Thursday, April 2, 2015

በፌስ ቡክ የምጽፈውና የእኔ ማንነት አይገናኝም፡፡ ምን ላድርግ?



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችኁ? ዛሬም ከአንባብያን ከተላኩልኝ ጥያቄዎች ለሦስተኛው ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ አቀርብላችኋለኁ፡፡ መልሱን የሚሰጡን በምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙርና የዘንድሮ ተመራቂ የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ የልድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም እዝነ ልቡናችን ይክፈትልን፡፡ አሜን!!!

ጥያቄ፡- “ሰላም ለእናንተ ይኹን መቅረዞች! ዛሬ ለጥያቄ ወደ እናንተ መጥቻለኁ፡፡ በፌስ ቡክ የምጽፈውና በትክክለኛው ሕይወቴ የምኖረው ክርስቲያናዊ ሕይወቴ ፍጹም አይገናኝም፡፡ ለሰው እጽፋለኁ፤ ለራሴ ግን አልጠቀምባቸውም፡፡ ምን ላድርግ? መጻፉንስ ላቁመዉን? መልሳችኁን በጉጉት እጠብቃለኁ፡፡”
ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- ይኽ ጥያቄ በፌስ ቡክ በሚጽፉ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይኾን በምንሰብክ፣ በምንዘምር፣ መንፈሳዊ መጽሔትንና ጋዜጣን በምናዘጋጅ ኹሉ የሚታይ ነው፡፡ በእውነቱ ኹል ጊዜ “የምጽፈው፣ የምመክረው፣ የማስተምረውና የኛ ማንነት ምን ይመስላል?” ብሎ ራስን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችኁን መርምሩ፤ ራሳችኁን ፈትኑ” ነው ያለን /2ኛ ቆሮ.13፡5/፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ኹሉ ራሱን ሊመረምር ይገቧል፡፡
    “የምሰብከውና እኔ አንድ አይደለንም፡፡ የምጽፈውና እኔ አንድ አይደለንም” ብሎ ራሰን ማገናዘብ በራሱ በጣም ትሕትና ነው፡፡ እግዚአብሔርም በትክክል ለትሑታን ጸጋን ይሰጣል /1ኛ ጴጥ.5፡5/፡፡ እንዲኽ ማሰብ በራሱ የሚደነቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚወደው ነው፡፡ አንድ አገልጋይ “ከእኔ የተሻሉ ካህናት፣ ሰባክያን፣ ሌሎችም ታላላቆቼ ሐሳብ ይሰጡበታል፤ ይመክሩኛል፤ ያስተምሩኛል” ብሎ ማሰቡ ትሕትና ነው፡፡ “እኔ በቀቻለኁ፤ ሰባኪ ነኝ፤ ጽሑፌን ብዙዎች ያነቡልኛል፤ ስብከቴን ብዙዎች ያዳምጡልኛል” ማለት ምናልባት ለጊዜው ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደሚሰጥ ኹሉ ይነሳል፡፡ ጸጋ ይርቃል፡፡ እግዚአብሔር ያዝንብናል፡፡ ውርደትም አለው፡፡ ጸጋ እግዚአብሔር ሲርቅ በሰይጣን ተዋረድን ማለት ነውና፡፡ እግዚአብሔር ትዕቢትን አይወድም፤ ትዕቢትን ይጸየፋታል፡፡ ከዚኽ አንጻር አንድ አገልጋይ “የምሰብከውና እኔ፣ የምጽፈውና እኔ፣ የምዘምረውና እኔ ምነው አልተገናኘንም?” ማለት እጅግ ለንስሐና ለቅን አገልግሎት ያነሣሣል፡፡
