Monday, April 28, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፩

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፲፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  የዚኽ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለው ወራት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይቀዘቅዝ ማበረታታት ነው፡፡
  በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ባለው ወራት ረቡዕንና ዓርብን ጨምሮ አይጦምም፤ አይሰገድምም፡፡ ይኽም ሠለስቱ ምዕት በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ሲሰበሰቡ በኻያኛው ቀኖኗቸው የወሰኑት ቀኖና ነው /ሃይ.አበ.፳፡፳፮፣ The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1250, 1738/፡፡ ይኽን ቀኖና ሲወስኑም ያለ ምክንያት አይደለም፤ ይኽ ወራት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለውን ሕይወታችን የሚያሳይ ስለኾነ ነው እንጂ፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት ተብሎ የሚደረግ ጦምም ኾነ ስግደት የለም፡፡ ሥጋ ሙሉ በሙሉ በዲያብሎስ ከመፈተን፣ ከእግዚአብሔር ውጪ የኾነ ሌላ ሐሳብን ከማሰብ ነጻ የሚወጣበት ወራት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ፈቃደ ሥጋ ከፈቃደ ነፍስ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ከድካሙ ነጻ ስለሚኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን ትጉኅ ነው፡፡ እንደ አኹኑ እንቅልፍ እንቅልፍ አይለውም፤ ዘወትር የቅዱሳን መላእክትን ምግብ ለመብላት ማለትም ለማመስገን የተዘጋጀ ነው እንጂ፡፡

Friday, April 18, 2014

በዓለ ትንሣኤ

በገብረ እግዚአብሔር
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፲፩ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የዚኽ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መስለው እንዲነሡ ማበረታታት ነው፡፡
 በክርስትና ታሪክ፥ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ትልቁና ጥንታዊው ነው፡፡ በዓሉ በዓቢይ ጾም፣ በሰሙነ ሕማማት፣ በአክፍሎት እንዲኹም ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለ የደስታና የሐሴት ወራት እንዲታጀብ መደረጉም ይኽን ታላቅነቱንና ጥንታዊነቱን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ምዕራባውያን ከትንሣኤ ይልቅ የልደትን በዓል በደመቀ አኳኋን ሲያከብሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ግን ትንሣኤን ርእሰ በዓላት አድርገው ያከብሩታል፡፡

Wednesday, April 16, 2014

"ዘበተከ እምኔነ ኩሎ ማእሰረ ኃጣውዒነ በህማማቲከ ማኅየዊት ወመድኃኒት"


በክፍለ ሥላሴ
 (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 8 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን


የኃይሉ ጥበብና ችሎታው ከፍጡራን ኅሊና በላይ የሆነ የቅዱሳን አምላክ ፈጣሪያችን ሰውን በፈቀደለት መንገድ እንዲመራና መንግስቱን እንዲወርስ የቅዱሳን እጆቹ የግብር ውጤት አድርጎ አበጀው:: ግና ህግን አፍርሶ በፈጣሪው ተከሶ እግዚአብሔር = አባቱን : ልጅነት= ሀብቱን : ገነት= ርስቱን..... ያጣው የሰው ልጅ መርገምን ወርሶ ቁርበት ለብሶ ወደ ምድር ተሰደደ:: በዚህ በሥጋ ከተፈረደበት የመቃብር ግዞቱ ላይ በሲኦል የነፍስ ርደት ስላገኘው የሞት ሞትን ሞተ እንላለን:: ቅዱስ ዳዊትም "ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ።" (መዝ.48:12) ያለው የቀድሞ ክብሩን ከኋላ ግብሩ ጋር እያጻጸረ ሲያመለክተን ነው:: ይህንን የነቢዩን ቃል አብራርቶ የሚያስረዳ መልዕእክት በቅዳሴ አትናቴዎስ ላይ እናገኛለን እንዲህ ይላል ሊቁ "ሰብሰ እንዘ ንጉሥ ውእቱ ኢያእመረ" ዳዊት ክቡር ያለው የክብሩ መገለጫ ንግሥናው ነው ግን ያንን ያላወቀው የሰው ልጅ ምን እንዳገኘው ተመልከቱ "አህሰረ ርእሶ በፈቃዱ ወኮነ ገብረ ወመለክዎ እለ ኢኮኑ አጋእዝተ" አዎ ራሱን በፈቃዱ አሰረ ባርያ ሆነ መግዛት መፍጠርና ማስተዳደር ለባህሪያቸው የማይስማማቸውን የሚያመልክ ሆነ:: ከዚህ ጊዜ አንስቶ ለአምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዓመታት የቀድሞ ጠላት ዲያቢሎስ ሰውን አስሮ "በግብርናት" የሚገዛው ሆነ::

Saturday, April 12, 2014

ሰሙነ ሕማማት



በሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት እጅግ ከሚወደዱ እና ከሚናፈቁ ወቅቶች አንዱ ሰሙነ ሕማማት ነው፡፡ በዕለተ ሆሳዕና ጀምሮ በዕለተ ትንሣኤ የሚጠናቀቀው እጅግ ላቅ ያለ መንፈሳዊ ሕይወት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ በላቲን Hebdomas Sancta or Hebdomas Maior በግሪክ ደግሞ γία κα Μεγάλη βδομάς, Hagia kai Megale Hebdomas  ታላቁ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ በኛ ደግሞ ሰሙነ ሕማማት፡፡

FeedBurner FeedCount