በቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ልጆቼ! ክርስቲያን ሲያርፍ አግባብ የሌለው ለቅሶ አይለቀስም፡፡ ታላቅ የኾነ ሥነ ሥርዓት እየተካሔደ
ሳለ ለቅሶ አይለቀስም፡፡ እማልዳችኋለሁ! እስኪ ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ! ኹላችንም በአንድ ቦታ ተሰብሰበን ሳለ የሀገራችን
ንጉሥ ለአንዳችን የጥሪ ወረቀት ልከው ለእራት ግብዣ ጠሩን እንበል፡፡ ከእኛ መካከል ወደ ንጉሡ ተጠርቶ ስለ ሔደው ሰው የሚያለቅስ
ማን ነው?
ልጆቼ!
ከእኛ መካከል በሞት የተጠራው ወንድማችን እኮ በንጉሠ ሰማይ ወምድር ነው፡፡ የሚያጅቡት የምድር ሰልፈኞች አይደሉም፤ ቅዱሳን መላእክት
እንጂ፡፡ ታድያ ለዚኽ ወንድማችን ይለቀስለታልን? ወንድማችን ወደ ላይኛው ቤቱ ሲሔድ የሚደረገው ምሥጢር አይታያችሁምን? እንደምን
ባለ ይባቤ፣ እንደምን ባለ ዕልልታ፣ እንደምን ባለ ምስጋና እየሔደ እንደኾነ አታስተውሉምን? ታድያ ይኼ የለቅሶና የዋይታ ሰዓት
ሊኾን ይገባዋልን? እየተፈጸመ ያለው እኮ ታላቅ መለኮታዊ ምሥጢር ነው፡፡ ነፍሱ የሥጋ አዳራሽዋን ትታ ወደ ጌታዋ ስትሮጥ እያየን
ልናለቅስ ደግሞም ፊታችንን ልንነጭ ይገባናልን? ሰው በልደት ቀኑ እንዴት ይለቀስለታል? ምክንያቱም የአኹኑ ልደት ከእናት ከአባታችን
ከተወለድንበት ልደት ይልቅ እጅግ ያማረና ያሸበረቀ ነው፡፡ በዚኹ ሰዓት ነፍስ ወደ ተለየ ብሩህ ዓለም ትሔዳለች፤ ከእሥራት ቤትዋ
ትላቀቃለች፤ ሩጫዋን ትጨርሳለች፡፡ በምግባር በሃይማኖት ለሔደ ሰው እንዲኽ ሊለቀስለት የሚገባ አይደለም፡፡
ሕፃናት
ሲሞቱስ እንዲኽ ልንኾን ይገባናልን? ምን የሚወቀስ ነገር አላቸውና ነው? አዲስ በተጠመቁ ክርስቲያኖችሳ? ስለምን እንዲኽ እናዝናለን?
ፀሐይ
በወጣች ቁጥር ፀዳለ ብርሃኗ እየጠራ ይመጣል፤ ነፍስም ከሥጋዋ አዳራሽ ስትወጣ ኹለንተናዋ እየጠራና በክብር እየደመቀች ትታያለች፡፡
የዚኽች ነፍስ ብርሃን አንድ ንጉሥ ወደ አንዲት ከተማ ሲመጣ ከተማዋን እንደሚሞላት ያለ ብርሃን አይደለም፡፡ ልጆቼ! ነፍስ በዚያ
ሰዓት የሚይዛትን መደነቅ፣ መገረምና ሐሴት እስኪ በዐይነ ኅሊናችሁ ሳሉት! ይኽን እያየ የሚያዝን ማን ነው?
ለቅሶ
የሚገባው ከእነ ኃጢአታቸው ለሞቱት ሰዎች ነው፡፡ ይኽን ዓይነቱ ኀዘን እኔም አልቃወምም፡፡ ይኽ ዓይነት ኀዘን ሐዋርያዊ ነው፡፡
ይኽ ዓይነቱ ኀዘን ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ከኃጢአቷ አልመለስ ስላለችው ኢየሩሳሌም አልቅሷልና፡፡ የኀዘናችንና
የለቅሶአችን ሥርዓት እንዲኽ መኾን አለበት፡፡
ከእነ
ኃጢአቱ ላልሞተ ሰው “እናቴ ሆይ ተመለሺ! ወንድሜ ሆይ አትሙትብኝ!” ዓይነቱ ከኾነ ግን ሊለቀስለት የሚገባው በሥጋ ለተለየው ሰው
ሳይኾን ለእኛ ነው፡፡ ከእነ ኃጢአቱ ከሞተ ግን አልቅሱለት፡፡ እኔም እንዲኽ ላለ ሰው አብሬ አለቅሳለሁ፡፡ “ለምን?” የሚጠብቀው
እሳት፣ የሚቆየውን አለንጋ እያየሁ አለቅስለት ዘንድ ያስገድደኛልና፡፡ እንዲኽ ከእነ ኃጢአቱ ለሞተ ሰውስ እናንተ ብቻ ሳትኾኑ የከተማይቱ
ሰው በሙሉም ቢኾን ሊያለቅሱለት ይገባል፡፡ እውነተኛው ሞት ይኼ ነውና፤ ክፉው ሞት ይኼ ነውና፤ የኃጢአተኞች ሞት!