     ነገር ግን በጐ ነገሮችን ከመጻፍ፣ ከመስበክ፣ ከመመስከር መገታት የለበትም፡፡ መፍትሔ እያፈላለጉ አገልግሎቱ መቀጠል አለበት፡፡ እንዲኽ ሲባል ግን ለምሳሌ አንድ ሰው ከባድ ሱስ ላይ ኾኖ “እየቀደስክ በዚኹ ዝለቅ” ለማለት አይደለም፡፡ ድክመት አስወግዶ ወደ ቅዳሴው ወደ ቁርባኑ ሊሸጋገር ይችላል፡፡ ከጽሑፍና ከስብከት አንጻርም ራስን ገታ አድርጎ ስለ መፍትሔ እያስኬዱ በጎ አድራጎትን ግን ማስተጓጐል አይገባም፡፡ ምክንያቱም በሌላ ወገን ሰይጣን በአጉል ትሕትና ሊጥለን ይችላል፡፡ “አንተን ብሎ ሰባኪ፤ አንተን ብሎ ጸሐፊ፤ ስንት ሌሎች እያሉ” እያለ በዛ ብዕር ብዙዎች እየተማሩበት፣ በዚያ ስብከት ብዙዎች እየተጠሩበት፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰጠው ጸጋ ብዙዎችን እያዳነበት ሳለ፥ ሰይጣን በሌላ መንገድ “አንተን ብሎ ሰባኪ” ይለውና ያ ሰው ተጸጽቶ ራሱን ማጠናከር ሲገባው ብትተወው ይሻላል የሚል መልእክት አምጥቶ ብዙ ነፍስን ለማዳን ምክንያት የኾነውን አንደበትና ምስክርነት ይስተጓጐላል፡፡ ስለዚኽ ራስን ማስተካከል እንጂ አገልግሎቱ መቋረጥ የለበትም፡፡ በተለይ ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ከጽሑፍና ከመመስከር ጋር የተያያዘ ሲኾን፡፡
በአጠቃላይ ግን አንድ አገልጋይ ከሚሰብከው፣ ከሚዘምረው፣ ከሚጽፈው፣ ከሚቀድሰው፣ ከሚመሰክረው ጋር ሕይወቱ ይጣጣምለት ዘንድ የሚከተሉትን ነጥቦች ማየት አለበት፡-
1.  ደካማ ጐንን መለየት፡፡ ለኹሉም አንድ ዓይነት ሐሳብ መስጠት ቢያስቸግርም እያንዳንዱ አገልጋይ ደካማ ጐን አለውና ማንነቴ አልታረቅ ያለው ለምን አልታረቅ እንዳለው ደካማ ጐኑን መለየት አለበት፡፡ መፍትሔውን የሚዠምረው ድካሙ የቱ ጋር እንደኾነ፣ ምን እንደኾነ ከለየ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ችግሩ ምን እንደኾነ ላልታወቀ ሕመም እንዲኹ መድኃኒት ለመውሰድ እንደ ማሰብ ነው፡፡
2.  ጉዳቱን ማስተዋል፡፡ አጉል ሕይወት ውስጥ ያለ ሰው የአጉል፣ የኃጢአት ሕይወትን ውጤት ማሰብ ያስፈለጋል፡፡ የኃጢአት ደመወዝ ምን እንደኾነ ማሰብ ሞት እንዳለበት ይገነዘባል፡፡ መሞት የሚፈልግ ሰው ደግሞ የለም፤ ያውም ዘለዓለማዊ ሞት፤ ዘለዓለማዊ እሳት፤ ዘለዓለማዊ ስቃይ፤ ዘለዓለማዊ ለቅሶ፣ ዘለዓለማዊ ጥርስ ማፋጨት፡፡ ስለዚኽ “ስለ ቅዱሳን፣ ስለ ነቢያት፣ ስለ ጻድቃን፣ ስለ ሰማዕታት ዘወትር እየመሰከርኩኝ እኔስ የት ነው ያለኁት? ለምንድነው ከዚኽ የማልወጣው?” ብሎ እንደየክስተቱ ጉዳቱን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ፍርድምኮ አለው፡፡
3.  ክፉን መተውና በጎውን መኖር እንደሚቻል ማመን፡፡ እንደምጽፈው፣ እንደምመሰክረው፣ እንደምዘምረው ላልኾን እችላለኁ ብሎ ራስን ከማስነፍ ይልቅ “ለሚያምን ኹሉ ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር ያስችለኛል፡፡ ምናልባት እስከ አሥረኛ ማዕረግ ላልደርስ እችል ይኾናል፤ ወጣኒ መኾን ግን ይቻላል፡፡ ፍቃደ ሥጋን ድል ማድረግ ይቻላል፡፡ በእኔ ላይ የነገሠው ንጉሥ ድል ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት አላውያንን ድል አድርገው ለስለት ሲዳረጉ እኔ ላይ የነገሠው ዘፈን፣ ፍቃደ ሥጋ ነው፣ አብዝቶ መብላትና