡ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜም ተመሳሳይ ነው፡- “በዕለተ ዐርብ ባደረገው ተልእኮ እስከ ምጽአት ድረስ ሲያድንበት የሚኖር ስለ ሆነ በእርሱ አስታራቂነት ወደ እግዚአብሔር የቀረቡትን ማዳን ይቻለዋል” /የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነ ትርጓሜው፣ ገጽ 434/፡፡ እንግዲያውስ ተወዳጆች ሆይ! “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል” የሚል ጥሬ ምንባቡን ብቻ በመያዝ እንዳይሳሳቱ ይጠንቀቁ፡፡ ይህ ማለት አስቀድመን እንደነገርንዎት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ዐርብ የማስታረቅ አገልግሎት ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እስከ ዕለተ ዐርብ ላሉት ሁሉ ብቻ ሳይሆን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በዚሁ የዕለተ ዐርቡ የማስታረቅ አገልግሎት እያመነ እንደሚድን ደሙም የማስታረቅ ችሎታ እንዳለው የሚገልጽ ነውና /ዮሐ.17፡20-21/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የሠዋው መሥዋዕት እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት መሥዋዕት ተረፈ ኃጢአት (ያልተደመሰሰ ኃጢአት) አስቀርቶበት አሁን ያንን ለማስተስረይ የሚወድቅ የሚነሣ አይደለምና፡፡ ጸሎቱና መሥዋዕቱ ምልአተ ኃጢአትን (ኃጢአትን ሁሉ) ለመደምሰስ አንድ ጊዜ ተፈጽሟልና /ዮሐ.19፡30/፡፡ ስለዚህ ይማልድልናል ስንል “የዕለተ ዐርቡ ቤዛነት፣ ካሣ፣ ሞት፣ ደም መፍሰስ አዲስና በየዕለቱ ንስሐ የሚገቡትን የሚያቀርብ የሚያድን ነው” ማለት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡  ስለዚህም ነው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች “ከእርሱ ውጪ ሌላ ሊቀ ካህን የለንም፤ ከቅዱስ ሥጋዉና ከክቡር ደሙ ውጪ ሌላ በየቀኑ የምናቀርበው መሥዋዕት የለንም” የምንለው፡፡ ክህነቱ የማይለወጥ፣ መሥዋዕቱም አንድ ጊዜ ቀርቦ በጊዜ ብዛት የማይበላሽ ሕያው አሁንም ትኵስ ነውና፡፡ ትኵስ መባሉም ነፍስ ስላለው ሳይሆን መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ነው፡፡
4. በእርሱ በኵል (እርሱን አምነው) ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድን የሚችል ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጌታችን ራሱ እንዲህ ብሏል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር (ደጅ) ነኝ… በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ (በእኔ ያመነ) ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል (ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል፤ መንግሥተ ሰማያትንም ይወርሳል)” /ዮሐ.10፡7፣9/፤ “እኔ መንገድና እውነት ነኝ (የሕይወትና የጽድቅ መንገዷ እኔ ነኝ) በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (እኔን ልጅ ካላለ በቀር አብን አባት የሚለው የለም አንድም በእኔ የማያምን ከአብ ጋር መታረቅ አይችልም)” /ዮሐ.14፡6-7/፡፡ እውነት ነው! የሕይወት መሥመር ክርስቶስ ነውና ክርስቶስን አምኖ የሚኖር ሰው ሕይወትን ያገኛል፡፡ ማንም ይሁን ማን ክርስቶስን ካላመነ ቢጾምም ቢጸልይም ያለ ክርስቶስ ዋጋ የለውም፤ በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ዓለም በራሱ ሕይወት የለውም፤ በክርስቶስ ቤዛነት የማያምን በሌላ በምንም መንገድ አይድንም፡፡
5. ድካም የሌለበት ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ድካምን የሚለብሱ እንደነበረ መጽሐፍ የሚሰክረው የታወቀ የተረዳ እውነት ነው፡፡ ይህም በጣም የተገለጠ ድካም በታየባቸው በኤሊ ልጆች መረዳት እንችላለን፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ የኤሊ ልጆች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ ለግል ጥቅማቸው በማዋል እግዚአብሔርን ያሳዝኑ ነበር፡፡ ይህም ሳይበቃቸው በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበር /1ሳሙ.2፡12-22/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ጻድቅና ቅን፣ ነቀፋ የሌለበት እውነተኛ፣ ከኃጢአት ሁሉ ፈጽሞ የራቀ የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ ነው /ዕብ.7፡26/፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን ሲመሰክሩ እንዲህ ይላሉ፡- “በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም” /ኢሳ.53፡9/፤ “ኃጢአት ያላወቀው” /2ቆሮ.5፡21/፤ “እርሱ ኃጢአትን አላደረገም” /1ጴጥ.2፡22/፤ “በእርሱ ኃጢአት የለም” /1ዮሐ.3፡5/፡፡ ጌታችንም ራሱ እንዲህ ብሏል “ከእናንተ ስለ ኃጢአት (ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ) የሚከሰኝ ማን ነው?” /ዮሐ.8፡46/፡፡ ለሞት አሳልፈው የሰጡት ተቃዋሚዎቹም ሳይቀሩ ይህን መስክረዋል፡- “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” /ማቴ.27፡4/፤ “በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” /ሉቃ.23፡4/፡፡  
6. ስለ ራሱ መሥዋዕት የማያሻው ነውር የለሽ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ዕሩቅ ብእሲና እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኞች ስለነበሩ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር በመሥዋዕት በጸሎት ከማስታረቃቸው በፊት ስለ ራሳቸው ቁርባን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር /ዘሌ.9፡7፣ ዘሌ.16፡6፣ ዕብ.5፡3-4/፡፡ ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስቀድመን እንደተናገርነው በባሕርይው ድካም የሌለበት ቅዱስ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት ንጹሕ፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሳይጐድልበት የሚያድል ባዕለ ጸጋ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ ቡሩክ፤ ከኃጢአተኞችም የተለየና ነውር የሌለበት ፍጹም ስለሆነ “እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈለገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና” /ዕብ.7፡27/፡፡ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር (ሳምንት ይቀጥላል)!

2 comments:

FeedBurner FeedCount