Thursday, October 2, 2014

ሰላም ተዋሕዶ

በብጹዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩ


ሰላም ተዋሕዶ ሰላም ኦርቶዶክስ
የአትናቴዎስ ሐውልት የዲዮስቆሮስ፡፡
  የአዳም መመኪያ የሔዋን ሀገር
  አንቺ አይደለሽም ወይ የቅዱሳን ክብር?
በከንቱ የሞተው የአቤል መሥዋዕት
የኄኖክ ሃይማኖት የአዳንሽው ከሞት
አንቺ የኖኅ መርከብ የሴም በረከት፡፡
  በአብርሃም ድንኳን ተወልደሽ ያደግሽ
  የይስሐቅ መዓዛ ወደር የሌለሽ
  ያዕቆብ በሕልሙ በቤቴል ያየሽ
  የዮሴፍ አጽናኙ ተዋሕዶ አንቺ ነሽ፡፡

Wednesday, October 1, 2014

ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ርዕይ፡-
ሕፃናትና ወጣቶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ዐውቀውና አክብረው በሃይማኖትና በምግባር ጸንተው ሲኖሩ ማየት፤

ተልዕኮ፡-

ለሕፃናትና ለወጣቶች ወንጌልን በማዳረስ ለቤተክርስቲያን ተተኪዎችን ማፍራት፤

ዓላማ፡-

ወቅቱን ያገናዘቡ መንፈሳዊ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕፃናትና ወጣቶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዓተ እምነትና ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ማስተማር፤

Tuesday, September 30, 2014

ለይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ የተሰጠ ምላሽ (ክፍል አንድ)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  የይሖዋ ምስክሮች የተባለው ተቋም እ.ኤ.አ. በ1870 ላይ የተመሠረተ ሲኾን፥ መሥራቹም ፔንሳልቫንያ በምትባለው የአሜሪካ ግዛት እ.ኤ.አ. በ1854 ላይ የተወለደው ቻርለስ ራስል የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ይኽ ሰው ከጓደኞቹ ጋር በየጊዜው እየተገናኘ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን በተለያዩ የክሕደት ትምህርቶች ውስጥ ወደቀ፡፡ ከክሕደቶቹ መካከልም “ነፍስ ትሞታለች፤ ሥላሴ የሚባል ትምህርት የለም፤ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ፤ ክርስቶስ በሥጋ አልተነሣም፥ በፍጹም ሥጋም ወደ ሰማይ አላረገም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ዘለዓለማዊቷ ገነት ይኽቺ የምንኖርባት ምድር ነች፤ ኃጢአተኞች ፈጽመው ከመኖር ወዳለመኖር ይጠፋሉ እንጂ የዘለዓለም ስቃይ የሚባል አያገኛቸውም፥ ሰይጣንም ቢኾን ወደአለመኖር ይጠፋል እንጂ አይሰቃይም፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ አካላዊ አይደለም” የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ለዚኹ ትምህርቱ ይረዳው ዘንድም መጽሐፍ ቅዱስን በማጣመም “የአዲሲቱ ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ” በማለት የራሱ የኾነ መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ በአኹኑ ሰዓትም ይኽን የክሕደት ትምህርታቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ብዙ ሰዎችን እያታለሉ ይገኛሉ፡፡ እኛም፥ እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን፥ እነዚኽ ተረፈ አርዮሳውያን በትምህርተ ሥላሴ ዠምረን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንድ በአንድ መልስ እንሰጥበታለን፡፡ ለዚኽም እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፤ አሜን!!!

Monday, September 29, 2014

ሥነ ፍጥረት (ለሕፃናት)- ክፍል ኹለት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 19 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 እንደምን ናችኁ ልጆች? ትምህርት በደምብ ዠመራችኁ? እንዴት ነው ታድያ ትምህርት? በጉጉት እየተከታተላችኁ ነው አይደል? ጐበዞች፡፡ አኹን የምትማሩት ትምህርት ለወደፊት ኑሮአችኁ መሠረት በመኾኑ ተግታችኁ ተማሩ፤ እሺ?! እግዚአብሔር ብርታትን እንዲሰጣችኁ፣ የእናንተንና የቤተ ሰቦቻችኁ ጤንነት እንዲጠብቅላችኁም ዘወትር ጸልዩ፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታችኁን እንዲሰማችኁም ለወላጆቻችኁና ለታላላቆቻችኁ በቅንነት ታዘዙ፡፡ ይኽን ካደረጋችኁ፥ ዕቅዳችኁና ምኞታችኁ ይሳካላችኋል፡፡
 ልጆች! ባለፈው ሳምንት የተማርነውን ታስታውሳላችኁ? እስኪ ምን ምን ተማርን? ጐበዞች!!! ጥያቄውንስ ሠራችኁት? ስንት አመጣችኁ? እናንተ ጐበዞች ስለኾናችሁ ደፍናችኁታል አይደል? በጣም ጐበዞች፡፡ ለዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር ረቡዕ፣ ሐሙስ እና ዓርብ ምን ምን እንደፈጠረ እንማራለን፡፡ እግዚአብሔር ልቡናችንን ይክፈትልን፡፡ አሜን!!!

FeedBurner FeedCount