መጠጣት፣ ፍቅረ ንዋይ ነውና ይኽን የመሰለ ኹሉ ድል ማድረግ ይቻላል” ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ሕይወት ልዩ የሚያደርገውም ይኸው ነው፡፡ ድል መንሻውን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሰጥቶናል፡፡ ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ምጽዋቱ፣ ስግደቱ፣ ንስሐው፣ በሥጋ ወደሙ፣ በቃለ እግዚአብሔር ተመርቶ መኖርን ሰጥቶናል፡፡ ከዚኽ አንጻር ከቅዱሳን ሕይወት በመማር ይቻላል ብሎ ሕሊናን ማሳመን ይገባል፡፡ “እነርሱ ታላላቁን ኃጢአት ድል እንደነሱ ኹሉ እኔም በዓቅሜ እግዚአብሔር ድል የምነሳበትን ኃይል ሰጥቶኛል፤ እችላለኁ” ማለት አለብን፡፡ በጥንቃቄ ስንመለከተውኮ አብዛኛውን ጊዜ እኛ ነን ወደ ኃጢአት የምንሔደው እንጂ ኃጢአት ወደ እኛ አይመጣም፡፡ አዳምና ሔዋን ጎምጅተው እጃቸውን ወደ ዕፀ በለስ ዘረጉ እንጂ ዕፀ በለስ ብሉኝ ብላ ወደነርሱ አልመጣችም፡፡ ዛሬም ሰዎች ወደ ክፉ ሥራ የምንሔው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ጠጣኝ ያለ መጠጥ የለም፤ እኛ ነን ወደ መጠጥ የምንሔወደው፡፡ አደንዛዥ ዕፆች ኪሳችንና አፋችን ውስጥ ገብተው አላስቸገሩንም፤ ዐቅደን የምንገዛው እኛው ነን፡፡ ብዙውን ጊዜ ቀጠሮ ይዘን ነው ኃጢአትን የምንሠራው፡፡ ስለዚኽ ቀጠሮ ይዘን ኃጢአት እንደምንሠራ ኹሉ ቀጠሮ ይዘን ንስሐ መግባትም እንችላለን ማለት ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምንወድቀው ሐዋርያው ያዕቆብ እንዳለ ከምኞቶቻችን የተነሣ ነው፤ በራሳችን ምኞት እንፈተናለን፡፡ ከሰይጣን ፈተና ባሻገር ሰው በራሱ ፈተና ይፈተናል፡፡ በራሱ ወደ ኃጢአት ይሔዳል /ያዕ.1፡13/፡፡ በራሳችን ምኞት ነው ወደ ክፉ ተግባር፣ ወደ ሱስ፣ ወደ ኃጢአት፣ ወደ ጠብ የምንሔደው፡፡ አንዳንድ ሰውኮ “እገሌን እንዲኽ እለዋለኁ” ብሎ ቀጠሮ ይዞ ለጠብ ተዘጋጅቶ የሚሔድ አለ፡፡ ለጥል ቀጠሮ ይዞ የሚወጣ ሰው ለዕርቅ፣ ንስሐ አባቱን ለማግኘት ቀጠሮ ይዞ የማይወጣው ለምንድነው? ወደ ጠብ የሔደውኮ ይኸው አካል ነው፡፡ ስለዚኽ ይኸው አካል መስመሩን ቀይሮ ወደ ዕርቅ መሔድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይኸው አንደበት ከዘፈነ ይኸው አንደበት አለመዘመሩ ለምንድነው? ሌላ የሚደረብብን አካል የለም፤ አንድ ራስ አንድ አዕምሮ ነው ያለንና፡፡ ከዚኽ አንጻር ክፉ ነገርን የወሰነ አዕምሮ በጎ ነገርን እንዲወስን ማስቻል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ይቻላል፡፡ እሳት እያዩ የወሰኑትኮ እንደ እኛ ሥጋ የለበሱት ናቸው፡፡ የአንበሳን አፍ እያዩ የወሰኑት እነ ዳንኤልኮ እንደኛ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ የለበሱትን ሥጋ ነው እኛም የለበስነው፡፡ የነርሱን ያኽል ከግዙፋን ነገሮች ጋር የመዋጋት ዓቅም ባይኖረንም በተሰጠን አእምሮ፣ በተሰጠን መንፈሳዊ ኃይል ግን የራሳችንን አካል የራሳችንን ፈቃድ መግታት እንችላለን፡፡ ብዙ ቆራቢዎችን የሚያይ ሰው እኔም እንደነርሱ ራሴን ገዝቼ መቁረብ እችላለኁ ብሎ ማመን አለበት፡፡ አሜሪካን ሀገር ኾነው የሚቆርቡ አሉ፡፡ ዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬትስ ኾነው የሚቆርቡ አሉ፡፡ መቀሌ ኾነው የሚቆርቡ አሉ፡፡ አርባ ምንጭ ኾነው የሚቆርቡ አሉ፡፡ አየር መንገድ ኾነው የሚቆርቡ አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጧት ማታ እየኖሩ የሚቆርቡ አሉ፡፡ መቁረብ የሚችሉት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለኖሩ ወይም ስላልኖሩ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ስላሉ ወይም በዓረብ ሀገር ስለሚኖሩ አይደለም፤ የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ ኹኔታውን አዘጋጅቶ የማመን ጉዳይ ነው እንጂ ቁርባን አንድ ነው፤ መንፈሳዊ ሕይወትም አንድ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በሰብአ ዓለም ኾነው በበጎ ምግባር ጸንተው መኖራቸውኮ መኖር እንደሚቻል በተግባር እያሳዩን ነው፡፡ በገዳምና በቤተ ክርስቲያን እየኖሩ ድል የነሱ አሉ፤ በዓለም መካከል እየኖሩ ድል ነስተው ለሥጋ ወደሙ የበቁም አሉ፡፡ እኛም እንችላለን ማለት ነው፡፡ ስለዚኽ የምንጽፈውን፣ የምንሰብከውን፣ የምንዘምረውን፣ የምንቀድሰውን፣ በስንክሳር የምናነበውን የአባቶችና የእኛቶች ሕይወት ከፊሉም ቢኾን መኖር እንደሚቻል ማመን አለብን፡፡
4.  መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ይኽም ማለት በሕይወታችን መርሐ ግብርን በማውጣት ዛሬን ጥሩ ኾኖ መዋል ነው፡፡ በበጎ ነገር ለመዋል ማቀድና ያንን ለመፈጸም ተግቶ መዋል፡፡ በዚኽ ውሎአችን ደግሞ እግዚአብሔርን ማመስገን፡፡ “በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል” ይላልና በአንድ ቀን በኹለት ቀን ጥንካሬአችን እግዚአብሔር በብዙ ይሾመናል፡፡ እኛ ክፉውን ለመተው፣ ከሱስ ለመራቅ፣ የምንጽፈውን የምንሰብከውን የምንቀድሰውን የምናነበውን የምንዘምረውን ለመኾን ስንዘጋጅ እግዚአብሔር ደግሞ መልስ ይሰጣል፡፡ ጠቢቡ፡- “የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው” እንዳለው ለመለወጥ መዘጋጀት /ምሳ.16፡1/፡፡ ይኽም ዛሬ መዠመር፡፡
5.  መገምገም፡፡ “ከትናንትናው ይልቅ ዛሬ ምን ያኽል ተሻሻልኩ?” ብሎ ራስን መገምገም፡፡ በዚኽም እግዚአብሔርን ማመስገን፡፡ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ግምገማ አለ፡፡ ይኽ ግምገማ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ በጣም ታላቅ ቦታ አለው፡፡ “ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጾሙ ወቅቱ እንዴት አለፈ? ምን ያኽል አስቀደስኩ? ምን ያኽል አገለገልኩ?” እያልን እንደየደረጃችን እንዲኽ ራሳችንን መገምገም አለብን፡፡ እያንዳንዳችን አገልጋዮች፣ ሰባኪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ አንባቢዎች “ምን ያኽል ለውጥ አለኝ? ምን ያኽል ከምጽፈው ከምመክረው ከምሰብከው ጋር ተዛምጃለኁ? እያንዳንዱን ዕለት ምን ያኽል በጥንቃቄ አሳለፍኩት?” ብለን መገምገም፡፡ ይኽን አድርገን ራሳችንን ስንመረምር ድክመታችንን ለይተን እናወጣለን፡፡ ከዚያም “ነገ ይኽን አርማለኁ” ብለን እንዘጋጃለን፡፡ ጠጠር ያለብን ካለ ደግሞ ከእኛ ወደሚሻሉት ሔደን ምክርን እንጠይቃለን፡፡ በለውጣችን ደስተኞች መኾን ይገባናል፡፡ ነገ ወደ ተሻለ ለውጥ ውስጥ የምንገባው በለውጣችን እጅግ ደስተኞችና አመስጋኞች ስንኾን ነው፡፡ የቅዱሳን አካሔድ እንደዚኽ ነው፡፡ መዠመሪያ መጾም የማይችሉ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ እስከ 3፡00 ሰዓት ቆይተው መጾም መለማመድ ይዠምራሉ፡፡ በነጋታው ወይም በሦስተኛው ቀኑ እስከ 6፡00 ሰዓት፤ በሳምንቱ እስከ 7፡00 ሰዓት ይጾማሉ፡፡ ጠንከር ሲሉ እስከ 9፡00፤ ከዚያም ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ እንዲኽ እያደረጉ በለውጣቸው እየተደሰቱ ይሔዱና በዚኹ ጣዕሙ እየጣፈጣቸው ይሔዳሉ፡፡ እፍኝ ወደ መቅመስ የሚሔዱት እንዲኽ ባለ መንገድ ወይም ልምምድ ነው፡፡ እንዲኽ እያደረጉ እስከ 40 ቀን ያለ እኽል ይዘልቃሉ፡፡ እጅግ የበረቱ ደግሞ ጭራሽ በሕይወት ዘመናቸው ከምድራዊ መብልና መጠጥ ርቀው የሚኖሩ አሉ፡፡ የመንፈሳውያን አባቶች መንፈሳዊ ዕድገት ስናይ እንደዚኽ ነው፡፡ ለዚኽ ኹሉ ያደረሳቸው በትንሹ ለውጣቸው እየተደሰቱና እያመሰገኑ ለአዲስ ሕይወት ሽግግር ራሳቸውን ያዘጋጁ ስለነበር ነው፡፡ የኛ ትልቁና አባቶቻችንን የማንመስልበት ነጥብ እዚኽ ጋር ነው፡፡ እኛ በለውጣችን አንደሰትም፤ አናመሰግንም፡፡ በመኾኑም የዕድገት ትርጉሙ ተዛብቶ ወደ ታች ይኾንብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የዠመረ ሰው በስሜታዊነት እስከ 12፡00 ሰዓት መጾም ይዠምራል፡፡ ተማርኩኝ፣ ዘማሪና ሰባኪ ዐወቅኩኝ እያለ ይሔዳል፡፡ ራሱን የሚገመግመው ማንን ዐወቅኩ ነው እንጂ ምንን ዐወቅኩ የሚል አይኾንም፡፡ በመኾኑም ከ12፡00 ወደ 9፡00 ይወርዳል፡፡ አኹንም ደግሞ ጳጳሱን ዐውቂያለኁ፤ ቄሱን ዐውቂያለኁ፤ ዩኒፎርም ለብሼ ዘምሪያለኁ፤ ጭራሽ ቀዳሽ ከኾነ ደግሞ ቀድሻለኁ ብሎ ተመጻድቆ ጾሙን ወደ 6፡00 ሰዓት ያወርዷል፡፡ ማኅበራትን ዐውቂያለኁ፤ ቤተ ክህነቱን ዐውቂያለኁ፤ ጽፊያለኁ፤ ሰብኪያለኁ፤ ዘምሪያለኁ፤ ያልቆምኩበት ዓውደ ምሕረት የለም ሲል ጧት 3፡00 ሰዓት ላይ መብላት ይዠምራል፡፡ የብዙዎቻችን “ዕድገት” ይኼ ነው፡፡ ለምንድነው እንደዚኽ የኾንነው? በለውጣችን እያመንንና እየተደሰትን ስላልሔድን፡፡ አለማመናችን፣ አለመገምገማችን፣ አለማመስገናችን፣ አለመደሰታችን ጭራሽኑ ወደ መመጻደቅና ወደ መውደቅ አመጣን፡፡ ከብዙዎቻችን በመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥ የጠፋው ከዚኹ የተነሣ ነው፡፡ ለውጣችንን አልገመገምነውም፡፡ ለውጣችንን አልተከታተልነውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ማደግህ በነገር ኹሉ እንዲገለጥ ይኽን አስብ፤ ይኽንም አዘውትር፡፡ ለራስኽና ለትምህርትኽ ተጠንቀቅ፤ በእነዚኽም ጽና፡፡ ይኽን ብታደርግ ራስኽንም የሚሰሙኽንም ታድናለኅና” ነበር ያለው /1ኛ ጢሞ.4፡1/፡፡ እኛ ግን መንፈሳዊ ዕድገትን በዚኽ መልኩ አይደለም ያስኬድነው፡፡ አባቶቻችን እንዲኽ ራሳቸውን እየመረመሩ፣ እየገመገሙ ስለሔዱ ነው ራሳቸውን ያዳኑት፤ የመዳንን ቃልኪዳን  ተቀብለውም ምክንያተ ድኅነታችን የኾኑት፡፡ ስንክሳሩም፣ ገድላቱንም ሌላውንም ብናይ ዕድገታቸውን በጥንቃቄ ሲከታተሉትና ሲገመግሙት ነው የምናገኘው፡፡ ተመስገን ሲሉ ጸጋ እግዚአብሔርም እየበዛላቸው ይሔዳል፡፡ የኛ ለውጥ ግን ከላይ እንደተናገርኩት ቁልቁሊት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴን ተምሪያለኁ፤ ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ደረስኩ ነው የምንለው፡፡ ትልቅ ለውጥ የምናደርገው ይኽን ነው፤ የዕውቀት ለውጥ፡፡ አንደኛ ዙር ተምሪያለኁ፤ ለኹለተኛ ዙር ደረስኩ ማለትን፡፡ አንደኛ ዓመት ላይ ስንማር እያማተብን የነበርን ሰዎች ኹለተኛ ዓመት ላይ ስንኾን ማማተብ እናቆማለን፡፡ በአንደኛ ዓመት ላይ ነጠላ አደግድገን ስንገባ የነበርን ሰዎች በሣልሳይ ወይም በራብዓይ ዓመት በካኔቲራ ቤተ ክርስቲያን ብንገባ ደስ ይለናል፡፡ በቀዳማይ ዓመት ተማሪ ሳለን ከግቢ ዠምረን ጫማ ካላወለቅን ስንል የነበርን ሰዎች ራብዓይ ስንደርስ ጫማ ተደርጎ ቢገባ ምን ችግር አለው እንላለን፡፡ ከዚኽ መረዳት እንደምንችለው ጉድለቱ ከተማርነው ቃሉ ሳይኾን ከእኛ ነው ማለት ነው፡፡ ቃሉማ አባቶቻችንን ሲለውጥ ዐይተኗል፡፡ የእኛ ዝግጀት ለለውጥ ስላልኾነ አንለወጥም፡፡ ዝግጅታችን ለዕውቀት ብቻ ስለሚኾን አንለወጥም፡፡ የስሜት ነው፡፡ ስለዚኽ ኹል ጊዜ “ይኽን ዐወቅኩ፤ ተመስገን፡፡ በሕይወቴ ደግሞ ይኽን መፈጸም እዠምራለኁ” ማለት አለብን፡፡ ስለ ጸሎት ስንማር ዓላማው ዳሽ ሙላውንና ምርጫውን እንድንመልስ አይደለም፤ በሕይወታችን ባዶ ቦታ ላይ እንድንሞላ ነው እንጂ፡፡ ስለ አጽዋማት ስናስተምር “ላላወቁ አሳውቃለኁ፤ ዐውቂያለኁ፤ ረቂቅያለኁ፤ ጳጳሱንም ቄሱንም በልጪያለኁ” ብለን እንድንመጻደቅበት ሳይኾን ጾሙ ምን ያኽል እየጾምኩት ነው? አምና እስከ 9፡00 ጾምኩ፤ ዘንድሮስ? አምና በንስሐ ነው ያሳለፍኩት፤ ዘንድሮስ በሥጋ ወደሙ ነው?” እንድንል ነው፡፡  የበዓላቱም ዓላማ፣ የአጽዋማቱ ዓላማ እንዲኽ እንድናስብ ነው፡፡ የለውጥ ዓላማን እንድናስብ፡፡ ልደትንና ትንሣኤን ስናከብር ድጋሜ ተወለደ፤ ድጋሜ ተነሣ እያልን እኮ አይደለም፡፡ የእኛ መወለድ የእኛ መነሣት እንድናስብና እንድንመረምር ነው፡፡ ጾመ ነነዌ ስንጾምኮ ለነነዌ ሰዎች ብለን አይደለም የምንጾመው፡፡ እነርሱማ በወቅቱ ተጠቀሙበት፡፡ ለራሳችን ብለን ነው፡፡ ልክ እንደዚኹ አበው የተጠቀሙበትን ሕግና ሥርዓት ለእኛ የተዉልን እንድንጠቀምበት ነው፡፡
     ስለዚኽ ዕውቀት በሕይወት ካልተገለጠ፣ ዕውቀት በእምነት ካልተገለጠ ከንቱ ነው፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ክርስትና ሕይወት ስሜት ይኾናል፡፡ የምንጽፈውም ስሜታዊ ነው፤ የምንሰብከውም ስሜታዊ ነው፤ የምንዘምረውም ስሜታዊ ነው፡፡ ልክ እንደ ኪነ ጥበብ ሰዎች ነው ስሜት (ሙድ) ውስጥ የምንገባው፡፡ ስሜታዊነት የተቀላቀለበት እንጂ ዝግጁ የኾነ ጸሐፊነት፣ ሰባኪነት፣ ዘማሪነት አይታይብንም፡፡ በእምነት ስንኾን ግን 24ቱን ሰዓት ቤተ ክርስቲያን በልባችን ውስጥ ትኾናለች፡፡ 24 ሰዓት ሙሉ ቤተ ክርስቲያን መዋል አንችል ይኾናል፡፡ 24 ሰዓት ቤተ ክርስቲያንን በልባችን ውስጥ ካዋልናት ግን ንግግራችን ቤተ ክርስቲያናዊ ነው፤ ሕይወታችን ቤተ ክርስቲያናዊ ነው፤ አረማመዳችን ቤተ ክርስቲያናዊ ነው፡፡ ስለዚኽ በለውጥ ሒደት ውስጥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለመጻፍ፣ ለመናገር፣ በስሜት ለመግለጥ ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያን ራሷን ልባችን ውስጥ ለማኖር መኾን አለበት፡፡ ሌሊትም ልቤ ውስጥ እንድትኖር፤ ዓረብ ሀገር ብኖርም ልቤ ውስጥ እንድትኖር፤ ሕንድም ውስጥ ብኖር ልቤ ውስጥ እንድትኖር መኾን አለበት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኾነን የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነው፡፡ ስለዚኽ አገልጋይ ስለተባልን፣ ጸሐፊ ስለተባልን፣ ዘማሪ ስለተባልን ሳይኾን የልብ ለውጥ፣ የሕይወት ለውጥ ሊታይብን ይገባል፡፡ ለዚኽ ልዩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡ እነ አፍኒን እነ ፊንሐስ መቅደስ ውስጥ ኖረው አልተጠቀሙበት፡፡ ፍጻሜአቸው አላማረም፡፡ አኹንም መቅደስ ውስጥ ኾነን የምንጽፍ፣ የምንሰብክ፣ ስለ መቅደሱ የምንመሰክር ኾነን ሳለ ካልተጠቀኩበት ስለተጠጋንና ታቦት አጠገብ ስለቆምን ብቻ አንድንም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሚያሰኘንን ሥራ ይዘን ታቦቱ ፊት ስንቆም ነው ጸጋ እግዚአብሔር የሚያድርብን፡፡ በክህነቱም በሌላውም ኹሉ እንደዚኽ ነው፡፡ አርዮስ ሊቅ ነበር፤ ክህነትም ነበረው፡፡ ይሁዳ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ነበር፡፡ ጌታችን በጸሎቱ ሐሙስ ላይ ለክብር (ለሥጋ ወደሙ) አብቅቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ኹለቱም አልተጠቀሙበትም፡፡
ዛሬ እነዚኽን የምንጠቅሰው አርዮስንና ይሁዳን ለመንቀፍ አይደለም፤ ስለ ራሳችን እንድናስብበት ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለአገልግሎት፣ ለመንፈሳዊ ሹመት፣ ለሌሎች መስካሪ አድርጎ አዘጋጅቶናልና በአገልግሎት ውስጥ የምንረዳውንና የምናምንበትን ቃለ እግዚአብሔር በልባችን ይዘን እንድንኖርበት ነው፡፡ ስለዚኽ እኛና የምንጽፈው፣ እኛና የምንሰብከው፣ እኛና የምንዘምረው፣ እኛና የምንቀድሰው ይስማማልን ዘንድ በትሕትና ራሳችን አይተን ደካማ ጎናችንን እንለየው፤ ጉዳቱን እናስተውለው፤ ክፉውን መተውና በጎ መኖር እንደሚቻል እንመን፤ ይኽንንም እንለማመደው፡፡ በለውጣችን እየተደሰትንም ለውጣችንን መከታተል ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! 

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount