(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 8 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
(ይኽ ጽሑፍ ከዚኽ
በፊት ተለጥፎ የነበረ ነው)
በቤተ
ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ባለው ወራት ረቡዕንና ዓርብን ጨምሮ አይጦምም፤ የቀኖና ስግደትም
አይሰገድም፡፡ ይኽም ሠለስቱ ምዕት በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ሲሰበሰቡ በሀያኛው ቀኖኗቸው የወሰኑት ቀኖና ነው /ሃይ.አበ.20፡26፣
The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1250, 1738/፡፡ ይኽን ቀኖና ሲወስኑም ያለ
ምክንያት አይደለም፡፡ ይኽ ወራት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለውን ሕይወታችን የሚያሳይ ስለኾነ ነው እንጂ፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ
ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት ተብሎ የሚደረግ ጦምም ኾነ ስግደት የለም፡፡ ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ በዲያብሎስ ከመፈተን፣
ከእግዚአብሔር ውጪ የኾነ ሌላ ሐሳብን ከማሰብ ነጻ የሚወጣበት ወራት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ፈቃዳችን ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር የተስማማ
ነው፡፡ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ከድካሙ ነጻ ስለሚኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን ትጉኅ ነው፡፡ እንደ አኹኑ እንቅልፍ እንቅልፍ አይለውም፤
ዘወትር የቅዱሳን መላእክትን ምግብ ለመብላት ማለትም ለማመስገን የተዘጋጀ ነው እንጂ፡፡
ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለው ሕልውናችን
በማያቋርጥ ብርሃን በደመቀችና በንጹሕ ፈሳሽ ውኃ በለመለመች፣ በማኅሌትና በይባቤ ድምፆችም በተመላች የተድላና የደስታ ዓለም መኖር
ነው፡፡ በዚያ ፀዋትወ መከራ የለም፡፡ ብካይ፣ ልቅሶ፣ ሐዘን፣ በልብ መቆርቆር፣ መዋረድ፣ ነፍስን የሚያሳዝናትና የሚያስደነግጣት
ምንም ነገር የለም፡፡ በፊትኽ ወዝ መብላት መጠጣት፤ እሾኽም አመኬላም የለም፡፡ ምቀኝነትና መፎካከር የለም፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ
በኋላ ሕማመ ሥጋ ሕማመ ነፍስ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ የለም፡፡ ብርሃን እንጂ ጨለማ፣ መዓልት እንጂ ሌሊት የለም፡፡ በሰማያዊው ሕይወታችን
ደም ግባት ማሸብረቅ አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ለዘለዓለም የማያልፈውን በጎ በጎውን ክብር ማግኘት ነው እንጂ መሻት፣ መሰልቸት፣
መራብ፣ ቁንጣን የለም፡፡
ሠለስቱ ምዕት ይኽን ቀኖና ሲቈንኑ
የትንሣኤያችን በኵር የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞታችንን በሞቱ ገድሎ ስለተነሣ በሐዘን ሳይኾን በፍስሐ ወበሐሴት
እንድናከብረው፥ አንድም ሊመጣ ያለውን ሰማያዊ ሕይወታችንን ገና በዚኽ ምድር ሳለን በዓይነ ልቡናችን እንድናየው፣ እንድናስበው፣
እንድንለማመደው፣ ደግሞም ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንድንቻኰል ለማድረግ ነው፡፡
ታድያ በዚኽ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች
በእውነት በዚኹ ወራት ይኽን እናስባለን ወይ? ይኽን ተገንዘበን ወደዚያ ሕይወት ለመሔድ እንቻኰላለን ወይ? መንፈሳዊ ሕይወታችንስ
ከማንኛውም ጊዜ በላይ የሚደክምበት ወራት አይደለም ወይ? ኹለት ወራት ጦመን ያገኘነውን ዕሴት በከንቱ የምናጣበት አይደለም ወይ?