የኃጢአተኛው ሞት ለቅሶ ይገባዋል፡፡ በክርስቶስ ፊት ቆሞ የሚመልሰው ሲያጣ ዐይቶ፣ አስፈሪውን የፍርድ
ቃል ሲሰማ ተመልክቶ ለእንዲኽ ዓይነቱ ሰው ኀዘን ይገባል፡፡ እንዲኽ ዓይነቱ ሰው ከኃጢአት ውጪ ለምንም ዓላማ አልኖረምና ሊለቀስለት
ይገባል፡፡ ለእነዚኽ ሰዎችስ ባይወለዱ ይሻላቸው ነበር /ማር.14፡21/፡፡
እስኪ
ይኽን አስተውሉ! አንድ ሰው ያለምንም ዓላማ ለሃያ ዓመታት ቢኖር ይኽን ያኽል ዘመን በከንቱ እንዳሳለፈ ቆጥሮ አያለቅስምን? ከሰው
ኹሉ የባሰ ሰነፍ እንደኾነ ራሱን አይቆጥርምን? ለአንዲት ቀን እንኳ ለነፍሱ ሳይኖር መላ ዘመኑን ለቅምጥልነት፣ ለክፋት፣ ለምቀኝነት፣
ለኃጢአት፣ ለዲያብሎስ ለኖረ ሰውማ እንዴት? እንዲኽ ላለ ሰው ሊለቀስለት አይገባምን? ከሚያገኘው እሳት ነጥቀን እንድናወጣው አንሻምን?
አዎ! ፈቃደኞች ከኾንን ይኽን ሰው ከሚያገኘው ምረረ ገሃነም ልናወጣው እንችላለን፡፡ ሳንሰለች የምጸልይለት ከኾነ፣ ሳናቋርጥ ምጽዋት
የምንሰጥለት ከኾነ ልናድነው እንችላለን፡፡ ድኅነት የማይገባው ሰው እንኳ ቢኾን እግዚአብሔር የእኛን ውትወታ ይሰማል፡፡
ቅዱስ
ጳውሎስ ምሕረት ለማይገባቸው እንኳን ምሕረት ሲያደርግላቸው ከነበረ /2ኛ ቆሮ.1፡11፣ 2ቆሮ.2፡10/ እኛ ደግሞ ከዚኽ በላይ
ልናደርግ ይገባናል፡፡
እንዲኽ ያደረግን እንደኾነ፣ ወደንና ፈቅደን ወንድማችንን የምንረዳው ከኾነ፣ ስለ ርሱ ብለን ቀዝቃዛ
ውኃ የምንሰጥለት ከኾነ ከዚያ አሰቃቂ እሳት ይድናል፡፡
በሕይወተ
ሥጋ ሳለ ምጽዋት አልሰጠምን? እግዚአብሔር በመጨረሻይቱ ቀን ያድነው ዘንድ ሚስቱ፣ ዘመዶቹ በእምነት ይስጡለት፡፡ ብዙ ኃጢአት ሠርቶ
ከኾነ ብዙ ምጽዋት ይስጡለት፡፡ ራሱ ትንሽ ቢሰጥ እንኳ በቂ የነበረ ቢኾንም እኛው ብዙ ከሰጠንለት ይበቃል፡፡ ልጆቼ! ለዚኽ ከእነ
ኃጢአቱ ለሞተው ሰው ሐወልት ልንሠራለት የምንጣደፍ አንኹን፡፡ በምድር ላይ መታሰቢያ ልናቆምለት ልናበጅለት የምንሯሯጥ አንኹን፡፡
እውነተኛ መታሰቢያ ይኼ ነው፤ ምጽዋቱ፡፡ በርሱ ስም እንመጽውት፤ ከዚያም ይጸልዩለት ዘንድ ለነዳያኑ ስመ ክርስትናውን እንንገርለት፡፡
ይኽን ስናደርግ እግዚአብሔር ይራራለታል፡፡ ሰውዬው ራሱ ይኽን ባያደርግ እንኳ ሌሎች ሰዎች ስለ ርሱ ሰጥተውለታልና፡፡ ይኽም ከእግዚአብሔር
ዘንድ ምሕረትን እንዲያገኝ ያደርጓል፡፡ እነዚኽ በርሱ ስም የተመጸወተላቸው ሰዎች ከአኹኑ ሞት ሳይኾን ከመጨረሻይቱ ሞት ይድን ዘንድ
በእግዚአብሔር ፊት ይማልዳሉ፡፡
ልጆቼ! ብቻ እኛ ቸልተኞች አንኹን እንጂ የእግዚአብሔር የማዳኑ ጥበብ ብዙ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን
ስለሙታን የምትጸልየው ጸሎት ለከንቱ አይደለም፡፡ ምጽዋት የሚሰጠው ለከንቱ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይኽን እንድናደርግ ያዘዘን
በከንቱ አይደለም፤ ርስ በርሳችን እንድንጠቃቀም እንጂ፡፡ ልጆቼ! የሞተው ወንድማችሁ ከምጽዋታችሁ እንደሚጠቀም ቅንጣት ታኽል የምትጠራጠሩ
አትኹኑ፡፡ በቅዳሴአችን ጊዜ ዲያቆኑ “በክርስቶስ ስላንቀላፉ ሰዎች ጸልዩ” ብሎ የሚያውጀው ለከንቱ አይደለም፡፡ ይኽን የሚያውጀው
ግን ዲያቆኑ እንዳይመስላችሁ፤ መንፈስ ቅዱስ እንጂ፡፡ ዲያቆኑ እንዲኽ ሲያውጅ በዙርያው አእላፍ መላእክት አሉ፤ ሊቃነ መላእክት
አሉ፤ ወልደ እግዚአብሔር አለ፡፡ ታድያ ይኼ አዋጅ ለከንቱ ይመስላችኋልን? ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ቀሳውስት፣ በአጠቃላይ
ስለ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የሚቀርበው ጸሎት ለከንቱ ይመስላችኋልን? በፍጹም! የሚደረገው ኹሉ በእምነት ነው፡፡
በዚያ በቅዳሴ ሰዓት ስለ ሰማዕታት የሚቀርበው መሥዋዕት ለከንቱ ይመስላችኋልን? ቅዳሴው ልዩ ምሥጢር
ነው ወዳጆቼ! በቅዳሴ እኮ የሌለ የለም፡፡ ስለዚኽ በዚያ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ማሳሰቧ ትክክል ነው፡፡ አንድ ምድራዊ ንጉሥ ከእናንተ
መካከል ቢገኝ ይኽን አድርግልን ይኽን አድርግልን እያልን የምንጠይቀው አይደለምን? ይኽን ብለን ከጠየቅነው በኋላስ የጠየቃችሁት
ኹሉ ከንቱ ነው ይላልን? አይልም፡፡ በቅዳሴው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ስለ ኹሉም ማሳሰቧማ እንዴት?
ስለዚኽ በእምነት እናቅርብላቸው እንጂ ምንም አይጠቅማቸውም ብለን ችላ የምንል አንኹን፡፡ ስለሞቱት
ወንድሞቻችን አላስፈላጊ የኾነን ኀዘን ከምናዝንላቸው፣ አላስፈላጊ የኾነን ሐወልት ከምናቆምላቸው ይልቅ እንመጽውትላቸው፤ እንጸልይላቸው፤
መሥዋዕት እናቅርብላቸው፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ እነርሱንም እንጠቅማቸዋለን፤ እኛም ራሳችን እንጠቀማለን፡፡ †
ምንጭ፡- ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች፣ ገጽ 106-110
Kale hiwet yasemaln
ReplyDeleteegziabhier yabertah.
ReplyDeleteKale heyoten yasemalin nebesachewen beaberham ekif yanurelin!!!
ReplyDeleteአንድ አባ ትምህርተ ወንጌል ሴሰጡ ከሞቱ በኋላ ያለው ፍትሃት ለመታሰቤያ ነው ። ሰራ በቁም እያሉ ነው ።ብለዋል ከዜህ ትምህርት ጋር እንዴት ነው?
ReplyDelete