ለእግዚአብሔር ስትታዘዝ የነበረችውን ሰውነት ዳግም በዲያብሎስ አሽክላ የምትያዝበት ወራት አይደለም ወይ? ለኹለት ወራት ተዘግተው
የነበሩት የምሽት ክበባትና የዳንኪራ ስፍራዎች ዳግም የሚከፈቱበትና ዲያብሎስ ያለምንም ከልካይ ነፍሳትን የሲዖል ሲሳይ የሚያደርግበት
ወራት አይደለም ወይ? ለኹለት ወራት እንዳልሰገድን፣ እንዳልጦምን፣ ጧት ጧት ለኪዳን እንዳልገሰገስን ኾነን ፍጹም በኾነ መዘናጋት
ተይዘን ዳግም ወደ ቀድሞ ኑሯችን የምንመለስበት ወራት አይደለም ወይ?
ቅዱሳን አባቶቻችን ይኽን ቀኖና
ሲቈንኑ ከላይ ያስቀመጥነውን ዓላማ ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ግን የእኛ ስንፍና ተጨምሮበት ይኽን እንዳንገነዘብ አድርጐናል፡፡
የዚኹ ወራት ዓላማ በጭራሽ እንድንስተውና እንደ ዕሪያ ወደ ቀድሞ ምልልሳችን እንድንመለስ አድርጐናል፡፡ እግዚአብሔር የሚመለከውና
የሚመሰገነው በወቅት እስኪመስል ድረስ በዚኽ ወራት መንፈሳዊ ሕይወታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲደክም ያደርጓል፤ አድርጐታልም፡፡
በማስተዋል ሳይኾን በልምድ እንድንመላለስ አድርጐናል፡፡ ታድያ እስከ መቼ ድረስ ነው እንዲኽ የምንቀጥለው? እስከ መቼ ድረስ ነው
ዲያብሎስ እያታለለን የምንኖረው? አንድ ሰው ዓይኑ ውስጥ ትቢያ ቢገባበት ለቅጽበት (ለሴኮንድ) ስንኳ ሊታገሥ ይችላልን? አይችልም!
ታድያ ዲያብሎስ በዓይነ ልቡናችን ላይ ያስቀመጠውን ያለማስተዋል ግንድ መቼ ነው የምናስወግደው? እንዴት አድርገንስ መንፈሳዊ ሕይወታችንን
በዚኽ ወራት በቀጭኒቱ መንገድ ማስጓዝ ይቻለናል? እንደምንስ የዲያብሎስን ተንኰል ከንቱ ማድረግ ይቻለናል? አንድ ክርስቲያን እነዚኽንና
መሰል ጥያቄዎችን ሊጠይቅ ግድ ይሏል፡፡ እነዚኽን ጥያቄዎች ሲጠይቅ መፍትሔውም ምን እንደኾነ ለመገንዘብ አያስቸግረውምና፡፡
እስኪ አንድ ኃይለ ቃልን መነሻ
በማድረግ ለመማማር እንሞክር፡፡ ቃሉ እንዲኽ ይላል፡- “እንግዲኽ
ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፡፡ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር
ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና፥ ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት
ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ” /ቈላ.3፡1-4/፡፡ ከዚኽ ኃይለ ቃል እጅግ በጣም
ብዙ ቁም ነገሮችን መረዳት እንችላለን፡፡ ለጊዜው ግን ከርእሳችን ጋር የሚሔዱትን ነጥቦች ብቻ ለማየት እንሞክር፡፡
1.
ሞተናል
ሐዋርያው ሲናገር “ሞታችኋልና” ይላል፡፡ ክርስቲያን ሕይወቱን የሚዠምረው
በሞት ነው፡፡ በጥምቀት ውኃ ሞቶ ሲቀበር ሕይወቱን ይዠምራል፡፡ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ስንወለድ ብጹዕ
የሚኾን ጳውሎስ በሮሜ ክታቡ፡- “ወተቀበርነ ምስሌኁ ውስተ ጥምቀት በሞቱ - ከሞቱ ጋር አንድ እንኾን ዘንድ በጥምቀት ከርሱ ጋር
ተቀበርን” እንዳለ ከክርስቶስ ሞት ተካፋዮች ኾነናል /ሮሜ.6፡4/፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ሞተናል፡፡ ይኽን ሞት ሞተን ስንቀበር
አሮጌው ሰውነታችን ላይነሣ ተቀብሯል፤ በምድር ሳይኾን በውኃ ውስጥ፡፡ አሮጌው ሰውነታችን በተፈጥሮ ሕግ ሳይኾን ከተፈጥሮ ሕግ በላይ
በኾነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሞቶ ግብዓተ ምድሩ ተፈጽሟል፡፡ ሞታችን በተፈጥሮ ሕግ ሞቶ ቢኾን ኖሮ ተመልሶ ሊመጣ ይችል ነበር፤
ነገር ግን የሞተው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይኸውም ልክ የአጋንንት ምሳሌ የኾኑት ግብጻውያን በባሕረ ኤርትራ ሰጥመው እንደሞቱት
ነው፡፡
ከዚኽ
መቀበር በላይ ደስ የሚያሰኝ ምንም የለም፡፡ በዚኽ መቀበር ፍጥረት ኹሉ በሐሴት ተመልቷል፡፡ መላእክት ሐሴት አድርገዋል፡፡ ደቂቀ
አዳም ሐሴት አድርገዋል፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ደስ ተሰኝቷል፡፡
ሰው
እንዲኽ ሲቀበር የመግነዝ ጨርቅ አያስፈልገውም፤ የሬሳ ሳጥንም አያስፈልገውም፤ እንዲኽ ያለ ሌላ ነገር ምንም አይፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው
አሚን ብቻ ነው፡፡
እሳት
ሰምን ያቀልጧል፤ ብረትን ግን ያጠነክሯል፡፡ እኛ ስንጠመቅ የኾነውም እንደዚኹ ነው፡፡ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ሰም ቀለጠ፤ አዲሱ
ሰውነታችን ግን እንደ ብረት ጠነከረ፡፡ አሮጌው ሰውነታችን ከመወገዱ በፊት ከመሬት መሬታውያን ነበርን፤ አዲሱን ሰው ከለበስነው
በኋላ ግን ሰማያውያን ኾነናል /1ኛ ቆሮ.15፡47/፡፡ አስቀድመን እንደ ሰም ነበርን፤ ከመሬት (ከአዳም) መሬታውያንም (አዳማውያን)
ነበርን፡፡ አሮጌው ሰውነታችንን ሳንጥል፥ እሳት ሰምን ከሚያቀልጠው
በላይ የኃጢአት እሳት የሚያቃጥለን ነበርን፡፡ ድንጋይ አንድን ሸክላ ከሚያደቅቀው በላይ የኃጢአት ዓይነት ያደቀቀን ነበርን፡፡ አኹን
ግን ሐዋርያው እንዳለው “ሞተናል”፡፡ ይኽን በፍጹም መርሳት የለብንም፤ በተለይ በዚኽ ወራት፡፡ ይኽን የምንረሳ ከኾነ መንገዳችንን
ስተናል፡፡
እስኪ
አንድ ጥያቄ እናንሣ፡፡ የሞተ ሰው ብዙ ቪላ ቤቶችን ስለመሥራት፣ በብዙ ጌጣ ጌጦች ስለማጌጥ፣ ስለሚለብሰውና ስለሚበላው፣ አብዝቶ
ስለ መብላትና ስለመጠጣት፣ ጊዜአዊ ደስታን ስለማግኘት ሊጨነቅ ይችላል ወይ? በፍጹም! እንግዲኽ ሐዋርያው እያለን ያለው፡- “እኛም
እንደዚኽ መኾን አለብን፡፡ ከሞትን (ከከበርን) በኋላ ዳግም ለሐሳር (ለኃጢአት፣ ለውርደት) አንነሣ፤ ኃጢአትን ለመሥራት ስንነሣሣ
የሞተውና አሮጌው ሰውነታችን ዳግም ሕይወት እንዲዘራ እናደርጓለን፡፡ አንድ ጊዜ ሞተናልና እንደሞትን እስከመጨረሻ መጽናት አለብን”
ነው፡፡
2.
ተነሥተናል
ሐዋርያው፡- “ሞታችኋልና” ብሎ አላቆመም፤ ጨምሮም፡-
“እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ” በማለት እንደተነሣንም ነገረን እንጂ፡፡ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፥ አሮጌው
ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደተሻገሩ ተሻግሯል
(ተነሥቷል)፡፡ ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡
መሬታዊው ሰዋችን ሞቶ ሰማያዊው ሰዋችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡ አኹን ከእኛ የሚጠበቀው
ይኽን ተፈጥሯችን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደተነሣን መዝለቅ፡፡ ይኽን ለማድረግ ከእኛ የሚጠበቀው ተራራ መውጣት አይደለም፤ የባሕር
እሳት መሻገርም አይደለም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ፈቃዳችንን ብቻ ነው፤ የሚሠራው ርሱ ነውና
/ዮሐ.15፡5/፡፡ ይኽ በእኛ ዓቅም እንደማይቻል የሚያውቀው እግዚአብሔር መጽንዒ (የሚያጸና የሚያጽናና) መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡ አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን
በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰዋችንን አውልቀን አሮጌውን ሰው ድጋሜ ለብሰነዋል፡፡
በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ስንፍና፣ ፍትወትም ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፡፡ ቢኖርም ታሟል፡፡
በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ዝሙት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌው ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡
ፋሲካን ማክበራችንም
ትርጕም የለውም፡፡ ምክንያቱም ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ነው፤ እግዚአብሔር
ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከውርደት ወደ ልዕልና፣ ከዲያብሎስ ባርነት ወደ ነጻነት፣ ከሲዖል ወደ ገነት አሻግሮናልና፤ ማዕዶት፡፡
ተወዳጆች ሆይ! የምናመልከውን አምላክ መስለን ካልተሻገርን የመሻገር በዓልን (ፋሲካን) ማክበራችን ምን ጥቅም አለው? ከጨለማ ሥራ
ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ካልተሻገርን ፋሲካን ማክበራችን ምን ረብሕ አለው? ብዙዎቻችን ፋሲካን አክብረናል፡፡
ነገር ግን ከዚኽ ዓለም ወደ አባታችን በሕይወት ሳንሻገር ነው፡፡ ክርስቲያን ኾኖ ሰማያዊውን ፋሲካ ሳይኾን ምድራዊ ፋሲካን የሚያከብር
ካለ ከምስኪኖች ኹሉ ይልቅ ምስኪን ነው፡፡ ይኼ ማለት የዲያብሎስ ዓለም ተመችቶታል፤ ከዚኽ በላይም መሻገርን አይሻም ማለት ነው፡፡
ታድያ ከዚኽ የባሰ ምስኪንነት ምን አለ? ስለዚኽ ተወዳጆች ሆይ! ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን
ክርስቶስ እንምጣና የመሻገር በዓልን እናክብር፡፡ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ
ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይኽን ዓለም የሚያሰነካክል ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሏልና እንሻገር፡፡
ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት መልአከ
ሞተ ከቤታቸው አልፏል፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ አምሳል በመኾኑ ነው እንጂ፡፡
እኛ ግን የአማናዊውን በግ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ኹሉ እንቀባና (እንቀበልና) እንሻገር፡፡ ይኽን ስናደረግ
በእባቡና በጊንጡ ማለትም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.10፡19/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለኾነ
ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.14፡6/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና ከተነሣን)
በሚመጣው ዓለምም ይኽን ደስታ ሊገለጽ በማይችል አኳኋን እንካፈላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.22፡15-16/፡፡
አባቶቻችን ይኽን ቀኖና የቈነኑልን ይኽን ፋሲካ እንድናከብር ነውና በእውነት እናክብረው፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት እናክበረው፡፡
አለመነሣት የእኛ የክርስቲያኖች ተፈጥሮ አይደለምና ከተፈጥሯችን ውጪ አንመላለስ፡፡
3.
ተቀምጠናል
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አኹን በክበበ ትስብእት ያለው በምድር
ሳይኾን በሰማያዊው ስፍራ ነው፡፡ ክርስቶስ ያለው በባሕርይ አባቱ ዕሪና ተቀምጦ ነው፡፡ እኛም፡- “ወአንሥአነ ወአንበረነ ምስሌሁ
በሰማያት በኢየሱስ ክርስቶስ - ከርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” እንዲል ከርሱ
ጋር ተዋሕደን ስለተነሣን ያለነው በሰማያዊ ስፍራ ነው ማለት ነው /ኤፌ.2፡7/፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀመጠ መባሉ የእኛን መቀመጥ
መናገሩ ነው፤ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ስንወለድ የርሱ ሕዋሳት ኾነናልና፡፡ ስለዚኽ ከክርስቶስ ጋር ተዋሕደን ለመኖር ትንሣኤ ልቡናን
ከተነሣን በኋላ ሰማያዊ ግብራችንን ትተን በምድራዊ ግብር ብቻ መያዝ ክርስቲያናዊ ተፈጥሯችን አይደለም፡፡ ክርስቲያናዊ ተፈጥሯችንን
ካልለቀቅን በስተቀር ይኽን ማድረግ አንችልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ እንደኾነ
ብዙ ጊዜ ተምረናል /ኤፌ.5፡23/፡፡ ታድያ የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን) ራስ ክርስቶስ በሌለበት ስፍራ ሰውነቱ ማለትም ክርስቲያኖች
እንደምን ሌላ ቦታ (ምድራዊ ግብር) ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ? ራስ በሌለበትስ ሌላው የሰውነት ክፍል ሕይወት ሊኖረው ይችላልን? አይችልም!
ታድያ ሰው ሕይወት በሌለበት ስፍራ እንደምን መቈየትን ይመርጣል? አንድ ሰው ራሱ (ጭንቅላቱ) ሌላ ቦታ፥ ሌላው የሰውነት ክፍሉም
ሌላ ቦታ ኾኖ በሕይወት መኖር አይችልም፤ ይኽ የተፈጥሮ ሕግ ነውና፡፡ የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወትም እንደዚኹ ነው፡፡ ምንም እንኳን
ለጊዜው በዚኽ ምድር የምንቈይ ብንኾንም ዘለዓለማዊ ስፍራችን (መኖሪያችን) ግን እዚኽ አይደለም፡፡ መጻተኞች ነን፡፡ ታድያ አንድ
መጻተኛ (ስደተኛ) በጊዜአዊ መጠለያ (ካምፕ) ውስጥ ኾኖ ብዙ ንብረትን ስለማፍራት ሊያስብ ይችላልን? በፍጹም! ባይኾን ሀገሩ ከገባ
በኋላ ሊያደርገው ስለሚገባው ነገር ሊያስብ ይችላል፡፡ የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወትም እንደዚኹ ነው፡፡ ልናስብ የሚገባው ሀገራችን
(መንግሥተ ሰማይ) ከገባን በኋላ ልናገኘው ስለሚገባን ክብር ነው፡፡ አኹን ተጓዦች ነን፡፡ ተጓዥ ደግሞ ስንቅ እንጂ ብዙ ሀብትና
ንብረት አይፈልግም፤ ንብረቱ ከብዶት ጉዞውን ሊያሰነካክልበት ይችላልና፡፡ ንብረቱ ለጉዞው አጋዥ ከኾነ ግን ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡
የእኛም እንደዚኽ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትምህርት እንድንማር ሲያደርገን ለጉዞአችን የሚኾን ስንቅን እንድናገኝበት ነው፡፡ ስንማር
ገንዘብ እናገኛለን፡፡ ክኂል እንቀስማለን፡፡ በገንዘባችን ደግሞ ራሳችንን ሳይኾን ወንድማችንን እናገለግልበታለን፡፡ በክኅሎታችን
ወንድማችንን፣ ቤተ ክርስቲያንን እናገለግልበታለን፡፡ ይኽን ስናደርግ በሰማያዊው ስፍራችን እስከ መጨረሻው እንዘልቃለን፡፡ ሐዋርያው፡-
“እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፡፡ በላይ ያለውን አስቡ
እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” የሚለንም ይኽን ሲያሳስበን ነው፡፡ ሞተናል፤ ተነሥተናል፤ ተቀምጠናልም፡፡ ሕይወታችን ሕይወት የሚኾነው
ይኽን ሳንረሳ የዘለቅን እንደኾነ ብቻ ነው፡፡
4.
እንገለጣለን፡፡
እስከ ፍጻሜ ድረስ በዚኽ በተቀመጥንበት
ስፍራችን የምንቈይ ከኾነ ክርስቶስ በክብር በሚገለጥበት ወራት እኛም በክብር እንገለጣለን፡፡ ከተቀመጥንበት ሰማያዊ ስፍራችን ለቅቀን
የምንነሣ ከኾነ ግን የምንገለጠው ከክርስቶስ ጋር በክብር አይደለም፤ የዲብሎስን መልክ ይዘን በሐሳር ነው እንጂ፡፡ ስለዚኽ አኹን
ከዚያ ስፍራ ለቅቆ መኖር የእኛ መገለጫ አይደለም፡፡ ይኽ ሕይወት ሌላ፣ ያም ሕይወት ሌላ ነውና፡፡ ክርስቶስ አኹን አልተገለጠም፡፡
የእኛም ሕይወት ገና አልተገለጠም፡፡ ስለዚኽ በክብር እስክንገለጥ ድረስ እዚያ ልንቈይ ያስፈልጋል፡፡ መቼ ነው ታድያ የምንገለጠው?
ሕይወታችን ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ፤ ዳግም ሲመጣ፡፡ ርሱ ሲገለጥ ሕይወታችን ይገለጣል፤ ክብራችን ይገለጣል፤ ደስታችን ይገለጣል፡፡
ብዙ ሀብትና ንብረት፣ እንዲኹም ሥልጣን ያለው ሰው የቅምጥልነት ኑሮ ደስ
ያሰኟል፡፡ ብዙ ልብላ ልጠጣ ስለሚልም በብዙ በሽታዎች ይያዛል፡፡ ለርሱ አብዝቶ መብላቱና መጠጣቱ እንጂ በበሽታ እየተያዘ መኾኑን
አያስተውለውም፡፡ ይኽን የተረዱ ወዳጆቹ ከዚኽ በሽታ ሊያስለቅቁት ቢሞክሩ እንኳን ሊጠላቸው ይችላል፡፡ “የእኔን ጥሩ ነገር የማይሻ፣
ቀናተኛ” ብሎም ሊሰድባቸው ይችላል፡፡ ታድያ ይኼ ሰው እንደምን ክብርን አገኘ፤ እንደምን ደስታን ገንዘብ አደረገ ልንለው እንችላለን?
ይኽ ሰው በበሽታ ተያዘ እንጂ እንደምን ከበረ፤ ተደሰተ እንሏለን?
ከደዌ ዘሥጋ ይልቅ ደዌ ዘነፍስ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ በሥጋው የታመመ
ሰው ለሐኪም አልታዘዝ ቢል ደዌው እየጠናበት ይሔዳል፡፡ በነፍስ የታመመ ሰውም ለዚኽ ከዳረገው ነገር እንዲወጣ ሲነገረው እሺ ካላለ
ኹለንተናው እየመረቀዘ (infected እየኾነ) ይሔዳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ሥጋ እየታመመ ሲሔድ እንደምን ሰውነት እንደሚደክም እናውቋለን፤
እንደምን ዓቅም እንደሚያጣ እንረዷለን፡፡ ክብርና ደስታ በሚመስል ነገር ነፍሳችንን ስናዋርዳትና ስናሳምማትማ እንደምን አትደክም?
እንደምን ዓቅሟን አታጣ? ለዚኽ ኹሉ ምንጭስ ክብር ወይም ደስታ ነው ብለን ያሰብነው በተለይ ደግሞ በዚኽ ወራት እጅግ የሚዘወተረው
ጭፈራው፣ መዝናናቱ፣ ስንፍናው አይደለምን? እንኪያስ ደጋግመን እንደተናገርነው ሰማያዊ ስፍራችንን አንልቀቅ፡፡ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ
እውነተኛው ትንሣኤያችንና ክብራችን ይገለጥ ዘንድ የእኛ ባልኾነ አገላለጥ አንገለጥ፡፡ የዚኽን ወራት ዓላማ አንሳተው፡፡
5.
እስክንገለጥ ድረስ ተሰውረናል፡፡
ከማይበሉ የዓሣ
ዝርያ ውስጥ የሚመደብ “ኦይስተር” የተባለ ዓሣ አለ፡፡ በሰውነቱ ውስጥም ለጌጣ ጌጥ የሚያገለግል ቅርፊት አለው፡፡ ነገር ግን ይኽ
ዓሣ እስካልተገለጠ ድረስ ይኽ ክብሩ አይታይም፡፡ የእኛም እንደዚኹ ነው፡፡ ክርስቶስ እስካልተገለጠ ድረስ ክብራችን አይገለጥም፤
የተሰወረ ነው፡፡ ሕይወታችን ገና ያልተገለጠና የተሰወረ ከኾነ በዚኽ ዓለም መኖር ያለብን እንደሞተ
ሰው ነው፡፡ ለምን? ሕይወታችን ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ እኛም በክብር እንገለጥ ዘንድ፡፡
ትናንት
ሥልጣናቸውን ለማንም ሳያጋሩ ሕዝቡን ቀጥ አድርገው ሲገዙ የነበሩ ኃያላን ዛሬ በቦታቸው ላይ የሉም፡፡ ባላቸው ሀብትና ንብረት ሲመኩ
የነበሩ ባለጸጐች ዛሬ በዚያ ስፍራቸው የሉም፡፡ ድምጻቸው ከፍ ብሎ ሲሰማ የነበሩ “ዝነኞች” ዛሬ ድምጻቸው አይሰማም፡፡ ብዙ ሲሮጡ
የነበሩ “ብርቱዎች” ዛሬ ደክመዋል፡፡ ሥልጣኑ፣ ሀብቱ፣ ንብረቱ፣ ዝናው፣ ብርታቱ ሐላፊና ጠፊ ነው ማለት ነው፡፡ የተገለጡት ድሮውም
የነርሱ ባልኾነ አገላለጥ ነበር ማለት ነው፡፡ ለእነዚኽ “ኃያላን”፣ “ባለጸጐች”፣ “ዝነኞች”፣ “ብርቱዎች” ለጊዜውም ቢኾን ብዙዎች
ጐንበስ ቀና ብለውላቸዋል፡፡ ኃይላቸው፣ ሀብታቸውና ንብረታቸው ከነርሱ እየራቀ ሲሔድ ግን “ጐንበስ ቀና” ሲሉላቸው የነበሩ ሰዎችም
ለነርሱ ያላቸው አመለካከት ይቀየራል፡፡ ስለዚኽ ጐንበስ ቀና ሲሉ የነበሩት ሰዎች ሲያከብሩት የነበረው ኃያላኑን፣ ባለጸጐቹን፣ ዝነኞቹን፣
ብርቱዎቹን ሳይኾን ሌላ ነገራቸውን ነበር ማለት ነው፡፡ ሰዎቹ ሲያከብሩት የነበረው በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው ሳይኾን አፈርና
ትቢያ የኾነውን ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ ታድያ ከዚኽ በላይ ምስኪንነት ምን አለ? ምንም የለም፡፡ ክብራችን ሞገሳችን ሀብት ወይም
ንብረት፣ ሥልጣን ወይም ዝና ሳይኾን እግዚአብሔር ከኾነልን ግን ክብራችን መቼም ቢኾን አይደበዝዝም፡፡ ይልቁንም እየደመቀ ይሔዳል
እንጂ፡፡ ስለዚኽ መገለጫችን ባልኾነ መንገድ አንገለጥ፤ እስክንገለጥ ድረስ ተሰውረን እንቈይ እንጂ፡፡
ወገኖቼ!
በዚኽ ወራት የምናሳልፈው ጊዜ የዕረፍት ጊዜ አይደለም፡፡ ይኽ ወራት ገና ስንዠምር እንደተነጋገርነው ነፍሳችን እንደምን ካለ ቀንበር
እንደተላቀቀች፣ ዳግመኛም በመንግሥተ ሰማያት የምታገኘውን ተድላና ደስታ የምናስብበት ወደዚያም ለመድረስ የምንቻኰልበት እንጂ ድጋሜ
በድንዛዜ የምንያዝበት ወራት አይደለም፡፡ ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን ክርስቶስ ካጸዳው በኋላ ድጋሜ የምናቆሽሽበት ወራት አይደለም፡፡
አሮጌው ሰውነታችን እንደሞተ የምናስቀጥልበት እንጂ አዲሱን ሰውነታችን ከተነሣበት የምንጥልበት ወራት አይደለም፡፡ በሰማያዊ ስፍራ
የተቀመጠው እኛነታችን፥ ሕይወታችን ክብራችንና ደስታችን ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ሰውረን የምናቆይበት እንጂ የእኛ ባልኾነ አገላለጥ
የምንገልጥበት ወራት አይደለም፡፡
ይኽን
እስከ መጨረሻ አጽንተን እንድንቆይ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፤ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment